ዳያስፖራ የሚባለው ቃል ለብዙዎቻችን በቅርብ የመጣ አዲስ ቃል ይመስለናል፡፡የቃሉ ምንጭ ግሪክ ሲሆን ዳያ ስፒሮ /dia speiro/ በሚል ይጠራል።
ከላይ መበተን፣ መዘራት የሚል ፍቺ አለው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለአማርኛ እንደ እንግዳ ሆኖ ብቅ ያለው ቃሉ በጥንታዊ ብራና መጽሐፎቻችን ጭምር ዲያስጶራ በሚል ስያሜ ይታወቅ ነበር።
የቃሉ ጽንሰ ሃሳብ የመነጨው በግሪኮቹ ሄለናውያን ዘመን ሲሆን፣ ድኅረ ልደተ ክርስቶስ በ6ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የኢየሩሳሌም ውድቀትን ተከትሎ የተበተኑትን አይሁዳውያን በማስታወስ ነው፡፡ ዳያስፓራዎች ለአገራቸው ዲፕሎማት፣ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ፣ ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ምንጭ በመሆን ይታወቃሉ። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ በተለይ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ ምንጭነታቸው ጎልቶ ይታያል።
ከስደተኞች ዳታ ፖርታል የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በጎርጎሮሳውያኑ 2020 ከዳያስፖራ ገቢ ካገኙ አምስት ፊታውራሪ አገሮች ውስጥ ህንድ 83 ቢሊዮን ዶላር ቀዳሚዋ ናት። ቻይና 60 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ህንድን ስትከተል፤ ሜክሲኮ 43 ቢሊዮን፣ ፊሊፒንስ 35 እና ግብፅ 30 ቢሊዮን ዶላር በማግነት ይታወቃሉ።
እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆች ዓመት ብቻ የህንድ ዳያስፖራዎች 87 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገራቸው ልከዋል። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በሰሜን አሜሪካ በአውሮጳ እና መካከለኛው ምስራቅ ይኖራሉ።
ከአራት ዓመት በፊት የደች ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ባወጣው መረጃ በኔዘርላንድ ብቻ 16 ሺ 347 ኢትዮጵያውያን ይኖሩ ነበር፡፡ በጎርጎሮሳውያኑ 2020 ከአገር ውጭ በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ እና ለተለያዩ ቢዝነሶች ማስኬጃ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት መላካቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ከባሕር ማዶ ወደ አገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሆን ፤ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች የሚያንቀሳቅሷቸው ቢዝነሶችም ከፍ እያሉ መጥተዋል። ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከ84 በላይ የሚሆኑ የዳያስፖራ ኢንቨስትመንቶች ብቻ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ስራ ላይ በማዋል ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል አስገኝተዋል። በአጠቃላይ 30 ሺህ ያህል የሥራ እድሎች በዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ኢንቨስትመንቶች ብቻ በተከፈቱ ዘርፎች ላይ የተፈጠሩ ሲሆን፣ ይህም ከመንግሥት ቀጥሎ ትልቁ ቀጣሪ የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት ነው።
መንግሥት ዳያስፖራው በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማራ በአገሪቱ ውስጥ ሕጋዊ፣ ተቋማዊ ጉዳዮች ለዳያስፖራ ኢንቨስተሮች ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ እና ዳያስፖራው ወደ አገሩ መጥቶ ሀብቱን ስራ ላይ እንዲያውል በማንቀሳቀስ፣ በማበረታታትና በመደገፍ ይሠራል። ዳያስፖራው እንዲጫወት የሚጠበቅበት ሌላው አብይ ተግባር ደግሞ ዲፕሎሚሲ ነው። ዳያስፖራው የአገሩ ዲፕሎማት ተብሎ ይታሰበል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የዲፕሎማትነት ሚናውን በሚገባ መጫወት የጀመረው ግብጽና ሱዳን ከተባባሪዎቻቸው ምእራባውያን ጋር በመሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጉዳይ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት በመላ ዓለም የሚያገኘው ዳያስፖራ ድርጊቱን ከማውገዝ በተጨማሪ በጉዳዩ ዙሪያ የውሃና የግድብ ባለሙያዎችን ሙያዊ አስተያያት በማቅረብ ታግለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያና የሕዝብ ጠላት መሆኑን ለዓለም እያስገነዝቡ ናቸው። ምእራባውያን ከትህነግ ጋር በማበር አገራቸው ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳረፍ እያደረጉ ያሉትን ጥረት ሲቃወሙ ቆይተዋል። እነዚህ ሃይሎች ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን በሀሰተኛ መረጃ
ላይ የተመሰረተ ስም የማጥፋት ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ ሲያካሂዱ ድርጊታቸውን በመቃወም እንዲሁም የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም አቀፍ ተቋማት ፣ ለውጭ መንግሥታት በማስገንዘብ ሰርተዋል፤ እየሰሩም ናቸው፡፡
አገሪቱ በአሸባሪው ትህነግና ምእራባውያንን የተቀናጀ ዘመቻ የተከፈተባትን መጠነ ሰፊ ጦርነት ከማውገዝ አንስቶ ጦርነቱ በድል እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ለአገራቸው ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል። ይህንንም ለመከላከያ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አረጋግጠዋል።
በትህነግ ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፎችን እያሰባሰበ በመላክ ለወገናቸው ፈጥኖ ደርሰዋል። እንደ አርቲስት ታማኝ በየነ ያሉት ደግሞ በዚህ ወቅት ከአገሬ አጠገብ ያልሆንኩ መቼ ልሆን ነው ብለው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከአገር መከላከያ ጎን የቆሙ፣ ለተፈናቃዮች ድጋፍ እያሰባሰቡ የሚያቀርቡም አሉ። ጦርነቱ በበርካታ ግንባሮች የሚካሄድ እንደመሆኑ በተለይ በዲፕሎማሲው መስክ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ ይገኛል።
ትህነግና ምእራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን በሀሰት መረጃ ላይ የተመሰረተ ፕሮፓጋንዳ በማጋለጥ እና የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም በማስገንዝብ በአገሪቱ ታይቶ በማያውቅ መልኩ የአገሪቱ ዲፕሎማት መሆን ችሏል። ምዕራባውያን በአገራችን ላይ የሚያደርሱት ጫናና ሐሳውያን ሚዲያዎቻው የሚያሰራጩት ዕኩይ ዜናን ተከትሎ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በያሉበት ከተሞች በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፤ እያሰሙም ይገኛሉ።
በተለይ በቃ! # No more! በሚል መሪ ቃል ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትየጵያውያን አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን አንሱ፤ በምእራቡ ዓለም የምትዘወሩ እንደ ሲኤንኤን ያላችሁ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ሚዛነቢስ ዘገባችሁን እንቃወማለን፤ በሚል ያሳዩት ሰላማዊ ሰልፍ ለኢትዮጵያ በክፉ ቀን የደረሰ ትልቅ የዲፕሎማሲ አቅም ሆኖ ተገኝቷል።
የዓለማችን ታላላቅ ከተሞች በእዚህ በተቀናጀ ሰላማዊ ሰልፍ ተጨናንቀው ታይተዋል። በአንድ ቀን ብቻ በ27 ዋና ዋና የምእራቡ ዓለም ከተሞች በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉባቸው ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ምእራባውያኑ እጃቸውን ከኢትዮጵያ እስከሚያነሱ ድረስ በአሜሪካ በየሳምንቱ እሁድ መካሄዱ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል። በእስራኤል ቴልአቪቭና ኢየሩሳሌም ፣ በጃማይካ ፣ በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞዋቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል።
አራት ዲፕሎማቶቿ ከአዲስ አበባ በተባረሩባት አየርላንድ ሳይቀር ዳያስፖራው ሳይፈራ ለአገሩ ቆሞ በመቃወም ኢትዮጵያን ያኮራ ነው። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በምዕራባውያን ከተሞች ያደረጓቸው የተቃውሞ ሰልፎች በእጅጉ የተቀናጁና የተናበቡ አንድ ዓላማ ያነገቡ ናቸው። ሁሉም ምእራባውያን እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ፣ ለአሸባሪው ትህነግ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያቆሙ፣ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ያሉ ጫናዎች ተገቢነት የሌላቸውና አገሪቱን በእጅጉ የሚጎዱ መሆናቸውን የሚያስገነዝቡና እንዲቆሙ የሚጠይቁ ናቸው።
በተለይ በአምስት አህጉሮች ከ40 በላይ በሆኑ ከተሞች ታላላቅ ሕዝባዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። ቀደም ሲልም በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ግብጽና ተባባሪዎቿ ምእራባውያን ተመድ ድረስ የዘለቀ አጀንዳ አስይዘው ኢትዮጵያ ላይ ጫና ሊያሳድሩ ሲሞክሩ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ካደረጉት መካከል ዳያስፖራው ይጠቀሳል።
አሁን ደግሞ በተለይ በኖሞር ዘመቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖ ማሳደር ያስቻለ ተግባር አከናውነዋል። ኢትዮጵያን አስመልክቶ ከ12 ጊዜ ያላነሰ ስብሰባ በዚህ ዓመት በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ተካሂዷል። በሁሉም ስብሰበሳዎች ኢትዮጵያን አስመልክቶ የተነሱ አጀንዳዎች ዋጋ እንዲያጡ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገሮች ከተጫወቱት ሚና ቀጥሎ ዳያስፖራው የዲፕሎማትነት ተግባሩን ተቀናጅቶ ተወጥቷል።
ዳያስፖራው ዲፕሎማት ሆኖ ለአገሩ በመታገል፤ ለሌሎች ምሳሌ የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ንቅናቄ በየሳምንቱ ሳይታክቱ በማድረግ ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ተፅዕኖ ማድረግ ችሏል።
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን የሚጎዳ ውሳኔ እንዳያሳልፍ ማስቻሉ፤ አፍሪካውያንን በአንድ ማሰባሰቡ በጥቁርነቱ ያመጣው ድል ነው። «በትግራይ የዘር ማጥፋት ተፈፅሟል» በሚል ኢትዮጵያን ለመወንጀል በአሜሪካ ሲረቀቅ የነበረው አዋጅ የተሰረዘውም አንድም ዳያስፖራው ባደረገው ብርቱ ተቃውሞ ነው። ዳያስፖራው እያካሄደ ያለው ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻ ተጠናክሮ ባለበት በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዳያስፖራው የዘንድሮውን የገና በዓል በአገሩ እንዲያከብር ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ዳያስፖራ ወደ አገሩ በስፋት እየገባ ነው።
ኢትዮጵያ በአሸባሪው ትህነግ ላይ ታላቅ ድል በተቀዳጀችበት በዚህ ወቅት ዳያስፖራው ወደ አገሩ ለመምጣት ቁርጠኛ መሆኑ ፋይዳው ብዙ ነው። ኢትዮጵያ ምእራባውያኑ ሲያራግቡ እንደቆዩት የሰላምና ደህንነት ስጋት ጨርሶ የሌለባት አገር መሆኗን ለጠላትም ለወዳጅም በሚገባ ለማሳየት ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሯል።
የአሸባሪው ትህነግ ወሯቸው በነበረ የአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ የመንግሥት ሃይሎች ታላቅ ድል በተቀዳጁበት በአንጻሩ የከሀዲው ትህነግ ቅዠት በእርግጥም ቅዠት በሆነበት ወቅት የሚመጡ እንደመሆናቸው ለድሉ መገኘት የዳያስፖራው ድርሻም የጎላ እንደመሆኑ ድሉን አብሮ ለማጣጣምም ያስችላል፡፡ ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ድል ተመትቷል፤ ይህ ድል የተመዘገበው ደግሞ ዳያስፖራውን ጨምሮ መላ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ባደረጉት ንቅናቁ ነው። ዳያስፖራው በገንዘብ ፣ በሞራል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን በመቆም አጋርነቱን አረጋግጧል።
ይህ አይነቱ ድጋፍ ኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ ችግር ውስጥ ባለችበት ወቅት ሁሉ ሲደረግ የቆየ ቢሆንም የዘንድሮው ድጋፍ ግን በአይነቱ በእጅጉ ይለያል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ጦርነት የተቀናጀና ዘርፈ ብዙ ነው።
በተለይ በፕሮፓጋንዳና በዲፕሎማሲው መስክ ከፍተኛ ስራን የሚጠይቅ አደጋ በአገራችን ተደቅኖባታል። ኢትዮጵያ እውነቷ ዋጋ እንዲያጣ እየተደረገ እነ ትህነግና ተባባሪዎቹ የሚሰሩት እና የሚያሰራጩት ሀሰተኛ መረጃ ኢትዮጵያን በእጅጉ ፈትኗታል። ይህን ሀሰተኛ መረጃ በማጋለጥ ፣ የኢትዮጵያን እውነት በማስረዳት በኩል ዲያስፖራው ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
በኖሞር ዘመቻም ዳያስፖራው በሰላማዊ ሰልፍ እና በመረጃ ቴክኖሎጂ/በትዊተር እና በመሳሰሉት/ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አስርድተዋል፤ ሀሰተኛ መረጃዎችን አጋልጠዋል። ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ ሊደርሱ ይችሉ የነበሩ አደጋዎች ተቀልብሰዋል፡፡
ጁንታው የፈጸመውን ግፍ ዳያስፖራው በተፈጸመባቸው ስፍራዎች እየሄደ እንዲጎበኝ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ትህነግ ምን ያህል ጸረ ሕዝብ እና አገር ስለመሆኑ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ይበልጥ ለማሳጣት የዳያስፖራው በእዚህ ወቅት ወደ አገራቸው መምጣት ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በኢትዮጵያውያኑ ላይ የተፈጸመው ግፍ ቃላት ሊገልጹት ከሚችሉትም በላይ እንደመሆኑ የእነሱ በስፍራው ተገኝቶ መጎብኘት ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
በመሰረተ ልማትና በተለያዩ ተቋማት ላይ ቡድኑ ባደረሰው ዘረፋና ውድመት የተጎዱ ተቋማትን መልሶ መገንባትና ማቋቋም ከፍተኛ ርብርብን ይጠይቃል። አንዳንዱ መልሶ ግንባታ ዓመታትን የሚወሰድና ብዙ ሀብትን የሚፈልግ እንደመሆኑ ዳያስፖራው በዚህ በኩል ብዙ ማድረግ ይጠበቅበታል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ምን ያህል ዋጋ ከፍለው ይህ ከሀዲ ቡድን ኢትዮጵያ ላይ ደግሶት የነበረውን አደጋ መቀልበስ እንደቻሉ ለማስረዳትና ለማሳየትም ይጠቅማል። በወረራው የተጎዱ ዜጎችን እንዲጎበኙ በማድረግ ችግራቸውን ተረድተው እንዲሄዱ በቀጣይ የሚደረጉ መልሶ የማቋቀቋም ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግም ይጠቅማል። ወቅቱ በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ ውይይት የሚደረግበት ነው። ዳያስፖራው በዚህ የሚሳተፍበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ነው።
በአገራችን በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው አገራዊ መግባባት ላይ የሚደረግ ውይይት ተጀምሯል። ዳያስፖራው በእዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ግንዛቤው አለው ተብሎ ስለሚታሰብ በእዚህ ውይይት ላይ ማሳተፍ ለሚሰበሰበው ግብዓት ይጠቅማል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥር 4/2014