በሜዳ፣ በመም እና በጂምናዚየም የሚ ኖረው ጥረት ላብን በማፍሰስ ይገለጽ እንጂ መደምደሚያው ግን የደስታ ሲቃ ነው። በተሰ ማሩበት የሥራ መስክ ሀገርን መወከል፤ ከዚያም አልፎ በአሸናፊነት ባንዲራን ማውለብለብ ታላቅ ክብርን እና ኩራትን ያቀዳጃል። አሸናፊነቱ የተገኘው የዓለምን ክብረ ወሰን በመስበር ጭምር ሲሆን ደግሞ ድሉ ክብርን በክብር ላይ የደረበ ይሆናል። በአትሌቲክስ ስፖርት በተለይም በረጅም ርቀት በዓለም ለነገሰች አገር ይህ አዲስ አይሆንም።
ምክንያቱም አትሌቶች እግር በእግር እየተተካኩ ለዘመናት ባንዲራዋን በሌሎች አገሮች ሰማይ ላይ ሲያውለበልቡና ብሄራዊ መዝሙሯንም በክብር ሲዘምሩ ቆይተዋል። ይህ የሆነው ደግሞ በወንድ አትሌቶች ብቻ ሳይሆን በሴቶችም ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች የዓለም ክብረ ወሰንን ጨብጠዋል። በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አዘጋጅነት ከሚካሄዱ ውድድሮችም በጥቅሉ ከአስር በላይ የሚሆኑት በበላይነት የተያዙት በኢትዮጵያውያን ነው።
በመካከለኛ ርቀት ወደር ያልተገኘላትና የእህቶቿን ዱካ ተከትላ መሮጥ የጀመረችው አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ሁለት ክብረወሰኖችን የግሏ አድርጋለች። አትሌቷ በምትታወቅበት የ1ሺ500ሜትር እ.አ.አ በ2015 ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች። የገባችበት ሰዓትም 3ደቂቃ ከ50 ሰከንዶች ከ07ማይክሮ ሰከንድ ነው።
ሌላው በአትሌቷ የተሰበረው ክብረወሰን ከሁለት ዓመታት በፊት በስፔን ያስመዘገበችው የ2ሺ ሜትር ውድድር ሪከርድ ነው። አትሌቷ ርቀቱን ለመሸፈን የፈጀባት ሰዓትም 5ደቂቃ ከ23ሰከንድ ከ75 ማይክሮ ሰከንዶች ብቻ ነው። ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በሚመራቸው የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሮችም ገንዘቤ በተመሳሳይ ንግስናውን ጨብጣለች። አምስት ክብረወሰኖችን የግሏ በማድረግ አይበገሬነቷን ያስመሰከረችው ገንዘቤ፤ እ.አ.አ ከ2014 እስከ 2017 ድረስ፤ 1ሺ500 ሜትር፣ አንድ ማይል፣ 2ሺ፣ 3ሺ እና 5ሺ ሜትር ድሏን ያገኘችባቸው ርቀቶች ናቸው።
በረጅም ርቀት የምትሳተፈው የገንዘቤ ታላቅ እህት ጥሩነሽ ዲባባም ለዓመታት ሊደፈር ያልቻለ የክብረወሰን ባለቤት ናት። ጥሩነሽ በተለይ በምትታወቅበት የ5ሺ ሜትር ርቀት ከ11ዓመታት በፊት የገባችበት ሰዓት 14ደቂቃ ከ11ሰከንድ ከ15 ማይክሮ ሰከንድ ነው። በ10ሺ ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በጥቁር ሴቶች የኦሊምፒክ መድረክ ለማጥለቅ ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ ከአሸናፊነት ባለፈ ክብረወሰኑን ለመቀዳጀት ዓመታትን አስቆጥራለች። ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ ከመወለዷ አስቀድሞ የተያዘውን ክብረወሰን እስክትሰብረውም 24ዓመታት አልፈዋል።
ወጣቷ አትሌት አልማዝ አያና ግን ከሁለት ዓመታት በፊት በሪዮ ኦሊምፒክ ታሪክ ሰራች። እ.አ.አ በ1993 በቻይናዊቷ አትሌት የተያዘውን ክብረወሰን ለመስበር የወሰደባት ጊዜም 29፡17፡45 ነበር። አትሌቷ ርቀቱን በ14 ሰከንዶች ያሻሻለች ሲሆን ይህም በመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ የማይጠበቅ ታላቅ ክብር ነው። በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄድ ነገር ግን በርካታ ውድድር በሌለውና ባልተለመደው የአንድ ሰዓት ውድድርም ክብረወሰኑ የተመዘገበው በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ነው።
ይህ ውድድር አትሌቷ በአንድ ሰዓት ውስጥ መሸፈን የሚችለውን ርቀት መሰረት የሚያደርግ ሲሆን፤ 18ሺ 517 ሜትሮችን በመሮጥ አሸናፊ የሆነችው ደግሞ አትሌት ድሬ ቱኔ ናት። አትሌቷ ርቀቱን በዚህን ያህል ሜትር በመሸፈን አሸናፊ የሆነችው እ.አ.አ በ2008 ሲሆን፤ እስካሁንም በአንድ ሰዓት ውስጥ የእርሷን ያህል ርቀት መሸፈን የቻለ አትሌት አልተገኘም። ሌላኛዋ ወጣት አትሌትና ወደ ፊት ኢትዮጵያን ያስጠራሉ በሚል ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አትሌት ነጻነት ጉደታ ተጠቃሽ ናት። አትሌቷ ባለፈው ዓመት በቫሌንሺያ የተካ ሄደውን የግማሽ ማራቶን ውድድር ያጠናቀቀችው በአሸናፊነት ብቻም ሳይሆን ክብረወሰን በመስበር ድርብ ድል ነው።
ነጻነት 21ኪሎ ሜትሩን ለመሸፈን የፈጀባት ሰዓትም አንድ ሰዓት ከስድስት ደቂቃ ከ11ሰከንዶች ነው። በጎዳና ላይ የሪሌ ውድድርም ፈጣኑ ሰዓት የተያዘው በኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ነው። እ.አ.አ በ1996 ኮፐንሃገን ላይ በተካሄደው በዚህ ውድድር አገራቸውን ወክለው የተሳተፉት፤ ገነት ገብረጊዮርጊስ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ አየለች ወርቁ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ጌጤነሽ ኡርጌ እንዲሁም ሉቺያ ይስሃቅ ርቀቱን ለመጨረስ 2ሰዓት ከ16ደቂቃ ከ04 ሰከንድ ነበር የፈጀባቸው።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በብርሃን ፈይሳ