በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ (political History) ወደ ሥልጣን የሚመጡ አካላት አንድም በሕዝብ ይሁንታ ተመርጠው የሚመጡ ባለመሆናቸው በሌላም በሃይል ወደ መንበረ ሥልጣን የሚመጡ ስለሆነ የሕዝቡን ቀልብና ልብ ሳያገኙ መንግሥት ሆነው ወደ መንግሥተ ሰማያት ወይም ወደ እንጦርጦስ ይወርዳሉ በዚህም ምክንያት ሕዝብና መንግሥት ሳይገናኙ ኖረዋል::
ይህ ማለት ለዛሬ የተውልን እርሾ የለም ማለት አይደለም ዛሬ ላይ የምናያቸው ወይም ያገኘናቸው የሚዳሰሱም ሆነ የማይዳሰሱት እሴቶች የትናንት ጥሪት ስለመሆናቸው ጥርጥር የለኝም ነገር ግን መልካም ነገሮችን በማስቀጠል የማያግባቡን ወይም ላለመግባባት ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮችን አንድ ቦታ ቆርጠን ልንጥላቸው ይገባል::
ለዚህም ይመስላል የኢፌዴሪ መንግሥት በፕሬዝዳንቷ አማካይነት በሁለቱ ም/ቤቶች የመክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ በ2014 ዓመት ከሚሰሩት ተግባራት ወስጥ አገራዊ የጋራ ምክክር መድረክ (National Dialogue) እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
በዚህ መሰረት ተቋማዊ በሆነ መልኩ የጋራ መግባባት በመፍጠር የጋራ አገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያስችል መሰረት ለመጣል ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሟል ብዙ ዜጎችም ተስፋ ጥለውበታል የዚህ ፅሁፍ ዓላማም እንደ አንድ ዜጋ ባልተግባባንባቸው ጉዳዮች ላይ ቀጣይ የውይይት አጀንዳ ቢሆኑ በሚል የግል ምልከታዬን ለመግለጽ ሲሆን በቀጣይ ግን ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ምሁራን የማህበረሰብ አንቂዎች ሲቪክ ማህበራት በአጠቃላይ ምልአተ ሕዝቡ ወዘተ ሃሳባቸውን የሚገልጹበት መወያያ መንገድ (Platform) ሊዘጋጅ እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ።
ለባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በተለይ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የብሄራዊ እርቅን አስፈላጊነት ሲወተውቱ ቆይተዋል ሆኖም ግን በመንግሥት በኩል ማን ከማንም አልተጣላም በሚል ስላቅ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል።
በአሁኑ ሰአት ከብሄራዊ እርቅ ባሻገር ከፍ ባለ መልኩ ብሄራዊ የጋራ የምክክር መድረክ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት የተደረሰ ይመስላል በዚህ በሂደት የሚያመጣውን ውጤት ሁላችንም የምንመለከተው ጉዳይ ቢሆንም ለስኬታማነቱ ግን የሁላችንንም ፈቃድኝነት እና ቁርጠኝነት ይጠይቃል ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካውም ይሁን ፖለቲከኛው አንድ ጽንፍ ላይ ከቆመ ለጋራ ጥቅም ሲባል በሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት አማራጭ ሃሳብን ወይም ሶስተኛ መንገድ መኖሩን ለመቀበል መዘጋጀት ላይ ትልቅ ተግዳሮት ነው።
በመሆኑም ሁሉም አካል ትውልድ ተሻጋሪ አገር መገንባት ይኖርብናል ትውልዶችም አገርን ወይም ኢትዮጵያዊነትን ለድርድር ወደ ገበያ የማያቀርቡበት መሰረት መጣል ብቻ ሳይሆን እትዮጵያውያንን የሚመስል ኢትዮጵያን መገንባት ይኖርብናል ስለዚህ በእኔ እይታ ልንስማማባቸው ወይም የልዩነት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶች እልፍ አእላፍ ናቸው ነገር ግን አንዳንድ ልዩነቶች የፖሊሲ ጉዳይ ከመሆን አይዘሉም ለምሳሌ የመሬት ስሪትን ማንሳት ይቻላል ስለዚህ አንኳር ወይም ለብሄረ መንግሥት ምስረታ እንቅፋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መደረስ ይኖርበታል። ኮሚሽኑም ከዚህ በፊት ከተቋቋሙት የእርቅ እና የሰላም ኮሚሽን እንዲሁም ከማንነትና ከአስተዳደር ወሰን ኮሚሽን ትምህርት ሊወስድ ይገባል።
በዘመናዊ ታሪክ እንደ እኛ ባሉ መልከ ብዙ ሕዝቦች ይቅርና ተመሳሳይ የሆኑ ሕዝቦችም እንደ አገር መቀጠል የቻሉት የቤት ስራቸውን በህገ መንግሥታቸው አጠናቀው ነው:: ስለዚህ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ከመሸጋገራችን በፊት ለሕገ መንግሥቱ መሰረት ወይም መነሻ የሚሆነው በቅድሚያ እንደ አገር አሁን የያዝነውን ሉዓላዊ ግዛት ወይም አገራዊ ቅርጽ ይዘን እንቀጥል ወይስ አንዳንድ ፖለቲከኞች እንደሚያነሱት ትናንሽ በርካታ አገር እንሁን ለሚለው ጥያቄ መልስ ከሰጠን በኋላ ኢትዮጵያ ማለት ለዘመናት ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች የራሷ የሆነ የአየር የውሃ የመሬት ግዛት ወይም ወሰን ያላት ልሳነ ብዙ ልዩ ልዩ ብሄረሰብና እና ባህል ያላት ሉዓላዊ አገር ናት በሚለው ከተግባባን ኢትዮጵያዊ ያደረገን የጋራ ማንነታችንን (National Character) አንጥረን በመለየት በጋራ ማንነታችን ዙሪያ መግባባት መፍጠር ይኖርብናል።
የጋራ የምክክር ከሚሽኑም በቅድሚያ ሊያነሳቸው እና መልስ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ቀዳሚ ተግባራት ናቸው።
ብሄራዊ የጋራ ማንነት ሲባል እኛ ኢትዮጵያውያንን ከኬንያውያን ወይም ከእንግሊዞች ወይም ከፈረንሳዮች የሚለየን መሰረታዊ ጠባያት ማለት ነው በሌላ አባባል አማራውን ኦሮሞውን ጉራጌውን ወላይታውን ሲዳማውን ወይም ጉምዙን ኢትዮጵያዊ ያደረገው የጋራ ማንነት ምንድናቸው ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ማለት ነው ስለዚህ የጋራ ታሪክ አለን? የጋራ ቋንቋ አለን? የጋራ ባህል አለን? የጋራ ግዛት አለን? ወዘተ ጉዳዮች መልስ ሲያገኙ ወደ ሌሎች ተናጥላዊ ጉዳዮች ልንሄድ እንችላለን በጋራ ማንነት ዙሪያ በአንዳንድ አማተር ወይም ዘረኛ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያዊነትን ሲነሳ አሀዳዊነት እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ ወይም የድሮ ሥርዓት ናፋቂነት አድርገው ሲፈርጁ ይስተዋላሉ። በዚህም ምክንያት የባለፈው የሶስት አሰርት ዓመታት ትውልድ ታሪኩን አንድም አያውቅም አንድም በተዛባ መንገድ የተረዳ ነው። ምናልባትም በራሱ ጥረት ብስልን ከጥሬው ለመለየት ጥረት አድርገው ትቂቶች ዉጪ ማለት ነው።
በመሆኑም የጋራ ማንነታችንን (National character) መለየት ሁሉም ዜጋ የጋራ ባደረጉን ማንነቶች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ይፈጥራሉ ከልዩነት ይልቅ ለጋራ ማንነታችን ትኩረት ይሰጣሉ በጋራ ማንነታችን ከተግባባን በሕዝቦች መካከል አመኔታ ይፈጠራል ጥርጣሬ ይወገዳል በዚህም ምክንያት አንድ በመሆን ከሚገኙ ትሩፋቶች ሁሉም በጋራ የመጠቀም መብት እንዳለው ይገነዘባል።
ለምሳሌ:- ጠላትን በጋራ መከላከል እንደሚችሉ ሁሉም አባል ሕዝቦች ያውቃሉ ስለዚህ የጋራ ብሄራዊ ጠባያት ከለየን በኋላ ወደ ተናጥል `ጉዳዮች በዝርዝር መግባት ይቻላል::
በዚህ መሰረት፡- አንደኛ- የጋራ ሕገ መንግሥት ሁለተኛ- የጋራ ሰንደቅዓላማ ሶስተኛ- የጋራ ብሄራዊ መዝሙር አራተኛ-የጋራ ቋንቋ ናቸው አንደኛ- ሕገ መንግሥት ለአገረ መንግሥት ግንባታ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በታሪክ ወይም በትርክት በፌዴራሉ የጋራ መቀመጫ ሳይቀር ፖለቲካዊ አጀንዳው ሆነው ሳንግባባባቸው ቀጥለዋል ነገር ግን በእኔ እምነት ለአገረ መንግሥት ምስረታ መሠረታዊ ጉዳዮች ከላይ ከእንድ እስከ አራት የተዘረዘሩት ጉዳዮች ብቻ ናቸው ማለት ባይሆንም በእነዚህ አራት ጉዳዮች መግባባት ከተቻለ በተለይ በሕገ መንግሥቱ ይዘት ላይ የጋራ ስምምነት መያዝ ከተቻለ ከ90 ፐርሰንት በላይ በጋራ ችግሮቻችን ላይ መግባባት እንችላለን ስለዚህ እያንዳንዱን ጉዳይ በዝርዝር ማየቱ ተቃሚ ነው።
በመሠረታዊነት በሰለጠነው ዓለምም ሆነ በአፍሪካ አገራት ሕገ መንግሥታት ሁለት መሠረታዊ ፍላጎት (Intention) ያንጸባርቃሉ እነዚህም በአንድ አገር ውስጥ ብዝሀ ብሄር ቋንቋ ባህል ወይም ሃይማኖት ካለ ልዩነትን ማጉላት ወይም የሚያበረታታ ሲሆን በሌላ በኩል ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ማበረታታት ዓላማ ያላቸው ሕገ መንግሥታት አሉ።
ከእኛ ሁኔታ አንጻር በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በመግቢያው እንደ ዓላማ ከተቀመጡት ሃሳቦች ውስጥ አንደኛው የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን በነጻ ፍላጎታችን በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ በጋራ መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ ያስቀምጣል።
በአንጻሩ ደግም እስካሁን በተለያዩ ፖለቲከኞች የተለያዩ አቋም ከሚያዙባቸው ጉዳዮች አንዱ አንቀጽ 39 የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን አንቀጽ ነው።
ወጣም ወረደም አሁን ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚያሰፋ እና የሚያበረታታ ስለመሆኑ ገሀድ ነው በመሆኑም ጋራ አቋም ሊያዝባቸው ከሚገቡ መሠረታዊና ቀዳሚ ጉዳዮች መካከል በሕገ መንግሥቱ ይዘት ላይ ብቻ ሳይሆን በቅርጹም ላይ ስምምነት (Consensus) መደረስ አለበት።
ከዚህ አንጻር የእኛ ሕገ መንግሥት ምን መሆን አለበት የሚለውን ጉዳዩ ለጉዳዩ ባለቤቶች እንተወውና ከሌሎች አገራት ልምድ ለዛሬ የናይጀሪያን ልምድ ማንሳት ጠቃሚ ነው። ናይጀሪያ እ.ኤ.አ በ1960 ከብሪቲሽ ቅኝ ግዛት ነጻነቷን ካረጋገጠች በኋላ ከቅኝ ግዛት አገዛዝ መንፈስ ተላቃ እንደአገር ለመቀጠል የቅኝ ግዛት አንጎበር ከፍተኛ ተግዳሮት ነበረባት ምክንያቱም የቅኝ ግዛት አስተዳደር መርህ ከፋፍለህ ግዛ የሚል ስለነበሩ የሃይማኖት የባህል የጎሳ እና የቋንቋ ልዩነቶችን ለቅኝ መግዢያ መሳሪያነት ተጠቅመውበታል።
ሆኖም ግን ከነጻነት በኋላ ትኩረት ሰጥተው የሰሩት አገራዊ አንድነትን (National Integration) የማጠናከር ስራ ነበር ሆኖም ግን በየክልሉ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች (Nationalists) ጎሳን ወይም ክልልን መሠረት ያደረጉ ፓርቲዎች ለምሳሌ የኡርባ የባህል ንቅናቄ፤ የኦዱዋ ተከታዮች ማሕበር የሰሜን ሕዝቦች ኮንግሬስ ወዘተ እንቅስቃሴ በመጀመራቸው የብሄር ውጥረት ብቻ ሳይሆን ልዩነቶች እየሰፉ በመሄዳቸው ምክንያት ለደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ሊገቡ ችለዋል።
ከዚህም አልፈው አንዳንድ ግዛቶች የራሳቸውን ነጻ መንግሥት እስከመመስረት የደረሰቡት ሁኔታ ነበር ለምሳሌ ግንቦት 1967, Lt. Col. Chukwuemeka Odumegwu Ojukwu, የምስራቅ ናይጀሪያ ወታደራዊ ገዢ the independent Republic of Biafra ብሎ በማወጁ ከ1967 እስከ 1970 ድረስ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ተካሂዷል። ነገር ግን የቢያፍራ ጦር ልክ እንደአሁኑ የእኛው ሕወሓት ተቀጥቅጦ ከተደመሰሰ በኋላ የናይጀሪያ ሕዝቦች አንድነታቸው ይበልጥ የተጠናከረበትን ሀኔታ ፈጥሯል።
ከእርስ በርስ ጦርነቱ መጠናቅ በኋላ የኛይጀሪያ መንግስት Gen. Yakubu Gowon በጦርነቱ ድል አድራጊም ተሸናፊም የለም ጦርነቱ የሁለት ወንድማማቾች ጦርነት እንደሆነ በማወጅ እና ሶስቱ R (Three R’s: rehabilitation, reconciliation, and reconstruction) ፖሊሲ በመንደፍ በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችንና ተቋማትን መልሶ በመገንባት እንዲሁም ከተቋማት እስከ አገልግሎት የለውጥ ወይም የሪፎም ስራዎች እንዲሰሩ አድርጓል።
ሆኖም የዚህ ጽሁፍ ዋናው መልእክት የሪፎም ስራዎች በተለይ የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት በኢትዮጵያ ልዩ ልኡክ እና የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት Mohammed-Obasanjo ስኬታማ የሆነ ለውጥ ማምጣት በቻሉባቸው ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ነው። በዚህ ረገድ ክልላዊ ፖለቲካ ወይም የጎሳ ፖለቲካ የፈጠረውን ችግር ለመፍታት አዳዲስ የፖለቲካ ተቋማት እና አስተሳሰብ ተግባራዊ አድርገዋል። ለምሳሌ በክልሎች ወይም በጎሳዎች እጅ የነበረውን ሥልጣን ለመቀነስ አስራ ሶስት የነበሩትን የክልል መንግሥታትን ወደ 19 ክልሎች ከፍ እንዲሉ አድርገዋል። ሁለተኛው ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል አገራዊ አንድነተትን ለማሳደግ የመንግሥት አወቃቀሩን የአሜሪካን አይነት ፕሬዝዳንታዊ የመንግሥት ሥርዓት አድርገውታል። እንዲሁም በፓርቲነት የሚመዘገቡ ድርጅቶችም አባሎቻቸው በሁለት ሶስተኛው ክልሎች የተውጣጡ እና ብሄራዊ ዓላማ ያላቸው እንዲሆኑ በሕገ መንግሥቱ እንዲካተት ተደርጓል።
ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት ለመተማመን ይረዳን ዘንድ የኢንግሊዝኛውን እንዳለ ማቅረብ ወደድኩ Another provision of the 1979 constitution aimed at eliminating past loopholes was the “federal character principle.” This was an affirmative action principle requiring that appointments to top government positions be made to reflect the regional and ethnic diversity of the country. This principle also applied to the composition of the armed forces and the distribution of national resources. ከሕገ መንግሥት ጉዳዮች ጋር የተያያዙትን ለማጠቃለል ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት በኢትዮጵያዊነት ማአቀፍ ወስጥ የበለጸገች ኢትዮጵያን በመፍጠር ሁሉም ዜጎቿ ባይተዋር ያለሆኑባት ኢትዮጵያ ለመገንባት የፌዴራሉም ሆነ የክልሎች ሕገ መንግሥታት እንደገና ሊቃኙ ይገባል ምክንያቱም ከላይ ለማየት እንደተሞከረው የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አገራዊ አንድነትን (National Integration) የሚያበረታታ ሳይሆን ልዩነትን በማስፋት በዜጎች ወይም በብሄሮች መካከል ጥርጣሬን ማንገስ ነው።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የቀደሙትም ተመሳሳይ መልክ ነው ያላቸው። ለምሳሌ የአጼ ኃይለስላሴ በፈረንጆች የ1929 ይሁን የ1955 ሕገ መንግሥት ንጉሱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ብቻም ሳይሆኑ በኢትዮጵያ ግዛት ወስጥ ያሉት የውሃ የየብስ ደሴቶች ሳይቀሩ የንጉሱ ናቸው የደርግ በፈረንጆች የ1987 ሕገ መንግሥትም 10 ፐርሰንት የሆነው ወዛደሮች እንጂ 90 ፐርሰንት ሆኑት አርሶ አደር እና የከተማ ነዋሪ አልነበሩም።
የሥልጣን ባለቤት በተመሳሳይ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥትም ኢትዮጵያን በጥቅል ከማንሳት ይልቅ በክፍልፋይ በማንሳት ከአገራዊ ማንነት ይልቅ ለቡድናዊ ማንነት ነበር ዋጋ የሰጠው በተመሳሳይ የክልሎች ሕገ መንግሥታትም በፌዴራሉ ሕገ መንግሥታዊ ማእቀፍ ውስጥ የተቀረጹ በመሆናችው አንደኛ ዜጋና እና ሁለተኛ ዜጋ ያለ በሚመስል መልኩ የተቃኙ ናቸው።
ለምሳሌ ለብያኔ ይመቻችሁ ዘንድ የአማራ ብ/ክ ህገ መንግሥት እኛ የአማራ ክልል ሕዝቦች ፣የአፋር እኛ የአፋር ሕዝብ ሲል ፣የቤኒሻንጉል ጉሙዝ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች የሚታወቁ ቢሆንም የክልሉ ባለቤት ብሄር ብሄረሰቦች በርታ ጉሙዝ ሺናሻ ማኦና ኮሞ ናቸው የደቡብ ክ/መ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች የክልሉ መንግሥት ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች ናቸው።
የኦሮሚያ ብ/ክ/መ የኦሮሞ ሕዝብና በኦሮሚያ ውስጥ ለመኖር የመረጡ ወዘተ በሚል የተቀመጡ በመሆኑ ሕገ መንግሥታቱ መመዘን ካለባቸው ለአገራዊ አንድነት በሚሰጡት ቦታ በአቃፊነታቸው በዜጎች እኩልነት እና በሕገ መንግሥቱ ፍላጎት (intention) ወዘተ ስለሚሆን የምክክር ኮሚሽኑም ይሁን አንባቢው ሊበይን ይችላል። በቀጣይ ቋንቋ በሄራዊ መዝሙር እና ሰንደቅ ዓላማ ለአገራዊ አንድነት የሚኖረውን ፋይዳ እንዳስሳለን::
እንዳለ ሀ. (ዶ/ር)
አዲስ ዘመን ጥር 3/2014