ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተፈጠሩና ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የመጡ ያልተቋጩ ሃሳቦች፣ በይደር የቆዩ አለመግባባቶች እንዲሁም አገር ትቀጥል ዘንድ ቅድሚያ ተነስቷቸው የቆዩ የማያግባቡ አጀንዳዎች የተሸከመች አገር ናት።
ውይይት የሞት ያህል የሚከብድበት፣ በአመለካከት የሚለዩ በጠላትነት የሚፈረጁበት አገር ሆናም ዓመታትን አስቆጥራለች። ‹‹እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ›› እኔ የማስበው ሁሌም ትክልልነው›› የሚል የአመለካከትና የባህሪ ችግር ኢትዮጵያን ረጅም ጊዜ ሲያደማት ከርሟል።
ይሁንና በአንድ አገር ማሕበራዊ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ላይ ውይይት በሳል ውሳኔን በማመንጨት፤ መተማመንን በማዳበር፤ ሕብረትን አንድነትን በማጠናከር፤ እንዲሁም አሰራርን ለማሻሻል እጅግ ወሳኝ መሆኑ አያከራክርም።
አገሪቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት የአሳታፊነት ባህልና ልምድ የሌለባት መሆኑ ደግሞ ችግሮች በቀላሉ ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙ፣ ውስጥ ውስጡን እንዲብላሉና ከትናንት እስከ ዛሬ እንዲከተላት ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይታል።
ይሁንና ከህልውና ባሻገር ስለ መፅናትና መቀጠል እንዲሁም ስለ ሁለንተናዊ እድገት ሲታሰብ ለእነዚህን ልዩነቶና አጀንዳዎች መፍትሄ መስጠት የግድ ያስፈልጋል። በተለይ ባለፉት ዓመታት የውይይት እሳቤ በኢትዮጵያ ምድር እውን ይሆን ዘንድ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ከተለያዩ አካላት ሲነሳ ቆይቷል።
‹‹ይሁን›› የሚል መልስ የሰጠ መንግሥት ግን አልነበረም። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግሥትም በአንጻሩ ይህን ታሪክ ለመለወጥ በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ቁጭ ብሎ ከመምከር በሩን ክፍት አድርጓል።
ውይይቱ እውን ይሆን ዘንድ በሁሉ ረገድ ፈቃደኛ መሆኑን የሚያመላክት እርምጃዎን እየተራመደ ይገኛል። ከቀናት በፊትም የአገራዊ የምክክር ኮሚሽንም አቋቁማል።
ኮሚሽነሮችን በሕዝብ ይሁንታ እንዲያገኙ ምርጫውን ተሳተፉ ብሏል። መድረኩም ከታች ከቀበሌ እስከ ላይኛው የመንግሥት መዋቅር፤ ከቸርቻሪ እስከ ጅምላ አከፋፋይ እስከ አስመጪና ላኪ ባለሀብት ነጋዴ፤ ከቀን ሰራተኛ ላብ አደር እስከ ፋብሪካ ባለቤት፣ ከለምኖ አዳሪ ደሃ አለ እስከተባለው ተሞላቆ ኗሪ ሀብታም፤ አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር ሁሉም እንደየአቅሙ የሚተነፍስበት፤ ተነጋግሮ የሚግባባበት፤ ዕድል ሊፈጠር እንደሚችል ይታመናል።
ይሁንና በኢትዮጵያ ምድር አገራዊ ምክክርና መግባባት እንዲፈጠር፣ መደማመጥ የግድ ነው። አንዱ ሌላውን ሲያዳምጥ ተራራው ሁሉ ተንዶ ሜዳ ይሆናል። ዳገቱን ለመውጣት ላብ እስኪያሰምጥ አጎንብሶ መፍጨርጨር ቀርቶ ቀና ብሎ መራመድ ይቻላል። ድካም ይቀንሳል፤ በደስታ የመኖር ዕድል ሰፍቶ ሕይወትን ማጣጣም ቅንጦት መሆኑ ያበቃል።
አገራዊ የምክክር መድረኩ ከሚፈጥራቸው እድሎች አንዱ ሌላውን ሲያዳምጥ በተለይ በአንኳር አገራዊ ጉዳዮች ላይ መደማመጥ ስፍራ አግኝቶ ብሔራዊ መግባባት ይፈጥራል። “ወንዞች ሁሉ ወደ አንድ አቅጣጫ ይፈሳሉ” የሚለው አባባል በኢትዮጵያ ምድር እውን ይሆናል።
ታዲያ ለእዚህ ከመሠረቱ እያንዳንዱ ሰው በሁሉ ረገድ በተለይም በአስተሳሰብ መሠልጠን ይኖርበታል። በሆደ ሰፊነት የሚቀርቡ ሃሳቦችን መካፈል፣ ዕይታን ለማስፋት ዝግጁ መሆን፤ የራስን ሃሳብ በትክክል ማቅረብና ምክንያታዊ መሆን ይጠበቅበታል።
መድረኩን ውጤታማ ለማድረግ ጥቅም ከራስ አንፃር፤ ከግለሰብ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከቤተሰብ ከዘመድ፣ ከጎሳ፣ ከብሔር እና ከአካባቢ አንፃር ብቻ አይቶ ሙግት መግጠም አያዋጣም። ጉዳዮችን ከአገር ጥቅም አንፃር በመመዘን ለተሻለው ሃሳብ ዕድል መስጠት ይበጃል።
በየመድረኩ ውይይቶች ሲካሔዱም ማን ምን እንደሚሰማው እድል መስጠት ያስፈልጋል። የተሰማው ስሜት ተገቢ ነው አይደለም ብሎ ከመከራከር ይልቅ ራስን በዛ ሰው ጫማ ከቶ ማሰላሰል እና እንዲናገር እድል መስጠት የግድ ይላል።
ሃሳብን በቀናነት መቀበልና መተማመን ፣ ከመከራከር ይልቅ ለመተማመን መመካከርን ብቻ ታሳቢ ማድረግም ግድ ነው። አንድ መታወቅ የሚኖርበት አብይ ጉዳይ ቢኖር ማንንም ቢሆን ያለፈ ታሪክ ሊያጣላው፤ ያለፈ ታሪክ ጦርነት እና ቁርሾ ውስጥ ሊከተው አይገባም።
መድረክ ተመቻችቶ የመናገር ዕድል ሲገኝ የሚሰማን ስሜት ሥርዓት ባለው መልኩ በትህትና መግለፅ ሲገባ፤ አድበስብሶ አልፎ ማጉተምተምና መድረኮችን ማንኳሰስ አይበጅም። እድልን መጠቀም የሚያስቡትን ማንፀባረቅ የግድ ነው።
በየቤቱ ጓዳ የሚወሩ ክርክር የሚያስነሱ ጉዳዮች አደባባይ ላይ ቁልጭ ብለው መታየት አለባቸው። ለአደባባይ ከበቁ በኋላ መውደቅ ያለበት ሃሳብ በመነጋገርና በመተማመን ይወድቃል። የበላይ ሊሆን የሚገባው ሃሳብ እና እውነት ቦታ አግኝቶ ይቀመጣል። በተቃራኒው ማዳመጥ አልፈግም ብሎ ወከባ መፍጠር፤ በታሪክ እና በነባራዊ ሁኔታ ተጎድቻለሁ ብሎ ምክንያት መደርደር፤ ‹‹ እኔ ብቻ ልደመጥ›› ብሎ መረበሽ፤ ከኔ ወዲያ ላሳር እያሉ መታበይ ምክክሩ ላይ ሳንካ ይፈጥራል።
አንድ ሰው ሃሳብ ከሰጠ በኋላ የተናገረው ሰው ትክክል አለመሆኑ ከታመነ፤ ወይም የተሻለ ሃሳብ ከፈለቀና የሃሳብ የበላይነት ከመጣ፤ የተሳሳተው ለመታረም ዝግጁ መሆንም ይጠይቃል። እንደደረቀ እንጨት በውስጥ ያለ የተደጋገመ ውሸት ላይ ሙጭጭ ብሎ እምቢ አልረታምም አይነት አካሄድ ለማንም እንደማያዋጣም መረዳት ያስፈልጋል። የደረቀ እንጨት መሰበሩ አይቀርም።
ራስን ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም ማዘጋጀት፤ ይልቁኑ ሌሎችም በተሳሳተ መንገድ እየተጓዙ ያሉትን ለመመለስ መሞከር የተሻለ አማራጭ መሆን ይኖርበታል። ማንም የፈለገውን ቢናገር ሌላው ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን አለበት። “ነገርን ከሥሩ እንደሚባለው” ነገሮችን በግልፅ ከመሠረቱ ጀምሮ ማዳመጥ ትልቅ መፍትሔ የሚመጣበትን ዕድል ለመፍጠር ያግዛል።
ትንሽም ሆነ ትልቅ በምንም መልኩ የሚጎረብጡ አገራዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶባቸው በግልፅ ተቀራራቢ ሃሳብ እና እምነት ተይዞባቸው የሚፈፀሙ መሆን ይችላሉ። ይህ ሲሆን ራሳቸውን እንደባይተዋር የሚቆጥሩ ብዙዎች የኢትዮጵያ ቤተሰብ እና ቤተኛ ይሆናሉ። ሁሉም የቤተኛነት ስሜት ሲሰማው ተደማምጦ ተነጋግሮ በአንድ መንገድ ለመጓዝ ያመቻል።
ተራርቆ ማዶ ለማዶ ጥግ ይዞ ጣት መቀሳሰር ያበቃል። መሃል ላይ ያለው ባሕር ድልድይ ተሠርቶለት ለመገናኘት የማያዳግትበት ደረጃ ላይ ይደረሳል። በየትኛውም አካል ለአገር እና ለሕዝብ የሚጠቅመውን በመለየት በየዓይነቱ በደርዝ እየቀረበ፤ በቀናነት ሁሉም እየተቀራረበ መነጋገር እና መደማመጥ ሲችል፤ እውነታውን ለማስቀመጥ ጥረት ሲደረግ የአገር ስኬት በአስተማማኝ መሰረት ላይ ይገነባል።
ተመጣጣኝ ዕድገት መረጋገጥ ይጀምራል። የሞራል አስተማማኝ እድገት ሲመጣም ኢትዮጵያችን የዓለም አውራ የምትሆንበት ጊዜ ያቀርበዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥር 3/2014