የዓለም ታሪክ ሴቶችን በስፖርት ዓውድ መመዝገብ የጀመረው ዘግይቶ ነው ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጥቂት ሴቶች በስፖርቱ ተሳትፎ ከማድረጋቸው በፊት ሴት ልጅ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የመሳተፍ አካላዊ ብቃት የላትም የሚል አመለካከት ነበር። በዚህ የተነሳም ሴቶችን ስፖርት ሜዳ ውስጥ መመልከት እንደ ነውር ይቆጠር ነበር። ይሁንና በጥቂቶች እንዲሁም የተሻለ እሳቤ በነበራቸው ሰዎች ጥረት የሴቶች የስፖርት ተሳትፎ እውን ሆኖ ዛሬ ካለው ነባራዊ ሁኔታ መድረሱን ታሪክ ያወሳል። የኢትዮጵያ ልምድም ከሌላው ዓለም የተለየ አልነበረም።
ሴት ልጅን ከጓዳ ብቻ ያዛመደውን ልማድ ለመቅረፍ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። ተሳትፎው በሂደት እየጎለበተም በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ስፖርቱን ቋሚ ሥራቸው በማድረግ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል እስከ መፍጠር ደርሰዋል። ብቃታቸውም ቢሆን ከኢትዮጵያም ባለፈ በኦሊምፒክም ጭምር ባስመዘገቡት ድል ተመስክሮላቸዋል። በ1990ዓ.ም በወጣው የኢፌዴሪ ስፖርት ፖሊሲ ላይ «ሴቶች በስፖርት እንቅስቃሴ ቀጥተኛ ተሳታፊና በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል» በሚል ሰፍሯል።
በዚህም መሰረት ከወንዶች እኩል በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችም ሆነ ሙያዊ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል። ይህ ብቻውን በቂ ባለመሆኑም በሴቶች እየተመራ ሴቶች ብቻ የሚፎካከሩበት መድረክም ተዘጋጅቶላቸዋል። ሴቶች በስፖርት ተሳታፊ በመሆናቸው በቅድሚያ ጤናቸውን ለመጠበቅ፣ የአካል ብቃታቸውን ለማዳበር እንዲሁም ተፈጥሯአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመቋቋም ያስችላቸዋል። ከዚህ ባ ሻገር በራስ የመተማመን ብቃታቸውእንዲያድግ፣ በስፖርት ምክንያት እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት እንዲዳብር እና የስፖርት ስነ- ምግባርንና ባህልን እንዲያውቁ የሚረዳቸው መሆኑን በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ናስር ለገሰ ይገልጻሉ።
በዚህም ከ2007ዓ.ም ጀምሮ «የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታ» በሚል በየሁለት ዓመቱ ውድድር ይካሄዳል። ውድድሩ ክልሎች የየራሳቸውን የውስጥ ውድድር ካጠናቀቁ በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ነው። የመጀ መሪያው ውድድር በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስተናጋጅነት ሲካሄድ፤ ሁለተኛው ደግሞ በሃረር ከተማ ተደርጓል። ሦስተኛው የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታም ትናንት በጅግጅጋ ከተማ አስተናጋጅነት መካሄዱን ጀምሯል።
ውድድሩ በሌሎች ውድድሮች የመሳተፍ ዕድል ያላገኙ ሴት ስፖርተኞች አጋጣሚውን እንዲጠቀሙበት እንዲሁም በመምራት በኩል ያላቸውን የራስ መተማመንም እንዲያሳዩ ይረዳቸዋል። የተሻሉና አገራቸውን መወከል የሚችሉ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚቻልበት ነው። የመገናኛ ብዙሃንን ሽፋን ማግኘታቸውም ውጤታማ ስፖርተኞች የሚበረታቱበት እንዲሁም ለክለቦችና ብሄራዊ ቡድኖች የሚታጩበት ዕድልም ያስገኝላቸዋል። ከዚህ ባሻገር ጥቂት ሴት የስፖርት ባለሙያዎች ከአገርም አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃም በመስራት ላይ እንደሚገኙ የሚጠቅሱት ዳይሬክተሩ፤ ከመሰረቱ መስራት ከተቻለ የተሻለ ተሳትፎ እንደሚኖርም ይጠቁማሉ።
ነገር ግን በርካታ ሴት ባለሙያዎች በሌሉ ባቸው ስፖርቶች ላይ ወንዶች እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፤ በሂደት ሴቶችን በማብቃት ወንዶቹ እንደሚቀነሱም አቶ ናስር ይጠቁማሉ። በመጀመሪያው ውድድር የነበረው የባለሙያዎች ተሳትፎ አናሳ ቢሆንም፤ በሁለተኛው ግን የተሻለ ቁጥር ለመመልከትም ተችሏል። በየውድድሩ መሻሻል እየታየ ሲሆን፤ ይህም በተለያዩ መንገዶች ይረጋገጣል። በክልሎች በኩል የእኔነት ስሜት በማሳደር ላይ እንደሚገኝ ክልሎች ከሚሰጡት ግብረ መልስ ለመረዳትም ይቻላል። ከባለሙያዎች ባሻገር ውድድሩ በየዓመቱ የተሳታፊዎቹን ቁጥር እንዲሁም ውድድር የሚካሄድባቸውን ስፖርቶች እያሳደገ ሲሆን፤ የባህል ስፖርት እንዲሁም መስማት የተሳናቸው በውድድሩ ተሳታፊ እንዲሆኑም ተደርጓል። የተሳታፊዎች ብዛትም እየጨመረ ይገኛል።
በመጀመሪያው 500 ስፖርተኞች ተካፋይ ቢሆኑም በሁለተኛው 700መድረስ ችለዋል። አሁን ደግሞ ከ 2ሺ በላይ ሴት ስፖርተኞች ተሳታፊ ሆነዋል። ሴቶች በስፖርቱ ያላቸው ተሳታፊነት ሲጎለብትም በማህበራዊ ህይወታቸው እንዲሁም በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከፍተኛ ይሆናል። ይህንን የሚደግፍም መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን፤ «ስፖርት ለሁለንተናዊ ለውጥ» የሚል ነው። ስፖርቱ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሰራ ለስፖርቱ ዕድገት እንዲሁም ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማንገስ ሚናቸው ከፍተኛ ይሆናል።
ህግ ማክበርን እንደሚያስተምሩ የሚጠቁሙት ዳይሬክተሩ፤ ለስህተቶች ላለመጋለጥ በጥንቃቄ እንደሚሰሩም ያረጋግጣሉ። ይህንንም ደግሞ ከዚህ ቀደም በተካሄዱት ውድድሮች ላይ በትክክል ለመገንዘብ ተችሏል። በርካታ የሚያስተምሩት ነገር እንደመኖሩም በስፖርቱ ዕድገት ላይ ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ ባሻገር ለውጥ ማምጣት ይችላሉ። ጤንነታቸው ሲጠበቅም በኢኮኖሚው ላይ የራሳቸው የሆነ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በብርሃን ፈይሳ