ሴቶች በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከወንዶች እኩል ከመሳተፍም ባሻገር በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመቀመጥም ስፖርቱን በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ፎርብስ የተሰኘው መጽሄት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ የዓለምን ስፖርት በበላይነት በመምራት ላይ የሚገኙ ሴቶችን ስም ዝርዝር አስታውቆ ነበር። የዛሬውን የሴቶች ቀን አስመልክቶም ጥቂቶቹን እንቃኝ፡- ቀዳሚዋ ፋጢማ ሲምባ ዲዩፍ ሳሙራ ናቸው። እኚህ ሴኔጋላዊት የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት በሚመራው ፊፋ ውስጥ ሁለተኛዋ ሰው ለመሆን ችለዋል። እ.አ.አ በ2016 የፊፋ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ፋጢማ፤ ይህንን ስልጣን የተቆናጠጡ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው።
ኃላፊነታቸውም ከፕሬዚዳንቱ ቀጥሎ የትኛውንም አመራር እንዲሁም ውሳኔ እንዲሰጡ የሚያደርጋቸው ሲሆን፤ በተለይም ከገንዘብ ጋር የተያያዘው ሥራ እርሳቸውን ይመለከታል። በዚህም እ.አ.አ ከ2016-2018 ድረስ 5ነጥብ6 ቢሊዮን ብር አንቀሳቅሰዋል። የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዲሁም የፊፋ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ብሩንዲያዊቷ ሊድያ ሳቃራ ደግሞ በዝርዝሩ ላይ ሁለተኛዋ በዓለም ስፖርት ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴት ናቸው። እ.አ.አ በ2013 የፊፋ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት እኚህ ሴት በወቅቱ የመጀመሪያዋ ሴት አባል ነበሩ።
ከዓመታት በፊት በፊፋ በተለይ ይስተዋል የነበረውን ሙስና በማጋለጥ እንዲሁም በመታገል ረገድም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውም ይነገርላቸዋል። በኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል በመሆን ወንበር የያዙትም እ.አ.አ ከ2009 ጀምሮ ነው። ፈረንሳዊቷ ፍሎረንስ ሃርዶን በዓለም ስፖርት አመራርነት ያላቸው ቦታ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣቸዋል። የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሥራ አስፈጻሚ አባል እና የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተሯ ናቸው። ከስፖርተኛነት ወደ አመራርነት የመጡት የአገራቸውን ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር በመቀላቀል ነበር። እ.አ.አ ከ2008 ጀምሮም ፌዴሬሽኑን በመምራት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት በሩሲያ ዓለም ዋንጫ ብሄራዊ ቡድኑ የዋንጫ ባለቤት መሆኑ እንደ ስኬት ይነሳላቸዋል።
ከአገራቸው አልፈው የአህጉር አቀፉን ማህበር የተቀላቀሉት እ.አ.አ በ2016 ሲሆን፤ በወቅቱም የመጀመሪያዋ ሴት ነበሩ።አራተኛዋ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴት ቻይናዊቷ አንጌላ ዶንግ ናቸው። ናይኪ የተባለው የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶንግ፤ በውጤታማነታቸው ተስተካካይ የላቸውም።ወደ ፕሬዚዳንትነቱ የመጡት እ.አ.አ በ2015 ሲሆን፤ ገቢውን ወደ 4ነጥብ 237 ቢሊዮን ዶላር በማሳደግ ውጤታማነታቸውን አስመስክረዋል። ይህም ድርጅቱ ቀድሞ ከሚያገኘው ገቢ የ1ነጥብ2 ቢሊዮን ዶላር ብልጫም ያለው ነው። ማሪና ግራኖቭካይ፤ የእንግሊዙ ክለብ የቼልሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት የሩሲያና ካናዳ ዜግነት አላቸው። እ.አ.አ ከ2010 ጀምሮ የክለቡ ባለቤት የባለሃብቱ ሮማን አብራሞቪች ተወካይ ነበሩ።
እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ ግን የክለቡን ቦርድ በመቀላቀል በአመራርነት እየሰሩ ይገኛሉ። ዋነኛው ሥራቸውም ከክለቡ የተጫዋቾች ዝውውር ጋር የተያያዘ ነው። ባርባራ ስላተር ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ዘገባዎችን በቢቢሲ ስፖርት በኩል ለዓለም በማሰራጨት የሚታወቁ ጋዜጠኛ ናቸው። እንግሊዛዊቷ ባርባራ ወደ ጋዜጠኝነቱ ከመግባታቸው አስቀድሞ የጂምናስቲክ ስፖርተኛ ነበሩ፤ በዚህም እ.አ.አ 1976 አገራቸውን በኦሊምፒክ መድረክ ወክለዋል። እ.አ.አ ከ1983 ጀምሮም ቢቢሲን በመቀላቀል፤ እ.አ.አ በ2009 የስፖርት ክፍሉ ዳይሬክተር የሆኑ የመጀመሪያዋ እንስት ናቸው።
አውስትራሊያዊቷ ሞያ ዶድ የእስያ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እንዲሁም በፊፋ የተጫዋቾችን ጉዳይ በሚመለከተው ኮሚቴ አባል ናቸው። እኚህ ሴት ፊፋን በአባልነት በመቀላቀል ቀዳሚ ከሆኑት እንስቶች መካከል አንዷ ናቸው። የቀድሞዋ እግር ኳስ ተጫዋች የአውስትራሊያ ብሄራዊ ቡድን አባል በመሆን በዓለም ዋንጫም ተሳትፈዋል። በተለይ የሚታወቁት ግን በፊፋ ስላለው ሙስና በግልጽ በመቃወም እንዲሁም በሴቶች ስፖርት ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነው። ፎርብስ በዝርዝሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ባያካትትም በስፖርት አመራርነት ላይ ያሉ በርካታ ሴቶች ግን አሉ። ከእነዚህ መካከል በቅድሚያ ተጠቃሽ የምትሆነው ደግሞ ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ናት። የቀድሞዋ ስኬታማ አትሌት አሁን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚ ዳንትነት ትመራለች። በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል ናት። ደራርቱ ከኢትዮጵያ ባለፈም የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮን ፌዴሬሽን የቦርድ አባል በመሆንም በቅርቡ ወደ ሥራ ገብታለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በብርሃን ፈይሳ