በጦርነት መጀመሪያ ላይ በሚካሄዱ አውደ ውጊያዎች በማን አለብኝት ወረራ የሚፈጽሙ አምባገነኖች በአብዛኛውን ጊዜ አሸናፊዎች ሲሆኑ ይታያሉ:: ወረራ የተፈጸመበት ወገንም ወራሪውን ፈጽሞ ሊመክተው የሚችል አይመስልም:: ማንም ሰው ጦርነቱን ማን ያሸንፋል? ገምት፤ ቢባል ግምቱ ጦርነቱን ለጀመረው ኃይል ማድረጉ አይቀሬ ነው ::
ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ አምባገነኖች ራሳቸውን ለጦርነት ቀድመው ስለሚያዘጋጁ እና በተቃራኒው የሚወረው አካል ደግሞ ራሱን ስለማያዘጋጅ እና ስለማያደራጅ ነው :: የኋላ ኋላ ግን የተወረረው አካል የተበዳይነት ቁጭት ስለሚያድርበት የወራሪውን ኃይል በእርግጠኝነት ማሸነፉ አይቀርም ::
የዓለም የጦርነት ተሞክሮች የሚያሳዩት ይህንን ሐቅ ነው :: ለዚህ ደግሞ አያሌ ምሳሌዎች ማሳየት ይቻላል :: ለዛሬው የተመረጡ ሶስት ጦርነቶችን በወፍ በረር እንመልከት:: አምባገነኖች በትዕቢት ሲወጠሩ ሕሊናቸው ግራ እና ቀኙን ፤ ፊት እና የኋላውን ማየት ስለሚያቆም ምድር ላይ ያለ ማንኛውም ኃይል ያለእነርሱ ፈቃድ መኖር እንደማይችል አድርገው ማሰብ ይጀምራሉ::
በእኔ ልክ የተቀደዱ ልብሶችን ልበስ ! ብለው ማስገደድ ይጀምራሉ:: ከዜጎቻቸውም አልፈው የጎረቤት አገራትን ሰላም ያውካሉ:: ከማወክም አልፈው ወረራ ይፈጽማሉ::
ከእነኝህ ዓይነት ሰዎች መካከል ናፖሊዮን ቦናፓርት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል:: ናፖሊዮን ቦና ፓርት መላ አውሮፓን መግዛት አለብኝ ብሎ ቆርጦ ተነሳ፤ የሚችለውንም ያህል ወረረ::
በዚህ ጊዜ አውሮፓውያን ናፖሊዮ ቦና ፓርትን ከፈጣሪ በታች ያለ ፈጣሪያቸው እስኪመስላቸው ድረስ አግዝፈው አዩት :: ናፖሊዮን ቦናፓርት በበኩሉ ራሱን ከፈጣሪው ጋር አስተካክሎ ተመለከተ:: የትኛውም ምድራዊ ኃይል ሊገዳደረኝ አይችልም ሲል ለራሱ ነገረ::
በድሮ ጊዜ አንዱን ፈላስፋ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት «ሊያዝኑለት የማያስፈልግ እና የማይገባው ነገር ምንድን ነው?» ፈላስፋውም « የክፉ ሰዎች መሞት !» አለ:: ናፖሊዮንም በአውሮፓ የክፉዎች ክፉ ተደርጎ ይቆጠር ስለነበር አውሮፓውያን በሰውየው ግብዝነት ቢያዝኑለትም የሠራቸው የግፍ ሥራዎች ያናድዳቸው ስለነበር ናፖሊዮን በዋተርሉ ጦርነት ሲሸነፍ ያልተደሰተ አልነበረም::
ሌላው አምባገነኖች ቀድመው በመውረራቸው እና በሚጠቀሙት ቅጥ ያጣ ጉልበት አሸናፊ መስለው የታዩበት ጦርነት የአንደኛው እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ተጠቃሽ ናቸው::
በእነዚህ ጦርነቶች ጀርመን እና አጋሮቿ በማን አለብኝነት ጠላቴ ብለው በፈረጇቸው አገራት ላይ ወረራ በመፈጸም ጦርነቱ እንዲስፋፋ ቀንደኛ ተዋናዮች ነበሩ :: በአንደኛው የዓለም ጦርነት ኢምፔሪያሊስት አገራት የአፍሪካ እና የኤዥያን የተፈጥሮ ሀብት ለመቀራመት እና በፋብሪካቸው የሚያመርቷቸውን ሸቀጦች ማራገፊያ ለማድረግ አስበው እኔ እበላ እኔ እበላ ሲሉ መፋጠጣቸውን ታሪክ ዘግቦታል::
ተፋጠውም አልቀሩ ጎራ ለይተው የወታደራዊ ትብብር ቡድን መሠረቱ:: ወታደራዊ የትብብር ቡድኖችን ለመመሥረት ኦስትሪያ እና ጀርመንን የቀደማቸው አልነበረም ::
እንግሊዝ እና ፈረሳይም ራሳቸውን ለመከላከል እና እንዲሁም በአፍሪካ እና በኤዥያ ያላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የጦርነት ትብብር ማዕቀፍ መሠረቱ:: የእነኦስትሪያ እና ጀርመን የጦርነት ትብብር ቡድን በእንግሊዝ እና በፈረሳይ የበላይነት የሚዘወረውን የጦርት ትብብር ቡድንን ለማጥፋት ቋምጦ ጦርነቱ ተጀመረ:: በጀርመን እና ኦስትሪያ የሚመራው ጥምር ጦር ወረራ በፈጸሙባቸው አገራት ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ ውድመት እና እልቂት ፈጸመ:: በዚህም መጀመሪያ ላይ በእነጀርመን እና ኦስትሪያ የሚመራው ቡድን በእንግሊዝ እና በፈረሳይ የበላይነት የሚዘወረውን የጦር ትብብር ቡድንን በኃይል የደፈቀው መስሎ ነበር ::
ይህ የሆነው በጀርመን እና ኦስትሪያ የሚመራው ጥምር ጦር ቀድሞ ስለተዘጋጀ እና ቀድሞ ወረራ ስለፈጸሙ ነበር:: የኋላ ኋላ ግን ጀርመን እና ኦስትሪያ በፊትአውራሪነት የሚመሩት ቡድን አይሆኑ ሆኖ ለመናገር በሚዘገንን መልኩ ለሽንፈት ተዳረገ::
በአፍሪካ እና በኤዥያ የነበራቸውን ግዛት እና ገበያ ተደራሽነት ለማስፋፋት ቋምጠው የነበሩት የእነጀርመን ቡድን አይደለም ከአፍሪካ እና ከኤዥያ ጥቅም ሊያገኙ ይቅር እና ቀደም ሲል በእነሱ ስር ይተዳደሩ የነበሩ ግዛቶች እና አስተዳደሮች በእንግሊዝ፣ ፈረንሳይ ፣ ጣሊያን እና ሌሎች አገራት ተቦጫጭቀው ተወሰዱ::
ይህ ብቻ አይደለም የተሸነፉት አገራት አሸናፊዎቹ ለጦርነት ያወጡትን የጦርነት ወጭ እንዲከፍሉ ተገደዱ:: በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም የእነጀርመን ፣ጃፓን እና ጣሊያን ወታደራዊ ቡድን ጠግበው እና በትዕቢት ተወጥረው የሚያደርጉትን አጥተው አቅላቸውን ሳቱ:: ጥጋባቸው አይሎ ያለመጠን ሆነ:: በእጃቸው ለማጨብጨብ ተጠይፈው በእግራቸው አጨበጨቡ::
ሰውን መግደል መዝረፍ መድፈርን እና መሰል ሰይጣናዊ ተግባራትን የዕለት ከዕለት የአስተዳደራዊ ሥራቸው አንዱ አካል እና መገለጫው አደረጉት:: አገራቱ በአውሮፓ፣ ኤዥያ እና በአፍሪካ የሚችሉትን ያህል አገር ወረሩ:: የሚችሉትንም ያህል ሰው ገደሉ:: የመጨረሻ መጨረሻ ግን የጀርመን ፣ጃፓን እና ጣሊያን የግፍ ሩጫ አሳፋሪ በሆነ ሽንፈት ተደመደመ:: በዓለም አቀፉ ፖለቲካ የነበራቸው ተጽዕኖ በዜሮ ተባዛ:: እነ እንግሊዝ እና ፈረሳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድምፅን በድምፅ የመሻር መብትን ያለማንም ከልካይ ሲወስዱ እነ ጀርመን ደግሞ ለኃያላኑ አገራት እንደ ገና ስጋ ለቅርጫ ቀረቡ::
ከሰማይ በታች እንደፈጣሪ በሚፈሩበት ዓለም ተዋረዱ:: ክብራቸው በቅኝ ግዛት ከተያዙ አገራት በታች ሆነ:: ሌላው በወፍ በረር እንድናየው ከመረጥኩት የአምባገነኖች ወረራ ደግሞ ዚያድ ባሬ (ዚያድ ባሬ) በኢትዮጵያ ላይ ያካሄደው ወራሪ ነው:: ፕሬዚዳንት አብዲራሺድ አሊ ሸርማርኬን በመንፈቅለ-መንግሥት ፈንግሎ ሥልጣን የጨበጠው ሜጀር ጄኔራል ዚያድ ባሬ (ዚያድ ባሬ ) መንበረ ስልጣኑን በያዘ ማግስት ድንበር ማስፋፋትን ዋነኛ ዓላማው አድርጎ ተነሳ ::
የወሰን ማስፋፋት ፍላጎቱን ጥሙን ለመወጣት መጀመሪያ ላይ ያነጣጠረውም የጥቁሮች መኩሪያ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ነበር:: የጥፋት ጥይቱን በኦጋዴን በኩል አሀዱ ብሎ ተኮሰ:: በ1966 ዓ.ም ሶማሊያ የአረብ ሊግን መቀላቀሏ የዚያድባሬን የሶማሊያ ልብ በግብዝነት እንዲደነድን አደረገው::
ሜጀር ጄኔራል ዚያድ ባሬ (ዚያድ ባሬ) ኢትዮጵያን በወረረ የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የሶማሊያ ጦር በሶቭዬት ኅብረት ይደገፍ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ከዩናይትስ ስቴትስ ጋር ወዳጅነት ነበረው ።
በወቅቱ በቀዝቃዛ ጦርነት ውስጥ የነበሩት ሶቪዬት ኅብረትና አሜሪካም በእንግድነት ተጋብዘው ይሁን በሌላ ምሥራቅ አፍሪካ መግባት ቻሉ።
ጦርነቱንም ከፍ ወደአለ ምዕራፍ ተለወጠ:: ከንጉሣዊ አገዛዝ ወደ ወታደራዊው አገዛዝ የተሸጋገረችው ኢትዮጵያ በይፋ ራሷን ማርክሲስት ስትል አወጀች:: ወዳጅነቷም ከሶቭዬት ኅብረት ጋር ሆነ። አሜሪካ ደግሞ ድጋፏን ለሶማሊያ አደረገች። የዚያድ ባሬ መንግሥት ወረራውን አጠናክሮ ወደ መሐል አገር ገሰገሰ :: በኢትዮጵያ ላይ እልቆ መሳፍርት የሌለው ጥፋትም አደረሰ:: በንፁሐን ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈጸመ ።
ወራሪው የዚያድ ባሬ ጦር ድንበሬ እስከ አዋሽ ነው በማለት ወደ ሐረር ገሰገሰ። ይህን ተከትሎ በለውጥ ውስጥ የነበረው አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ምንስ አዲስ ቢሆን ከአባቶቹ የወረሰውን አምባገነኖች ጦርነትን በጀመሩት ልክ ጨርሰው አያውቁም !! አገር የማስቀጠል አደራ መወጣት ነበረበት:: ይሄኔ ነው በኢትዮጵያ ክተት የታወጀው ። የክተት አዋጁን ተከትሎ አያሌ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ታጠቅ የጦር ሰፈር ደረሱ:: በአጭር ጊዜ ወታደራዊ ስልጠናቸውን ጨርሰው በግንባር ተገኙ:: በወቅቱ የኩባ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፎ ተዋጋ ::
የዚያድ ባሬ መንግሥት ኩባ የኢትዮጵያውያን ጦር ደግፋ እየወጋችኝ ነው ሲል ለዓለም መንግሥታት ወቀሳ አቀረበ:: ይህንን ወቀሳውን እውነት መሆኑን ለዓለም ማኅበረሰብ ለማሳየትና ለማሳመን በማሰብ በዓውደ ውጊያ የሚማረኩ የኩባ ወታደሮች በማስገደድ ለጋዜጠኞች መግለጫ እንዲሰጡ ተደረገ።
ውሎ አድሮ ቀን ቀንን ሲወልድ የኢትዮጵያ ጦር ራሱን በሰው ኃይል እና በመሣሪያ አደራጀ:: የዚያድ ባሬን ጦርም እያሳደደ ከመሬቱ ይደባልቀው ያዘ:: በወረራ ተይዘው የነበሩ በርካታ ግዛቶችም በኢትዮጵያ ጀግኖች ቁጥጥር ስር ዋሉ:: የመጨረሻው ውጊያም ካራማራ ላይ ተካሄደ። በወቅቱ በዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታገዘው የኢትዮጵያ ጦር በሰማይና በምድር ጥቃቱን በማጠናከር የሶማሊያን ጦር ድባቅ መታው ! በወራራ ይዞት በነበረው መሬትም ጠላትን ደቆሰው:: እንዳይነሳ አድርጎ አርቆም ቀበረው::
ጦርነቱም የተገፋቸው ኢትዮጵያም ጦርነቱን በአሸናፊነት ደመደመች:: በግብዝነት እና በአጉል ትዕቢት ተወጥሮ ኢትዮጵያን በወረራ ይዞ የነበረው ሜጀር ጄኔራል ሲያድ ባሬ (ዚያድ ባሬን ) ከሽንፈቱ በኋላ ተቀባይነቱ እንደጠዋት ጤዛ ታይቶ ጠፋ :: ታላቋ የሚል ቅጥያ የነበራት ሶማሊያም ከካራማራው ጦርነት በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት መታመስ ጀመረች።
ዚያድ ባሬም 1983 ዓ.ም ከሥልጣን ተወገደ:: ከስልጣን የተባረረው ዚያድባሬ እግሬ አውጭኝ ብሎ ወደ ናይጄሪያ ሸሸ። እዩኝ እየኝ ሲል የነበረው ዚያድባሬ ናይጄሪያን አድኑኝ ሲል ተማጸነ:: ናይጄሪያም ልመናውን ሰምታ አስተናገደችው:: ሕልፈተ ሕይወቱም ለአራት ዓመታት በስደት በቆየባት ናይጄሪያ ሆነ። ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ለማንሳት ያስፈለገኝ አሸባሪው ሕወሓት ፍጻሜ ምን ሊሆን ይችላል ለሚሉ ሰዎች ማረገጋጫ እንዲሆንላቸው በማሰብ ነው:: ቡድኑ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሠራው ግፍ አልበቃው ብሎ የአገራችን የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን መከላከያችንን በተኛበት በአሰቃቂ ሁኔታ አጥቅቷል :: ይህን ተከትሎ መከላከያ ሠራዊቱ እራሱን ፈጥኖ በማደራጀት አሸባሪውን በሁለት ሳምንታት ወስጥ ብትንትኑን አውጥቶታል::
ከጁንታው መበታተን በኋላም መንግሥት የአገር አባት ስለሆነ የትግሬ ልጆቼ እንዳይራቡብኝ እና እንዳይጠሙብኝ ብሎ በሕግ ማስከበር የሚያወጣውን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጭ ቀንሶ አብዛኛው ትኩረቱን በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳችን ለማሳለጥ፤ ቡድኑ ያወደማቸውን የመሠረተ ልማቶችን መጠገን እና መልሶ ማደራጀት ላይ አደረገ::
“የአህያ ስጋ ከአልጋ ሲሉት ከአመድ ሆነና” ነገሩ መንግሥት የወደሙ መሠረተ ልማቶችህን ልጠግንልህ፣ ሕዝቡ ወደነበረበት ሕይወቱ እስከሚመለስ ስንዴ እየገዛሁ ላብላህ ማለቱ በአሸባሪው ሰፈር እንደኃጢያት ተቆጠረ:: መከላከያንም ለሁለተኛ ጊዜ ወጉት::
በዚህም ደስታቸው ዳር ስቶ ሲያበላ እና ሲያጠጣቸው የነበረውን መንግሥት ውለታ መክፈል ሲገባቸው «ወንድ ከሆነ ይግጠመን» በማለት ታበዩ:: ከትግራይ ክልል ወጥተውም የአማራ እና የአፋር ክልልን በግፍ ወረሩ:: በግፍ በያዟቸው የአፋር የአማራ ክልሎች የሚገኙ የመሠረተ ልማቶችን መቶ በመቶ አወደሙ::
ሰዎችን ገደሉ ! ደፈሩ! አፈናቀሉ!:: የትግሬ ወራሪ ኃይል ይህን በሚያደርጉ ጊዜ በተለይም የኢትዮጵያ መጥፋት የሚያስደስታቸው እነ አሜሪካ እና መሰሎቿ በደስታ አቅላቸውን ሳቱ::
በተቃራኒው ወረራ የተፈጸመባቸው የኢትዮጵያ ልጆች በከፍተኛ እልህ እና ቁጭት እጅ ለእጅ ተያያዙ:: በተባበረ ክንዳቸው የትግሬን ወራሪ ኃይል ቀጠቀጡት :: መውጫ መግቢያ አሳጡት:: እድለኞች ተርፈው ወደመጡበት ዋሸ ተመለሱ:: አብዛኞቹ ግን በወረራ በያዟቸው መሬቶች ተቀበሩ:: ይህ የአምባ ገነኖች ፍጻሜ ነው ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2014