ዓለም ስለ ኢትዮጵያ እኛ ከምናውቀው በላይ ታውቃለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ በቂ መረጃ አላት፡፡
ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ፣ አሸባሪው ሕወሓት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን እንደነበር ፤አሁንም ምን እያደረገ እንደሆነ አሜሪካና ግብራአበሮቿ በደንብ ያውቃሉ ።ትልቁ ነገር እውነታውን መቀበል አለመፍቀዳቸው ነው ፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም በአሁኑ ሰዓት ሕዝብ መንግሥትን ደግፎ ቡድኑን ለመታገል አደባባይ የወጣበትን ምክንያትና ሕዝብ ከመንግሥት መንግሥትም ከሕዝብ ጋር ያበሩበትን እውነት አልሳቱትም ግን ከዚህ እውነት በተቃራኒ ናቸው፡፡
አሜሪካም ሆነች ምዕራባውያን ኢትዮጵያን በተመለከተ ሐቁ አልጠፋቸውም፤ እውነት የጠፋቸው መስለው የሚደናበሩት ሆን ብለው ነው፡፡ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር የተመሳሰለ ዓላማ ስላላቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያን የማፈራረስ፣ ደካማና የይስሙላ መንግሥት የመፍጠር ዓላማ ስለተዋሃዳቸው ነው፡፡ ይሄ ዓላማቸው እንዲሰምር ደግሞ አስታራቂ መስሎ መግባት አዋጪ መስሎ ስለታያቸው ነው። አሁን ላይ በአሸባሪው እና በኢትዮጵያ መካከል ለመግባት የሚታትሩት፡፡ የእባብ ልጅ እባብ ነው..የእባብ ልጅ ርግብ ሆኖ አያውቅም፡፡ የእባብ ልጅ ግብሩን አይረሳም፡፡
ዛሬ ላይ እየነደፉን ያሉት፣ ዛሬ ላይ እያደሙን ያሉት አሸባሪው ሕወሓት ወልዶ ያሳደጋቸው ጀሌዎቹ ናቸው፡፡ ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያ መከራ እየሆኑ ያሉ ኃይሎች ትላንትና በቡድኑ የተፈጠሩ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ አሜሪካና አሸርጋጅ የውጪ ኃይሎች ዛሬ ላይ የብዙኃኑን ኢትዮጵያ ሕዝብ እውነት ገፍተው ከነፍሰ በላው ቡድን ጎን የቆሙት የባህሪ አንድነት ስላላቸው ነው፡፡
አሸባሪው ሕወሓት አድጎ አሁን ላለበት የደረሰው በአሜሪካ ነው፡፡ ይሄን ለማወቅ ደግሞ እንዴት ብሎ ወደ ስልጣን እንደመጣ ጥቂት ዓመታትን ወደ ኋላ ሄዶ ማየት ይበቃል፡፡ ቡድኑ ሕዝብ የመረጠው ድርጅት አይደለም፡፡ በሕዝብ ይሁንታ ስልጣን የያዘ ቡድን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም በአሜሪካ ከፍያለ ድጋፍ ስልጣን ያያዘ ነው፡፡
በስልጣን በነበረባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥም ለኢትዮጵያ ምን አይነት መንግሥት እንደነበረ በግልጽ አሳይቷል፡፡ አሁን ድረስ መከራ እያየንባቸው ያሉ ስቃዮቻችን በዚህ ከሀዲ ቡድን የተፈበረኩ የተንኮል ሀሳቦች ናቸው፡፡
ትላንትና በነአሜሪካ ታቅፎና ተደግፎ ወደ ስልጣን ሲመጣ በምክንያት ነበር፤ ዛሬም አንቅሮ በተፋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥላቻ ውስጥ አሜሪካ ገብታ ላሸማግል ማለቷ ዓላማው ምን እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡
አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ከአሸባሪው ሕወሓት አስተሳሰብ ነጻ ለመውጣት እየታገለች ነው፡፡ እውነትና ንጋት እያደር መጥራታቸው አይቀርምና ኢትዮጵያዊነት በመከራ ውስጥ ተፈትኖ የሚወጣበት ጊዜ ላይ ይገኛል ፡፡ በዚህ አገር የመፍጠር ሂደት ውስጥ ሕወሓት ከነአስተሳሰቡ፣ ከነክፋቱና ከነእብሪቱ ወደ ኋላ እየቀረ ኢትዮጵያዊነት እየለመለመና እየጎመራ የመጣበት ሰሞን ላይ ነን፡፡ ኢትዮጵያ ምን ፈልጋና ምን ይዛ እንደምትታገል ዓለም ያውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ እውነትን ፈልጋና ፍትሕን ሽታ ነው እየታገለች ያለችው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸባሪውን ሕወሓት እንደማይፈልገው በግልጽ ያሳወቀ ቢሆንም ግን ጥቂት ራስ ወዳድ አገራት ይሄን የሕዝቦች ስሜት ወደ ጎን ብለው ለነፍሰ በላው ቡድን ሽፋን በመስጠት ከማይችሉት ኢትዮጵያዊነት ጋር ግብ ግብ ውስጥ ናቸው፡፡
አሁን ላይ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለአሜሪካና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስረዳት ለቀባሪ የማርዳት ያክል ሹፈት ነው የሚሆነው ። ምክንያቱም ከትላንት እስከዛሬ በዚች አገር ላይ አሸባሪው ሕወሓት በሕዝቦች ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል ያውቃሉና ነው፡፡
አሁን ላይ የኢትዮጵያውያን ዓላማ ምን እንደሆነ፣ ምን ፈልገን እንደምንታገል ዓለም ያውቀዋል፡፡ አሁን ላይ የመንግሥትም ሆነ የዜጎች ፍላጎት፣ ዓላማና ሀሳብ ምን እንደሆነ ከጅምሩ ጀምሮ ይታወቃል ።እየሆነ ያለው ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ ምክንያቱም አሸባሪው ሕወሓትም ሆነ አሜሪካ የኢትዮጵያን ከፍታ ማየት አይሹምና ነው፡፡
ዓላማና እቅዳቸው በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ የራሳቸውን ቤት መሥራት ነው፡፡ ሁሉን ትተን የቢቢሲና የሲኤን ኤን የሐሰት ዘገባ ብናይ እንኳን ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ያለውን የተዛባ አመለካከት እንደርስበታለን፡፡ ‹አዲስ አበባ ተከባለች፣ ሕወሓት አዲስ አበባን እየተቆጣጠረ ነው› የሚል ዘገባ በቢቢሲና በሲኤን ኤን በኩል ወጥቶ ሰምተናል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ሕወሓት አይደለም አዲስ አበባ ሊገባ ቀርቶ ካለበት ስፍራ እንኳን መሸሽ አቅቶት የአሜሪካም ሆነ የምዕራባውያን ጩኸት ከሩጫችን የሚያደናቅፈን አይደለም ፡፡ በጀመርንው ጎዳና መቀጠል እንጂ ለምንም ነገር እድል መስጠት አይኖርብንም፡፡ በዛም በዚም ጩኸት ቢበረታብንም የያዝንው ዓላማ ትልቅ ነውና በዓላማችን ኃይል ልንበረታ ይገባል፡፡
ጊዜው ለአሸባሪው ሕወሓት የምጽአት ቀን፣ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ የትንሳኤ ዋዜማ ነው፡፡ ሕወሓትን ጥለን በትንሳኤ ለመቆም ሰሞነ ህማማት ላይ ነን ፡፡ በትንሳኤ ዋዜማ ሁሌም ስቃይና መከራ አለ፡፡ አሁን ላይ እየሆነብን ያለው ነገር የሳቃችን ዋዜማ ነው፡፡ ይሄ ጊዜ ለአሸባሪው ሕወሓትና ለአስተሳሰቡ የፍጻሜ ዋዜማ ነው፡፡
ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ጠላቶች ዳግም እንዳይነሱ ሆነው እየተቀበሩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በመከራዎቻችን ደስ ሊለን ይገባል ቀሪው ነጋችን የሚያለመልም ነው ፡፡
መጪው ጊዜ የኢትዮጵያ ጊዜ ነው፡ እርግጥ እንደናቀፍ ይሆናል፣ በክፉ እንፈተን ይሆናል መጨረሻችን ግን በብርሃን እንደሚሆን አትጠራጠሩ፡፡ የመጨረሻ ቀን ሁልጊዜም መከራ አለው፡፡
ሊነጋ ሲል እንደሚጨልም ሁሉ በአዲስ ቀን ሰሞን መፈተን ግድ ነው፡፡ ከእንግዲህ እኛ እንጂ የአሸባሪው ሕወሓትና አሸርጋጆቹ አይኖሩም፡፡ የቢቢሲና የሲኤንኤን የሐሰት ትርክትም ምክንያቱ የሕወሓት ስንብት ነው፡፡ ጊዜው ለሕወሓት ስምንተኛው ሺ ነው፡፡ ድጋሚ በሰውነት፣ ዳግም በአስተሳሰብ ወደዚች ዓለም አይመጣም፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኢትዮጵያን ይሰናበታታል፡፡
በመጨረሻው ሰዓት አሸናፊዎች መከራ ይበዛባቸዋል.. መከራ በገጠመን ቁጥር እያሸነፍን እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል፡፡ የአሸባሪው ሕወሓት ውድቀት ገና ብዙ ነገር ሊያሰማን ይችላል፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የደረሱብን የውጪ ተጽዕኖዎች በቡድኑ የስቃይ ድምጾች የተፈጠሩ ናቸው ፡፡
በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ከወደ አሜሪካም ሆነ ከወደ ምዕራቡ በኩል የተሰሙ የዛቻና የማስፈራሪያ ድምፆች የቡድኑ የድረሱልኝ ተማጽኖ የወለዳቸው ናቸው ፡፡ የውጪ ጫናዎች በበረቱብን ቁጥር ሕወሓት እየሞተ እኛ እየተነሳን እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል፡፡ አሜሪካ በሕወሓት ውድቀት ውስጥ እንጂ መነሳት ውስጥ ጮሃ አታውቅም፡፡ የአሜሪካ ድምጽ ወንበዴ የማንገስ ድምፅ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አሜሪካም ሆነች ምዕራባውያን ለኢትዮጵያ የሚሆን የፍትህ ድምፅ የላቸውም፡፡
የፍትሕ ድምፅ ያለው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ነው፡፡ ይሄ ድምፅ ኢትዮጵያን ካልፈጠረ ሌላ ኢትዮጵያን የሚፈጥር ድምፅ የለም፡፡ አሸባሪው ሕወሓት አገር ለማፍረስ የተነሳ ቡድን ነው እነአሜሪካ ደግሞ ይሄን ቡድን ከበው በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ዕጣ የሚጣጣሉ ናቸው፡፡
ከማንም የምንጠብቀው አንዳች ፍትሕ የለም ፍትሕን ከሕዝባችን ጋር ሆነን እናመጣዋለን፡፡ ከውጪው ማኅበረሰብ የምንጠብቀው አንዳች ፍትሕ የለም ፍትሕን ከሕዝባችን ጋር ሆነን እናመጣዋለን፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 2/2014