«ለወረዳ 11 ነዋሪዎች በሙሉ!… በነገው እለት…በወረዳው መሰብሰቢያ አዳራሽ…የሴቶች ቀንን የተመለከተ ስብሰባ ስለተጠራ…የወረዳው ነዋ ሪዎች እንድትገኙ ተብላችኋል…» ጡሩንባ ተነፋ፤ ዜናው ተለፈፈ። ወረዳው በተራ ቁጥር ከፊቱና ከኋላው ካሉ ወረዳዎች ተሽሎ ለመገኘት ነዋሪው ላይ ሥራ አብዝቷል። «ደግሞ ምን ሊሉን ነው?» ይላል ሁሉም በየቤቱ፤ እንኳን አበል የሌለበት ስብሰ ባና አበል አለው ተብሎም የሚሰበሰበው በግድ ነው።
እርሷም ቤት የጡሩንባው ድምጽ ደርሷል፤ ትዕግስት ቤት፤ጥሪውን ሰምታለች። ያቺ ትንሽ፤ በጭቃና በማዳበሪያ የተደጓጎሰች ቤቷ ድምጹን ተከላ ክላ ልታስቀር አትችልማ! ደግሞም ቀደም ባለው ቀን በየበራቸው እየተንኳኳ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። «ሰላም! የፊታችን የካቲት 29 የሴቶች ቀንን ስለምናከብር እን ድትገኙ ለማለት ነው።» አለቻት አንዲት ወጣት። አንዴ ለጥናት፣ አንዴ ለዘገባ ደግሞም እንዲህ ለስ ብሰባ እያሉ ያዘነበለ በሯን የሚደበድቡ ሰዎችን አት ወድም። ግን አታስቀይማቸውም፤ «እሺ…እመጣ ለሁ» ብላ መልሳ በሩን ትዘጋለች። ከዓመት በፊት እንዲህ ሆና ነበር፤ አንዲት ቄንጠኛ ሴት ጠየቀቻት «ሶስና እባላለሁ። ከ… አገር በቀል ድርጅት ነው የመጣሁት። ብድር ለመ በደርና ሥራሽን ወደ መካከለኛ ደረጃ ለማሳደግ አላ ሰብሽም?» ብላ።
ትዕግስት ግን በቶሎ መልስ አል ሰጠችም። ይልቁንም ስታያት ነበር፤ ጸጉሯ የራሷ ይሁን የገበያ ለመለየት እየጣረች። «ይሄ ነገር እንደ ሚባለው መለየት እስከሚያስቸግር ድረስ ከተፈጥሮ ጸጉር ጋር አንድ ዓይነት ነው ማለት ነው?» እያለች ስታስብ ነበር። ለምን? ለምን ጥያቄውን መመለስ ትታ ስለ ተራ ነገር ለማሰብ ፈለገች? ብድር የሚለውን ቃል ስለማ ትወደው ነው። ለእርሷ ቤቷን ያፈረሰውና ኑሮዋን መቅኖ ያሳጣው፤ የልጆቿን አባት ይዞ የጠፋው ብድር ነው።
እናም በምንም መንገድ ቃሉን መስማት አትፈልግም። «አልሰማሽኝም? ለሴቶች የሚዘጋጀ ብድር አለ፤ እርሱን አላገኘሽም ወይ?» ጠያቂዋ ከቀ ድሞው ይልቅ ወደ ትዕግስት ጆሮ ቀረብ ብላ ጥያቄውን ደገመችው። «አይ አልፈልግም» ቃሏ በፍጥነት ነው የወጣው፤ ትዕግስት። በመደብ ያስቀመጠቻቸውን ድንች፣ ቲማቲምና ቃሪያ ነገሩን ሰምተው እንዳይደነ ግጡ ብላ ይመስል ትነካካቸው ጀመር።
«ለምን ታፍሪያለሽ…ችግር የለውም፤ የምትነግሪኝን’ኮ ለራሴ ብቻ ነው የምይዘው? ስምሽንም አልጠይቅሽም ብዬሽ የለ?» ቄንጠኛዋ ሴት ቀጠለች። ትዕግስት ግን አስቀድማ ለቃለመጠይቅ ፈቃደኛ መሆኗ ሳይቆ ጫት አልቀረም፤ ፊቷን ከጠያቂዋ አራቀች። ከዛም በኋላ ምንም መልስ አልሰጠቻትም፤ ልጅቱ ተናድዳ ሄደች።
«ድሮም ሲረዷችሁ አትወ ዱም! ችግር አለባችሁ!» ብላ በጥቂት በጥቂቱ እየ ተራመደች፤ ሌላ ተጠያቂ ፍለጋ። ስትሄድላት የት ዕግስት ሰውነቷ ተፍታታ፤ ተነፈሰች። እንዲህ ያሉ ሰዎች እንዲደርሱባት አትፈልግም። የማትፈልገ ውን ነገር ስለሚያነሱባት፣ ተረጋግቶ ተኝቶ ሰላም የሰጣትን ተስፋ ስለሚቀሰቅሱባት፣ ጥቂት የበራ ቀን ሰጥተው ብዙውን ቀን በንዴት ጨለማ ውስጥ ስለ ሚከቷት፤ ችግሯን ሊያጠኑ የሚቀርቧትን ሰዎች አት ወዳቸውም።
«እማ! ትሄጃለሽ እንዴ?» አላት ልጇ፤ ከሃሳቧ ባነነች«የት?» ስታማስለው ወደ ቆየችው ከሰል ላይ ወደ ተጣደው ብረት ድስት ሃሳቧን መለሰች፤ «የሴቶች ቀን ነዋ? የሆነ ነገር ያደርጉላችሁ ይሆ ናል’ኮ!» አላት፤ ደረቅ ፈገግታ አሳየችውና ዝም አለች። እንደ አዋቂ የሚያወራት የመጀመሪያው፤የአስር ዓመት ልጇ የዝምታዋን ትርጉም ያውቃልና እርሱም ለአፍታ ዝም አላት።
በቤቷ ውስጥ ዝምታ ስልጣን ለማግኘት ቢጥርም አልሆነለትም። የሚንተከተከው የድንች ወጥ ከፍ ብሎ ይሰማል፤ ልጇ አልፎ አልፎ ደብተሩን ሲገልጥ ድምጹ ይታከላል። እንቅልፍ የወሰዳቸው ሁለት ትንንሽ ልጆች የቱንም ድምጽ ሆነ ንግግር አይ ሰሙም፤ ራት እስኪደረስ ተኝተዋል። «ባለፈው ለነ በረከት እናት’ኮ ይሄ በድንጋይ የተ ሠራው ምድጃ አለ አይደለ? እርሱ ተሰጥቷቸዋል» አላት ልጇ፤ ከወጡ መንተክተክም፣ ከወረቀቱ መን ኮሻኮሽም የበለጠ ድምጹን አጉልቶ።
ሃሳቡን በተለየ መንገድ ሲያቀርብላት ነው፤ ሰማችው። ለእርሱ ሲል ሎተሪ ይደርሳታል? ቢደርሳት ግን ትመኛለች፤ እንደው ለእርሱ መሻት ሲል ቢሆንላት። «እነርሱ እድል አላቸዋ ዓለሜ» አለችው፤ የም ትኖርለት ልጇን ትወደዋለች፤ ዓለሟ እርሱ ነው። «አሃ! እድል ደግሞ ምንድን ነው? እንደ ቲቪናእንደ ዲሽ ነው እንዴ? እንደ መጫወቻ ኳስ እና እንደ አዲስ ልብስ ነው እንዴ? የነበረከት እድል ምኑ ጋር ነው ያለው? የትኛው ነው?» ጠየቃት። ፊደል ቆጥራለች፤ ሁለት ብሔራዊ የተባሉ ፈተናዎችን ተፈ ትናለች፤ ለልጇ ጥያቄ መልስ መስጠት ግን በእው ቀት ጥግ እንኳ እንደማይቻል ታውቃለች። «እድል የሚደርስህ ነገር ነው።
እሱን ተወውና አሁን ትምህርትህን አጥና።» ሌላ ጥያቄ እንዳያነሳ ስትዘጋ ነው። ማማሰያውን ከብረት ድስቱ አውጥታ ወደ እጅ መዳፏ አድርሳ ከወጡ ቀመሰች፤ ምሬቷን በሚጣፍጥ ወጥ ልትሸፍን፤ ትንሽ ጨው አከለች በት። «አሁን እህቶችህን ቀስቅሳቸውና ራታችሁን ብሉ» አለችው፤ ሥራዋን ቀጥላ። «እና የሴቶች ቀን የሚባለው ላይ አትሄጂም ማለት ነው?» አላት ልጇ፤ ነገሩ ከሃሳቡ ሊወጣ አል ቻለም። እርሷም ብረት ድስቱን ከዳድና ካወጣች በኋላ በዘመን ብዛት የተሸበሸበ የሚመስለውንና የጠቆረ የሻይ ማንቆርቆሪያ ከሰሉ ላይ ጣደች። «ምነው ብትተወኝ ዓለሜ…እንድሄድ ፈልገህ ከሆነ እሄዳለሁ።
ግን ሄጄ ምን ልሠራ ነው? » «የሚሉትን ትሰሚያለሽ…በዛ ላይ የሴቶች ቀን ነው’ኮ…አንቺም ሴት ነሽ…» «የኔ ዓለም…ነገሩኮ ድግስ ነው፤ ምን ያደርግል ኛል?» «እንደ በረከት እናት ድንጋይ ነገሩን ምጣድ ብታገኝስ?» «አላገኝማ…» «ለምን?…ደግሞ ኑ የተባለበት ቦታ ከሄድሽ ያው የአንቺም ቀን ሆነ ማለት አይደለ እንዴ?» «እስቲ ብትተወኝ ምን አለ? እህቶችህን ብትቀ ሰቅስልኝ አይሻልም?» «እና የሴቶች ቀን ዝግጅት ላይ አትሄጂም በቃ!» «ዓለሜ ምነው በዚህ ምሽት ባታደርቀኝ…እን ድሄድ ከፈለግህ እሄዳለሁ። ግን ምንም አላደርግም። ይሄኛው የእነርሱ ቀን ነው። የሚደግሱት…የሚያ ወሩት…የሚናገሩት…የሚተርኩት፤ የእነርሱ ቀን ነው» አለችው። ለአፍታ ዝም ተባባሉ፤ እርሱም እህ ቶቹን እየነቀነቀ ይቀሰቅሳቸው ጀመር።
ቤቱ ዳግም ከትንሽ ኳኳታ በቀር የጎላ ድምጽ ጠፋው። «እና እማዬ…የአንቺ ቀን መቼ ነው?» አላት። ከየት መጣ የማይባል እንባ ዓይኗን ሞላው። ወደ ልጇ አልተመለከተችም፤ ራሷን ከለለች። የልጇ ጥያቄ የእርሷም ጥያቄ ነበር፤ «መች ነው የእኔ ቀን?» እናም ራሷን ከለለች። ለልጆቿ ውሃ እንደምታመጣ ሁሉ ተነስታ ከቆራጣው ባሊ አጠገብ ቁጢጥ አለች። ለልጆቿ ጀግና ናታ! እንባዋን አይተው አያውቁም፤ አታሳያቸውም።
ለልጆቿ ብርቱ ናታ! ድካሟን ገል ጻላቸው አታውቅም። ግን ቀኗ መቼ ነው? እያንዳንዱ ቀን፣ የእያንዳንዱ ቀን ፀሐይና ጨለማ፣ የእያንዳንዱ ቀን ደቂቃና ሰዓት በእርሷ እየተገፋ እንደሚሄድ እስኪሰማት ያህል ኑሮ ተጭ ኗታል። «በዚህ ኑሮ ላይ ሌላ ልጅ!» የተባለችባ ቸው፤ ብቻዋን ያመጣቻቸው ይመስል ሦስት ልጆች ሕይወቷ ላይ ተደምረዋል፤ ልጆቿ። እምነቷን፣ ተስ ፋዋን፣ ኑሮና ሕይወቷን በእነርሱ ላይ አኑራ ታስተም ራቸዋለች። የተሻለ ቀን እንዲያዩ ለማድረግ፣ ሳይጠ ይቁ የመጡ ልጆቿ የጠየቁትንና የፈለጉትን ሁሉ እን ዲያገኙ ትደክማለች።
ግን የእርሷስ ቀን መቼ ነው? «እማ! አትነግሪኝም?» ልጇ ደግሞ ጠየቃት። የእንባዋ ዘለላዎች ከቆራጣው ባሊ ውሃ ውስጥ ተን ከባለው ገቡ። ከድምጿ ውስጥ ሃዘኗ እንዳይታወቅ ተጠንቅቃና አንገቷን ሳታቀና ተናገረች፤ «የእኔ ቀን ገና አልመጣም። ከመጣም ቀና ብዬ የምሄድበት፣ እናንተ ልጆቼ ጎበዝና መልካም ሰዎች ሆናችሁ የማ ይበት ነው። ሰው የሚያከብረው ደስ የተሰኘበት ንና የልቡን የሞላበትን ቀን አይደለ እንዴ? ስለዚህ ይህኛው የሴቶች ቀን የእኔ አይደለም…የኔ ዓለም፤ የእኔ ቀን መቼ እንደሆነ ወደፊት ታያለህ…» አለች።
የእንባዋን ብዙ ዘለላዎችን ከዋጠው ቆራጣ ባሊ ውሃ ቀድታ ለልጆቿ እጅ መታጠቢያ አቀረበች። «አሁን እህቶችህን ቀስቅሰናቸው ራታችንን በልተን ብንተኛ አይሻልም?» አለችው፤ የሚያቅፉ እጆች ያሉት የሚመስል የሚያሞቅ ፈገግታ ለልጇ ሰጥታ። «እሺ እማዬ…ለቀንሽ ያድርሰን!» ብሏት እህቶቹን ድጋሚ ይቀሰቅስ ጀመር። «አሜን!» አለች በልቧ፤ ልጇም በገባው፤ እርሷም በተረዳችው መንገድ ምር ቃቱን ተቀብላ። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በሊድያ ተስፋዬ