መክረሚያቸውን ሰላም ያጡት ጥንዶች ዛሬን ብሶባቸው አድሯል። የሰሞኑ ጠብና ጭቅጭቅ ከኩርፊያ ተሻግሮ መቀያየማቸውን እያጎላው ነው። በቤቱ ፍቅርና ሰላም ከጠፋ ሰንበቷል። መግባባት መስማማት ይሉት ጉዳይ ርቋል። ይሄኔ ወይዘሮዋ ቤታቸውን ትተው ሊወጡ አሰቡ። ውሳኔያቸው ውሎ አላደረም። ሀሳባቸው አልተቀየረም። ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ማልደው ተነሱ። የጎሸ ልባቸውን ለማከም ርቆ ከመሄድ ወዲያ ምርጫ አልነበራቸውም።
ትንሿን ልጃቸውን አዝለው መለስ ሲሉ ታላቂቱን ተመለከቱ። እሷም ብትሆን ገና ጨቅላ ነች። ነፍስ ያላወቀች እምቦቃቅላ። ወይዘሮዋ ይህ ሁሉ አልጠፋቸውም። ልባቸው እያዘነና አንጀታቸው እየተንሰፈሰፈ እንደጎጇቸው ለአባወራው ትተዋት ሊሄዱ ነው። አሁን ምርጫቸው አንድ ብቻ ሆኗል። ዕንባቸውን እያዘሩ በሆነው ሁሉ እያዘኑ ከአካባቢው መራቅ። ምሽቱ ገፋ። ሌቱ አልፎ ቀኑ መሽቶ ነጋ። አንዷን ጥለው ሌላዋን አንጠልጥለው የወጡት ወይዘሮ ወደቤት አልተመለሱም።
ይሄኔ ደጅ ደጁን ስታይ የዋለችው ህጻን በእናቷ ናፍቆት ዋለለች። ድምጽ ስትሰማና ሌሎችን ስታይ እሳቸው መስለዋት ተሳቀቀች። ሆደባሻዋ ልጅ ለአይኗ ርሀብ ፣ ለናፍቆቷ ምላሽ አላገኘችም። ከደጇ ራቅ ብላ ከአንዱ ጥግ ስትቀመጥ ዕንባዋን እንዳዘራችና ሆድ እንደባሳት ነበር። ያለችበት ስፍራ ቁልቋል የበዛበትና አመድ የሚደፋበት ነው። የጸሀዩ ግለትም አናት የሚበሳ ቃጠሎ ። ይህ ሁሉ ሲሆን ብቸኛዋን ልጅ ነገሬ ያላት አልነበረም። በለቅሶ ብዛት አይኗ ማበጡን ፣ በቁልቋሉ ደም ፊቷ መለወጡን፣ ያስተዋለ የለም። ጨኸቷን እንደ ልጅ ለቅሶ ብቻ የቆጠሩ አንዳንዶች «አይዞሽ» በምትል ቃል አባብለዋታዋል።
ይህ ግን ለእሷ ምኗም አልነበረም። ቃሉ እናቷን ሊያመጣላት፣ ዕንባዋን ሊያደርቅላት አልቻለም። ጀንበር ጠልቃ ማታ ወደቤት ስትመለስ ህመሟ የጸና ሆነ ። የዓይኖችዋ ማቃጠል ብሶ እረፍት ነሳት። ስቃይዋ በበዛ ቁጥር እንደሳት የሚፈጃት ትኩስ ዕንባ ደም ቀላቅሎ ያለማቋረጥ ፈሰሰ ። ሌሊቱን በለቅሶ አነጋች። ማለዳ ምክንያቱ «ምች» መሆኑን የጠረጠሩት አባት ለመፍትሄው ወደ ባህል ህክምና ወስዷት። እንደልምድና ወጉ ቅንድቦችዋ ተቆርጠው ደም እንዲፈስ ተደረገ። ይህ ሁሉ ግን የዘገየ መፍትሄ ነበር ። የህጻኗ አይኖች አስቀድመው በመጥፋታቸው ብርሀን ከልሏቸዋል። ውሎ ሲያድር እናት የሆነውን ሁሉ ሰሙ። «የልጅሽ አይኖች ጠፍተዋል» ይሉት መልዕክትም ከነበሩበት አጣድፎ ቤት አደረሳቸው።
ወይዘሮዋ ጊዜ አልፈጁም። መድሀኒት ይገኝበታል በተባለ ስፍራ ሁሉ ልጃቸውን ይዘው ተንከራተቱ። ከህክምና እስከ ባህል አዋቂ፣ ከመንደር ምክር፣ እስከ አባይ በርሀ ተጉዘው ይበጃል ያሉትን ሁሉ ሞከሩ። በመጨረሻ ግን ደሴ ወደሚገኘውና በወቅቱ «ቦሩሜዳ» ይባል ወደነበረው ሆስፒታል ለመሄድ ወሰኑ። ይህ ውሳኔያቸው መልካም ውጤት እንደሚኖረው ገምተው ነበር። የህጻኗ የዓይን ምርመራና የተገኘው ዜና መልካም አልሆነም። የአይኖችዋ ብሌን ባጋጠማቸው የከፋ ጉዳት ሙሉ ለሙ ሉ መቃጠላቸው ታወቀ ።
ይህ እውነት እሳቸውን ጨምሮ በስፍራው ለነበሩ ሁሉ እጅግ ከባድ ነበር። በዚህ ድንጋጤ መሀል ግን ለወደፊት ህይወቷ የሚበጅ አንድ የምስራች ከአካባቢው ተሰማ። በወቅቱ ለአገልግሎት የመጡ ጀርመናውያን እሷን ጨምሮ ሌሎችን ወደሀገራቸው ወስደው ለማስተማር ፈቀዱ። በወቅቱ አብረው የነበሩ የእናቷ አጎት በተገኘው ዕድል ተደሰቱ። እናቷንም አሳምነው ልጅቷን ለጉዞ አዘጋጁ። በተባለው ቀን በስፍራው የተቀጠሩት እናት ቢጠበቁ ቀሩ። ጥቂት ቆይቶም ልጃቸውን ለመሰወር ሲሉ በሌሊት ቦረና ወደሚባል ቦታ እንደጠፉ ታወቀ። ይህን የሰሙ ሁሉ በእናቲቱ ውሳኔ ተናደዱ።
በተለይ አጎት ልጅቷን «መለመኛና ዶሮ ጠባቂ ልታደርጋት ነው» በሚል በእጅጉ አዘኑ። ተበሳጩ። አሁን ህጻኗ ጥቂት በዕድሜ ጠንክራለች። ክፉ ደጉን መለየቷም ማንነቷን እንድታውቅ እየረዳት ነው። ለልጃቸው «አሰገደች» ሲሉ ስም ያወጡላት እናት ዘወትር ስለእስዋ ይጨነቃሉ። እንደልጅ የሚገባትን ባያጎድሉም ጸጸትና ቁጭት አብሯቸው ሆኗል። ዛሬ እንደትናንት አይደለም። ዓይነስውር ልጃቸውን ትተው ከቤት መውጣት ይቸግራቸዋል። አንድ ቀን ግን የማይቀሩበት ጉዳይ ሆኖ ገበያ መውጣት ፈለጉ። አሰገደችን ይዘው መሄድ ስለማይችሉ አደራ መስጠት ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ከወንድማቸው ሚስት የቀረበ እንደማይኖር አምነዋል። ወይዘሮዋ ደርሰው እስኪመለሱ «እባክሽ» ያሏት ሴት አላሳፈረቻቸውም። አደራውን ተቀብላ በወጉ ልትጠብቅላቸው ቃል ገባች። እናት ብዙም ሳይቆዩ ከገበያ ተመለሱ።ውሎው አድክሟቸዋል።
የልጃቸው ድምጽ ናፍቋቸዋል። ግቢውን አለፍ ብለው ከቤት እንደቀረቡ አሰገደችን ተመለከቷት። እሷ እንደእኩዮችዋ አይደለችም። እናቷ ከገበያ ስትመጣ ሮጣ አትቀበልም። ቆም ብለው ከወትሮው በተለየ ስሜት አስተዋሏት። ልጅቷ አደራ እንደተባለችው ሆኖ ከቤት አልተገኘችም። የተሰጣትን ረዥም እንጨት ይዛ የተሰጣውን እህል ከዶሮና ወፍ እየጠበቀች ነው። ይህኔ እናት የወንድማቸውን ቃል አስታውሰው ራሳቸውን መቆጣጠር ተሳናቸው። አለመማሯ ሳያንስ ስጥ ጠባቂ መሆኗ ከልብ አስለቀሳቸው። ይህ ብቻ ያልበቃቸው ወይዘሮ ሲንደረደሩ ወደአደራ ተቀባይዋ ገሰገሱ። ከቤቷ ሲገቡ ያዘጋጀችውን ገንፎ አቅርባ እየበላች ደረሱ። ይህ መሆኑ ይበልጥ ቢያበሳጫቸው የምትበላውን ገንፎ አንስተው ፈቷ ላይ ለጠፉት። በዚህ ምክንያትም ከወንድማቸው ሚስት ጋር ተቆራረጡ። ይህ አጋጣሚ አሰገደችን ይዘው ከአካባቢው ለመራቅ ሰበብ ሆነ። የልጃቸው እኩዮች ሲዳሩና ሲኳሉ የማየትን ቀን ይፈሩት ለነበረው እናት ምክንያቱ በቂያቸው ነበር። አዲስ አበባ ሲገቡ ሌሎች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት አስመዘገቡ። አይነስውሯ አሰገደች ግን የመማር ዕድሉን ሳታገኝ ቀረች። ይህ መሆኑ ደግሞ ቤት የምትውለውን ህጻን በእጅጉ አስከፋት። እህት ወንድሞችዋ ተምረው ሲመጡ የበይ ተመልካች በመሆኗ ማልቀስና መተከዝን ልማዷ አደረገች። ቤት በዋለች ግዜ ታናሽ እህቷ ካደጉበት የወሎ ምድር የለጋምቦ ሜዳ እጇን ይዛ የምታጫውታት ትውስ ይላታል። የዛኔ አኩኩሉ፣ ዝላይ፣ ሩጫና የልጅ ጨዋታዎች ሁሉ ቀርተውባት አያውቁም።
እህቷም ብትሆን ለእሷ የነበራት ፍቅርና እንክብካቤ የተለየ ነበር። ዛሬ ግን ያቺ ደግ እህት ከጎኗ እንዳትሆን ትምህርት ቤት ገብታለች። እሷ ደግሞ ኮቴዋን እያዳመጠች ቤት ልትጠብቃት ግድ ብሏል። አንድ ቀን እግር የጣላቸው እንግዶች ወደ እነ አሰገደች ሰፈር ዘለቁ። ሰዎቹ ቤት ለመከራየት የመጡ አይነስውራን ተማሪዎች ነበሩ። እያደር የቤተሰቡ ከእነሱ ጋር መቀራረብ ለአሰገደች የትምህርት ጉዳይ ፍንጭ የሚሰጥ ሆነ። እናት ስለትምህርቷ በቂ መረጃ ቢያገኙም ልጃቸውን አምነው ለመላክ አልወሰኑም። የተባለውን ሁሉ የሰማችው ህጻን ግን በእናቷ ሀሳብ አልተስማማችም።
«ትምህርት ቤት ካልገባሁ፣ አሻፈረኝ» ስትል ሞገተች። እናት የልጃቸውን ፍላጎት እንደዋዛ ማለፍ አልተቻላቸውምና ወደ አይነስውራን ማህበር በመሄድ ጉዳዩን አስረዱ። በወቅቱ የማህበሩ ምላሽ እንደታሰበው አልነበረም። ቆይቶ ግን በአንዳንድ ሰዎች መልካምነት ወደ ሰበታ መርሀ ዕውራን አዳሪ ትምህርት ቤት እንድትገባ ተፈቀደላት። አሰገደች ይህን ስታውቅ ደስታዋ ወሰን አጣ። እሷም ወግ ደርሷት ተማሪ ልትባል ነውና እንባዋን አብሳ በፈገግታ ተሞላች። አሁን አሰገደች ከቤተሰቦቿ ተነጥላ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብታለች። ነፍስ ካወቀች ጀምሮ አለማየቷን የምታውቀው ልጅ በትምህርቷ ከሌሎች የላቀች ለመሆን ጊዜ አልወሰደባትም። ከዕውቀት ጋር በአንዴ ተግባባች። የፊደልን ቀለም ፈጥና ለየች። ንቁና ብሩህ አዕምሮዋ የደረጃ ተማሪ አደረጋት። በምስጋናና በተለየ ሽልማት የምትታወቀው ተማሪ በጉብዝናዋ እንደቀጠለች እስከአስረኛ ክፍል ዘለቀች።
ከአዳሪ ትምህርት ቤቱ እንደወጣች ግን የኮረዳነት ዕድሜዋ ይፈትናት ያዘ። የፍቅር ጓደኛ አበጀች፣ ቋንቋና ጨዋታዋም ተለየ። ተከራይታ መኖሯ ነጻነቷን ሰጣት። ይህ ስሜት ግን እምብዛም አልዘለቀም። አስረኛ ክፍልን እንዳጋመሰች ነፍሰጡር ስለመሆኗ አወቀች። አሰገደች በማርገዟ አንዳንድ ሰዎች ስለእሷ የሚኖራቸውን ግምት መዘነች። ብዙዎች እሷን መሰል አይነስውራን እንደሌሎች የሚያረግዙና የሚወልዱ እንደማይመስላቸው ታውቃለች። ይህን አድርገው ከተገኙም እንደነውር ይቆጥሩታል። የፍቅር ጓደኛዋ እንደእሷ አይነስውር ነው። የዩኒቨርስቲ ተማሪ መሆኑና ስራ አለመያዙ ቢያስጨንቀውም ከአጠገቧ አልራቀም። ሆዷ እየገፋ ሲሄድ መምህራኖችዋን ለማግኘት አፈረች። ያም ሆኖ ግን ከትምህርቷ አልቀረችም። የአስረኛ ክፍል ፈተና እንደጨረሰች ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ታቀፈች።
የትናንቷ ትምህርት ናፋቂ ወጣት ዛሬ የልጅ እናት መሆኗ ቀጣዩን እቅዷን ለወጠው። ዩኒቨርስቲ የመግባት ህልሟ፣ ነገን የማሸነፍ አቅሟ ተቀየረ። ሊያግዟት በሰራተኝነት የተቀጠሩ አንዳንዶች አለማየቷን ተጠቅመው ብዙ በደሏት። እሷም ስለልጇ ስትል ፈተናዎችን ሁሉ ተቋቋመች። የአስራ አንደኛ ክፍል ትምህርት እንደድ ሮው አልቀጠለም። ክፍል ተቀምጣ ልጇን፣ ቤቷ ሆና ደግሞ ትምህርቷን የምታስበው ተማሪ ለጥናት የሚሆን ግዜ አልተረፋትም። ከአዳሪ ትምህርት ቤቱ የሚከፈላት የኪስ ገንዘብ ለቤት ኪራይ፣ ለወተትና ለሰራተኛ ክፍያ አልበቃም። ቤተሰቦችዋ በሆነው ሁሉ ባይደሰቱም ሊተዋት አልፈቀዱምና ከነልጇ ተቀበሏት። በቂ ጊዜ ለትምህርቷ ባትሰጥም አስራ ሁለተኛ ክፍልን ተፈተነች። ውጤቷ ጥሩ አልነበረም።
ያም ሆኖ ግን ተስፋ አልቆ ረጠችም። ነጥቧን ለማሻሻል ሌት ተቀን ጥረት ጀመረች። አሁን ለእሷና ለልጇ የሚሆን ገቢ ያስፈልጋታል። ለዚህ ደግሞ ቤተሰቦችዋን ማስቸገር እንደሌለባት ታውቃለች። አንድ ቀን አስር ብር በእጇ እንደጨበጠች በሀሳብ ስታወጣና ስታወርድ ዋለች። የሀሳቧ ዳርቻም ከአንድ ውሳኔ አደረሳት። በማግስቱ ብሩን ዘርዝራ አንድ ኪሎ ገብስና ሽንብራ ገዛችበት። ወዲያውም ቆሎውን አሽጋ ለሽያጭ ይዛው ወጣች። በዕለቱ ሁሉም ተሽጦ ገንዘብ ይዛ ተመለሰች። በሸጠችው እየገዛች፣ በገዛችው እያተረፈች ኑሮዋን መደጎም ያዘች። ይህን ስታደርግ ለእጇ ገንዘብ ተረፋት። ለልጇም ያሻውን መግዛት ቻለች። አሰገደች ነገ የተሻለ እንደሚሆን ታውቃለች። የልጅ አባቷ ትምህርቱን ሲያጠና ቅቅ አብረው የመኖርን ዕቅድ ይዘዋል። የትናንቱን መንገድም «ነበር» ሲሉ በትውስታ ያወጉታል። በዚህ ሁሉ መሀል የጥንካሬ ጉዞዋ አልተገታም። እየተማረችና ቆሎ እየሸጠች ልጇን እያሳደገች ነው። አንድ ቀን የልጅ አባቷ በጥብቅ እንደሚ ፈልጋት ነገራትና በአካል ተገናኙ። እንዲህ በሆነ አጋጣሚ ሁሌም ስለልጃቸውና ስለወደፊቱ ኑሯቸው መወያየት ለምደዋል። የዛን ዕለቱ ቆይታ ግን ከወትሮው የተለየ ነበር።
«አብሮኝ ነው» የምትለው አካሏ ሊለያትና ሌላ ሴት ሊያገባ መሆኑን ነገራት። በወቅቱ በሁኔታው ተገረመች። ወዲያው ግን ለውስጧ ጥንካሬን አላብሳ «ይቅናህ »ስትል በፈገግታ ሸኘችው። ቆይታ ምክንያቱን ስትሰማ ግን «ሁለት አይነስውራን ጥንዶች ትዳር አያቆሙም» በሚል ተለምዷዊ አመለካከት ምርጫውን እንደለየ ተረዳች። ይህን ባወቀች ጊዜም በግል አስተሳሰቡ ተገረመች። እሷ በርካታ አካል ጉዳተኞች ስኬታማ መሆናቸውን ታውቃለች። በሌሎች ዘንድ የተሳሳተ ግምት ቢኖርም በራሱ በአካል ጉዳተኛው ግን ይህ አመለካከት ሊንጸባረቅ አይገባም። አሁን አሰገደች ብቻዋን ናት። ልጅ የማሳ ደጉ ኃላፊነት በእሷ ትከሻ ወድቋል። ይህ አጋጣሚ ደጋግማ እንድታስብ ምክንያት ሆናት። ልጇን ይዛ ከቤተሰቦችዋ ቤት መው ጣቷ በቆሎ ችርቻሮ ብቻ የሚያኖራት አልሆነም። እናም ሌላ መፍትሄ ፈለገች። ድንች እየቀቀለች በሚጥሚጣ መሸጥ ጀመረች። አሁንም የሚገዟት በረከቱ። ከቀናት በኋላ ጥቂት የቤት ዕቃዎችን ገዝታ ከጎዳና ዳር ተቀመጠች። ሁኔታዋን ያዩ መንገደኞች ዕለቱን ገዝተው ጨረሱላት። በማግስቱም እንዲሁ ገበያው ቀናት። የሙያዊ ስልጠና ዕድል ስታገኝ አልተወ ችውም። እየሰራች ሰለጠነች።
በጎዳናው ንግድ ከደንቦች ጋር መሯሯጡ ግን አመቺ አልሆነም። ተስፋ ያልቆረጠችው አሰገደች ራሷን ለመቻል አማራጮችን አሰፋች። ጀብሎ ጭምር እየሰራች የሳምንት ዕቁብ ጀመረች። አሁን ለእሷና ለልጇ የሚቸግራት የለም። ይሁን እንጂ በእጅጉ የምትጓጓለት የትምህርት ጉዳይ ዛሬም በእንጥልጥል ቆሟል። ከቀናት በአንዱ ሪፍት ቫሊ ኮሌጅ ለአይነ ስውራን በሰጠው ነጻ የትምህርት ዕድል የመወዳዳሩን አጋጣሚ አገኘች። ለስኬቱ የተለመዱ ውጣውረዶች ቢኖሩትም አሸናፊ ነትን የነጠቃት አልነበረም። ትምህርቱን ስትጀ ምር የጎዳና ላይ ንግዱ ቀዘቀዘ ። በኮሌጁ የጀብሎ ንግዷን መቀጠሏ ግን ኑሮዋን ደገፈላት። የጀመረችውን የህግ ትምህርት በመልካም ውጤት አጠናቃ ከተመረቀች በኋላ ስራ ለማግኘት ባዘነች።
አሁንም ግን «ስለምን?» ስትል ተስፋ አልቆረጠችም። የትናንቱን ጥንካሬ ተላብሳ ነገን በበጎ አለመችው። አምስት ዓመታት ያለስራ ባከኑ። አንድ ቀን ግን ከዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው በማህበር ከተደራጁ ስራ ፈላጊዎች ጋር ድንገት ተገናኘች። በወቅቱ አይነ ስውራንን ለመቅጠር ፍላጎት ባልነበራቸው ተቋማት ሰበብ ሁኔታዎች ጊዜ ወሰዱ። አሰገደች ግን በሙያዋ ተቀጥራ ባለደሞዝ ልትሆን ጊዜው ደረሰ። ይሄኔ ያለፈችበትን መንገድ ዞር ብላ አሰበችው። በውጣውረድ የተሞላ፣ በፈተና የተከበበና ድካም የበዛበት ነበር። ዛሬ ግን ያ ሁሉ አልፎ እዚህ ደርሳለች። ስለሆነው ሁሉ «ለምን?» እያለች ከራሷ ጋር አትሞግትም። የእሷ ዓላማ እንደ ሁልግዜው ሁሉ ህልሟ ነገን በተሻለ ማሰብ ነው። አሁን አሰገደች በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ ዘጠኝ ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የህጻናት መብትና ስርጸት ማስፋፊያ ባለሙያ በመሆን ታገለግላች።
ለስራዋ የሚያግዛት ባለሙያ በመቀጠሩም ተግባሯን በስኬት ለመከወን አትቸገርም። ዘወትር በርካታ ባለጉዳዮችን እየተቀበለች ለችግሮች መፍትሄ ትሰጣለች። ስለእሷ የስራ ባልደረቦች ዋና ኃላፊዎቿ ጠንካራ ግምት አላቸው። ይህ መሆኑ ደግሞ ለአሰገደች የዘወትር ብርታት ሆኗል። እነሆ! ዛሬ እነዛ መከራዎች ሁሉ አልፈዋል። የአካል ጉዳተኝነቷን መሰናክሎች በስራና በትምህርቷ አሸንፋቸዋለች። አሁን የእሷ የህይወት መንገድ ለሌሎች ጭምር ምሳሌ መሆን ይቻለዋል። አሰገደች በውጣ ውረድ ካለፈችበት መንገድ አረፍ ብላ የራሷን ህይወት መቃኘት እንደጀመረች ከአሁኑ ባለቤ ቷ ጋር ትዳር ለመመስረት በቃች። የዛኔ የልጅ አባቷ «ሁለት አይነ ስውራን ጎጆ ማቆም አይችሉም» ያላትን አትረሳም። የእሱ አባባልም በእጅጉ ሲያስገርማት ቆይቷል።
ዛሬ ግን ይህ እሳቤው ስህተት ስለመሆኑ አይነ ስውር የትዳር አጋሯን ከጎኗ ስታደርግ ይበልጥ አውቀዋለች። ጠንካራ ማንነትን በብርታት፣ ማግኘት እንደሚቻል የምታምነው ወይዘሮ ዛሬም ራሷን ለማሸነፍ ከትምህርት ገበታ አልራቀችም። አሁን ላይ ሆና ስታስብ የዛኔ በጨቅላ ዕድሜዋ በአጎቷ ሚስት የሆነውን አጋጣሚ በበጎነት ትወስደዋለች። «አጋጣሚው ባይፈ ጠር ኖሮ አዲስ አበባ የመምጣትና የመማር ዕድሉን አላገኝም ነበር» ስትልም ታወጋዋለች። ዘወትር ስለ አካል ጉዳተኝነት ከመናገር ችግሮ ችን ተቋቁሞ በድል ማሸነፍ ዛሬም የአሰገደች እንድሪስ የማንነት አቋም ሆኗል።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በመልካምስራ አፈወርቅ