የአካል ጉዳት ያላንበረከካት ክንደ ብርቱ

 

አንዳንድ ጊዜ መክሊታችን ምንድነው የሚለውን በውል ባለመገንዘብ ለምን ሕይወቴ፣ ሥራዬ፣ ትምህርቴ … አልተሳካልኝም። ለምን ውጤታማ መሆን አልቻልኩም በሚል የሚበሳጩ ብዙ ናቸው። «ለምን» የሚል ጥያቄን በማንሳት ብቻ ወርቅ የሆነውን ጊዜያቸውን ያለ ውጤት ያባክናሉ። ሁሉም ሰው ውጤታማ የሚሆነው ሰዎች ተሳክቶላቸው ያየውን ሥራ ለመሥራት በመሞከር ብቻ አይደለም። አንዳንዶች የራሳቸው የሆኑ ሞዴሎች ይኖሯቸውና ያንን ተከትለው ለውጤታማነት ይበቃሉ። ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው። ነገር ግን የራሱን መክሊት ፈልጎ ያገኘ ሰው ምንም ቢሆን አይወድቅም። የማደግና የስኬታማነት እድሉ ሰፊ ነው።

በተለይም አካል ጉዳት ያጋጠመው ሰው ብዙ ጊዜ ጥገኛ ላለመሆን ምን መሥራት እንዴት መሥራት እንዳለበትና ሕይወትን ማስቀጠል እንደሚችል ከማሰብ ይልቅ አእምሮን ወደ አንድ መንገድ ብቻ ይመራል። አካል ጉዳተኛ ሠርቶ መለወጥ አይችልም ብለው የሚያስቡ ጥቂቶች አይደሉም። ነገር ግን ሙሉ አካል ላላቸው ሁሉ አርአያ የሚሆኑ ጀግና የሆኑ አካል ጉዳተኞች አሉ። የአካል ጉዳታቸው ሳይበግራቸው በጥረታቸው ዝናን ያተረፉ አንቱ የተባሉ። ከእነዚህ ክንደ ብርቱዎች መካከል የሀዋሳዋ ወጣት ያብስራ ፍሬው አንዷ ናት። ያብስራ ችግርን እንዴት ተጋፍጦ ማሸነፍ እንደሚቻል ከሕይወት ተሞክሮዋ ያሳየች ወጣት ነች። ተወልዳ ያደገችው ሲዳማ ክልል አለታጭኮ በሚባል ቦታ ነው። ገና ስትወለድ ጀምሮ እጇ ላይ የአካል ጉዳት አጋጥሟታል። ቤተሰቦቿ የእርሷን አካል ጉዳት ተቀብለው የሚቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉላትም ራሷን ካወቀች በኋላ የተለያዩ ጥያቄ ታነሳ ነበር።

ማንነቷንም ለመቀበል ረጅም ዓመታትን ፈጅቶ ባታል። ጥያቄዎቿ መልስ በማጣታቸውና ራሷን ማሸነፍ ባለመቻሏ አንዳንዴ ጭምት ሆና ራሷን አግልላ ትቀመጣለች። አንዳንዴ ደግሞ ተናዳጅና ተደባዳቢ እንዲሁም ለቤተሰቡ አስቸጋሪ ልጅ ትሆናለች። በዚህ ባሕሪዋ ግን ማንም አይወቅሳትም፤ ተይም ሊላት አይወድም። ይልቁንም ንዴቷ ከምን የመነጨ እንደሆነ ስለሚረዷት ይህንን ብታደርጊ ነገሮችን ማቅለል ትችያለሽ እያሉ መልካም መንገዶችን ይመሯታል። ጭንቀቷን የሚያስረሱ ሃሳቦችንም ይሰጧታል። ይህንን ተጠቅማ ሕይወቷን ማስተካከል ችላለች።

አስተማሪው ፈልም

ያብስራ ማንነቷን መቀበል ከቤተሰቦቿና ጓደኞቿ ምክር ባልተናነሰ ከአካል ጉዳት ጋር ተያይዞ ያሉ ፈልሞችንን መመልከቷ አስተዋጽኦ ነበረው። በፊልሞቹ ፈጣሪ በምንም መልኩ እንደማይሳሳት ተምራለች፤ ለዓላማ መፈጠሯን እንድትረዳ ሆናለች። በተለይም ከእርሷ የባሰ አካል ጉዳት የገጠማቸውን ስታይ ለምን ለሚለው ጥያቄዋ አወንታዊ ምላሽ አግኝታበታለች።

‹‹የሕይወቴ መቀየር መሠረት የሆነው ሚግ(ሚኪ) እየተባለ የሚጠራው እጅም እግርም የሌለው የውጭ ሀገር ዜጋ የሚያከናውናቸው ተግባራት ናቸው›› ትላለች። እርሷ ምንም የአካል ጉዳት ያልገጠማቸው እግሮች አሏት። በጥቂቱም ቢሆን ሊይዙ የሚችሉ ጣቶችም እጇ ላይ አላት። ስለዚህም ምንም ማድረግ እንደማያቅታት ብርታት ሰጥቷታል። ይህንን አቅሟን እንድትጠቀም ደግሞ የሚያግዟት፤ የሚያበረታቷት ቤተሰቦችና ጓደኞች ስላሏት ደስተኛ ሆና ታደርገዋለች፤ እያደረገችው እንደሆነ ታስረዳለች።

ያብስራ ፊልም ማየት ከምንም የመነጨ አይደለም። ቤተሰቦቿ ይህንን ብታደርጊ እያሉ የመከሯት ነው። የጓደኞቿም ድጋፍ ታክሎበት ነው። በዚህ ደግሞ ትምህርቷን ጭምር እንድትገፋበት አግዟታል። የመጀመሪያ ዲግሪዋን በቢዝነስ ማኔጅመንት እንድትመረቅና ሥራ ተቀጥራ መሥራት ችላለች። ከጓደኞቿና ከአካባቢው ማኅበረሰብ የሚደርስባትን ጫና መቋቋም ችላለች።

ያብስራ ከዚህ በመነሳትም ስለቤተሰቦቿና ጓደኞቿ የምትለው አላት። ‹‹እኔ የቤተሰቦቼ ድምር ውጤት ነኝ። በጣም ደካማና ምንም አልችልም በሚል ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ብርታት ሰጥተውኝ ከጨለመው አስተሳሰቤ አውጥተውኛል። ሁሌም አንቺ ታደርጊዋለሽ እያሉ ከፍታዬን ገንብተውልኛልም። ጓደኞቼም ስብራቴን የጠገኑ ናቸው። እኛ ምን ሠራን እያሉ ብርቱነትን አጎናጽፈውኛል። በተስፋ እንድራመድ፤ እድሎቼን እንድጠቀምባቸው አስችሎኛልና ስለ ውለታቸው ዘወትር አመሰግናቸዋለሁ›› ትላለች።

እግርን እንደ እጅ

እያንዳንዱ የሰውነት ክፍላችን የራሱ አገልግሎት ቢኖረውም ያብስራ ጋር ግን ይህ አይሠራም። በተፈጥሮዋ ጉዳትን ያስተናገደች በመሆኗ ለእርሷ እግር የእጅንም አገልግሎት ያከናውናል። በእርግጥ አገልግሎቱን ለማስጀመር ጥረትን ፤ ልምምድንና ፈተናን መጋፈጥን የግድ ይላል። ያብስራም ይህንን በአግባቡ ለመወጣት በብዙ ታግላለች፤ ተፈትናለችም። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ጠንከር ያለ ጉዳይን አጫውታናለች። ይህም ከወር ግዳጇ ጋር በተያያዘ የተፈተነችበት ነው።

በወቅት ሞዴስ እንዴት እንደምታደርግ አታውቅም፤ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ላይም አይደለችም። ስለዚህ ምርጫዋ የሌሎችን እርዳታ መጠየቅ ነው። ሀፍረትን ገልጦ ለሌሎች ማሳየት ደግሞ በጣሙን ይሰቃል። ስቃዩ የአንዱ ሰው ብቻ ሳይሆን በሁለቱም ወገን የሚመጣ ነው። ግን ምርጫ የላትምና ለዓመታት ምላሽ እስክታገኝ ድረስ አድርገዋለች። በዚህ ውስጥ ግን ተፈጥሮዋን በየጊዜው ታማርር ነበር። ብስጭቷም መና ሆኖ ቆይቶ ነበር። አንድ ቀን ግን ከሰዎች ጫንቃ ላይ ለመውረድ ቪዲዮችን መከፋፈት ጀመረች።

በእግሯ ነገሩን ማከናወን እንደምትችልም አወቀች። ተለማምዳም ተፈጥሮዋን በተፈጥሮ መልሳ ደስታዋን ወደራሷ አመጣች። ከዚህ የተነሳም ዘወትር ለራሷ አንድ መርህ አስቀምጣለች። ይህም ‹‹ተፈጥሮ ለራሷ ተፈጥሯዊ ምላሽ አላትና ከማማረር ይልቅ ለምላሽ መፋጠን ያስፈልጋል›› የሚል ነው።

ያብስራ አንዱ አካላችን ቢጎልም በአንዱ ተጠቅሞ ችግሩን ማለፍ ይቻላል የሚል እምነት ያላት ወጣት ነች። በዚህም እግሯን ለተለያዩ አላማዎች መጠቀም ችላለች። በእርሷ የሕይወት ጉዞ ውስጥ ሽንኩርት የመከተፍ ሥራ የእጅዋ ብቻ ሳይሆን የእግሯ ነው። ከበድ ያሉ እቃዎችንም ማንሳትና ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ የእጇ ተግባር ሳይሆን የእግሯ ዋነኛ ሥራ ነው። እግሯ የእጅን ተግባር በሙሉ ይከውናል።

ልክ እንደ እጇ ጸጉሯንና ሰውነቷን የምትታጠብው፤ዘወትር አልጋ የምታነጥፈው፤ ቤት የምታጸዳው፤ ልብስ የምታጥበውና ዋና የሚባሉ ተግባራትን የምትከውነው በእግሯ አማካኝነት ነው። ያብስራ ባሏት ጣቶች አንዳንድ ሥራዎችን ትሰራለች። ወጥ ታማስላለች፤ ገላዋንም ትታጠባለች፤ በኮምፒውተር ላይ ትጽፋለች። ይህንን በማድረጓ ደግሞ አካል ጉዳተኛ እንደሆነች ሳይሰማት ጊዜዋን እንድታሳልፍ አግዟታል። ማንኛውም ሰው የሚሰራውን መሥራት እችላለሁ እንድትልም ወኔ ሰጥቷታል። በሁነቶች እንዳትማረርና እንዳትሸነፍም አግዟታል።

ያብስራ ዛሬ እንደ ትናንቱ አትቆዝምም፤ አትናደድም፤ ተበሳጭታ ነገሮችን ከማድረግ ወደ ኋላ አትልም። እንዳውም አዲስ ነገር ፈጥራ ሰዎችን ማስደመምና አትችልም ሲሏት የነበሩትን ማሳፈር ምርጫዋ ታደርጋለች። ሁልጊዜ ሀዘኗን ወደ ደስታ ቀይራ ደስታን ትፈጥራለች። ፍልቅልቅ ሆና ለሰዎች በመታየቷ ደስታን ታጋባለች።

የእሷ ጥንካሬ ለሌሎችም የሚጋባ ዓይነት ነው፤ ጽናቷ ሌሎችን የሚያበረታ ነው። ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ትኩረት ስለምትሰጥም ትምህርቷም ሌሎችን ወደ ከፍታው የሚያሻግር፤ ምክሯ ከስህተታቸው የሚመልስ ነው። ደጋግሞ በመሞከር የምታምን ትዕግሥትን የተላበሰች፣ ባልተሳካው ጉዳይ ፀፀትና ቁጭት የምታዘወትር በመሆኗም በማኅበራዊ ሕይወቷም ሆነ በሌሎች ተግባራቶቿ ብዙዎችን ታስቀናለች። በዙሪያዋ ያሉ ሁሉ ለማደግ እንዲንጠራሩ ታደርጋለች።

ሰዎች ማንነታቸውን ከተቀበሉ ድከመታቸውን ማረም እንደሚችሉ፤ ጥንካሬያቸውን ለሰው ሁሉ እንደሚያሳዩ፤ ለሌሎች ሰዎች መብራት እንደሚሆኑና ራሳቸውን ከጨለማው ወደ ብርሃኑ ማውጣት እንደማይሳናቸው ታስባለች። በዚህ ውስጥ ደግሞ እርሷ ለሌሎች የነገ መውጫቸው መሰላል እንደሆነችም ትገነዘባለች።

ያብስራ ትናንትን በብዙ እያማረረች ብትቆይም ዛሬ ላይ ግን ማንንም ሳትወቅስ ወደፊት ትራመዳለች። እንደውም አሁን ላይ ቆም ብላ ስታስበው ‹‹በእኔ እንዲህ መሆን ማንም ተወቃሽ የለም›› ትላለች። ‹‹ፈጣሪ በዚህ ደረጃ የፈጠረኝ መጥፎ ስለሆነ ወይም ቤተሰቦቼ ኃጢአት ስለሠሩ አይደለም። እኔን ስለሚወደኝና ቤተሰቦቼም የበለጠ ጠንካራ እንደሆኑ ስላሰበ ነው። ሌሎች በእኔ ውስጥ ተምረው ደስተኛ ኑሮን እንዲኖሩ ስለፈለገ ነው። እኔም ደስታዬ በሌሎች ለውጥ ውስጥ እንዲሆን ስለፈለገኝ ነው እንጂ ፈጣሪ በፍጥረቱ የሚሳሳት ሆኖ አይደለም።» በማለትም በእርሷ አካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ተወቃሽ የሚባል ነገር እንደሌለ ትናገራለች።

ፈጣሪ ለእርሷ የሰጣት ልዩ ጸጋ እንዳለ የምታምነው ያብስራ፤ በዛሬዋ ውስጥ ማንም ሰው እርሷን ካገኘ የተፈጠረበትን ዓላማ እንዲረዳ የማድረግ አቅም እንዳላት አውቃለች። በዚህ ደግሞ ፈጣሪዋን ታመሰግናለች፤ ለዚህ ያበቋትን ቤተሰቦቿንና ጓደኞቿን አመስግና አትጠግብም።

ምሳሌ ፋውንዴሽን

ያብስራ ማንም ሰው በሕይወቱ ስኬታማ ለመሆን ስንፍናንና አልችልም ባይነትን ማስወገድ ነው የሚል አቋም አላት። በተለይም ራስን ማሸነፍና ራስን መቀበል ከምንም በላይ ለሕይወት ጉዞ አስፈላጊ እንደሆነም ታምናለች። በዚህ አቋሟም ላይ ሆና በመንቀሳቀሷ ከፍታዋን እንደገነባች ታስባለች። ምክንያቱም ዛሬ ላይ ያብስራ የተለዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች። አንዱ ከራሷ አልፋ በጎ አድራጎት ድርጅት ከፍታ ለሌሎች መድረስ ችላለች።

ድርጅቱ ምሳሌ ፋውንዴሽን ይባላል። ዋና ተግባሩ በየዓመቱ በበዓላት እና በትምህርት ማስጀመሪያ ወቅት በኢኮኖሚያቸው ዝቅ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማገዝና የማዕድ ማጋራት ሥራ ማከናወን ነው።

ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን ማቅረብ፤ አቅመ ደካማን ከእነ ቤተሰባቸው በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ ማገዝ ሲሆን፤ ትኩረት የሚሰጣቸው የማኅበረሰብ ክፍሎቹም የአዕምሮ እድገት ውስንነት፤ ሴተኛ አዳሪዎች፤ ጎዳና ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ሰዎችና ጧሪና ቀባሪ ያጡ አዛውንቶች ናቸው። እናም በሁለቱ ወቅት ቢያንስ 700 ቢበዛ ደግሞ 1000 ሰዎችን እንዲታገዙ ለማድረግ በሀዋሳ ከተማ አካባቢ ያሉ አጋሮቿ ጋር በመተባበር ተግባሩን ትከውናለች።

ያብስራ በድርጅቷ በኩል ብቻ አይደለም ሰዎችን የምታግዘው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታይ ቲክቶከር በመሆኗ የራሷን ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ ማስታወቂያቸውን ከመሥራት ጎን ለጎን ወጣቶችን በተለያየ አግባብ ታስተምራለች። በርካቶችን ታነቃቃለች፤ ለተሻለ ሥራም እንዲነሱ ታበረታታለች። ከዚያ ወጣ በማለትም በግሏም ሆነ በቡድን ለወጣቶች ማይንድ ሴትአፕ ላይ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ትሰጣለች። ተቀጥራ በምትሠራበት መሥሪያ ቤት በኩልም አርሶ አደሩ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆንም ትተጋለች።

መልዕክት ያብሰራ

የሰዎች ታላቅነት የሚመዘነው ባላቸው አቅምና እድል ተጠቅመው ለሌሎች መትረፍ ሲችሉ እንደሆነ የምታምነው ያብስራ፤ አካል ጉዳተኞችን መደገፍ የአንድ አካል ብቻ እንዳልሆነ አበክራ ትናገራለች። ቤተሰብ ግዴታው ቢሆንም ማኅበረሰቡ ካልደገፈው ውጤታማ መሆን አይችልም ባይ ነች። ደከመኝ ሳይሉ፤ ለነገ የሚሆናቸውን ነገር ሳይሰስቱ ሊሰጧቸው እንደሚገባ ታነሳለች።

አካል ጉዳት ተፈልጎ የሚመጣ ባለመሆኑ በሁሉም በኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ከመንግሥት እስከ ቤተሰብ ድረስ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እንክብካቤ ሊያደርግላቸው ያስፈልጋል። በሁኔታዎች ሁሉ ያልተገደበ ድጋፉን ማድረግ ይገባል። ማኅበረሰቡም ቢሆን ከማሸማቀቅ ይልቅ ብርታት ሊሆነው ያስፈልጋል ትላለች።

ማንነትን አለመቀበል ለነገሮች ውስብስብነት ያጋልጣል፤ ወቃሽነትን ያመጣል፤ ተስፋ መቁረጥንና አለመሥራትን ከፍ ያደርጋል። ይህ ደግሞ በሰው ጫንቃ ላይ እንድናርፍ ያስገድደናል። ሕይወትንም ጨለማ ያደርጋል። ስለሆነም አካል ጉዳተኞች ጉዳታቸውን ተቀብለው መጓዝና ለጥያቄዎቻቸው በራሳቸው መፍትሔ ማምጣት ነው በማለት ትመክራለች።

ራሳችንን ለመለወጥ የምንሠራው ሥራ፤ ስለራሳችን ጠንካራ ግምት የምንሰጥ ከሆነና ከውስጣችን የምናወጣቸው ቃላቶች ሳይቀሩ ይገነቡናል። እናም ለዓላማ የተፈጠርን እንደሆንን ለማወቅ ለራሳችን የምንነግረውን ነገር እንምረጥ ትላለች። እስትንፋስ ያላቸው ሁሉ ምንም ዓይነት አፈጣጠር ይኑራቸው ለዓላማ ተፈጥረዋልና አደርገዋለሁ ብለው ከተነሱ ተአምር መሥራት ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ እድልም፤ ተስፋም አላቸው ባይ ነች።

የያብስራ የመጨረሻ መልዕክት ራሳችን ላይ እንሥራ የሚል ነው። ራሳችን ላይ ስንሰራ አሸናፊ እንሆናለን፤ የምንፈልገው ላይ እንደርሳለን፤ ጠንካራ ነሽ የሚሉ ሰዎችን እናበረክታለን። በአካል ጉዳታችን የሚያሸማቅቀንም ሆነ አትችሉም የሚለንን እንቀንሳለን ትላለች።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You