
ሥራ አጥነት ትልቁ የወጣቶች ፈተና ነው። ሥራ በማጣታቸው ኃይል፣ ጉልበት እና አቅም ስላላቸው ብቻ ሮጠው እንደሚያመልጡ አስበው በስርቆት፣ በግጭት እና ከጦርኝነት ጋር በተያያዙ መንገዶች ላይ ወጣትነታቸውን ካሳለፉ ያሰቡበት ለመድረስ፤ የፈለጉትን ለማግኘት ይቸገራሉ፤ በጉልምስና በተለይም በእርጅና ዘመናቸው በመከራ ውስጥ ሕይወታቸውን ለመግፋት ይገደዳሉ። በሌላ በኩል በየድርጅቱ ሥራ ለማግኘት ሲንከራተቱ የቆዩ ወጣቶች በጨዋነት እና አርቆ አሳቢነት የትኩስነት ዕድሜቸውን በበጎ ዓላማ ላይ ከዋሉ ተጠቃሚ ይሆናል። አይከስሩም ቆይቶም ቢሆን ያተርፋሉ። ይህን ለመፃፍ የተነሳሁትም አንዲት ወዳጄ በወጣትነቱ ስለጠፋ አንድ የአጎቷ ልጅ ነግራኝ ነው፡፡
ጦርነት እና ግጭት ሲነሳ ተደጋግሞ የሚጠቀሰው፤ ሴቶች እና ሕፃናት ተጎጂ ይሆናሉ የሚል ሃሳብ ነው። ሆኖም ፊት ለፊት የሚጋፈጡት ወጣቶች መሆናቸውንም መዘንጋት አይገባም። በተለያዩ ምክንያቶች እና በተለያዩ ግለሰቦች ፍላጎት የተነሳ ሌሎች ሰዎች ለመኖር መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንደኛው የሆነውን ሰላምን ያጣሉ። ወጣቶች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ግጭትን እየሳቡ ወደ ራሳቸው በመጎተት ለመሞት ይጣደፋሉ። ከሰላም አደፍራሾች ጋር ተቀላቅለው ሕይወታቸውን ያበላሻሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለጦርነት ተመልማዮች ሆነው ባልገመቱት እና ባላሰቡት መንገድ ሕይወታቸውን ይገብራሉ፡፡
ወዳጄ እንደነገረችኝ፤ ወጣቱ እንደ ብዙሃን የሀገሬው ወጣቶች ፊደል ከመቁጠር አልፎ፤ ብዙ መንገድ በእግሩ ተጉዞ እና እንቅልፍ አጥቶ አጥንቶ የዩኒቨርሲቲ ደጃፍን ለመርገጥ በቅቷል። ዩኒቨርሲቲ መግባት ብቻ አይደለም፤ በጥሩ ውጤት በኢንጂነሪንግ ዲግሪ መያዝም ችሏል። ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በመመረቁ ተወልዶ ላደገባት የገጠር መንደር ትልቅ ደስታ ቢፈጥርም፤ ደስታው ብዙ አልቆየም። ወጣቱ እርሱም ሆነ ቤተሰቡ እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዳሰበው በቀላሉ ሥራ አግኝቶ ቤተሰቡን መደገፍ አልቻለም። ቀን ቀንን እየተካ፤ ወራት አልፈው ተርፈው ዓመታት ተቆጠሩ። ወጣቱ ሥራ ለመቀጠር በየከተማው እየዞረ የትምህርት ማስረጃውን ቢበትንም ጠርቶ የሚቀጥረው ድርጅት አጣ።
እርሱ ብቻ አይደለም፤ አብረውት የተመረቁ ወጣቶችም ከጥቂቶቹ በቀር ብዙሃኑ ሥራ አላገኙም። እንደ እርሱ ሁሉ ሌሎችም ሥራ ፈላጊዎች እንጂ፤ ሥራ ለመፍጠር የሚያስቡ አልነበሩምና በወጣትነታቸው ሥራ ማጣት አብረከረካቸው፤ ተስፋ መቁረጥ ጀመሩ። ብዙም ሳይቆዩ ተሸነፉ። እናም ከእርሱ ውጭ ያሉት ወጣቶች በቡድን ተደራጅተው ነፃ አውጪ ነን በሚል ስም ከተደራጁ ጋር ተቀላቀሉ። መንገደኛን ከሚዘርፉ ሽፍቶች ጋር ሆነው ገንዘብ አገኙ፤ ወጣቱ ይህንን ሰማ። ለተወሰኑ ጊዜያት ራሱን ተቆጣጥሮ በቤት ውስጥ እናት እና አባቱን በእርሻ እያገዘ ቆየ። ምንም እንኳ ስለ ሕግ ቢያስብም፤ ኃይል፣ ጉልበት እና አቅም ስላለው ከወታደርም ሆነ ከፖሊስ ከማንም እና ከምንም የፀጥታ ኃይል ሊያመልጥ እንደሚችል ተማምኖ ከቤቱ ወጥቶ ከሽፍቶቹ ጋር ተቀላቀለ። ገንዘብ ፈልጎ ሊገድል ሲሄድ ሊገደል እንደሚችል አልገመተም፡፡
ወጣቱ ዕድሜ የሚያመጣውን የስሜት ፈተና ተቋቁሞ ማለፍ ተሳነው። ተጠልፎ ወደቀ። እንደ ወጣቱ ሁሉ በሀገራችን ተመርቀው ሥራ የሚጠባበቁ ወጣቶች ቁጥር ቀላል አይደለም። ሥራ ሲጠባበቁ በአደገኛ መጥፎ መረብ የሚያዙ፤ የተጠለፉበትን መረብ በጥሰው ለመውጣት የሚቸገሩም ብዙ ናቸው። አንዴ ከተጠለፉ በኋላ ዕድል ቀንቷቸው ቀድመው ካልባነኑ የጉልምስናም ሆነ የእርጅና ሕይወታቸውን በጉስቁልና ውስጥ የሚያሳልፉም ብዙ እንደሚሆኑ አያጠያይቅም። ለዚያውም ሕይወታቸው ከተረፈ ነው፡፡
በርግጥ በስሜት ለሚገፉት አንዳንድ ግብዝ ወጣቶች በምድር መኖር ተራ ነገር ነው። በዚህ አስተሳሰባቸው ሳይኖሩ ለሞት ይበቃሉ። ራሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎችን ይጎዳሉ። የሞቱለትን ዓላማ ሳያውቁ፤ ተፈጥረው ሳይኖሩ ምድሪቷን ይሰናበታሉ። በወጣቶቹ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብም ሆነ ሀገር መጠቀም ሲኖርባቸው፤ በእንደዚህ ዓይነት ወጣቶች ዋጋ ይከፍላሉ። በብዙ መልኩ ይጎዳሉ። እንደዚህ ዓይነት ወጣቶች የሀገር ባለውለታ ሳይሆኑ፤ የሀገር አጥፊ የነበረ ትውልድ ተብለው መጥፎ የታሪክ ዐሻራን ጥለው ያልፋሉ።
በአንዲት ሀገር ውስጥ ሰላም ከሌለ ማንም በምንም መልኩ መኖር እንደማይችል እሙን ነው። ለሕዝብ እዋጋለሁ እያሉ መንገደኛ አስቁመው መዝረፍ፤ አልፎ ተርፎ ማገት እና መግደል፤ ወጣቱ የተፈጠረበትን ዓላማ ዘንግቶ የመኖርን ሚስጥር ረስቶ የሕይወት ዘመኑን በፀፀት እንዲያሳልፍ የሚያደርግ መሆኑን መንገር ለቀባሪው እንደ ማርዳት ይቆጠራል። ሆኖም በተደጋጋሚ የሚገለጸው በዋናነት ወጣቶች ለሰላም መደፍረስ ምክንያት መሆናቸውን ነው።
በአንድ ሀገር ውስጥ እየኖሩ መነጋገር ሲቻል ለምን መገዳደል አስፈለገ? በዚህ ላይ ወጣቱ ቀድሞ ሊያስብበት ይገባል። ነገር ግን ከማሰብ ይልቅ በስሜት የሚነዳው በዝቶ ሁኔታዎች አሳሳቢ መሆን ከጀመሩ ውለው አድረዋል። አሁን መደመም የጀመርነው አልዋጋም በሚል ወጣት ነው። በርግጥ አንዳንዶች ግጭቶች ውስጥም ሆነ ጦርነት ላይ የሚሳተፉት ገንዘብን ብቻ አስበው አይደለም። በአንዳንድ አፈ ቀላጤዎች ተታለው ነው።
ከሚያለያዩዋቸው ይልቅ የሚያቀራርቧቸው ብዙ ጉዳዮች እያሉ የፖለቲካ ትርፍ የሚፈልጉ አረመኔዎች፤ ለልዩነት ቦታ እንዲሰጡ ደጋግመው በተለያዩ መንገዶች ይነግሯቸዋል። ሳይገፉ እየተገፉ ስለመሆኑ እየነገሩ ያሳምኗቸዋል። አንድን ነገር ሲያጡ፤ ያጣችሁት የእዚህ ብሔር ተወላጅ በመሆናችሁ ነው እያሉ ስሜታቸውን በሚኮረኩሩ ጉዳዮች ይቆሰቁሷቸዋል። ወጣቶቹም ልባቸውን ሰጥተው ባልገባቸው እና ግራ ባጋባቸው ጉዳይ ሕይወታቸውን ለማጣት ይሰናዳሉ።
እነርሱ ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ሀገር እንደምትራቆት አይገነዘቡም። በውጭ ምንዛሪ ስለሚገዙት ተተኳሽ ጥይቶች አያስቡም። እነርሱ በሚተኩሱት ጥይት ሕይወታቸውን ስለሚነጠቁ ሌሎች ወጣቶች አያስተውሉም። ሀገር ለዘመናት ገንዘቧን አውጥታ ያስተማረቻቸው ወጣቶች ሀገራቸውን ሳይረዱ፤ አንድ ርምጃ ለማራመድ አንድ ጠጠር ሳይጥሉ፤ ጦርነትና ግጭት ውስጥ መግባታቸው ሀገራቸውን መቅበር መሆኑን አይገነዘቡም። የጥንት ወጣቶች ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ ሲያስጠሩ፤ የአሁን ትውልድ ወጣት ጦርነት እና ግጭት ውስጥ በመሳተፍ ለማያውቀው፣ ለማያምንበት ዓላማ ሕይወቱን እየሰዋ ሀገር ያወድማል።
አንድ ሀገር ከሌላ ሀገር ጋር መንግሥታቱ መካከል ባለ ግንኙነት ግጭት ውስጥ ሲገቡ፤ መንግሥታት የጦርነት ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት መደራደር ያስፈልጋልና ብለው በድርድር ብዙውን ችግር ለመፍታት ይጥራሉ። ይህንን የሚያደርጉት በጦርነት የሚመጣው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ስለሚረዱ ነው። ጦርነት እና ግጭት ለሀገሩ ሊሠራ የሚችለውን ወጣት እንደሚበላ ይገነዘባሉ። በኢኮኖሚያቸው ላይ የሚያስከትለውን በቅጡ ይረዳሉ። ስለዚህ ለመነጋገር እና ለመደራደር ቅድሚያ ይሰጣሉ። በሌላ በኩል ያለው ሀገር መንግሥት በተቃራኒው የሌላዋን ሀገር ሉዓላዊነት የሚነካ ተግባር ከፈፀመ ከሀገር የሚበልጥ የለምና ለሀገር ሲባል ጦርነት ላይ መሳተፍ መጥፎ አይደለም። ነገር ግን ገና ለገና የሚዘረፍ ገንዘብ ለማግኘት፤ በውሸት ተታሎ የሌሎችን ፍላጎት ለማሟላት የገዛ ወገን ላይ መዝመት ትልቅ ውርደት እና ከጨዋነት ያፈነገጠ ስግብግብነት ነው።
ሰላም ከገንዘብም ሆነ ከሥልጣን በላይ ነው። ሰላም ከሌለ እና ሀገር ከፈረሰ ገንዘብም ሆነ ሥልጣን ሁለቱም ዋጋ የላቸውም። ወጣትነት ብዙ ነገርን ያስመለክታል። በርግጥ መጥፎውን ብቻ ሳይሆን መልካሙንም ያሳያል። ዕድሜ የሚያመጣቸውን ቶሎ የፈለጉትን የማግኘት እና መሻታቸውን ሲያጡ ቶሎ ተስፋ የመቁረጥ የስሜት ፈተናዎችን ተቋቁመው የሚያልፉ ብልሆች፤ ለተቸገሩ የሚደርሱ ወጣቶች ብዙ ናቸው። መንገድ ላይ የወደቁ አዛውንቶችን የሚያነሱ፤ ተስፋ የቆረጡ ወጣቶችን በማበረታታት በጋራ ሥራ የሚጀምሩ፤ ጦርነት እና ግጭት ውስጥ ከመግባት ይልቅ አብረው እየወደቁ እና እየተነሱ ለማደግ ዝግጁ የሆኑም ጥቂት አይደሉም። እነዚህኞቹ በስሜት ተገፍተው ተወልደው ገና ከማደጋቸው የሞትን አፍንጫ ከሚያሸቱ ወጣቶች በእጅጉ የተለዩ ናቸው።
ለብልሆቹ ወጣቶች ሕይወትን ማጣት አርግዛ ወልዳ ያሳደገች እናታቸውን፤ በብዙ መከራ ውስጥ ሆኖ ያሳደገ አባታቸውን እንዲሁም በድህነት ውስጥ ሆና ያስተማረች ሀገራቸውን ማሳዘን መሆኑን ይገነዘባሉ። የተፈጠሩበትን ዓላማ በሙሉ ዘንግቶ ከንቱ ሆኖ መቅረት መሆኑን ያምናሉ። ስለዚህ ሕይወታቸውን አብዝተው ይወዳሉ። ሕይወትን ማጣት ቀላል አለመሆኑን ስለሚገነዘቡ፤ ቢወድቁ ለመነሳት ይጥራሉ። ምንም እንኳ ሥራ ቢያጡም ብልህ ሆነው በዘዴ ይኖራሉ። ተስፋ አይቆርጡም። ሁለት ዶሮ ገዝተው ለማራባትም ሆነ ጫማ ጠርገው ሕይወታቸውን በማቆየት፤ ነገ ታላቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረት ያደርጋሉ። የተለያዩ ሥራዎችን ይሞክራሉ። እንደ እዮብ መቶ ጊዜ ቢወድቁ መቶ ጊዜ ለመነሳት ጥረት ያደርጋሉ። ተስፋ አይቆርጡም።
ሕይወታቸውን ለመቀየር ጓጉተው የፈጠሩት ሥራ አልሳካ ሲላቸው ሌላ ይሞክራሉ። የሚወዱትን ሥራ አግኝተው ጉልበታቸውን ሰጥተው ደጋግመው ሲሞክሩ ይሳካላቸዋል። ወጣትነትን በብዙ ትዕግስት ያልፏታል። በሂደት የሚመኙትን እና የተፈጠሩበትን ሠርተው የማንም መጠቀሚያ ሳይሆኑ ተሳክቶላቸው፤ ዘመናቸው በበረከት ይጥለቀለቃል። በሽምግልና ዘመናቸው ተከብረው እና ታፍረው በድሎት ሕይወታቸው ይረዝማል።
ብልሆቹ ወጣቶች ዕድሜያቸው ስለሚረዝም መልካም ታሪክ የሚሠሩበትን ጊዜ ያገኛሉ። የተፈጠሩበትን ዓላማ አውቀው ከቤተሰባቸው እና ከሀገር አልፈው ዓለምን የሚጠቅሙበትን ዕድል ያገኛሉ። ወገኖቻቸውን ያኮራሉ። መልካም ስማቸውን ይተክላሉ። ሲሸመግሉ ሕክምና ቢስፈልጋቸው መድኃኒት አጥተው ጉድጓድ አይገቡም። በብዙ እንክብካቤ ሕክምናው አለ ወደተባለበት ሀገር ሄደው ይታከማሉ። ያሻቸውን መድኃኒት ገዝተው ከሞት ያመልጣሉ። በጠዋት ትክክለኛውን መንገድ በመያዛቸው ሲመሽ ማደሪያ ቤት ማረፊያ አልጋ አያጡም። አርጅተው ቢመቱም አይረሱም፤ በብዙዎች ይታወሳሉ።
የዘመኑ ወጣት ብልህ መሆን ይጠበቅበታል። በአጭበርባሪዎች ተታሎ ለማያውቀው ዓላማ፤ ለአንዳንዶች መጠቀሚያ ሲል ሕይወቱን ለመስጠት ወደ ግጭት ለመግባት መስማማት የለበትም። ሆኖም ቂላቂሎቹ ወዳጄ እንደነገረችኝ ወጣት ሳይኖሩ ቤተሰባቸውን እና ማኅበረሰቡን እንዲሁም ሀገራቸውን ጎድተው ሁለት ሞት በመሞት የታሪክ ተወቃሽ ለመሆን የሚያኮበኩቡ ይኖራሉ። ይሄ ምርጫ ትክክል አይደለም። ማጣት ቢያጋጥምም፤ ከመሞት መሰንበት ይሻላል። መኖር ደጉ ይባል አይደል። ያጣም ጊዜውን ጠብቆ ያገኛልና ከግጭት ይልቅ ሰላምን መምረጥ ይሻላል። በርግጥ ሰላም ይሻላል ብቻ ማለት በቂ አይደለም፤ ሰላም የሚሆንበትን ሁኔታ ከቤተሰብ ደረጃ ጀምሮ ማኅበረሰብ አጠቃላይ ሕዝቡ እና በዋናነት መንግሥት በደንብ ሊያስቡበት ይገባል። ሰላም!
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም