“ሰማይና ምድር” የመኖሪያ ግቢያችን የሚጎራበተው ችምችም ባሉ ሕንጻዎች በተወረረ አንድ የሪል እስቴት “ከተማ” ነው ።
በጅምር ተገትረው በቀሩት የሪል እስቴቱ ሕንጻዎች ውስጥ የተፈለፈሉትን እያንዳንዱን የመኖሪያ አፓርትመንት (units) እንቁጠር ከተባለ ሰልችቶን መቁጠሩን ካላቆምን በስተቀር የበረታ ሰው ከተያያዘው ሺህ ተምናምን እንደሚሆን በፍጹም አልጠራጠርም ። ያውም ካላነሰ! በግል የንባብ ክፍሌ ውስጥ ከመጻሕፍቶቼ ገጾች ጋር የማደርገውን መስተጋብር ገታ አድርጌ ለቅጽበታዊ እረፍት ዐይኖቼን በመስኮቱ በኩል ወርወር ሳደርግ ፊት ለፊቴ ተገሽሮ የማስተውለው ይህንኑ በአጽሙ የቆመውን የብሎኬት ክምር “ከተማ” ነው ። ባለንብረት ነኝ ባዩ ወራሪ ግለሰብ ማን እንደሆነ ለመገመት አይከብድም ።
ጠብመንጃና ጊዜ አጀግኖት ከእኔ በላይ ላሳር እያለ የኖረ አንድ ጎምቱ የሕወሓት ሰው ንብረት እንደሆነ መንግሥት ደርሶበት በጥብቅ እግድ ሥር እንደወደቀ በስፋት ይወራል ። የባለቤቱን ፍጻሜ በተመለከተ ውስጥ ለውስጥ የሚወራው የመርዶ ሹክሽታ ጥርት ብሎ በይፋ ሲገለጥ እኔም ደፈር ብዬ እከሌነቱን አስተዋውቃለሁ ።
ይህ ሀብት ለግለሰቡ የኢምንት ያህል የሚቆጠር እንጂ መሰልና አምሳያ የሌላቸው ቀሪዎቹ ቢዘረዘሩማ የአገርን አንጡራ ቅርስ ግማሽ ሊሆኑ እንደሚችሉ በብዙዎች ይገመታል ። ይህ ግለሰብ ቁጥሩና መስፈሪያው የማይታወቀውን ይህንን መሰል ሀብት ያካበተው ላቡን በመገበር ወይንም ነግዶ በማትረፍ ሳይሆን በጠራራ ፀሐይ ፊት ዘርፎና አዘርፎ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም ።
ይህንን ጉዳይ ተመልሼ ስለምቋጨው ላባቸውን አንጠፍጥፈው የከበሩ፤ ሀብት ማፍራት ብቻ ሳይሆን መርካቶንና ዙሪያዋን “የገነቡ” የአርአያ ሰብ ባለታሪኮችን ዜና መዋዕል ለማነጻጸሪያነት እንዲያግዝ በታላቅ አክብሮት እንዘክራለን ።
ብርሃኑ ሰሙ ግሩም ጋዜጠኛና ብርቱ ደራሲ ወዳጄ ነው ። በብዙ ምሳሌያዊ ሥራዎቹ እጅግም ያልተዘመረለት ይህ የብዕር ሰው “ከእንጦጦ ሐሙስ ገበያ እስከ መርካቶ” በሚል ርእስ በ2003 ዓ.ም አንድ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል ።
የመጽሐፉ ገጾች የተሸከሙት ከ100 በላይ የሆኑ የአገራችንን ስኬታማ የንግድ ሰዎችን ታሪክ ነው ። የብዙዎቹ “የንግድ እትብት የተቋጠረው ከመርካቶ ጋር” መሆኑንም ማስታወስ ያስፈልጋል ። “ሞላ ማሩ – የጥረት አብነት” በሚል ርዕስም በ2012 ዓ.ም ብርሃኑ ሁለተኛ መጽሐፉን ለአንባቢያን አድርሷል ።
በእነዚህ ሁለት መጻሕፍት ውስጥ የተዘረዘሩት አብዛኞቹ ባለታሪኮች “የእምዬ መርካቶን” ስም በትጋት ያስጠሩ ዘመን አይሽሬ ጀግኖች መሆን ብቻ ሳይሆን ትተውት ያለፉት አሻራም ከዘመን ዘመን የሚሸጋገር ነው ። ይበልጥ የአድናቆት ቃላት እስኪያጥር ድረስ ለመግለጽ በጣሙን ያዳግታል ።
ጥቂት አብነቶችን እንጠቃቅስ፡- አንዳንዶች ከመንገድ ዳር ሊስትሮነት የሥራ ጥረታቸው አስፈንጥሮ ሽቅብ ወደ ሀብት ማማ ያጎናቸው ምሳሌዎች ናቸው ። ዝነኛውን ባለ አረቄ ፋብሪካው ባለቤት ሞላ ማሩን ይመለከቷል ።
አንዳንዶች ቆዳና ሌጦ በአናታቸው እየተሸከሙ በመሸጥ ድህነትን ረትተው አንቱ የተሰኙ ነጋዴዎች ነበሩ ። አቶ ነጋሽ ቢርቢሶ አንዱ ናቸው ። ስማቸውም ከመርካቶው አስፋው ወሰን ቡና ቤት ጋር ጎልቶ ይጠራል ። በሽቶ ንግድ የሚታወቁት የመርካቶው አቶ ሁነኛው መራ ከዘይት ችርቸራ ተነስተው የሚሊዮኖችን ቤት ጠረን በመዓዛ ያወዱ ስመ ግዙፍ ነጋዴ ነበሩ ። አጎናፍር ወልደየስ ከድርና ማግ ንግድ ተነስተው በበርካታ ሕንጻዎች መርካቶን ያቆነጁ ነጋዴ ነበሩ ።
ከትግራይ ምድር ተነስተው አዲስ አበባ የዘለቁት አዝማች መሐመድና ሦስቱ ወንድሞቻቸው አንዋር መስጊድ ፊት ለፊት የተሰደሩትን ፎቆች የገነቡት ከዜሮ ተነስተው በላባቸው ወዝ ጥረው ግረው ከስኬት ማማ ላይ በመድረስ ነው ። የኦሮሞ ተወላጆቹ አቶ ታደሰ ደስታ ከጎዳና ንግድ ተነስተው በጥረታቸው ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሦስቱ ልብስ ሰፊዎች መካከል አንዱ ለመሆን የበቁ ነበሩ ።
በሆቴል ንግድ ስኬትም ስመ ጥር ነበሩ ። አቶ በልዳ በንቲ፤ መርካቶ ሸራ ተራ ስማቸው የሚጠራው ከትልቅ አክብሮት ጋር ነው ። አቶ አደም አሎም እንዲሁ በሥራቸው ትጋት ከትንሽ ተነስተው የገዘፉ አርአያ አባት ነበሩ ።
ኤርትራዊያኑ አቶ ኪዳኔ በየነ (አምባሳደር ሲኒማ ፊት ለፊት ያለው የኪዳኔ ሕንጻ ባለቤት)፣ በኬካቸውና በዳቧቸው ስማቸውን የተከሉት ወንድማማቾቹ አቶ በላይ ተክሉና አቶ ዘሙይ ተክሉ፣ የካዛንቺስ ቶታሉ ባለቤት ሚ/ር (አቶ) ሣላህ አህመዲን መነሻቸው የተሟላ ካፒታል ሳይሆን ትጋታቸውና ጥረታቸው ብቻ ነበር ።
ሀጂ ኡመር ኢማም (የመዲና ሕንጻ ባለቤት)፣ አህመድ ሣላህ ኤልዛህሪ፣ ሰዒድ ዓሊ ካሉስና የኪኪያን ቤተሰቦችን የስኬት ታሪክ ማድመጥና መስማት ከትቢያ ላይ ተነስቶ መክበር ምን እንደሆነ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው ። የገነቧቸው ሕንጻዎችም አፍ አውጥተው ይመሰክሩላቸዋል ።
ሸንኮራ አገዳ በሳንቲም እየቸረቸሩ የከበሩ፣ ከሰል ተሸክመው እየዞሩ በመሸጥ የከበሩ፣ ከሳር ንግድ ተነስተው አንቱ የተባሉ እጅግ ብዙዎች ናቸው ። መርካቶን መርካቶ አሰኝተው ደማቅ ታሪክ ያስመዘገቡ እኒህን መሰል ሺህዎች መዘርዘር ቢቻልም ለማሳያነት ግን የመረጥናቸው እነዚህ ጥቂቶቹ ይበቁ ይመስለናል ።
እነዚህ ታላላቅ የሕዝብ ባለውለታዎች የሀብት ማግኛ ዘዴያቸው ዘረፋና ቅሚያ ሳይሆን ስራና ጥረት ነበር ። ሀብታቸውን አግበስብሰው ወደ ውጭ አገር ማሸሽ ሳይሆን በአገራቸው ኢንቨስት በማድረግ ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል ። ልጆቻቸውንም ተክተው በእነርሱ ፋና እንዲጓዙ ምሳሌ ሆነዋል ።
የስኬታቸው ዋናው ማጠንጠኛ እሴት ሥራ! ሥራ! ሥራ! ብቻ ነበር ። “አስጨናቂው ደርግ” በትረ ሥልጣኑን እንደጨበጠ ባይቀጠቅጣቸው ኖሮና ንብረታቸውን ወርሶ ባያራቁታቸው ኖሮ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ምን መልክ ሊኖራት ይችል እንደነበር በዐይነ ህሊናችን መመልከት ይቻላል ።
ወታደራዊው መንግሥት በሶሻሊዝም መንፈስ ሰክሮ አገሪቱን በማመሳቀሉ ሀብት ማፍራት እንደ ነውር ተቆጥሮ ድህነት እልል እየተባለ እንደተሞገሰ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው ። ደርግን ተከትሎ የመጣው የአሸባሪው ሕወሓት መንግሥት ደግሞ ይበልጡኑ ሰብዓዊ አውሬ ሆኖ ሕዝቡን በመከራና ስቃይ፣ የአገሪቱን ሀብት በማን አለብኝነትና በእብሪት ሙልጭ አድርጎ በመዝረፍ እነሆ ከላይ እንደገለጽነው ያሉ ደፋር የቡድኑ ሹመኞች አዲስ አበባን፣ ዋና ዋና ከተሞችንንና የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ሙልጭ አድርገው በመዝረፍ በጭካኔ በትር እየቀጠቀጡን ሃያ ሰባት ዓመታት ያለ ከልካይ እንደፈለጉ ሲፋንኑ ኖረዋል ።
ወድቀው ከተንኮታኮቱም በኋላ “ከኮብራ እንቁላል የርግብ ጫጩት እንደማይፈለፈል ሁሉ” ዋናዎቹ የአሸባሪው ሕወሓት መሪዎች በቀደዱት የጦርነት ቦይ አማራና አፋር ክልል ጎርፉ ያደረሳቸው ወራሪዎቹ ጫጩት ልጆቻቸው እንደ መሪዎቻቸው የግለሰብና የአገር ሀብት እየዘረፉ ወደ ትግራይ ሲያጓጉዙ የከረሙት “የእሳት ልጅ ረመጥ” የሚሉትን ብሂል በመተግበር ነበር ።
አለቆቻቸው በሰፈሬ እንዳለው የሪል እስቴት ከተማን ሲያንጹ፣ ልጆቻቸው ደግሞ በላብ የተገነቡ የአገራችንን ከተሞች ያወድሙ የነበረው እየተጋቱ ያደጉትን የግፍ ዋንጫ እየተጎነጩ ነበር ። ደግመን ደጋግመን የምንጠይቀውን ጥያቄ ዛሬም ደግመን እንጠይቃለን ። የትምህርት ቤቶችን፣ የኮሌጆችንና የዩኒቨርሲቲ ንብረቶችንና ሀብቶችን ሙልጭ አድርገው በመዝረፍ ወደ መቀሌ አጓጉዘው በመከመር ልጆቻቸውን ሊያስተምሩበት እየተከፋፈሉ እንደሆነ ይሰማል ።
በሌብነት ዘርፈው በወሰዱት የላብራቶሪ ማይስክሮኮፕ ሌንስ ውስጥ ተማሪዎቻቸው አፍጥጠው እያዩ የሚመራመሩባቸው ጀርሞች በሽታ አምጭ ተህዋስያን ሳይሆኑ በአባቶቻቸው ደም ውስጥ የነበረ ዘረኛና ትውልድ ገዳይ ደዌን ነው ።
ዘርፈው የወሰዷቸው የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎችና መድኃኒቶችም የያዛቸውን ክፉ የጥላቻ ደዌ ሊፈውሱላቸው ስለማይችሉ ጥቅም ላይ የሚያውሏቸው ፈውስ ለማግኘት ሳይሆን የማይፈወስ የግፍ ሽል ዲ.ኤን.ኤያቸው ውስጥ ለማራባት እንደሆነ ሊረዱት ይገባል ። ከማጀት የሰረቁት የደሃ ቤተሰቦች ሽሮና በርበሬ ቃር ሆኖባቸው ለትውከት ካልዳረጋቸው በስተቀር ሆዳቸው ውስጥ ገብቶ ሊረጋ አይችልም ።
የአማራና የአፋር ልጆችን ተስፋ ገድለው የእነርሱ ልጆች ተስፋ ይለመልማል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ። አባቶቻቸው የአገር ሀብት በጠራራ ፀሐይ ዘርፈው ወደ ውጭ አስኮበለሉ ። ልጆቻቸው ደግሞ የወንድም ሕዝቦችን ሀብት ዘርፈው ወደ ትግራይ ክልል አጓጓዙ።
ልዩነቱ “እሳት ካየው ምን ለየው” ካልሆነ በስተቀር “ያንጠለጠለም ሆነ ያዘለ ያው ተሸከመ” እንዲሉ ነው። ሕወሓት አገሪቱን ካቆሰለ በኋላ ሊሞት እየተንፈራገጠ ያለው በአንድ ታላቅ አገራዊ እሴት ላይ የማይሽር ጠባሳ እየጣለ ነው፤ “ሀብት የሚገኘው በላብ ውጤት ተደክሞና ተለፍቶ ሳይሆን ተሰርቆና ተዘርፎ ነው” የሚል ።
ይህን ፍልስፍናውን የፈለፈላቸው የትግራይ ወራሪ ወጣቶች ተራቀውበታል ። አገር አስተምራ ለቁም ነገር ያበቃቻቸው የክልሉ ምሁራን ተክነውበታል ።
ተከታዩ ትውልድም ይህንንው ፈለጋቸውን ተከትሎ እንዲራመድ እየቀሰቀሱትና እያሟሟቁት እንዳሉ እያደመጥን ነው ። አንዳንድ ጉዳዮችን እያስታወስን ዝም ብለን እናሰላስለው ።
ከድሃው አማራና አፋር ጎጆ በተሰረቁት የማዕድ ቤት ዕቃዎች ላይ ምግብ አቅርበው ሲበሉ ኅሊናቸው ምን እያለ ይሞግታቸው ይሆን? የተዘረፉትን የቤት እንስሳት እያረዱ ሲመገቡስ እንደምን ከጉሮሯቸው ይወርድላቸዋል? በተዘረፉ አልባሳት ሲዝናኑስ ሰውነታቸውን አይቀነቅናቸውም? የተዘረፉ የንጹሐንን ገንዘብ እንዳሻቸው ሲመነዝሩ ውስጣቸው ምን ይላቸዋል? ከፋብሪዎች ነቃቅለው የወሰዷቸው ንብረቶች መቀሌ ውስጥ ሲተከሉ ሌብነታቸውን ወደ ገንዘብ ቀይረው ስቶክ ላይ የሚያሰፍሩት ስንት ብር ዋጋ ተምነው ነው? ከትምህርት ቤቶች በዘረፏቸው ሀብቶች “ምሁራን” ሊያፈሩ፣ ከነጋዴዎች በዘረፉት ንብረት “ባለሀብት” ሊያፈሩ እግዚኦ ወደ ፈጠራቸው! ምን ይሉት እፉኞች ናቸው? አገሬ ልትረባረብባቸው ከሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል አንዱ ለረከሰው እሴቷ መቀደስ ቅድሚያ በመስጠቱ ላይ ሊሆን ይገባል ።
“ሀብት የሚከማቸው በዘረፋ ነው” የሚለውን የሕወሓት የከረፋ ፍልስፍና አለቅልቆ በመድፋት “የላብን ክብር” በማሳየት ትቢያዋን ማራገፍ ። ሀብትን ዘርፎ ከአገር ማስኮብለልን ሳይሆን ሀብት በአገር ውስጥ እንዲበዛ ማበረታታት ። በተረፈ በምድራዊ ሲኦል ተጋርደው ላሉትና የሰማያዊ ገሃነም ቤታቸው ለሚጠብቃቸው የአሻባሪው ሕወሓት ወላጆችና ውላጆች መልእክታችን እንዲህ የሚል ነው ።
በቅርቡ በፍትሕ አደባባይ ቆማችሁ የግፋችሁን ዋንጫ ትጎነጫላችሁ ። ሳይውል ሳያድር እጃችሁ በሰንሰለት ታብቶ ለአደባባይ ትገለጣላችሁ ።
መኖሪያችሁ ወህኒ፣ ዘለዓለማዊ ማረፊያችሁም ገሃነም እንደሚሆን አንጠራጠርም ። ኢትዮጵያ በልጆቿ ዳግም አንሰራርታ ትደምቃለች! በፈጣሪዋ ተራዳዒነት ተመክታም ትለመልማለች! ሰላም ይሁን!::
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30/2014