ኢትዮጵያውያን ስለ አገራቸው ያልጮሁበት ጊዜ አለ ብዬ አላስብም። በተለይ ያለፉት አስራ ሁለት ወራቶች ስለ አገራችን አብዝተው የጮሁባቸው ጊዜያቶች ነበሩ ማለት ይቻላል።
የነጻነት ምድር የሆነችው አገራችን የነጻነትን ዋጋ በማያውቁ ጣልቃ ገቦች በእጅጉ ስትፈተንና እኛም ስንታገል ነበር…። ከሰሞኑ በብዙ ነገር ላይ ሰልፍ ወጥተናል። በብዙ ነገር ላይ ድምፃችንን አሰምተናል።
ከመከላከያ ጎን ለመቆም፣ የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት በመቃወም፣ የውጪ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ የሚዘግቡትን የተሳሳተ ዜና በመቃወም፣ አገር ለማፍረስ የተነሱትን አሸባሪዎቹን ሕወሓትንና ሸኔን በመቃወም በዚህ ሁሉ ስለ አገራችን ጮኸናል።
እንደ እያሪኮ ቅጥር የጠላቶቻችንን እብሪት በኃይል ለመደምሰስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድ የሆንበት ሰሞን ቢኖር ይሄ ጊዜ ነው ። አንዳንዶች ይሄን ጊዜ ከአባቶቻችን በአድዋ ከፈጠሩት አንድነት ጋር ያዛምዱታል። እውነት ነው ይሄ ጊዜ የነጻነት ግዜያችን ነው ኢትዮጵያን የምንስልበት።
በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ሕዝብ ስለ አገሩ እየተናገረ ነው፣ሕዝብ የኢትዮጵያን መጻዒ ዕድል ለመወሰን እየታገለ ነው። ኢትዮጵያን በመሳል ውስጥ የተፈጠረ ታላቅ የሕዝብ ንቅናቄ ነው። የአሸባሪው ሕወሓት እብሪት ከዛም የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ይሄን ሁሉ ተከትሎ ደግሞ ስለአገራችን የሚዘገቡ ያልተገቡ ዜናዎች ሕዝብን ከማስቆጣት አልፈው አደባባይ አውጥተውታል።
እነኚህ ድምፆች የአንድነት ድምጾች ናቸው..እኚህ ድምጾች የእውነትና የፍትሕ ድምፆች ናቸው። እነኚህ ድምፆች ትላንትና አገር አቁመው ነበር ፤ዛሬም አገር የሚያቆሙ ናቸው። አገር ሰው ትፈልጋለች፣ ሰው ደግሞ አገር ያሻዋል ይሄ እውነት ድሮም የዘለቀ እውነታችን ቢሆንም እንደ ዛሬ ግን ገብቶን አያውቅም። አገርን የሳሉ፣ ትውልድን ያስቀደሙ የሕብረት ድምጾች ቅያሜና የተቆርቋሪነት ስሜት ተላብሰው በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እየናኙ ነው። ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደሙ፣ እኛነትን የተላበሱ ፍትሕ ናፋቂ የሕዝብ ድምጾች በአገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ አሸባሪውን ሕወሓት በመኮነን ጀግናው መከላከያ ሠራዊትን በማወደስ እንዲሁም ደግሞ የምዕራባውያኑን ጣልቃ ገብነት በመኮነን ስለ እውነት እየጮሁ ነው።
ሕዝብ በአንድነት ከተነሳ፣ እውነት ፈላጊ ነፍሶች አንድ ላይ ከቆሙ ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ ናት። በታሪክ እንደሰማነው የእስካሁኑ የኢትዮጵያ ከፍታ በአንድነት በቆሙ ሕዝቦች የተገኘ ነው። በአሸናፊነት የተጠናቀቀው ትላንትናዊ ታሪካችን ሁሉ በሕዝብ ድምጽ የተገኘ፣ የሕዝብ ድምጽ የወለደው የአንድነት ውጤት ነው።
ዛሬም እየሆነ ያለው ተመሳሳይ ነገር ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ሕዝብ ተነስቶ፣ ሕዝብ በአንድነት ቆሞ ውጤት ያላመጣ ታሪክ የለንም። አብዛኛው ታሪኮቻችን ሕዝብ ወለድ ናቸው። ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚጮሁ አንደበቶች፣ ኢትዮጵያን አትንኩ የሚሉ ድምጾች፣ ኢትዮጵያን ለጠላቶቻችን አሳልፈን አንሰጥም የሚሉ የጀግንነት መፈክሮች ከረጃጅሙ ሰልፍ መሐል የሚሰሙ የአንድነት ድምፆች ናቸው። ወኔ የሚቀሰቅሱ፣ኢትዮጵያዊነትን የሚጭሩ ጠንካራ የአንድነት መንፈስ የሚያላብሱ መፈክሮችን የሚስተናገዱባቸው ናቸው።
በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ውስጥ አገር ለማፍረስ ባህር ተሻግረው መጥተው ፈርሰው የተመለሱ በርካታ አገራትን እናውቃለን። በጦር ሠራዊቷ ብዛት ከዓለም ቀዳሚ የሆነችውን ጣሊያንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት ኢትዮጵያን ነክተው ጉድ ሆነዋል። ኢትዮጵያን ለማፍረስ፣ ሕዝቦቿን ለመለያየት ጉድጓድ ሲምሱ የነበሩ ሁሉ በቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ራሳቸው ገብተው የጠፉበት በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ።
የአሸባሪው ሕወሓትና የአሜሪካ ጥምር ሴራም ከዚህ የዘለለ አይደለም። አሸባሪው ሕወሓት ሕዝብ እያስጨነቀ፣ ከድሀ አገር ላይ እየዘረፈ በግፍ ያገኘውን ሥልጣንና ጥሪት መቀበሪያው ካልሆነ በስተቀር እንደማይበላው የታወቀ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያን ነክቶ ሰላም ያገኘ አገርና ጠላት የለምና ነው።
ኢትዮጵያ የአሸናፊዎች አገር ናት..ነጮቹ ኢትዮጵያን በተመለከተ ዛሬም ድረስ ያልተመለሰላቸው አንድ ጥያቄ አለ…እርሱም በጽኑ የአገር ፍቅር ውስጥ ያለው የማሸነፋችን ምስጢር ነው። የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ምስጢር የሕዝቦች አንድነት ነው። አሁን ላይ አሸባሪውን ሕወሓትና ምዕራባውያን እየተፋለሙ ያሉት ከሕዝብ ጋር ነው…የሕዝብ እውነት ደግሞ ከግለሰብና ከቡድን እውነት የላቀ ነው።
ለዚህም ነው ሁሌም ሊለያዩንና ሊበታትኑን በሚፈልጉ ጠላቶቻችን ላይ የበላይ ሆነን የምንገኘው። ለዚህም ነው ጠፉ ባሉን ሰዓት የምንበዛው፣ አለቀላቸው ባሉን ጊዜ ተስፋ የምንሰንቀው።
ለዚህም ነው ጠላቶቻችን እያፈሩ እኛ በክብር ማማ ላይ የምንሰቀለው። እየተራበና እየተጠማ ይሄን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ አገር ለመሥራት እየከፈለ ላለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ክብር ይገባዋል። የአሸባሪው ሕወሓት መንገድ ጠራጊዎች እነአሜሪካ ሕዝብ ባይታገላቸው ኖሮ እሄኔ ኢትዮጵያዊነት ሌላ መልክ ይኖረው ነበር።
እድሜ ለሕዝባችን..እድሜ ለአንድነታችን ።ሕዝባችን ከማን ጋር እንደሚዋጋ፣ ጠላቱ ማን እንደሆነ በደንብ አውቆታል። ኢትዮጵያዊነትን አስቀድሞ ፣ አሸባሪውን ሕወሓት አስወግዶ ታሪክ ለማድረግ አንድ አይነት አቋም ይዟል ። የምዕራባውያኑን ያልተገባ አካሄድ በመንቀፍ ለውጪው ማኅበረሰብ አቤት የሚሉ ብሶት የወለዳቸው ድምጾቹን በቁጣና በእልህ አስተጋብቷል ።
አሸባሪው ሕወሓትንና አስተሳሰቡን ለመጣል ከመከላከያ ጎን መቆም የሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ፍላጎት ነው። የኢትዮጵያ የከፍታ ስፍራ ያለው በእኛ የአንድነት መንፈስ ውስጥ ነው ፤ ይሄ የአንድነት መንፈስ ደግሞ ከመከላከያ ጎን በመቆም የሚገለጽ ነው። ያለ መከላከያ ሠራዊት አገርና ሕዝብ ሉዓላዊነትም ምንም ናቸው።
ከትላንት እስከዛሬ በጠላቶቻችን ላይ የበላይ ሆነን የምንታየው ዳር ድንበር በሚጠብቁ መከላከያ ሠራዊቶቻችን ነው። ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መቆም ከአገርና ሕዝብ ጎን መቆም ነው።
ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መቆም ለራስ ክብር፣ ለራስ እውነት መገዛት ነው። ይህን ታላቅ እውነት ለሰጠን ሠራዊት ክብር መስጠትና ድምፅ መሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው። በትላንት ታሪካችን ላይ ከጻፍናቸው ደማቅ ገድሎቻችን ውስጥ የመከላከያ ሠራዊት አሻራ ትልቅ ነው።
በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ላይ ከመከላከያ ጎን በመቆም አጋርነታችንን ከማሳየት በተጨማሪም ያልተከፈለ እዳችንን መመለስ አለብን። እኔና እናንተ የተጻፍነው በደም ነው። ኢትዮጵያዊነት ከሚገለጽባቸው ቁምነገሮች ውስጥም አንዱ መስዋዕትነት ነው። እኔና እናንተ በመከላከያ ሠራዊት መስዋዕትነት የተገኘን የደም ፍሬ ነን ማለት ነው።
ትላንትም ዛሬም ነገም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከሚገለጹበት መንገዶች ውስጥ አንዱ ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ነው። እርሱም መከላከያ ሠራዊት ነው..እርሱም ኢትዮጵያዊነት ነው.. እርሱም እኔና እናንተ ነን።
አገር ላቆመ፣ ትውልድ ለሠራ አገር ወዳድ ሠራዊት ፍቅራችንን ክብራችንን ብንሰጥ ያንስበታል እንጂ አይበዛ በትም።
በአሸባሪው ሕወሓትና በአስተሳሰቡ ክብርና ልዕልናዋን ላጣችና እያጣች ላለች አገር ዘብ ለመቆም አደባባይ ብንወጣ ይሄም ለአገራችን ከምንውለው ውለታ ትንሹ ነው።
ዛሬ ላለችው፣ ነገም ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ ከመከላከያ ጎን በመቆም የዜግነት ግዴታችንን በመወጣት አገርና ሕዝባችንን እንደ አሸባሪው ሕወሓትና አሜሪካ ካሉ ከሀዲና አስመሳይ ጠላቶች እንታደግ እላለሁ። አበቃሁ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 30/2014