መቼም በእነ ደብረፂዮን ከሚመራውና በገዛ አገሩና ወገኑ ላይ ከዘመተው ቡድን የማይሰማ ጉድ፤ የማይፈፀም ደባ፤ የማይጎነጎን ሴራ፤ የማይሸረብ ተንኮል፤ የማይጠለፍ ጥልፍ … የለምና፤ እነሆ አሁን 2ኛ ሳምንቱን የያዘው የጀነራል ፃድቃን ነው የተባለውና ለአለሙ የተላከው ደብዳቤ ሲያነጋግር ነበርና ስለ እሱ አንዳንድ ሀሳቦችን እንለዋወጥ።
(ለታሪክና ፍርድ ይመች ዘንድ፣ ማየት ብቻ ሳይሆን ማንበብም ማመን በመሆኑ እንደወረደ ማስፈሩ አስፈልጓልና ለጽሑፋችን ቋንቋ ዥንጉርጉርነት ከወዲሁ ይቅርታ እንጠይቃለን።) ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ አውዶች ሲያነጋግር የነበረው መሰረቱን ኬንያ፣ ናይይሮቢ ባደረገውና Elephant በሚባለው ኢንተርኔት ሚዲያ አማካኝነት የአሸባሪው ትህነግ ጦር አበጋዝ ፃድቃን ገብረ ተንሳይ የድርጅታቸውን ድረሱልኝ ጩኸት በተመለከተ ለንባብ ያበቁት ደብዳቤ ሲሆን፤ ደብዳቤው “በግል” ይባል ዘንድ በግለሰብ ስም ይውጣ እንጂ የድርጅቱን አቋም ይዞ የወጣ ስለመሆኑ እስካሁን የተጠራጠረ ሰው አላጋጠመም።
ይህ፣ የወቅቱን ጉዳይ በማስመልከት “Pertinent Issues on the War in Tigray” በሚል ርእስ ለንባብ የበቃው የፃድቃን ተብዬ ጽሑፍ ምንም አይነት አዲስ ነገር ይዞ አልመጣም የሚሉ ወገኖች የመኖራቸውን ያህል፤ አይ፣ ብዙ ነገር ይዟል፤ ዋናውም ሽንፈቱን (በተለይ በአማራና አፋር ክልሎች መቀጥቀጡንና እግሬ አውጭኝ ማለቱን) እያመነ፣ የድረሱልኝ ጥሪውን እያሰማ መገኘቱ ነው የሚሉም ቁጥራቸው ከዛኛው ወገን ከፍ ያለ ነው።
የእነዚህ ወገኖች መረጃና ማስረጃም ይሄው የፃድቃን ደብዳቤ የተባለውና እሱኑ በማብጠልጠል ላይ ያሉት የውጪ ሚዲያዎች (ወደ ህሊናቸው በመመለስ ላይ ያሉ የሚመስሉት እነ ሮይተርስን ጨምሮ) እየሰጧቸው ካሉት አስተያየቶች ይመዘዛል። ጽሑፉ በወጣ በነጋታው “19 Blatant Lies of General Tsadkan” በሚል ርእስ የወጣውና የሰውየውን በያ እፍረት በግልፅ መዋሸት (blatantly) ያጋለጠው ጽሑፍ እንዳመለከተው ሰውየው ሲበዛ ውሸታም፤ አቻ የሌለው ቆርጦ ቀጥልና ሲመቸውም አጭበርባሪ ነው።
ይህንንም “the War in Tigray” በሚል ንኡስ ስር (ከርእሱ ጀምሮ) ያሰፈረውን ሀሳብ በማየት ማወቅ ይቻላል። ከዚህ ፌዴራል መንግስቱ ለሰላም ሲል ከክልሉ ጦሩን በማስወጣት የአንድ ወገን ተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ በመድረስ ክልሉን ለቅቆ መውጣቱን ከካደ ደብዳቤ እንዴት አድርጎ እውነት ማግኘት እንደሚቻል የሚያስቸግር መሆኑን በመጥቀስ ነው አስተያየት ሰጪዎች ስለ ሰውየው (እና አሸባሪው ትሕነግ) ከመዋሸትና መቅጠፍ እስከ ማጭበርበር ድረስ የዘለቀ መሆኑን የሚያስረዱት።
ይህ ደግሞ ማንንም ሳይሆን ከጎንህ ነን የሚሉትንና እራሱን እንጂ የሚጎዳው ማንንም ስላልሆነ ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ታተርፋለች እንጂ አትከስርም።
ጽሑፉ በዚህ ጀመረ እንጂ ገና አላበቃም። የቀጣፊውን ቅጥፈት ካጋለጠባቸው ሁለተኛው ከማንም ጋር ባልሆኑበት በዚህ ወቅት፤ ሁሉም በአንድነት እነሱ ላይ በተነሳበት በዚህ ጊዜ፤ በጋራ ክንዱ እየወቀጣቸው ባለበት ሁኔታ፤ ገና ለገና ከአሸባሪው ሸኔ ጋር ስለተወዳጀ ብቻ “ከሶማሊ፣ አፋር፣ ኦሮሞ … ህዝብ ጋር ግንባር ፈጥረናል” (We have joined forces with the Oromo, Somali and Afar) ማለቱን በመጥቀስ ነው። በዚህም ምክንያት “አጭበርባሪ” ነው ይለዋል ጽሑፉ ሰውየውን።
ሌላው ሰውየውን (በተዘዋዋሪ አሸባሪው ትሕነግን) አውላላ ሜዳ ላይ እርቃኑን የጣለውና እራሱን በራሱ እንዲጋለጥ ያደረገው የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ከስሩ የናደው እሱ እራሱ ሆኖ ሳለ፤ አስቴር አወቀ “እራሱ በድሎ / እራሱ አለቀሰ” እንዳለችው ፃድቃንም “እየታገልን ያለነው ሕገመንግስታዊ መርሆዎችን ለማስከበር ነው” (We are fighting to protect the principles of the Federal Constitution of Ethiopia) ሲል በደብዳቤው ላይ ማስፈሩ ለቀጣፊነቱ ማረጋገጫ፤ ለአጭበርባሪነቱ ተገቢ ማሳያ ሆኖ አገልግሏል፤ ከዋሹ አይቀር እንዲህ ነው በማለት ጽሑፉ ይህንን ውሸት አለም በአግባቡ እንዲረዳው ያሳስባል።
“የምእራቡ አለም ተግባር ከወሬና የቃላት ጨዋታ ባለፈ ምንም አይነት ድጋፍም ሆነ እርዳታ አላደረገልንም” (“Western nations’ actions did not go beyond rhetoric”) የሚለው ይህ የአሸበሪው ትህንግ ጽሑፍ (አቤቱታ) ሁሉንም ነገር ያመነ፤ ጦርነቱ የውክልና ጦርነት መሆኑን በደማቁ ያሰመረበት ከመሆን የዘለለ አይደለምና አትራፊነቱ ለኢትዮጵያ እንጂ ለቡድኑ አለመሆኑን እንኳን የተገነዘበ አልነበረም፤ ለዛውም በተስፋ ብቻ፣ በአይዟችሀ አለንላችሁ ብቻ ተገፋፍቶ ያለ አቅሙ የገባበት ጦርነት መሆኑን ጭምር ወለል አድርጎ ያሳየ ጽሑፍ ነው።
“The ENDF fights like a rag-tag horde of feudal levies” በማለት እሳቸው የሚመሩትን ሰራዊት ከኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል (ENDF) አብልጦ ለማሳየት የሄዱበት መንገድ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ሲሆን ከሁሉ የሚገርመው ይህንን ያሉት በፊት ቢሆን ባልገረመና ዛሬ ድቁስ ድቁስቁስ በተደረጉበት ሰአት ይህንን ማለታቸው በእውነት እጅጉን አሳፋሪ፤ በታሪክም አስወቃሽ ነው። ሌላውና የቀድሞውን ጀነራል ለትዝብ የዳረጋቸው ጉዳይ በደብዳቤያቸው (Administrative structures have collapsed across the country) “በአገሪቱ የመንግሥቱ መዋቅር ምንም የለም፤ ፈርሷል።” በማለት ያሰፈሩት ሲሆን፤ ይህ በተለይ በበርካቶች (ወዳጆቻቸው በሆኑትም ባልሆኑትም) በኩል እጅጉን አስወቅሷቸዋል።
አገር አንድ ሆኖ፣ ከመንግሥት ጋር አብሮና ተባብሮ አሸባሪውን ትህነግን እያደባየ ባለበት በዚህ ሰአት፤ ውጪ ያለው ዲያስፖራ ሳይቀር ወደ አገር ቤት እየተመመ ባለበት በዚህ ገና ወቅት አገር የፈረሰ (ምኞታቸውን) ለማስመሰል በአጠቃላይ አገሪቱ የአስተዳደር መዋቅሩ ፈራርሷል ማለታቸው በአድናቂዎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ሳይቀር የሰላ ሂስ እንዲዘንብባቸው አድርጓቸዋልና ፃድቃኔ ተሸውደዋል።
እዚህ ላይ አንድ ሳይጠቀስ ሊታለፍ የማይገባው ነገር አለ። ያሸማቀቀውና አፍን በእጅ ያስጫነው ይህ ጉዳይ ጀነራሉ ደብዳቤያቸው “እኛ ጦርነቱን እየመራንና ወደ አዲስ አበባ እየገሰገስን ባለንበት ወቅት ወደ አዲስ አበባ እንዳንገባ ያደረገችን አሜሪካ ናት።
ከገባችሁ ማእቀብ እጥልባችኋለሁ በማለት ነው ያገደችን” (“The US openly opposed the advance of the TDF to Addis Ababa, threatening the government of Tigray with sanctions if our forces approached the city”) በማለት ጦርነቱ የውክልና ጦርነት መሆኑን፤ መመሪያ ሁሉ ሳይቀር ከእነ ማን እንደሚቀበሉ፤ እርዳታው፣ ምክሩ፣ ትእዛዙ ወዘተ ሁሉ ከእነማን እንደሆነ ዳግም ያረጋገጡበት መልእክታቸው ነው።
ሌላው ከእሳቸው፣ ከባለ ደብዳቤው በላይ የሚያወቀው የሌለውን አንድ ትልቅ እውነት የጨፈለቁበት አረፍተ ነገር ነው።
አረፍተ ነገሩ “Abiy has demolished peace and security architecture for the Horn” የሚል ሲሆን፤ እውን የኢትዮጵያን ሰራዊት “በመብረቅ ፍጥነት …” ከጀርባው የመታው ማነውና ነው ዐቢይን ፀረሰላምና የመከላከያና ደህንነት መዋቅሩን እንዳፈረሰ ተደርጎ የሚቆጠረው? እንደዛስ ሆኖ ፀሀፊው “እውን የኢትዮጵያ ሰራዊት ፈርሷልን?” ተብለው ቢጠየቁ መልሳቸው ምን ይሆን? አሸባሪው ትህነግን እጅጉን የጎዳው እራሱን አለመሆኑና በራሱ ከመተማመን ይልቅ አሜሪካና ሸሪኮቿን ከፈጣሪ በላይ ማመኑ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ “አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ወደ ሰላም ለማምጣት ትጥራለች” (The US is appeasing Abiy Ahmed) የሚለውና አሜሪካ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ መውሰድ የሚገባትን እርምጃ አለመውሰዷን የወቀሰበት የደብዳቤው መልእክት ነው።
ተረቱም ቢሆን “ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች” ነው የሚለው። ጌታዋ ዞር ያለ ለት ላቷ በጎበዝ እንደሚሰለቀጥ ለአፍታም እንኳን አልታሰባትም። ትህነግም ያው ነው።
ዐቢይን ከስልጣን አስወርዳለሁ ብሎ ሳይሆን ወደ ጦርነት መሰስ ብሎ የገባው አሜሪካ አለችልኝ ብሎ ነበር። ግን ምን ያደርጋል አሜሪካ ያው አሜሪካ ነችና ወደ ጦርነት ትማግዳለች እንጂ አትገባም።
ሌላውና አስደናቂው የትህነግ/ፃድቃን ተግባር የማላገጥ ተግባር ሲሆን እሱም በጌታቸው ረዳ አማካኝነት “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ መውረድ ካለብን እንወርዳለን” ባለበት አፉ፤ ዛሬ ደግሞ የዚህን ተቃራኒና ኢትዮጵያን የማዳን እቅዱን በፃድቃኔ አማካኝነት “We need to save Ethiopia from this fate” ይለናል።
እውነት እንደ አሸባሪው ትህነግ በአገር፣ ሕዝብና በራሱ የሚቀልድ በአለም ይኖር ይሆን?? አሸባሪ ትህነግ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሀሳብና አስተሳሰብን ለአደባባይ ማብቃትን የተካነ ድርጅት ስለመሆኑና በዚህም ምንም የማይሰማው መሆኑ በብዙዎች የተመሰከረለት ድርጅት ነው። ይህ ከአሁኑ “የፃድቃን …” ከተባለው ደብዳቤ በግልፅ መረዳት የሚቻል ሲሆን ማስረጃችንም The “TDF is fighting absolutely alone. It has no international allies and no military or other material assistance from abroad.” የሚለውና ብቻዬን ነው እንጂ ኢትዮጵያን የተዋጋሁት አንድም አጋር አልነበረኝም ሲል የሚናገረው ነው።
ይህ ብቻ አይደለም። የፃድቃኔ ደብዳቤ አይኑን በጨው አጥቦ የትግራይ ህዝብ አንድም የውጭ እርዳታ አልተቀበለም (Tigrayan people do not even receive humanitarian aid) ይላል። ይህንን አንባቢ ይፈርድ ዘንድ ትተነው ወደ ሚቀጥለው እንሂድ።
“We have a long and proud history of fighting against invaders of our land [Tigray]” የሚለውን የፃድቃኔን የተጋዳላይነት ፉከራም ከወቅቱ ጋር አያይዘን እንፈትሸው ዘንድ እያሳሰብን ብናልፈው የተሻለ ይሆናል።
በተለይ የቦርከናው ፀሀፊ ጉዳዩ “Tigray exceptionalism”ን ከማንፀባረቅ አንፃር ነው መታየት ያለበት ካሉት ጋር አያይዘን ለሌላ እይታ አሳልፈን ብንሰጠው የተሻለ ይሆናል። “We are repeating the heroic feats of our predecessors”፣ “We are undefeated” ወዘተ ወዘተ። (የቴዲ አፍሮ “ጉራ ብቻ …” ወደ አእምሯችሁ አልመጣም?) የቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ “የማያባራ ጦርነት …” ይሉ የነበረውን በሚያስታውስ መልኩ የጦርነቱን ቀጣይነት “the war will continue not only in Tigray but in other places in Ethiopia as well.” በማለት ያሰፈሩትም ሊታሰብበት የሚገባ ቢሆንም፤ እንደማይሆን እያሰብን እንታዘባቸው ዘንድ እድል ይሰጠናልና እዚህ ስንጠቅሰው (ከላይ ካልናቸው ጋር ለማነፃፀር ብቻ ሳይሆን) ለታሪክ ፍጆታ መሆኑንም ከስሩ በማስመር ነው።
በመግደልና በማውደም ገና ምንም ያልረኩት ፃድቃንና ኩባንያቸው ተጨማሪ ውድመት እንደሚያስከትሉም “There will be more loss of lives; economic destruction and whatever political and social fabric that might have persisted up to now will be destroyed which means saving the Ethiopian multinational federal state as we know it becomes very difficult” በማለት ነበር የገለፁት። ይህ የሰውየውን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የኩባንያውን እብደት ጭምር የሚገልፀው እውነት እቺ አገር አገራቸው ነችን ብለን ጠይቀን ከማለፍ ውጪ እዚህ ጋር ሌላ ማለት አስፈላጊ አይደለም።
(የሰሞኑ እንግሊዛዊ ፀሀፊ “ቲፒኤልኤፍ የሚባል ድርጅት ካልጠፋ .…” ያለበት ምክንያት አሁን በጣም ግልፅ ነው።) ሌላው የአሸባሪው ትህነግን የከፋና እስከ መጨረሻው ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም እንደ ያዘ የሚያጋልጠው የገዛ አገሩን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ለማጣላት የሄደበት ርቀር ሲሆን ይህን ርቀቱም በማር በተለወሰ እሬት አቀራረቡ “Ethiopia is unique but it is also an African country where Africa’s principles and wisdom are much needed.” በማለት ገልፆት እናገኘዋለን። መቼም ቡድኑ ይህን ሲል ኢትዮጵያ ለአፍሪካ (ከ1951 ጀምሮ በሰላም ማስከበር) የዋለችው ውለታ ጠፍቶት አይደለም። በቃ ኢትዮጵያን ማፍረስ እቅዱ ስለሆነ ብቻ ነው ይህንን የሚለው።
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ቡድኑ ርቆ በተሰቀለ ተስፋ የተሸወደበት አጋጣሚ ነው። አሜሪካ ሳምባዬ ነች ብሎ የተነሳው የሽብር ሀይል፡ “የፃድቃን …” የተባለው ደብዳቤ በወጣ ሶስተኛ ቀኑን ሳይደፍን፣ አሜሪካ ለማድረግ የምትፈልገውንና የምታራምደውን ሀሳብ ማንሸራሸሪያ ነው በሚል የሚታወቀው “ፎሬኝ ፖሊሲ” መጽሔት ለንባብ ያበቃውን ሀሳብ ስንመለከት ፃድቃን ምኞትና ተስፋ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የቸለሰ ሆኖ እናገኘዋለን።
መጽሔቱ እንደሚለው ከሆነ የባይደን አስተዳደር በሚከተለው የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምክንያት አሜሪካ አፍሪካ ቀንድና አካባቢው ላይ ያላትን ጥቅምም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን እያጣች፣ ለሩሲያ፣ ቻይናና አረቡ አለም እያስረከበች ትገኛለች።
ይህ አካሄድ የአሜሪካንን ህዝብ ምንም የማይጠቅምና ፍፁም ስህተት ስለሆነ ባይደን ባስቸኳይ ሊያርሙት ይገባል። ከኢትዮጵያ ጋር የገቡበትን ቅራኔ ባስቸኳይ አቁመው ወደ ነበረው ሰላማዊ ግንኙነት መመለስ አለባቸው። ለዚህ ሁሉ ደግሞ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ከመቃወም አንስቶ እስከ ማውገዝ፤ የመንግሥት ተቃዋሚው ለሆነው የትግራይ ኃይል የሚያደርገውን ድጋፍ ባስቸኳይ ማቆም ድረስ የባይደን አስተዳደር ሊሄድ ይገባል ሲል ምክር አዘል ጽሁፍ አስፍሯል። ማጠቃለያ፦ ከላይ እንደተመለከትነው “የፃድቃን …” የተባለው ደብዳቤ አንድም ቦታ እውነት ሲያወራ አይገኝም። አንድም ቦታ ትህነግ እራሱን ችሎ ስለመቆሙ የሚያሳይ አረፍተ ነገር የለውም።
አንድም ቦታ ግልፅ የሆነ አላማን አላስቀመጠም። አንድም ቦታ አገርንና ህዝብን ለጦርንነት ሊማግድ የሚችል ገፊ ምክንያት ስለመኖሩ አልተናገረም። አንድም ቦታ የአገርና የወገን ፍቅር አለኝ ሲል አይታይም።
አንድም ቦታ ለእናት አገሩ ኢትዮጵያ ሲያስብ አይታይም። አንድም ቦታ ለፈሰሰው የንፁሀን ደምና ለወደመው ንብረት ሲፀፀት አይታይም። አንድም ቦታ ….። አለመታደል ይሏል ይህ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 29/2014