በአለማችን በጦርነት ወቅት አንድ ፎቶግራፍ ወይም አሳዛኝ የህይወት ቅንጣት ፤ ታሪክን የመቀየር ወይም እንደ አዲስ የመበየን ኃይለኛ ጉልበት እያለው፤ እኛ ጋ ሲደርስ ምነው ጉልበቱ ራ’ደ !? ዛለ !? ቄጥማ ሆነ !? ለዛውም በአሸባሪው ሕወሓት በሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን በግፍ ተጨፍጭፈው ፤ የዘር ማጥፋት ፤ የጦር ወንጀል ፤ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ወንጀል ተፈጽሞ ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ በቡድን አስገድዶ ደፋሪዎች ቅስማቸው ተሰብሮ ።
አሜሪካውያን የቬትናም ጦርነትን ዳር እስከ ዳር ሆ ብለው እንዲቃወሙ ያደረጋቸው ጦርነቱ ፍትሐዊ ስላልሆነ ወይም ወደ 60ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች በመሞታቸው ብቻ አይደለም።
በደቡብ ቬትናም በተፈጸመ የአየር ድብደባ የናፓል ቦንብ ፍንጣሪ ያቃጠላት የዘጠኝ አመቷ ታዳጊ ፋን ቲ ኪም ቃጠሎው የፈጠረባትን ኃይለኛ የሚያነገበግብ ህመም እንዲያስታግሱላት ልብሷን አውልቃ እርቃኗን እጇን ዘርግታ ከሌሎች ህጻናት ጋር በፍርሀትና በስቃይ ከፍንዳታው ስትሸሽ የአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ፍቶ አንስቶ ወደ አሜሪካ ከላከው ከቀናት በኋላ ኒውዮርክ ታይምስን ጨምሮ በሌሎች ጋዜጦች መታተሙ የአሜሪካውያንን የጸረ ጦርነት ተቃውሞ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋገረው ።
አሜሪካም ብዙ ሳትቆይ ከቬትናም በሽንፈት ለቃ ወጣች ። ሰሜኑና ደቡቡ ቬትናምም ተዋሀደ ። የፎቶ ጋዜጠኛው የፑሊትዘርና የሌሎች ታላላቅ ሽልማቶች አሸናፊ ሆነ። የጦርነቱን ምዕራፍ የቀየረችው የዛኔዋ ብላቴና ኪም ዛሬ በከናዳ ቶሮንቶ የልጅ ልጅ አይታ ከመኖር ባሻገር በየአጋጣሚ የጦርነትን አስከፊነት ትገልጻለች።
ታሊባን ሴቶች እንዳይማሩ እስከግድያ ይደርስ የነበረን አፈናውን ለአለም ያሳወቀችው ከታሊባን ጥይት በተአመር የተረፈችው የሴቶች የመማር መብት ተሟጋቿ የኖቤል ተሸላሚዋ ብላቴና ማላላ ዮሱፍዚ ናት ። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች እንዳሉ ሆኖ ፤ የሕዝብን ይሁንታ ለማግኘትና አስተያየቱን ለማስቀየር ትናንትም ሆነ ዛሬ ሀሰተኛ ሁነቶችና ምስክሮችን ሲዘጋጁ ተመልክተናል ።
ጆርጅ ቡሽ የኢራቅን የኩየት ወረራ ለመቀልበስ ሕዝባዊ ድጋፍና የኮንግረስ ይሁንታ እንዲያገኝ ደጋፊዎቹ ረጅም ርቀት ሄደዋል ።
በኩየት የአሜሪካ አምባሳደር ልጅ የሆነችው የ15 አመቷ ናይራህ አልሳባብ በሀሰት በጎ ፈቃደኛ ነርስ እንደሆነችና የኢራቅ ወታደሮች በምትሰራበት የኩየት ሆስፒታል መጥተው 312 በህጻናት ማቆያ (ኢንኩቤተር) የነበሩ ጨቅላዎችን አውጥተው ቀዝቃዛ ወለል ላይ ስላስቀመጧቸው ህይወታቸው ወዲያው ማለፉን አሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርባ እንባ እየተናነቃት በሀሰት በመመስከሯ ጦርነቱን ይቃወሙ የነበሩ የኮንግረስ አባላት ደግፈው ድምጽ እንዲሰጡ ፤ ጦርነቱን ይደግፉ የነበሩ አሜሪካውያን ቁጥርም ከ17 በመቶ ወደ 41 በመቶ ከፍ ሊል ችሏል።
አሸባሪው ሕወሓት በዘረፈው ዶላር የቀጠራቸው ሎቢስቶች እየታገዘ ሀሰተኛ የዘር ማጥፋት ፤ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምና አስገድዶ መድፈር የሚሉ የፈጠራ ክሶችን በመደረት እያወናበድ ይገኛል ።
እነዚህ በአብነት ያየናቸው ሁነቶች ታሪክን እስከ መቀየር የደረሰ ተጽዕኖ ማሳደር የቻሉት ለሰው ልጆች ስሜት የቀረቡ እንዲሆኑ ተደርገው በመቀረጻቸው ነው ። የእኛ የሚዲያዎቻችንም ሆነ የመንግሥት የኮሙኒኬሽንና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት የጎደላቸው ይህ ነው።
በዋናነት ተግባቦታችን በሚጠበቅበት ደረጃ ውጤታማ ሊሆን ያልቻለው በዚህ የተነሳ ነው። የተግባቦት(ኮሙኒኬሽን)ስራዎቻችን ሶስት ዋና ዋና ልምሻዎች አሉባቸው። የመጀመሪያው በጥበብና በፈጠራ ስራዎች በማዋዛት መረጃዎች ሰው ሰው እንዲሸቱ የማድረግ ፤ ሀለተኛው ተደራሲዎችን(ኦዲየንስ) የመለየት ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ መልዕክቱን በአግባቡ የመቅረጽ ችግሮች ናቸው። በተለይ የቀውስና የጦርነት ጊዜ የተግባቦት ስራዎች ለሰው ልጅ ስሜት የቀረቡ ሆነው መቀረጽ አለባቸው ።
ወሰን ፣ ዘር ፣ ቀለም ፣ ጾታ ፣ እድሜ ፣ ሀይማኖት ፣ ርዕዮተ አለም ፣ መደብና ሌላ ልዩነት ሳይገድባቸው መላ የሰውን ልጅ ስሜት ገዝተው ለድርጊት የሚያነሳሱ መሆን አለባቸው። ከዚህ አንጻር ያለፉት ሶስት አመታትን በተለይ ደግሞ ያለፈውን አመት መለስ ብለን ስንገመግመው አፍን ሞልቶ ድክመቱን መናገር ይቻላል ።
ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ/ሕወሓት ባለፈው አንድ አመት በሕዝቤ በአገሬና በሰሜን ዕዝ ከፈጸመው ኅልቆ መሳፍርት ከሌለው ለመስማት የሚሰቀጥጥ ለማየት ከሚዘገንን ሰቆቃ ፣ ግፍ ፣ ጭፍጨፋ ፣ ዘረፋ ፣ ውድመት ፣ ወዘተረፈ ባልተናነሰ ዛሬ ድረስ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግበኝ አገሬ ሕዝቤ ሰራዊቴና መንግሥቴ የክህደትና የጥቃት ሰለባ ሆነው እያለ ተወጋዥ ፣ ተከሳሽና ተወቃሽ መሆናቸው ነው።
እውነትንና ፍትሕን ታቅፈው ባዶ እጃቸውን አጨብጭበው መቅረታቸውን ሳስብ ጥርሴን እያፋጨሁ እቃትታለሁ። እቃጠላለሁ። እበግናለሁ። ከትጥቅ ትግሉ አንስቶ በተለይ አገዛዝ ላይ በነበረባቸው 27 የጨለማ ፣ የግፍ ፣ የጭቆና ፣ የኢፍትሐዊ ፣ የኢዴሞክራሲያዊ ፣ የዘረፋ ፣ የክህደት፣ ወዘተረፈ አገዛዙ ሳያንስ ፤ በሕዝባዊ አመጽና በኢህአዴግ ውስጥ በተነሱ የለውጥ ኃይሎች የተናበበ፣ የተቀናጀና የተንሰላሰለ ትግል በልክህ ሆነህ የለውጡ አካል ሁን ፤ ስለግፍህና ዘረፋህ ይቅርታ ጠይቀንልሀል ሲባል እኩልነትን እንደ ሽንፈት ፣ ሀጢያትና በደል የሚያየው እፉኝቱ ትህነግ በመማጸኛ ከተማው ሆኖ በሁለት አመታት ብቻ በአገሪቱ አራት ማዕዘናት ለቆጠራ የሚያታክቱ በማንነት ላይ የተመሠረቱ ግጭቶችን ጎንቁሎ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ተገድለዋል ።አካለ ጎድሏል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፏል። ወድሟል። ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ይሁንና ብዙኃን መገናኛዎችም ሆኑ የመንግሥት አካል መረጃውን ለሰው ልጆች ስሜት በቀረበ አግባብ ቀርጾና በፈጠራ አዋዝቶ በልኩና ለአገሬውም ሆነ ለውጭ ሚዲያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና መንግሥታት ማሳወቅ ባለመቻሉ ሀቅንና ፍትሕን ታቅፎ ሀሰተኛና ሆን ተብሎ የተዛባ መረጃን እንደ ፍላጻ ያለእረፍት በሚያንበለብለው የሽብር ኃይል ብልጫ ሊወሰድበት ችሏል።
ላለፉት 21 አመታት የቀን ሀሩር የሌሊት ቁር እየተፈራረቀበት ፤ በቀበሮ ጉድጓድ የዕድሜውን ሲሶ ገብሮ ሲጠብቀው ፤ በትግራይ ሕዝብ ደስታና ሀዘን ተካፋይ ፤ በእርሻው በዘሩ በአረሙ በአጨዳውና በበራዩ እንዲሁም አንበጣን በመከላከል እንደ ተቀጣሪ አገልጋይ( ቀንጃ )ተለይቶት በማያውቀው፤ ከሬሽኑ እየቀነሰ ለልጆቹ ትምህርት ቤትና ጤና ተቋም ሲገነባ፤ በኮቪድ 19 ለችግር ለተጋለጡ አሁንም ከእጅ ወዳፍ ከሆነች አበሉ ያካፈለ እሩህሩህና ለወገኑ ሟች የሆነ ሰራዊት በአረመኔውና ጉግማንጉጉ የትህነግ እፉኝት ቡድን ለማየት የሚዘገንንና ለመስማት የሚሰቀጥጥ ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ ተፈጽሞበታል። በዚህም ከ6ሺህ በላይ የሰራዊቱ አባላት በተኙበት በውድቅት ሌሊት በግፍ ተጨፍጭፈዋል ። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ስንቁ ትጥቁ ከባድ መሳሪያው ተዘርፏል።
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓም ከ1ሺህ 200 በላይ ንጹሐን በማይካድራ በማንነታቸው ሳምሬ በተባለ የሕወሓት ወጣት ገዳይ ቡድን ተጨፈጨፉ። ሆኖም ይህን የዘር ማጥፋት ፣ የአገር ክህደትና የጦር ወንጀል ጊዜ ወስደን ለሕዝባችን ለወዳጅና ጎረቤት አገራት ፤ ለአፍሪካ ሕብረት ፣ ለኢጋድ ፣ ለመንግስታቱ ድርጅት ፣ ለአሜሪካና ለምዕራባውያን በልኩና በአግባቡ ባለማሳወቃችን የሕግ የበላይነት የማስከበር እና የሕልውና ዘመቻችንን ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ እጅን በአፍ በሚያስጭን ወታደራዊ ድል ብንቋጭም ፤ በአሸባሪው ሕወሓት መሰሪና ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ትግራዋይም እነ አሜሪካም ስለተነሱብን የሰራዊታችንም ሆነ የመንግሥታችን መልካም ስም ከመጠልሸቱ ባሻገር ፤ በዘር ማጥፋት ፣ እርዳታን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም ፤ በአስገድዶ መድፈርና በዘረፋ የፈጠራ ክስ ተፈርጀን ጫናው በመበርታቱ እንደ አገርም እንደ ሕዝብም ሰለባ ሆነን ሳለ እንደ ወራሪና ወንጀለኛ በመታየታችን በተናጠል የተኩስ አቁም ከትግራይ ልንወጣ ችለናል።
አሸባሪው ሕወሓት ይህን የሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም የተናጠል የተኩስ አቁም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአማራና የአፋር ክልሎች በሕዝባዊ ማዕበል በመውረር ፤ በጭና ፣ በንፋስ መውጫ ፣ በጋሊኮማ ፣ በአጋምሳና በወረራቸው ሌሎች አካባቢዎች ትህነግ በዘር ማጥፋት ፣ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በሚፈጸም ወንጀል እና በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቀውን ጅምላ ጭፍጨፋ ፈጽሞል።
ህጻናትን ሴቶችን አረጋውያንን መነኮሳትን በቤተሰባቸው ፊት በጠመንጃ በማስፈራራት በቡድን አስገድዶ ደፍሯል ።
ሌሎች ለመናገርም ሆነ ለማድመጥ የሚከብዱና እውነት ይህ ወራሪና የሽብር ኃይል ከትግራዋይ ፣ ከኢትዮጵያውያን እና ከሰው ልጅ አብራክ የተገኘ ነው የሚል ጥያቄ የሚያስነሱ ነውሮችን ፈጽሟል። በመጀመሪያ በሰሜን ዕዝ በኋላ በማይካድራ የፈጸመውን የክህደትና የጦር ወንጀል እንዲሁም የዘር ማጥፋት ወንጀል በልኩ በተጠናና ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ የተግባቦት የሕዝብ ግንኙነት ስራ ባለመስራታችን ብዙም ያልተጋለጠው ያልተጠየቀውና ያልተከሰሰው ከሀዲው ሕወሓት የልብ ልብ ስለተሰማው በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የማይካድራን ዘር ማጥፋት የሚያስንቅ የዘር ማጥፋት ሊፈጽም ችሏል። ወደ 10ሺህ ፤ የሚጠጉ የጤናና የትምህርት ተቋማት ተዘርፈዋል።
ወድመዋል። የወሎ ፣ የወልድያና የመቅደላ ዩኒቨርሲቲዎች እና የሰቆጣ የመምህራን ኮሌጅ ተዘርፈዋል። ወድመዋል። የሕዝቡ ሀብት ንብረት ተዘርፏል ። በተረፈው እንዳይገለገል ሆን ተብሎ እንዲወድምበት ተደርጓል ።
አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች ረክሰዋል። ወታደራዊ ካምፕ ፣ ምሽግና የከባድ ጦር መሳሪያ ማጥመጃ ሆነዋል። በከባድ መሳሪያ ተደብድበዋል። መጽሐፍ ቅዱሳት ፣ ቅዱስ ቁራናትና ሌሎች መንፈሳዊ መጽሐፍት ሆን ተብሎ ተቃጥለዋል። የተረፉት እየተቀዳደዱ መጸዳጃ ሆነዋል። በአፋርና በአማራ ክልሎች በተለይ በኮምቦልቻና አካባቢው ከ40 በላይ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ተዘርፈዋል። ወድመዋል። በዚህ የተነሳ በ10ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ስራ አጥተዋል።
ከተሞች መርፌ ሳይቀር ተዘርፈዋል። እርቃናቸውን ቀርተዋል። ለዚህ ነው ነዋሪዎች ኮምቦልቻ ፣ ደሴ ፣ ወልድያና ሌሎች በወራሪው ስር የነበሩ ከተሞች ወደ መቐሌ ተጭነው ሔደዋል የሚሉት ። የቀሩት እርቃናቸውን ነው ለማለት በሁለቱ ክልሎች የተዘረፈውና የወደመው ሀብት ወደ ግማሽ ትሪሊዮን ብር ይገመታል። ከተሞች 20 እና 30 አመታት ወደኋላ ተመልሰዋል ።
ለዘመናት በላቡና በደሙ ያፈራው የአርብቶና የአርሶ አደሩ ጥሪት ተዘርፏል። እንደ ልጆቹ የሚያያቸው እንስሳት ታርደው ተበልተዋል። የተረፉት በጥይት ተደብድበው ተገለዋል። የሚያሳዝነው ዛሬም ይህን ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ወንጀል ሰው ሰው የሚሸቱ ወቅታዊ መልዕክቶችን ቀርጸን ፤ እንደ ታዳሚው ስብጥር የተቃኙ መረጃዎችን በፈጠራ አዋዝተን ማቅረብ አልቻልንም። በዚህ የተነሳም እውነትንና ፍትሕን ይዘን በሀሰተኛ መረጃ ብልጫ ተወስዶብናል ።
የአስገድዶ መድፈር ተጠቂዋ የሽዋሮቢቷ ኢክራም ለብቻዋ በራሷ ተነሳሽነት ወደ ሚዲያው በመምጣት የፈጠረችውን ተጽዕኖ መፍጠር አልቻልንም። እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ኢክራምንና ዘሐራን ጨምሮ በየከተሞች የአስገድዶ መድፈር ፤ የግድያ ፣ የሰብዓዊ መብት ጥቃትና ስቃይ ሰለባ የሆኑ ዜጎችን ሕመም እንዲያመን እንዲሰማን በማድረግ የማይናቅ ጥረት አድርጓል ።
ሰሞኑን “ስለኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ያሰናዳው የፎቶግራፍ አውደ ርእይ ይህን የታሪክ ጠባሳ ሰዋዊ አድርጎ ለሕዝብ አቅርቧል። አሁንም ቢዘገይም አልረፈደምና ሚዲያዎቻችን ፤ የመንግሥት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሪፖርት ማንበብን ቀነስ አድርገው፤ የደለበውንና በእጃቸው ያለውን የተግባቦት ግብዓት በጥበብ ሊጠቀሙበት ይገባል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናትና ሴቶች በቡድን ተደፍረው ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ በግፍ ተገድለው ፤ የጅምላ መቃብራቸውን ታቅፈን ፤ ወደ 10ሺህ የሚጠጉ የጤናና የትምህርት ተቋማት ወድመው ፤ በሰሜን ዕዝ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ወደ ጦርነት ተገደን ገብተን ፤ ወዘተረፈ እንዴት የሕወሓትን ሽብር ፣ የጦር ወንጀል ፣ የዘር ማጥፋት፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ፤ ወዘተረፈ ለአለም ማጋለጥ ያቅተናል !? እናሸንፋለን ! አንጠራጠርም !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28/2014