የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት/ተመድ/ ከተቋቋ መበት ዓላማ ዋና ዋናዎቹ የዓለም አገራት የትብብር መንፈስ እንዲኖራቸው ፤የሰላምና ጸጥታ ስጋቶች እንዲወገዱ፤ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ የጤና እና የትምህርት ተደራሽነት እንዲስፋፋ፤ የሴቶችና የህጻናት ጥቃት እንዲቆም፤ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱ ሰዎች ድጋፍ እንዲያገኙ የሚሉ ቅዱስ ሀሳቦችን ያነገበ ነው፡፡
እነዚህን ሀሳቦቹን ተግባራዊ ለማድረግም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር በርካታ ተቋማት ተፈጥረዋል። እንደ ዩኔስኮ ፣ ዩኒሴፍ ፣ የአለም የምግብ ድርጅት ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ፣ የጸጥታው ምክር ቤት እና የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ድርጅቱ በአመዛኙ የገንዘብ ድጎማ የሚያገኘው ከአሜሪካ መንግሥት በመሆኑም ፣ በአሜሪካ የመዘወሩ ጉዳይ ብዙ እየተባለለት ነው። ከተቋቋመለት ዓላማ አፈንግጦ የአሜሪካን ጥቅሞችና የበላይነቷን ለማስጠበቅ እየሰራ ስለመሆኑም ከስሞታ ባለፈ ተጨባጭ እውነታዎች የአለም አደባባዮችን ሞልተው እየተስተዋሉ ነው፡፡
‹‹ያልደረሰበት… ›› እንዲሉ እንዲህ አይነቱ በድርጅቱ ላይ የሚቀርቡ ክሶች በቀደሙት አመታት ለኢትዮጵያውያን ምናችንም አልነበረም፡፡ በዚች አንድ ዓመት ውስጥ ግን የአሜሪካንና የተመድን ጥብቅ ትስስር የተረዳንበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፤ ገመናቸውን እንድናውቅ ያደረጉ አስገራሚ እና አሳፋሪ አቋሞችንም አይተናል፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከአጎራባቾቿ ጋር በተለይም ከሶማሊያና ኤርትራ ጋር የፈጠረችው ወዳጅነት ለአሜሪካ ራስ ምታት ሆኖባታል። ይህንኑ ጠንካራ የትብብር መንፈስ ለማጥፋት ሌት ተቀን እየተጋች ነው፡፡
የአፍሪካ ቀንድ አገራት ትብብርና መቀራረብ አሜሪካ በቀጣናው ማስጠበቅ የምትፈልገውን ጥቅም የሚያሳጣት ወይም በጂኦ ፖለቲክሱ የበላይነት እንዳይኖራት የሚያደርግ ነው የሚል ስጋት ካደረባትም ውሎ አድሯል።
በዚህ ስጋት የተነሳም የኢትዮጵያን መንግሥት ማዳከም ካልሆነም ጥቅሟን የሚያስከብርላት ተላላኪ መንግሥት ለማስቀመጥ እየሰራች ነው፡፡ የሕወሓት አሸባሪ ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር አገርን ወደ አላስፈላጊ ጦርነት ካስገባ ማግስት ጀምሮ አንድ ጊዜ ራሷን ችላ ሌላ ጊዜ ደግሞ በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አስገዳጅ ጫናዎችን ስታደርግ ከርማለች።
‹‹አፍንጫ ሲመታ አይን ያለቅሳል›› እንዲሉ አገራት የትብብርና የመቀራረብ መንፈስ እንዲኖራቸው እሠራለሁ የሚለው ተመድ ፣ በአሜሪካ ሳንባ እየተነፈሰ ከተቋቋመበት መርህ ያፈነገጡ ተግባራትን ሲፈጽም እያየን ነው፡ ፡
የአሜሪካን ጉዳይ አስፈጻሚ መሆኑን በአደባባይ እያስመሰከረ ነው። ለዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመርህ በወጣ መንገድ በአገራችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ያሳደራቸውን ተፅዕኖዎች መመልከት ይቻላል፡፡
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማውን በገሃድ አውጆ ጥፋት ማድረስ ሲጀምር አሜሪካም ትሁን የጸጥታው ምክር ቤት አላወገዙትም። ለምሳሌ የጸጥታው ምክር ቤት መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀውን ቡድን ከማውገዝ ይልቅ ከጸጥታ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለውን የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ወስዶ ጫና ማሳደር የፈለገው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪ ቡድኑ ላይ የሚወስደውን ርምጃ አቁሞ ድርድር እንዲያደርግ ጫና ሲያደርግ ነበር። እንደውም ስለቡድኑ ጦረኝነትና አይበገሬነት እየመሰከረ የኢትዮጵያ መንግሥት ከድርድር ውጭ አማራጭ እንደሌለው ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ለሰብዓዊ መብት መከበር ቆሜያለሁ የሚለው ተመድ በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ ቀርቶ ድርጊቱን አላወገዘም፤ ከጤና ኬላ እስከ ሆስፒታል ያሉ ተቋማት ዳግም አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገው ሲወድሙ ተመድ ትንፍሽ አላለም። ትምህርት ቤቶች ሲወድሙና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ሲፈናቀሉ አንድም ነገር ሊል አልወደደም፡፡
ከብላቴና እስከ መነኮሱ እናቶች ሲደፈሩ፤ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግር ሲዳረጉ ዝምታን መርጧል። አሸባሪ ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአማራና አፋር ክልሎች ስላወደማቸው የጤና ተቋማትና ስለፈጠራቸው ችግሮች የዓለም የጤና ድርጅት ዝምታው ለምን ይሆን? በርካታ ቁጥር ያላቸው የጤና ተቋማት መውደማቸውን ተከትሎ ነፍሰ ጡሮች፣ ስኳር ታማሚዎች ፣ የኤች አይቪ ታማሚዎች የመድሃኒት አቅርቦትና የጤና ክትትል ማድረግ ባለመቻላቸው ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡
አካባቢዎቹ ነጻ የወጡ ቢሆንም ዛሬም ድረስ የጤና ተቋማቱ አገልግሎት መስጠት በሚያስችል ደረጃ ላይ አይደሉም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ሰው የሚመሩት የዓለም የጤና ድርጅት አንድም ቃል ትንፍሽ አለማለቱ የሚያስገርም ነው፡፡
ለነገሩ የዓለም የጤና ድርጅትን የሚመሩት ሰው የአሸባሪ ቡድኑ ደጋፊ ስለሆኑ ችግሩን እያዩ ምንም አለማለታቸው ላያስገርመን ይችላል፡፡ ግለሰቡ ሥራቸውን ትተው ለዚህ ቡድን ጥብቅና እስከመቆም የደረሱ በመሆናቸው የምንጠብቀው መልካም ነገር ላይኖር ይችላል። ነገር ግን የሚመሩት ድርጅት ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ሰዎችን ያለልዩነት የማገልገል መርህን እከተላለሁ ስለሚል መርጦ አልቃሽ መሆን አልነበረበትም፡፡
ለነገሩ የጤና ተቋማትን ያወደመው የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ሆኖ ሳለ ከዚህ ቡድን የወጣ ሰው የሚመራው የዓለም የጤና ድርጅት የወደሙ የጤና ተቋማት ጉዳይ ያስጨንቀዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ምክንያቱም ሕወሓት በባህሪው ዘረኛ አስተሳሰብ የተጸናወተው በመሆኑ አባላቱ በየትኛውም ደረጃ ላይ ቢገኙ ይህንኑ አስተሳሳብ የሚያራምዱ ናቸው።
በዚህም ላይ አሜሪካ በቀጣናው ያላትን ጥቅም ለማስከበር ተላላኪውን የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ምርጫዋ ስላደረገች ከዚህ ቡድን ወጥቶ የዓለም የጤና ድርጅትን የሚመራው ግለሰብም የራሱንም የአሜሪካንንም ፍላጎት ለማስፈጸም ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረለት መገመት አይከብድም፡፡ እንደዚያማ ባይሆን ይህ ሁሉ የጤና ተቋም ዳግም አገልግሎት እንዳይሰጥ ተደርጎ ሲወድም እያየ ዝም ባላለ ነበር፡፡
ለነገሩ የዓለም የጤና ድርጅት ብቻ ሳይሆን በተባባሩት መንግሥታት ስር የሚገኙት ሌሎች ተቋማትም ቢሆኑ ተመሳሳይ ተግባራትን እየፈጸሙ ስለመሆናቸው ለመናገር አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የዓለም የምግብ ድርጅት ከአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ሕወሓት ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች ያደረገላቸው የምግብ ድጋፍ ይህ ነው የሚባል አይደለም።
እንደውም በኮምቦልቻና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኘው የእህል መጋዘኑ በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሲዘረፍ ቡድኑን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ የምግብ ድጋፍ የማድረግ አቅም የለኝም የሚል መግለጫ ነበር ያወጣው።
የእርዳታ እህል ጭነው ወደትግራይ የገቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ከባድ መኪናዎች ጭነታቸውን አራግፈው መመለስ ሲገባቸው ለአሸባሪ ቡድኑ ታጣቂዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ሲደረግም ድርጅቱ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ድምጹን አጥፍቷል፡፡
ዓለማቀፉ የምግብ ድርጅት አበረታች ንጥረ ነገር ያላቸው ቡስኩቶችን ለታጣቂዎቹ እያቀረበ በትግራይ ህዝብ ስም አሸባሪ ቡድኑን ሲረዳ እንደነበርም ታዝበናል፡፡ በአማራና አፋር ክልሎች በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡
በመጠላያ ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮችና በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ያሉ ሰላማዊ ሰዎች በአሸባሪ ቡድኑ የከባድ መሳሪያ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ሌሎች ንጹሀንም የመንግሥት ደጋፊ ናችሁ በሚል በግፍ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ከብላቴና እስከ ባልቴት፤ ከባልቴት እስከ መነኮሳት ተደፍረዋል፡፡ አንደፈርም ያሉትም በጥይት ተደብድበዋል።
ታዲያ እንዲህ አይነት የሰብኣዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም የድርጅቱ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቋም ዝምታን መርጧል። ተጎጂዎችን ትቶ ከወንጀለኞች ጎን ቆሟል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ሳይንስና ባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በአፋርና አማራ ክልሎች ከአምስት ሺ በላይ የትምህርት ተቋማት ሲወድሙና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ቅርሶች አደጋ ላይ ሲወድቁ አሸባሪ ቡድኑን የሚያወግዝ መግለጫ አላወጣም፡፡
በመልሶ ግንባታው ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱንም አልተናገረም፡፡ ተቋሙ ከተቋቋመበት መርህ ወጥቶ በአገርና በህዝብ ላይ የሚደረግ ጫና ያልተገባ ተግባር የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካን ፍላጎት የሚያከብር ቢሆን ኖሮ የተለየ ገጽታ እንደሚኖረው ለመገመት አይከብድም፡፡ ብዙ እጅ መንሻዎችን ይዞ ብቅ የማለቱም እውነታ የአደባባይ ሚስጥር ይሆን ነበር።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28/2014