የሥዕል ጠበብት (ፎቶግራፍንም ይጨምራል) እና የብዕር ባለተሰጥኦዎች “የእኔ ሙያ ይበልጥ የእኔ” የሚል የረጂም ዘመናት ሙግት ነበራቸው ይባላል። ክርክሩ በዘመን ርቀት፣ በቴክኖሎጂ ርቅቀትና በአስተሳሰብ ምጥቀት ተዳኝቶ ይቋጭ አይቋጭ ማረጋገጫ ማግኘት ያዳግታል።
ለማንኛውም በየትኞቹም ሙያዎች መካከል አሸናፊና ተሸናፊ ይኖራል ብሎ ለማመን አዳጋች ስለሚሆን ለማሳያነት እንዲያግዘን ብቻ ሠዓሊያኑና ደራሲያኑ “የራሳቸውን የሙያ ቆዳ ለማዋደድ” ይጠቀሙባቸው የነበረውን አንድ አባባል አስታውሰን ወደ መነሻ ጉዳያችን እናቀናለን።
ሠዓሊያኑ (የፎቶግራፍ ባለሙያዎች) “ከሺህ ቃላት አንድ ሥዕል የበለጠ ይናገራል” በማለት ሙያቸውን ሲያደንቁ፤ በአንጻሩ ደግሞ የደራስያኑ ምላሽ እንዲህ የሚል ነው። “እርግጥ ነው ከሺህ ቃላት አንድ ሥዕል መብለጡ አይካድም። ችግሩ ግን ከሺህ ቃላት አንድ ሥዕል መብለጡን ለማረጋገጥ ሺህ ቃላት ማስፈለጉን ያለማወቅ ነው።” የእኩል ለእኩል ፉክክር ማለት እንዲህ ነው።
በእኩል እውነት፤ እኩል አሸናፊነት። ሁለቱንም ሙያዎች የተካነ ግለሰብ ወይንም ተቋም አለሁ ቢልስ? እንዲህ ከሆነማ ዳኝነቱም ሆነ ብያኔው ላይከብድ ይችል ይሆናል። ምክንያቱም “ሽልማት የሚኖረው ከሆነ” ሁለቱንም “የሽልማት ወርቆች” ጠቅልሎ ስለሚረከብ “የሻምፒዎኖች ሻምፒዎን” በመሆን ያለተወዳዳሪ ብቻውን ምሥጋናው ተትፍርፎ ይደርሰዋል።
ከታሪክም የወሮታ ሞገስ ያጎናጽፈዋል። በዚህ ጽሑፍ ትኩረት ሰጥተን የምንቃኘው “ሽልማቱ እንኳን ቢቀር” ለዚህ ክብር ተገቢ ነው ያልነውን የዚህን የአዲስ ዘመን ጋዜጣና በተለያዩ ቋንቋዎች ለሚታተሙ ወንድሞቹ “አበ ቤት” የሆነውን የ80 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ተቋም የፕሬስ ድርጅትን ይሆናል። ፕሬስ ድርጅት የዕለት ዜና ቀላቢ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያና ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ነበር ዜናዎችን (በዛሬ ምልከታ ታሪኮችን)፤ በፎቶግራፍና በጽሑፍ ሰንዶ ከትውልድ ትውልድ የሚያቀባብል ባለ አደራ ተቋምም ነው። “በሦስት የተሸረበ ገመድ አይበጠስም” እንዲሉ፤ ይህ ድርጅት ክብሩ ከፍ ያለ ነው የምለው ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን አጣምሮ የአገሪቱን ዜና መዋዕል በመሰነድ ተቀዳሚ ተቋም ስለሆነም ነው።
ታሪክ የአገር ምሰሶ፣ ባህሎችም የምሰሶው መሰረት፣ ኢኮኖሚውና ማሕበራዊው መስተጋብር ማገር፣ ቋንቋዎች ውበት፣ ፖለቲካውም አዛዥ የመሆናቸውን እውነታ ሳያዛንፍ የእያንዳንዱን ቀን ክስተት በአግባቡ ሰንዶ ማስቀመጥ በራሱ የአገር መልክ መገለጫ ስለሆነ አንቱታው ተገቢነት ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ የአንድ ዘመን ብሩህ መልክ፣ ወይንም የአንድ ወቅት ጉስቁል ፊት፣ አለያም ዝንጉርጉር ዜና መዋዕሏ ድርጅቱ በሚያሳትማቸው ጋዜጦች ውስጥ ወለል ብሎ ስለሚገኝም ተቋሙ በአገር መስታወት ተምሳሌነት ቢጠቀስ ይበዛበታል የሚል እምነት የለንም። መንግሥታዊ ልሳን በመሆኑም የዘመኑ ገዢዎች መልክ ይጎላበታል ተብሎ መወቀሱ አግባብ እንዳልሆነ በእግረ መንገድ ሃሜታውን ገስጾ ማለፍ ተገቢ ይሆናል።
ይልቅስ እንኳንም ትናንትን አሸጋገሮልን፤ እንኳንም ዛሬን ሰንዶልን፤ እንኳንም ለነገ ትውልድ ባለአደራ ሆኖልን ቀርቶ ዕድሜው ራሱ ስለሚያስከብረው “ሽበቱ – ሺህ ውበቱ ነው።” “ስለ ኢትዮጵያ” – የእናት አገር የዛሬ መልክ፤ ይኸው አንጋፋ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዓይነቱ ለየት ያለ፣ በይዘቱ ወቅታዊ የሆነ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ አዘጋጅቶ ለጉብኝት ሕዝቡን የጋበዘው ከታህሳስ 25 – ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆይ መርሃ ግብር ነድፎ ነው። ይህ ታሪካዊ ዝግጅት ትኩረቱ የአሸባሪውን የትህነግ ቡድን አርመኔያዊ ድርጊቶችና ሽንፈቱን “ከሺህ ቃላት ይበልጣል” በሚል ይትብሃል በሚጎላመሰው ፎቶግራፍ አማካይነት ወለል አድርጎ በማሳየት እርቃኑን የሚያስቀር ጥሩ ማሳያ ጭምር ነው።
አሸባሪው እኩይ የትህነግ ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜኑ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ከወሰደው የክህደት እርምጃ እስከ ዛሬው ሽንፈቱ ድረስ ያለው የፍልሚያው ዜና መዋዕል በሚገባ በፎቶግራፍ ተሰንዶ መቅረቡ ፋይዳው ከፍ ያለ እንደሆነ ከትርዒቱም ሆነ በመክፈቻው ዕለት ከተደረጉት ውይይቶች ለመረዳት ተችሏል። የትህነግ ወራሪ ቡድን መልክ ተራቁቶ የቀረበበትን ይህንን ዝግጅት ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የገለጹት እንዲህ በማለት ነበር።
“ትህነግ ለአገር ሕግ፣ ለሞራል ሕግ፣ ለባህል ሕግም ሆነ ለሃይማኖት ሕግ የማይገዛ አረመኔ ቡድን መሆኑ በዚህ የፎቶግራፍ ዐውደ ርእይ በሚገባ ተንጸባርቋል።” አስተያየት ሰጭው የገለጹበት ማሳያ በርግጥም ተገቢ እንደሆነ ለማሳየት አጠቃላዩን ምልከታቸውን በአጭሩ እናስታውስ። ትህነግ ወረራውን የፈጸመው “ራሱ አርቅቆ ላጸደቀው ሕገ መንግሥት” አልገዛ ብሎ በማመጽ ስለመሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል። የማዕከላዊ መንግሥትን አላደምጠም፣ አልታዘዝም እና አልተባበርም ብሎ በራሱ ምህዋር መሽከርከሩ በብዙ ማሳያዎች ተገልጧል።
ከሁሉም የከፋው በጀግናው የሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ክህደት ነው። የክህደቱ አተገባበር ብቻም ሳይሆን ቀደም ባሉት ዓመታት ይህ ጀግና ሠራዊት በትግራይ ሕዝብ መካከል ሲኖር ያበረከታቸው ማሕበራዊ ተሳትፎዎች ምን መልክ እንደነበራቸው በጥቂቱም ቢሆን በፎቶግራፎች ምስክርነት ለማሳየት ተሞክሯል። የተሳትፎዎቹ ማሳያ ፎቶግራፎች ትንሽ ቁጥራቸው በርከት ቢል መልካም ነበር።
ይህን መሰሉ የሠራዊቱ በጎነት ትህነግ አስተዳድረዋለሁ በሚለው ክልል በገሃድ ተፈጽሞ እያለ ለጀግናው ሠራዊት የተከፈለው ግን ከምሥጋና ይልቅ ክህደትና ጥቃት ነበር – አጸያፊ የታሪክ ቅርሻት። ዝርዝሩ በሚገባ በፎቶግራፎቹ ስለተሰነደ ሙሉውን ሥዕል ለማሳየት በቂ ወካይ ነው። ሁለተኛው የትህነግ ዝቅጠት ለማሕበረሰቡ የሞራል ሕግ አልገዛ ብሎ ያፈነገጠባቸው ተግባሮቹ የተወከሉበት የፎቶግራፍ ስብስብ ነው።
በእነዚህ ፎቶግራፎች አማካይነት አሸባሪው ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የፈጸማቸው እጅግ አሰቃቂ ክፋቶች በሚገባ ተሰንደዋል። ሕጻናት ሴቶችን፣ ነፍሰጡሮችን፣ የዕድሜ ባለጸጋ እናቶችንና ለፈጣሪ ያደሩ መነኩሲቶችን ሳይቀር ለገማና ለከረፋ ፍትወታቸው ማርኪያ ማድረግን በምን ቋንቋ ለመግለጽ ይችላል።
አንዲት መነኩሲት እናት “ከዚህ በኋላማ የምንኩስና ቆቤ ረክሶ ምኑን እማሆይ ተባልኩ” በማለት በእንባ እየታጠቡ የሚታዩበት አንድ ፎቶግራፍ ሺህ ስሜቶች የተስተናገዱበት ነው። እንዲህ ዓይነቱ አረመኔነት የሞራል ዝቅጠት ተብሎ ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን ወደፊት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ጭምር ገትሮ ለክፋታቸው ጥግ ማሳያነት በማስረጃነት ጭምር የሚቀርብ ሠይጣናዊ ድርጊት ነው።
የአሸባሪውና የወራሪው ጀሌዎች ዓይን እያላቸው የማያዩ፤ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ ኅሊናቸውና መንፈሳቸው የሞተ የቁም ሟቾች እንደሆኑ ከዚህ በላይ ምን ማረጋገጫ ማቅረብ ይቻላል። መመገቢያን መጸዳጃ፣ የግለሰቦችን ቤትና ተቋማትን የቡድናቸው መቀበሪያ ማድረግንስ ምን ስም ይሰጡታል? ለመሆኑ ከአሁን በፊት በተፈጸሙ የዓለም ታሪኮች ውስጥ መሰል ኢሞራላዊ እርኩሰቶች ተፈጽመው ያውቁ ይሆን? በሦስተኛነት የተደራጁት ፎቶግራፎች የሚያመለክቱት የአሸባሪውን ቡድን የባህል ሕግ ጥሰት ነው።
የአገር መገለጫ የሆኑ ታሪካዊ መረጃዎች እንዲወድሙ፣ ሰነዶች እንዲቃጠሉ፣ ቁሳቁሶች እንዳልነበረ ሆነው እንዲንኮታኮቱና መታሰቢያዎች እንዲፈርሱ ወዘተ. በማድረግ ምን ትርፍ ማግኘት ይቻላል። የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማርከስንስ ምን ይሉታል? የውጭ ወራሪዎች ያልፈጸሙት ድርጊት በእኛዎቹ የዲያቢሎስ መልዕክተኞች ተፈጽሞ መታየቱስ በምን ቋንቋ ሊገለጽ ይችላል። ይብላኝ ኅሊናቸው ለሻገተባቸውና መንፈሳቸው ለበከተባቸው የቁም ጣዕረ ሞት ምልክቶች! ኢትዮጵያስ አንሰራርታ ለመቆም ጊዜ አይወስድባትም።
ለእነርሱና እነርሱን ለሚነዳው ኃይል ግን በምድር ብቻ ሳይሆን የፀባኦት ፍርድም የሚዘገይ አይደለም። አራተኛው የወራሪዎች ግፍ የተፈጸመው ሃይማኖትን በማርከስ ነው። ቤተመቅደሶችንና መስጊዶችን በከባድ መሳሪያዎች ሆን ብለው አፈራርሰዋል፣ አውድመዋል፣ ዘርፈዋል። ነዋየ ቅድሳትን አክፋፍተዋል። የሃይማኖት አባቶችንና እናቶችን አዋርደው፣ ገድለዋል፣ አቁስለዋል፣
ተዘባብተዋል። ንፁሐንን ያለ ርህራሄ ጨፍጭፈዋል። ይህ ድርጊታቸው በውሱን ፎቶግራፎች ወካይነት ቀረበ እንጂ ተሟልቶ ቢሰነድ ኖሮ ብዙ ጉዶችንና ሠይጣናዊ ድርጊቶቻቸውን በሚገባ ማሳየት ይቻል ነበር።
“እኔን ስታሙኝ የኖራችሁት ወያኔን ባታውቁት ነው” አለ ሠይጣን፤ የሚለው የአንድ ሰሞን ቀልድ ለፈገግታ ብቻም ሳይሆን እውነት መሆኑ ማረጋገጨም ጭምር ነው። ለካንስ ሰይጣን የሚኖረው በጥልቁ ውስጥ ሳይሆን በወያኔዎች ጥልቅ ልብና መንፈስ ውስጥ ኖሯልና! እነዚህን ይዘቶች አካቶ ከሺህ ቃላት በተሻለ ገላጭነት የቀረበው የፎቶግራፉ ዐውድ ርእይ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎችም እንዲታይት የምረቃው ተሳታፊዎች ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።
በተለይም የመከላከያ ሠራዊትን ወክለው የተገኙት ማእረግተኛ መኮንን እንደገለጹት፤ ይህን መሰሉ የወያኔ ግፍና ጭካኔ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ፤ በተለይም ለሠራዊቱ ትልቅ ትምህርት የሰጠ ብቻም ሳይሆን በርካታ በጎ ውጤቶችም ከውስጡ በቅለው የወጡበት ክስተት ጭምር እንደሆነ በብዙ ማሳያዎች ሊያስረዱ ሞክረዋል።
ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎበት የተገኘው ድል እንደተጠበቀ ሆኖ የአገር መከላከያ ሠራዊቱ አቅም እንዲጎለብት፣ ክብሩ ከፍ እንዲል፣ በሰው ኃይሉ፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ አቅሙም ሠራዊቱ ከፍ እንዲል አስችሎታል። በተለይም ወታደርነት ወጣቶች እየተለመኑ የሚገቡበት ተቋም ሳይሆን በእሽቅድምድም የሚፈለግ ሙያ ወደመሆንም መሸጋገሩ ሌላው ትሩፋት ነው።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በግንባር ተገኝቶ ጦሩን መምራት ለወደፊቱ ተተኪ መሪዎች ደረጃውን በእጅጉ ያገዘፈ መሆኑንም በማስረጃ ጭምር እያብራሩ ገለጻ አድርገዋል።
ምናልባትም የወደፊቶቹ መሪዎች የሥልጣን ወንበር ሲያልሙ የወታደርነትን ሙያ በብቃትና የአገርንና የሕዝብ ፍቅራቸውን ደግሞ በተግባር አስፈትሸው እንዲወዳደሩ መንገዱን ሳያመላክት እንዳልቀረም ግምታቸውን ሰንዝረዋል። ከልብ ጠብ የሚል አስተያየት ነበር።
በታሪካችን ውስጥ የወታደሩን ሬሽን እየተመገቡ በግዳጅ ቀጣና ውስጥ ውሎ በማደርና አመራር ሰጥተው ለአሸናፊነት ካበቁን መሪዎች ተርታ ስማቸውን ያስመዘገቡት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ውሏቸው ምን መልክ እንደነበረም በሚገባ ተመልክቷል። ምናልባትም ያ ክስተት በቃላት ይመላከት ቢባል ሳያስቸግር የሚቀር አይመስለንም። ይህ የዘመናችን “በላ” የሆነው አሸባሪውና ወራሪው ቡድን በምን ቋንቋ ተገልጾ ልብ እንደሚረካ በእጅጉ ለማስረዳት ያስቸግራል።
የደሃ ገበሬን የእህል ጎታ በጥይት ማቃጠል፣ የዕለት ቀለቡን ከማዕዱ ላይ አሟጦ መዝረፍ፣ እንስሳቱን በአረር መደብደብ፣ ተገደው በቤታቸው ያስተናገዱትን ንጹሐን ገድሎ በድናቸውን እዚያው ምድጃ ዳር ጥሎ መሄድ፣ ሲከፋም በበድናቸው ላይ በር ቆልፎ በማቃጠል በነበልባሉ እሳት የእብሪቱን ቆፈን ማሞቅ . . . ምን ይሉት እርኩሰት፣ ምን ይሉት አውሬነት ነው!? ለካስ ቃላትም እውነትን ለመግለጽ አቅም ያንሳቸዋል? የፎቶግራፉ ዐውደ ርእይ ሰንቆ የያዘው ይህንን መሰሉን የጊዜያችንን መከራና የጀግኖችን ድል በማጣመር ነው።
ከሠራዊቱ አባላት የማይተናነስ ዋጋ እየከፈሉ እነዚህን ታሪካዊ ፎቶግራፎች ላስቀሩልን የፕሬስ ድርጅት የፎቶግራፍ ባለሙያዎች፣ ለድርጅቱ ባልደረቦችና አመራሮች በሙሉ ከፍ ያለ ምሥጋናችን ይድረሳቸው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 27/2014