አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ኢትዮጵያን አፈራርሳለሁ፤ በፍርስራሾቿም ታላቋን ትግራይ እገነባለሁ በሚል ቀቢጸ ተስፋ የማይሞከረውን ሞክሮ የማትደፈረዋን ኢትዮጵያ ደፍሯል። በድፍረቱም ሰዋዊ ያልሆነና የከረፋ ባሕሪውን ለድፍን ዓለም አሳይቷል።
ይህንንም በዕብሪት ተወጥሮ በድፍረት የጭካኔውን ጥግ በሰው ልጆች ላይ እያደረሰ ባለው እኩይ ተግባሩ አረጋግጧል። አንድ ዓመት በተሻገረው ጦርነትም የሰው ልጅ ሊፈጽመው ቀርቶ ሊያስበው የማይቻለውን ዘግናኝ ድርጊቶች በንጹሐን ላይ ሲያደርስ ቆይቷል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በሰዎች ላይ ካደረሰው ግፍና መከራ ባሻገር በመሠረተ ልማቶች ላይም በርካታ ውድመት አድርሷል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በእንስሳት ላይ ያደረሰው ግፍ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ የሚጠፋ አይደለም።
“የግፍ ግፍ አንገፍግፍ “ እንዲሉ ምንም የማያወቁ እንስሳትን ያለ ሐጥያታቸው የጅብ እራት ማድረጉ አይረሳም። በአካል ጎልምሶና ፈርጥሞ በአስተሳሰብ ግብሩ የቀነጨረው ሰው የሚለውን ካባ የደረበው ቡድን ሰዋዊ ባህሪ የሌለው በመሆኑ ገበሬው እንደ ህጻን ልጆቹ የሚሳሳላቸውን ከብቶቹን በጥይት ገድሎ አፈር ሲገፋ የኖረውን ኢትዮጵያዊ ገበሬ አንገት በማስደፋት ማቅ አልብሶ ቅስሙን ሰብሯል።
ቡድኑ ‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሰይጣንም ጋር ቢሆን እናብራለን›› በማለት ከሰይጣን አስር እጥፍ የሚበልጠውን የጭካኔውን በትር በሰዎች ላይ አሳርፏል። በተለይም ወረራ በፈጸመባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ላይ ሰብአዊ፣ ቁሳዊና ሥነልቦናዊ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ‹‹እኛ እያለንላት ኢትዮጵያ አትፈርስም›› ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን በልበ ሙሉነት ከዳር እስከዳር ተነቃንቀው የአሸባሪውን አከርካሪ በመምታት ረብ የለሽ ሀሳቡን ከመንገድ ማስቀረት ችለዋል። ቡድኑ አዲስ አበባ ከተማ ለመግባት ምንም የሚያግደው እንደሌለ በነገረን ማግስት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ሜዳ ተጉዘው የአገሪቱን ሠራዊት ለመምራት በወሰኑበት ቅጽበት የአሸባሪው ግስጋሴ መገታቱና ወደ መንደሩ መመለሱ የሚታወስ ነው። ታድያ መራራውን እውነት ከመጋት ውጭ ምርጫ የሌለው ይህ ቡድን ትናንት ‹‹ጦርነቱ ተጠናቅቋል፤ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው? ቀጣዩ ጉዞአችን የሽግግር መንግስት አቋቁመን ሪፍረንደም ማካሄድ ነው›› ባለበት አንደበቱ ዛሬ ደግሞ የድረሱልኝ ተማጽኖውን ማሰማት ጀምሯል።
ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ሆኖ ሕልሙ የተጨናገፈበት ይህ አሸባሪ ቡድን ታድያ “ካፈርኩ አይመልሰኝ“ በሚል የሞኝ ጨዋታ ዛሬም በለመደ አፉ አይኑን በጨው አጥቦ ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጌያለሁ ይለን ጀምሯል።
ከሳምንታት በፊት በርካታ የአማራ ክልል ከተሞችን ተቆጣጥሮ ከአዲስ አበባ 200 ኪሎ ሜትሮች ባነሰ ርቀት ውስጥ ደርሶ የአራት ኪሎ ቤተመንግሥት በአይነ ሕሊናው ሲዞር የነበረው ይህ ቡድን አሁን ላይ ወትሮም የማይሞላው ሀሳቡ ቀን ጎድሎበት ተሰናክሏል። የድረሱልኝ ተማጽኖው የት ሊደመጥ እንደሚችል ባይታወቅም ቅሉ ለበርካታ አገሮች መፈራረስ ምክንያት የሆነችው አሜሪካና አጋሮቿም ቢሆኑ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ያቀጣጠሉትን ሕዝባዊ ንቅናቄን መቋቋም የሚሆንላቸው አይመስልም።
በተለይም አኩሪ ገድል መፈጸም የምንጊዜም መገለጫው የሆነው የኢትዮጵያን ሠራዊት እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ያለውን ጥምር ጦር ክንድ ቀምሶ ወደ መቀሌ የፈረጠጠውን አሸባሪ ቡድን ለማዳን የሚቀርጹት አጀንዳ ያለ አይመስልም። እርግጥ ነው አሜሪካ የአፍራሽና አንጋሽ ጨዋታን የተካነች አገር በመሆኗ በርካታ አገሮች በእርሷ ምክንያት ‹‹ነበር›› ሆነው መቅረታቸውን ታሪክ ይነግረናል።
ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ለሉዓላዊ ክብራቸውና ለዳር ድንበራቸው በሚከፍሉት የበዛ ዋጋ እንዲሁም በጸና አንድነታቸው ምክንያት ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች እንጂ አትፈረካከስም ‹‹ነበር›› ም አትሆንም። አሜሪካ ዛሬ በገሃድ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ካለ ባንዳ ጋር ጋብቻ ብትፈጽምም ላለፉት በርካታ ዓመታትም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተሞክሮ ያልተሳካ ሕልም እንደነበርም ይታወቃል።
ኢትዮጵያውያን የቱንም ያህል የውስጥ ችግሮች ቢኖሩባቸውም በአገር አንድነት ለመጣ ጠላት ግን ቀፎው እንደተነካ ንብ መሆናቸው የማይታበይ ሀቅ ነው። በሽብር የሚፍረከረክ ህዘብ የሌላት ኢትዮጵያ ታድያ ዛሬም እንደ ትናንቱ አገርን አፈርሳለው ላለው ውስጣዊ ጠላትም ሆነ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ልጫንብህ ላለው የትኛውም ኃይል ተገቢውን ምላሽ በመስጠት አኩሪ ገድል አስመዝግባለች። ከወር በፊት በተከታታይ ስንሰማቸው የነበሩ የድል ዜናዎች በተለይም ከአፋር ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ ከአማራ ክልል ከሰሜን ሸዋ፣ ከደቡብ ወሎ እንዲሁም ከሰሜን ወሎ ቁልፍ ስፍራዎች የዘረፈውን ሽሮና በርበሬ ሳይቀር እያንጠባጠበ የወጣው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን አንዱ ምስክር ነው።
ታድያ በቀዳሚነት በስልታዊ ውሳኔ ይዘዋቸው የነበሩ ቦታዎችን መልቀቃቸውን ሲገልጹ የቆዩት የቡድኑ መሪዎች ለቀረበላቸው የሰላም ጥሪ በራችን ዝግ ነው ሲሉ እንዳልቆዩ አሁን ላይ ከአፋርና ከአማራ ክልሎች መልቀቃችን ተሸንፈን ሳይሆን “ለሰላም ዕድል” ለመስጠት ነው በማለት ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ ላሞኛችሁ አይናችሁን ጨፍኑ እያሉን ነው። እነሱ ይህን ይበሉ እንጂ “እንደራደር” የሚለው ጨዋታ ያረጀና ያፈጀ ቁማር ሆኗል። በዚህ የሞኝ ቀልዳቸው ምናልባትም የትግራይን ህዝብና በሩቅ ያለውን ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሊያታልሉበትና ሊያጭበረብሩበት ይጠቅማቸው ከሆነ እንጂ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፈፅሞ ማታለል አይቻልም።
ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራን ተከናንቦ ትጥቅና ስንቁን በየመንገዱ አንጠባጥቦ የፈረጠጠን አሸባሪ ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጎ መጣ ብሎ የሚቀበል የትግራይ ሕዝብ ካለ እሱን ማሞኘት ይቻላል።
ቀሪው የትግራይ ሕዝብ ግን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ ቆም ብሎ በማሰብ የአሸባሪውን ቡድን ውንብድና እንዲሁም በሕዝቡ ስም እያደረገ ያለውን ክህደት በመረዳት እራሱን ነጻ ማውጣት ይኖርበታል። ከዚህ ሰው በላ ቡድን በቀላሉ ነጻ መውጣት የማይቻል ቢመስልም ሕዝብ በአንድነት ሆ ብሎ ከተነሳ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለምና ነገ ዛሬ ሳይል ሕዝቡ አሸባሪውን ሊሞግተው ይገባል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ ሲፈናጠጥ እርሱን ሊነቀንቅ የሚችል የትኛውም ኃይል ያለ አይመስልም ነበር።
ዳሩ ግን ‹‹ብርሌ ከነቃ አይሆንም ዕቃ›› ነውና ተረቱ ሁሉም ነገር ነበር ሆኗል ። የሰማይ ስባሪን ያህል ገዝፈው፤ በቱባ ስልጣናቸው ምክንያት በሕዝብ ላይ ግፍና መከራን አድርሰው እነሱ ግን በኢኮኖሚ ደርጅተው የምድር ገነት የሆነ ሕይወት የፈጠሩ ቢመስላቸውም ፤ ዛሬ የግፋቸው ጽዋ ሞልቶ የህርድ ቀን ሆኖባቸዋል ።
የትግራይ ህዝብ ሆይ ቆምንልህ ታገልንልህ የሚሉትን ፌዝ ወደ ጎን በመተው ልጆችህ የት እንደደረሱ ጠይቅ፤ ህጻናቱን ሳይቀር ለእኩይ ተግባሩ በማሰለፍ በጦርነት ማግዶ ምድሪቱን ባዶ ስለማድረጉም ሞግት፤ በአማራና በአፋር እህት ወንድሞችህ ላይ የደረሰው ግፍና መከራ ስለምን ይሆን ? ብለህም መርምር እንጂ መነገጃ አትሁን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 27/2014