አዲስ አበባ፡- የሲንቄ እናቶች በሰላም ዙሪያ እያከናወኑ የሚገኙት ተግባር የአገር ችግርን ከመፍታትም የሚዘልቅ አቅም እንዳለው የኢትዮጵያ የግጭት አፈታት ሥርዓትን ልምድ ለመቅሰም በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የሱዳን ልኡካን ቡድን አባላት መግለጻቸው ተጠቆመ።
ሱዳናውያኑ በጉብኝቱ ወቅት የሰጡትን ግብረመልስ አስመልክተው በጉብኝት መርሐ ግብሩ አስተባባሪነት የነጋዴ ሴቶችን በመወከል የተሳተፉት የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ነጋዴ ሴቶች ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የሱዳን ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ በመገኘት የሀገሪቱን የግጭት አፈታት ተሞክሮ ቀስሟል።
ሱዳናውያኑ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች ይፈጠራሉ፤ ወዲያው ይቀዘቅዛሉ፤ ይፈታሉም›› ሲሉ መግለጻቸውን ወይዘሮ እንግዳዬ ጠቅሰው፣ ‹‹ይህ የሆነውም እንዳየነው ባህሎቻችሁ መፍትሄ ሰጪዎች ስለሆኑ ነው፤ ባህላችሁን ትኖሩታላችሁ፤ ግጭትን መፍቻ ፣ሰላምን ማስፈኛም ታደርጉታላችሁ›› ሲሉ መናገራቸውን አስታውቀዋል። ‹‹በሱዳን በየጊዜው ግጭት ይቀሰቀሳል፣ በቀላሉም የሚቀዘቅዝና የሚፈታ አይደለም። ስለዚህ ይህ ባህላችሁ ለእኛ ጥሩ ተሞክሮ የሚሆንና ችግሮቻችንን እንዴት መፍታት እንዳለብን ግንዛቤ ያስጨበጠን ነው። ስለዚህም ይህንን ባህላችሁን በሚገባ ማወቅና መተግበር እንፈልጋለን›› ማለታቸውንም ገልጸዋል።
በተለይ የሲንቄ እናቶች በሰላም ማስፈኑ ዙሪያ የሚጫወቱትን ሚና ሲመለከቱና በአካባቢውም የሚሰ ጠውን ልዩ ክብር ሲገለጽላቸው እጅግ መደሰታቸውን የተናገሩት ወይዘሮ እንግዳዬ ፣ ይህ ሥርዓት ለአገር ችግር መፍቻ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ከዚያ አልፎ ለዓለምም መሆን እንደሚገባው መጥቀሳቸውን አመል ክተዋል ። ወይዘሮ እንግዳዬ እንዳሉት፤የሱዳን ልዑካን ቡድን መሪ ፕሮፌሰር ሜኪ ሀሻብሊ ኢትዮጵያ ግጭቶችን በባህላዊ መንገድ በመፍታት ረገድ ጥሩ ተሞክሮ እንዳላት አስታውቀዋል።የሱዳኑ ልዑክ በተለይም በሴቶች የመሬት ባለቤትነት ዙሪያ ጥሩ ተሞክሮ እንደቀሰሙም ገልጸዋል።
ተሞክሮውን በአገራቸው ለመተግበር ከባህላቸው ጋር እንደሚያስተሳስሩት ገል ጸዋል። ጉብኝቱን ካስተባበሩት አንዱ የሆነው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ወይዘሮ ወይንሸት ኃይለማርያም እንደተ ናገሩት፤ልዑኩ የ«ሲንቄ» ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት የኢትዮጵያውያን ጀኔሬተር ነው ሲል መግለጹን ጠቅሰዋል። ወይዘሮ ወይንሸት እንደተናገሩት ፤ የልዑካን ቡድኑ ይህ ባህል ሰላም ለማስፈን ትልቅ አቅም መሆኑን አስታውቋል።
በዚህም አገር ወደ ልማትና ብልጽግና እንድትሸጋገር እንደሚያደርግ ፣ይህን ያህል ኃይል ያለውን ባህላዊ ስርዓት መጠበቅና ለሌሎችም ማስተዋወቅ እንደሚገባ አመልክቷል። የገዳ ሥርዓት አንዱ አካል የሆነው የኦሮሞ ሴቶች «ሲንቄ» ባህላዊ የእርቅ ሥርዓት በአገር ላይ የሚ ፈጥረው ሰላም ትልቅ እንደሆነ ተናግረዋል። ለዚህም ምስክሮቹ ይህንን የሰላም ማስፈን ሥራ ልምድ ለመውሰድ ከሱዳን የመጣው የልዑካን ቡድን መሆኑን ጠቅሰዋል። «ሲንቄ» ሴቶች ነፃነታቸውና መብታቸውን የሚያስከብሩበትና ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚሸከሙበት ባህላዊ ሥርዓት ነው። በዚህ ብዙ ችግሮች ይፈታሉ።››
ያሉት ወይዘሮ ወይንሸት፣ ይህን ያህል አቅም ያለው ባህል ሳይታይ መቆየቱን ተናግረዋል። እንደ ወይዘሮ ወይንሸት ማብራሪያ፤ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን በዚህ ባህል ላይ ጥናት አድርጓል።በቀጣይም ይህንን የማስተዋወቅ፤ ከትውልድ ትውልድ የማስተላለፍ ሥራ ይሰራል። ባህላዊ ሥርዓቱ ሰላም የማስፈን ሚና ከአገር ሊያልፍ ይገባልና በዚህ ላይ በተለይ የባህሉ ባለቤቶች ሊሰሩበት ይገባል።
ሱዳናውያኑ ያደረጉትን ጉብኝት ያስተባበሩት የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበርና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ናቸው። የልኡካን ቡድኑ አባላት የ ሲንቄ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቱን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ኮፌሌ ከተማ በመገኘት ጎብኝተዋል።ከአባ ገዳ አባቶች ጋርም ተወያይተዋል። ቡድኑ ልምድ እንዲቀስሙ ያደረገው የአፍሪካ ልማት ባንክ መሆኑም ታውቋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው