በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1970 የካቲት ወር የታተሙ ዜናዎችን ለመቃኘት ሞክረናል፡፡ በወቅቱ የነበረውን የሶማሊያ ወረራ ጦሩ ከመከላከል አልፎ ወደ ማጥቃት መሸጋገሩንና በወራሪው ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውን ኅብረተሰቡ ለማቋቋም ሲያደርግ የነበረውን ርብርብና ትብብር እንዲሁም በባቡር ሐዲዱ ድልድዮች ላይ የደረሰውን ውድመት በመጠገንና ለአገልግሎት በማብቃት መንግሥት ያደረገውን ጥረት እናይበታለን፡፡ ይህም አሁን በአሸባሪው ወራሪ የተጎዱ ሰዎችን ለማቋቋም ህዝባችን እያደረገ ካለው ጥረት ጋር ተመሳሳይ ይመስላል፡፡እነሆ ብለናል፡-
“የሶማሊያ ወራሪ ወታደር በኢትዮጵያ አብዮታዊ ሠራዊት ክንድ እየተደቆሰና ብትንትኑ እየወጣ ነው“
– ጓድ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ
«በአሁኑ ጊዜ በኦጋዴን ውስጥ ወርሮ የገባው የሶማሊያ ወታደር ከፍተኛ ውድቀት ስለደረሰበት በረኃብና በውሃ ጥም ከመሰቃየቱም በላይ በአብዮታዊ ሠራዊታችን ክንድ እየተደቆሰና ብትንትኑ የወጣ ሲሆን ግማሹ እግሬ አውጪኝ ብሎ ያለ የሌለ መሣሪያ በመጣል ወደ ሶማሊያ ሲፈረጥጥ ግማሹ እጁን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ »ሲሉ ጓድ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ የጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዋና ጸሐፊ ገለጡ፡፡ ጓድ ሻምበል ይህን ያስታወቁት ፤ትናንት ከቀትር በኋላ በብሔራዊ ሸንጎ ተገኝተው ዓለም አቀፍ ኢምፔሪያሊዝም እና አሻንጉሊቶቹ በኢትዮጵያ አብዮትና አንድነት ላይ ስለሚያደርጉት ቡርቦራና ወረራ ለአገር ውስጥና ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ለሆኑ የውጭ አገር የዜና ወኪሎች መግለጫና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡ ጓድ ዋና ጸሐፊው፤አድኃሪው የሞቃዲሾ
መንግሥት በዓለም አቀፍ ኢምፒሪሊዝም እየተረዳ በኢትዮጵያ ላይ ስለሚፈጽመው ወረራና ይህን ወረራ ለመከላከል በአብዮታዊት ኢትዮጵያ በኩል ስለተወሰደው ርምጃ ሲያስረዱ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሠራዊት የሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት ከግዛታችን ረግጦ ለማስወጣት በሚያካሂው ጦርነት ፤በአጭር ጊዜ ውስጥ ድልን እንደሚቀዳጅ አንጠራጠርም ብለዋል፡፡
(ጥር 30 ቀን 1970 ከወጣው አዲስ ዘመን )
በወረራው ቤት ንብረት ለጠፋባቸው መቋቋሚያ ተሰጠ
አሰላ (ኢ-ዜ-አ-) በአርሲ ክፍለሀገር የጭላሎ አውራጃ ሕዝብ በሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት ምክንያት ቤትና ንብረታቸው ለፈረሰባቸው በሴሩና በሌላው ቆላማ ክፍል ለሚገኙ አርሶ አደሮች መቋቋሚያ ፳፫ሺህ ፫፻፩ ብር ከ፲ ሳንቲም አዋጣ፡፡ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ የሥሬና የፈለገ ብርሃን ከተማ ነዋሪ ሕዝብ ፰፻፺፭ ብር፤ የሔጦሳ ወረዳና የኢተያ
ከተማ ነዋሪ ሕዝብ ፱ሺህ ፮፻፺፲፩ብርከ፴፭ ሳንቲም ፤የገደብ አሳሳ ወረዳ አርሶ አደሮች እና የከተማው ነዋሪ ሕዝብ ፮ሺህ ፸፻፺፬ ብር ከ፸፭ ሳንቲም፤ በጠቅላላው ፳፫ሺህ ፫፻፩ ብር ከ፲ ሳንቲም ገቢ መሆኑን የአውራጃው አስተዳደር ዋና ጸሐፊ ገልጠዋል፡፡ ከነዚሁ ከ፫ ወረዳዎች ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ የገደብ አሳሳ ወረዳ የገበሬ ማኅበር ፬ሺህ ብር፤ የገደብ አሳሳ ወረዳ ነጋዴዎች ፩ሺህ ብር፤ የሰፋፊ እርሻዎች ውይይት ክበብ አባሎች ፪፻ ብር ፤የወረዳው የአርሲ ገጠር ልማት ድርጅት ፪፻ ብር፤ የከባድ ዕቃ ጫኝና አውራጅ ወዝአደሮች፪፻ ብር፤ የሻይ ቤትና ቡናቤት ሠራተኞች ማኅበር ፪፻ ብር ፤የኢተያ አካባቢ ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት ፩ሺህ ብር፤ የገዌ 13 ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት ፩ሺህ ብር፤ የአላደዊ 13 ገበሬ ማኅበራት ፰፻ ብር፤ የቀጩ ሌንጫ 7 ገበሬ ማኅበራት ፯፻ ብር፤ የጐንጤ ቀበሌ ማኅበራት ፯፻ ብር የፈለገ ብርሃን 01 ቀበሌ ኅብረት ሥራ ማኅበር ጽ/ቤት ፩ሺህ ብር አዋጥተዋል፡፡ ሌሎችም አገር ወዳድ ግለሰቦችና መንግሥታዊ ድርጅቶች ከ፩ ብር እስከ ፮፻ ብር ድረስ የለገሱ መሆናቸውን የአውራጃው ዋና ጸሐፊ በተጨማሪ ገልጠዋል፡፡
( የካቲት 3 ቀን 1970 ከወጣው አዲስ ዘመን )
አምስት የባቡር ድልድዮች ተጠግነው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ፡፡
አሰበ ተፈሪ (ኢ-ዜ-አ-) ጓድ ሌተናል ኮሎኔል ጌታቸው ባንጃው ሺበሺ የአብዮታዊ ዘመቻ ጥበቃ መምሪያ ዋና ኃላፊ እና ጓድ ምክትል መቶ አለቃ ባንጃው የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ቋሚ የደርግ አባል በአርዶም ወረዳ ከሙሉ እስከ አፍደም ከተማ ባለው ሥፍራ ላይ እንደገና ተጠግነው አገልግሎት መስጠት የጀመሩትን ፭ የባቡር ድልድዮች ባለፈው ሐሙስ ጐበኙ፡፡እነዚህ ፭ ድልድዮች የአድኃሪው የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች በጣሉት አደጋ ፈራርሰው አገልግሎት ከመስጠት ተቋርጠው ነበር፡፡ ከሁለቱ የደርግ አባሎች በባቡር ከሙሉ እስከ ቡራፊ ድልድይ ድረስ በመጓዝ የተሠሩትን አምስት ድልድዮች ተመልክተው ፤በጥገናው ሥራ ላይ የተሰማሩትን ወዛአደሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ድልድዮችን ጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረጋቸው አመስግነዋል፡፡
ድልድዮቹን ለመጠገን በጠቅላላው 33 ቀኖች የወሰደ ሲሆን፤ሥራውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ የቻለው ወዝአደሮቹ በአደረጉት ከፍተኛ ጥረትና በአካባቢው የጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማሩት የሚሊሺያ ጦር አባሎች ከወዝአደሮቹ ጋር ተባብረው በመሥራታቸው ጭምር መሆኑን የጥገናው ኃላፊ ገልጠው የሚሊሺያው ጦር አባሎች በተጨማሪ ያበረከቱትን ከፍተኛ የሥራ ድርሻ ጠቅሰው አመስግነዋል፡፡ ቀደም ብሎም ሥራቸው የተጠናቀቁትን 4 ድልድዮች ለመሥራት 28 ቀን የፈጀ ሲሆን በመጨረሻ የጥገና ሥራው የተጠናቀቀው ድልድይ ደግሞ በአምስት ቀን ብቻ ተጠግኖ በአገልግሎት ላይ ለመዋል መቻሉን የጥገናው ኃላፊ ገልጠዋል፡፡
በአካባቢው ለሚገኘው ሠፊው ጭቁን ሕዝብ እንቅስቃሴና የኑሮ መሠረት የሆነው ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ድረስ ያለው የባቡር አገልግሎት በቅርብ ቀን ውስጥ እንደሚጀመር ተረጋግጧል፡፡በሠላሳ ሦስት ቀናት ውስጥ ተጠግነው አገልግሎት መስጠት የጀመሩት አምስት ድልድዮች የዳካ߹ የዳባ߹ የወንገዩ߹ የዶባና የሰሎ ናቸው፡፡
(የካቲት 19 ቀን 1970 ከወጣው አዲስ ዘመን )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26/2014