ተገቢውን ትኩረት-ለእናቶች ጤና

ዜና ሐተታ

የእናት መኖር ዋጋ ያለው ለአንድ ቤተሰብ ብቻ አይደለም። እናት ለሰፊው ማህበረሰብ ላቅ ሲልም ለሀገርና ወገን ወሳኝና ጥብቅ መሰረት ነች። ይህች ለብዙኃን የመኖር ዋስትና የሆነች ሥጦታ በወጉ ኖራ ትውልድን ትተካ ዘንድ ጤናዋ ሊጠበቅ የግድ ይላል።

እ.ኤ.አ በ2017 በተባበሩት መንግሥታት የተረጋገጠው ጥናት እንደሚጠቁመው፤ በዓለማችን በየዓመቱ ቁጥራቸው 295 ሺህ የሚጠጋ እናቶች ከእርግዝናና ወሊድ ጋር ተያይዞ ህይወታቸውን ያጣሉ። ከእነዚህ ውስጥ 94 በመቶ ሆነው የተመዘገቡት ደግሞ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚገኙ ናቸው።

በሀገራችንም ከእርግዝናና ወሊድ ጋር በተያያዘ በዓመት 14 ሺህ ያህል እናቶች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ጥናቶች ይጠቁማሉ።ይህን አሳሳቢ የእናቶች ሞት ለመቀነስ ጤናማ የእርግዝና ክትትልና ድጋፍ ማድረግ የግድ ይላል። ይህ እውነት ተገቢና አስፈላጊ ቢሆንም በርካታ እናቶች በተለያዩ ምክንያቶች ዛሬም ህይወታቸውን ለማጣት ይገደዳሉ።

እ.ኤ.አ በ2023 በደቡብ አፍሪካ ላይ በተደረገው የጤና ሪፖርት ኢትዮጵያ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። በዚህም ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት በተሻለ መልካም የሚባሉ ለውጦች ታይተዋል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ሕፃትና አፍላወጣቶች የእናቶች ጤና አገልግሎት ዴስክ አስተባባሪ ሲስተር ዘምዘም መሀመድ እንደሚሉት፤ የተገኘውን የተሻለ ውጤት ለማስቀጠል ኃላፊነቱ የሁሉም ወገን ሊሆን ይገባል። የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ፣የሚመለከታቸው ኃላፊዎችና የሚዲያ አካላትም ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ይገልጻሉ።

የእናቶችን ሞት ከሚያፋጥኑ ምክንያቶች አንዱ የመሰረተ ልማቶች አለመሟላት ነው። በሀገራችን አምቡላንስና መኪና የማይደርስባቸውና በቂ ውሃ የማይገኝባቸው ስፍራዎች ጥቂቶች አይደሉም የሚሉት ሲስተር ዘምዘም፤ ይህን ችግር ለመፍታት ሁሉም የሚመለከታቸው ተቋማት የድርሻቸውን መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ በ2014ዓ.ም በተደረገው የእናቶች ሞት ኦዲት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 800 እናቶች በወሊድ ምክንያት መሞታቸው ተረጋግጧል።

ሲስተር ዘምዘም እንደሚሉትም፤ በ2016 ዓ.ም የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባደረገው ጥናት በኢትዮጵያ 71 በመቶ የሚሆኑ እናቶች በህክምና መከላከል በሚቻል የጤና ችግር ህይወታቸውን ያጣሉ።

በሀገራችን ቁጥር አንድ የእናቶች ሞት ተብሎ የተመዘገበው የደም መፍሰስ ችግር መሆኑን የሚገልጹት ሲስተር ዘምዘም፤ ይህ ችግር በተለይ ከወሊድ በኋላ ከተከሰተ ለእናቶቹ በህይወት የመኖርን ዕድል ከሁለት ሰአት በላይ ጊዜ እንደማይሰጥ ይናገራሉ። ይህ አይነቱ አጋጣሚ፣ከመሰረተ ልማት እጦት ፣ ከግንዛቤ ማነስና ከቸልተኝነት ተዳምሮ ችግሩን የሚያባብሰው ይሆናል።

እኤአ በ2019 የተደረገው ጥናት እንደሚጠቁመው፤ በኢትዮጵያ 48 በመቶ የሚሆት እናቶች ብቻ በሆስፒታል የሚወልዱ ናቸው። ይህን ለመታደግም በአሁኑ ጊዜ በየገጠሩ ላሉ ወላዶች የሚያገለግሉ የእናቶች ማቆያዎች ተዘጋጅተው ችግሮችን እየቀረፉ ይገኛል።

በጤና ሚኒስቴር የሥነተዋልዶ ፣የእናቶችና ሕፃናት ጤና ቴክኒካል አማካሪ አቶ ታከለ የሺዋስ በበኩላቸው፤ ነፍሰጡር እናቶች የቅድመ ወሊድ፣ ድህረ ወሊድና የወሊድ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። ይህም መሆኑ አስቀድመው መታከም ለሚኖርባቸው ህመሞች መፍትሄ ለመስጠት ያግዛል። አንዲት ነፍሰጡር እናት እስከምትወልድ ድረስም ለስምንት ጊዜያት የጤና ክትትል ልታደርግ ግድ ይላል። የዚህ አሰራር ተግባራዊነትም በሁሉም ክልሎች እየተሰራበት ይገኛል።

አንዲት እናት ከወለደች በኋላ ለሃያ አራት ሰአት በጤና ማዕከሉ መቆየት ይኖርባታል የሚሉት አቶ ታከለ፤ ይህ አሰራር ተግባራዊ መደረጉ ከወሊድ በኋላ ለሚያጋጥም ደም መፍሰስ፣ደም ግፊትና ደም ማነስ መፍትሔ ለመስጠት ያግዛል።

በአሁኑ ጊዜ ባለው ጥናት ከ50 በመቶ የማያንሱ እናቶች በቤት ውስጥ የሚወልዱ ናቸው።ይህን ችግር ለመታደግም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ጥረቶች እንደቀጠሉ ናቸው።

አቶ ሸለመ ሁምኔሳ በጤና ሚኒስቴር የእናቶች ጤና ቴክኒካል አሲስታንት ናቸው።በዓለም ጤና ድርጅት ጥናት መሰረት ከሚያረግዙ አንድ መቶ እናቶች መካከል ከ5 እስከ 15 የሚሆኑት ከፍተኛ የጤና ችግር እንደሚያጋጥመቸው ይናገራሉ። ከዚህ አኳያም ለእነዚህ እናቶች የተዘጋጀ አስቸኳይ የቀዶ ህክምና ሊኖር ይገባል። በሀገራችንም ድንገተኛ ቀዶ ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ማዕከላት እየተስፋፉ ነው። በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን 432 የመንግሥት ሆስፒታሎች፣ 4 ሺህ ጤና ጣቢያዎች፣ 17 ሺህ ጤና ኬላዎች ይገኛሉ።

ድንገተኛ ቀዶ ህክምናን ከሆስፒታል ለማሻገር በተደረገው ጥረትም በአሁኑ ጊዜ 125 ጤና ጣቢያዎች አገልግሎቱን እየሰጡ ናቸው። በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ3 ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ እናቶች ያረግዛሉ ተብሎ ይገመታል።

አቶ ሸለመ እንደሚሉት፤ አሁን ላይ ለሁሉም እናቶች ተደራሽ የሚሆን የአልትራ ሳውንድ አገልግሎት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። የጤናውን ዘርፍ ችግሮች ለመታደግ 3 ሺህ 900 አምቡላንሶች ተገዝተው ተሰራጭተዋል። በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአየር ላይ አምቡላንስን ሥራ ለማስጀመርም በጤና ሚኒስቴር በኩል ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

የጤናማ እናትነት ወር በየዓመቱ የተለያዩ መልዕክቶችን መርህ በማድረግ በመላው ዓለም ይከበራል። ዘንድሮም በዓለም ለ38ኛ ፣በሀገራችን ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ ይከበራል።

ከጥር 1 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በሚኖረው ቆይታ ከእርግዝናና ወሊድ ጋር የእናቶችን ሞት ለመታደግ በሚያስችሉ መልዕክቶችና ግንዛቤ ማስጨበጫዎች በመስጠት ወሩን ሙሉ የሚከበር ይሆናል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You