ትናንትን በዛሬ፣ ከአዲስ ዘመን ዘመን አይሽሬ የትውስታ መንገዶች ላይ ካገኘናቸው መካከል “የዳቦ ነጋዴዎቹ እየቆመሩብን ነው” ለመሆኑ ምን ይቆምራሉ… ያደባባዩ አማጭ ደግሞ በጆሮ ከቀዳው ለአንባቢያኑ ያካፍላል:: ጥቂት ከዓለም ወሬዎችም ከሚባለው እንካፈልና በዛሬ እይታ ውስጥ ፈገግታን ሊያጭሩብን ከሚችሉት ከጥንቱ ማስታወቂያዎች እንተዋወቅ::
የዳቦ ነጋዴዎች እየቆመሩብን ነው
ዳቦ-ድሮ ቀረ ከሚባሉ ነገሮች አንዱ ነው:: ዳቦ መጠኑ በሚያሳዝን ሁኔታ እየቀነሰ ጥራቱም እያሽቆለቆለ፣ ዋጋው ደግሞ እየተተኮሰ ይታያል::
…
የድሮ ዳቦ ዳቦ መልኩ ብቻ ይበቃ ነበር ብል የምን ማጋነን ነው እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ::
…
ወዝ የሌለው ዳቦ በየቦታው ሞልቷል:: ዳቦ ከተባለ ማለቴ ነው:: እንቡጥ አይገኝበትም:: ያሳስራል፣ ያስቀጣል፣ ተብለው ይሆን ውሃ አጥቶ እንደደረቀ ቅጠል የሚያቆረፍዱት፤ በእዚህ ላይ መጠኑ በጣም እጅግ ያስገርማል:: ኪኒን እያከለ መጥቷል:: በእዚህ ላይ ተፈርፍሮ የሚያልቀውና ቤት የሚያበላሸው አይነሳም:: የሀምሳ ሳንቲም ዳቦ ስትገዛ የሁለት ብር መጥረጊያ መግዛትህን እንዳትረሳ እየተባለ የሚነገረውም ለዚሁ አይደል፤ የሱሙኒ ዶሮ የብር ገመድ ይዛ ጠፋች አይነት መሆኑ ነው::
…
ዛሬ ሕጻናት ሁለት ዳቦ በልተው አይጠግቡም:: እረ ይጨመርልን በሚል እያጉተመተሙ ነው ወደ ትምህርት ቤት የሚጓዙት:: ገና አንድ ክፍለ ጊዜ ሳይጨርሱ ሆዳቸው ምግብ ይጠይቃቸዋል:: አዋቂዎች አፋቸው ባዶ ባዶ እንዳይል ካልሆነ በስተቀር የዘመኑ ዳቦ አላረካቸውም:: ግማሹ ለአፈር የተቀረው ለከንፈር በመሆኑ ከሆድ አይደርስም::
…የምንበላው ሳይሆን የምንስመው ዳቦ መጥቷል:: የዳቦ ነጋዴዎች እስከመቼ ነው የሚቆምሩብን፤ ነዳጅ ጨመረ ሲባል በዚያው ልክ ዋጋ ይጨምሩብናል:: በ20 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ዛሬ እየቀረ ነው:: አንዳንዶቹ የ20 ሳንቲሙን 50 ይቀበሉበታል:: ግፍ የፈሩ ደግሞ የ50 ሳንቲሙን 60 ይቀበሉበታል::
…
የዳቦ ነጋዴዎች በእኛ ስቃይ እንዴት ይከብራሉ፤ ባንገዛቸውስ፣ ሌላ መላ መፈለግ አቅቶን ነው፣ እንደኔ እምነት ግን በአንድ ሰሞን ዘመቻ ዳቦ ቤቶችን ልክ ማግባት የሚቻል ይመስለኛል:: ዘንድሮስ እየቆመሩብን አይኖሩም የእስካሁኑ ይበቃል ባዮች በዝተዋል:: እባካችሁ ጉዳዩ የሚመለከታችሁ ሁሉ የዳቦ ቤቶችን አሠራር የሚያስተካክል አፋጣኝ እርምጃ ውሰዱ:: (አዲስ ዘመን መጋቢት 24 ቀን 1984ዓ.ም)
ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ወሬዎች
ከዮሐንስበርግ፤ (ደቡብ አፍሪካ) በኤልሳቤጥ ቤል ከተማ ውስጥ በታወቀው (ቆኢሊር) በተባለው የቴአትር አዳራሽ ውስጥ በሚታየው የሼክስፒር ቴአትር ውስጥ ገብተው ለመመልከት አንድ ጠይምነት ያለው መምህርና 4 ተማሪዎቹ ገንዘባቸውን ከፍለው የመግቢያ ወረቀታቸውንም ካስቆረጡ በኋላ በመልካቸው ያለመገርጣት ምክንያት ተከልክለው ገንዘብ በሚከፈልበት በር ላይ ተገፍትረው ወጥተዋል:: ገንዘቡም አልተመለሰላቸውም::
(አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 1952ዓ.ም)
ከሞስኮው “ሰማይ ለሁሉም ክፍት ነው” ሲል የአሜሪካ መንግሥት ያቀረበውን አሳብና ለራሱ ሚስጢር ፍለጋ የሚጠቀምበትን ጉዳይ አንስተው የሞስኮብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ግሮሚክ ሲያመለክቱ “ይኸንን የሞስኮብ መንግሥት ይቀበለዋል ማለት ዘበት ነው” ካሉ በኋላ የሞስኮብ መንግሥት ሰማይ ዝግ ነው:: ለወደፊቱም ቢሆን ዝግ እንደሆነ የሚኖር ነው” ብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ መለሱ::
(አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 1952ዓ.ም)
ያደባባዩ አማጭ
መቼም ያየሁትንና የሰማሁትን አልደብቅም እናገራለሁ ብያለሁና አሁንም እንደ አፍዛዥ ሆኖ የሰማሁትን ላውራላችሁ::
ግንቦት 1 ቀን 1952ዓ.ም ያንኑ ሰብሳቢውን አውቶብስ ለመጠበቅ(ለመሳፈር) ከኪንግ ጆርጅ ቡና ቤት በስተ ጎን ካለው የአንበሳ መቆሚያ ቆሜ የፓሪስን ውዝግብ ጋዜጣ ሳነብ በአጠገቤ አንዲት ድንቡልቡል፣ ሽቅርቅር ብላ በሀገር ልብስ አጊጣ አድራሽ አጥታ እንደኔው አውቶብስ ስትጠብቅ አንዱ ለፍቶ፣ ደክሞ አዳሪ ቀረብ ብሎ “እንደምን አድረሻልና መቼ እንገናኛለን? ብሎሻል ጋሼ” አላት:: እርሷም “ደኅንነቱንስ ያው ነኝ፤ ኸረ ለመሆኑ እርሱ ከኔ የሚፈልገው ምንድር ነውና ይህን ያህል አንተን ያመላልስሃል? ምን እንዳደርግለት ይፈልጋል? አንተስ ጉዳዩን ገልጸህ ለምን አትነግረኝም?” አለችው:: ያም አማጭ ከአንቺ የሚፈልገው እሺታሺን ነው:: ዓላማውም ለትዳር ነውና እሺ በይው ምንም እንኳን አንቺ በመምህርነትሽ የኔንና የርሱን ሁኔታ ብታርሚና የወር አበልሽም በርከት ያለ ቢሆን እርሱም…ነውና የተፈላለጋችሁበት ጉዳይ የተሳካ ይሆናል አለና የአማጭነቱን ያህል አስረዳ::
ወይዘሪትም (ግን እንጃ) እስቲ ሁሉንም ነገር አብራርቶ በቁጥር…በስልክ ደውልልኝና በሰፊው እንነጋገርበታለን:: እኔና አንተ ብቻ እዚህ ልንጨርሰው አልበቃንም፤ እንዳይረሳ አስጠንቅቀውና ስልክ እንዲደውልልኝ” ብላው አውቶብሱ ላይ ቁጢጥ አለች:: እኔ እዚህ ላይ ስለሁለት ነገሮች ብቻ አዝናለሁ::
1ኛ/ ጋብቻን ያህል ነገር አጀማመሩ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ በመሆኑ ፍጻሜው አያምርም ያው ነው::
2ኛ/ በቀደም እንዳወራኋችሁ ሁሉ የመንግሥቱ ስልክ እንደዚህ ለመሰለው የእንቆቅልሽ ጨዋታ እንደፈረደበት ተተኝቶበት መዋሉ ነው:: የሆነ ሆኖ ፒያሣ ላይ ከተጫጩ ተድረው ፒያሣ ላይ ለመታየት ያብቃቸው:: ግን ሁለቱ ፒያሣ ተጠፋፍተው እንዳይቀሩ ያድርጋቸው::
ማሞ ውድነህ(ዋግ ድሃና)
(አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 1952ዓ.ም)
ማስታወቂያ
ፊልም በሚታይበት ጊዜና ፊልም ለመለወጥ ብርሃን በሚደረግበት ጊዜ የብልግና ድምጽ ምልክት የሚሆን ፉጨት ድምጽ ሰሚዎችን እስከማደንቆር ይሰማል:: ይህ ከጠላት የተወረሰ የብልግና ድምጽ እንዳይሰማ እያስጠነቀቅን፤ የፉጨት ድምጽ የሚያሰሙትን የሚያስገድዱ ፖሊሶች መታዘዛቸውን እናስታውቃለን:: (አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 1941ዓ.ም)
ጥቅምት 18 ቀን ሐሙስ ጧት ባለ ቀንድ መያዣ የዓይን መነጽር ዑራኤል ስለጠፋብኝ፤ አግኝቶ ጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት ድረስ ላመጣልኝ ወሮታውን እከፍላለሁ::
(አዲስ ዘመን ጥቅምት 20 ቀን 1951ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም