ዜና ትንታኔ
የአክሲዮን ገበያ ለዜጎች፣ ለመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የገንዘብ ምንጭ በመሆን ለምጣኔ ሀብት እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ምሁራን ይናገራሉ። በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ ለመጀመር ከውሳኔ ተደርሶ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ በጥር 2017 ዓ.ም እንደሚጀመር ይፋ መደረጉ ይታወቃል።
የአክሲዮን ገበያ እንደ ሀገር ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ምን የተለየና አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል? ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግረን የሚከተለውን ምላሽና ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል።
በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ መጀመር አጠቃላይ ለሀገራዊ ኢኮኖሚውም ሆነ ለዜጎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው የሚሉት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲንና በአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ
አቶ በረከት ሶርሳ፤ ይህንን ለመገንዘብ በቅድሚያ የአክሲዮን ገበያ ምንድን ነው? የሚለውን መረዳት ያስፈልጋል። አክሲዮን ማለት በአጭሩ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ማለት ነው። ይህ ሰነድ የሚሸጥበት እና የሚገዛበት አደረጃጀት ደግሞ የአክሲዮን ገበያ ይባላል። የአክሲዮን ገበያ በስፋት ሀብት ለማሰባሰብ የሚረዳ ሲሆን መነሻ ጭብጡ ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት ካለበት እጥረት ወዳለበት እንዲተላለፍ ማድረግ ነው ይላሉ።
ለምሳሌ አንድ ተቋም ካለበት ደረጃ ራሱን ለማሳደግ ስራውን ለማስፋፋት ፈልጎ የገንዘብ እጥረት ቢገጥመው የባለቤትነት ሰነድን አሳትሞ ለማህበረሰቡ በመሸጥ የሚፈልገውን ገንዘብ መሰብሰብ ይችላል። የገንዘብ እጥረት ያለባቸው ነገር ግን ጥሩ ሀሳብ ያላቸውና ያንን ወሰደው ወደ ገንዘብ መቀየር ያልቻሉ ማናቸውም ግለሰቦች ወይንም ተቋማት የገንዘብ እጥረታቸውን የሚፈታላቸው እንደሚሆን ያመለከቱት ምሁሩ፤ ይህም ድርጅቶቹ እንደ ተቋም ራሳቸውን እንዲያሳድጉና እንዲያዘምኑ በር የሚከፍትላቸው ይሆናል። የሂሳብ አያያዝ ሥርዓታቸውን ሳይንሳዊና ዓለም አቀፋዊ እንዲያደርጉ በር የሚከፍት ይሆናል ነው ያሉት።
በዚህ አይነት የሚቋቋሙ ተቋማት ስራቸውንና ተደራሽነታቸውን የሚያሰፉ ከሆነ እንደ ሀገር ለኢኮኖሚው የሚኖረው ጠቀሜታ ሰፊ ነው። ባለ አክሲዮኖች ከሚያገኙት ገቢ ለመንግሥት የሚከፍሉት ግብር ለሀገር ኢኮኖሚ የሚጠቅምም ይሆናል። ተቋማቱ ራሳቸውን ህብረተሰቡ የተሻለ ምርት ለማግኘት እድል የሚኖረው ሲሆን፤ እግረ መንገዱንም ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጠር ይሆናል። ይህ እንደ ሀገር የሚገኘው ተጠቃሚነት ነው። በተጨማሪ የአክሲዮን ገበያ መስፋፋት የተቋማትን ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ በመሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲያመርቱ ይረዳል ሲሉ ያብራራሉ።
ተጠቃሚነቱን አክሲዮን በሚገዙት ሰዎች ወገን ሲታይም ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን ማግኘት ይቻላል የሚሉት አቶ በረከት፤ የመጀመሪያው ግለሰቦቹ የገዙትን አክሲዮን መልሰው በትርፍ የመሸጥ እድል አላቸው። አክሲዮንን አትርፎ ለመሸጥ ግን አክሲዮኑን የሸጠው ተቋም ትርፋማና በማህበረሰቡ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ ተስፋ የተጣለበት ሊሆን ይገባል። ሁለተኛው ጥቅም አክሲዮን የገዛው ተቋም በየወቅቱ የሚያካሂደው ዓመታዊ የተጣራ የትርፍ ክፍፍል ይኖራል። በዚህ መንገድ የሚገኘው ገቢ እንደየ ተቋማቱ የተለያየ ቢሆንም ጥሩ የሚባል ገቢ ይገኝበታል ይላሉ።
ይህም ሆኖ አንድ በአክሲዮን የተቋቋመ ድርጅት ኪሳራ ቢያጋጥመው አክሲዮኑን የገዙት ተጎጂ ይሆናሉ። በመሆኑም አክሲዮን ለገበያ የሚያቀርቡ ተቋማት አደረጃጀታቸውና ህጋዊነታቸው የተፈተሸ መሆን ይጠበቅበታል። ይህ የሚረጋገጠው ደግሞ ተቋማቱ የሀገሪቱን ደንብና መመሪያ ተከትለው የተቋቋሙና የሚሰሩ መሆናቸው ሲረጋገጥ እንደሆነ ይገልጻሉ።
አንድ ድርጅት የራሱን አክሲዮን ለመመስረት ለመሸጥ ማሟላት ያለበት ነገር ይኖራል። ይህም ማለት በቅድሚያ የአክሲዮን ገበያን እንዲያስተዳድር ስልጣን በተሰጠው አካል የተመዘገበ መሆን አለበት። የምዝገባውና የቁጥጥሩ አላማ ተቋሙ በየዓመቱ የትርፍ ገቢ ለአክሲዮኑ ባለቤቶች ግልጽ ማድረግ ይኖርበታል። ይህንን ለመተግበር የሚያስችል የተማረ የሰው ኃይልም በሀገሪቱ አሉ። ምን አልባት የቴክኖሎጂ ውስንነት ሊገጥም ይችላል። ይህም ቢሆን እንደ ሀገር የተሻለ እንቅስቀሴ ስላለ አደረጃጀቱን ተከትሎ በሂደት የሚፈታ በመሆኑ እንደ ስጋት አይታይም ነው ያሉት።
በተመሳሳይ የአክሲዮን ገበያ መቋቋም አጠቃላይ ለሀገራዊ ኢኮኖሚም ሆነ ለዜጎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ያሉት ደግሞ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አበራ ባይሳሳሁ (ዶ/ር)፤ የአክሲዮን ገበያ ኩባንያዎች ያለባቸውን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ ሁነኛ መንገድ መሆኑን ይናገራሉ።
ይህም ኩባንያዎች ባለቡት ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የሚያስችል ነው። ከዚህም በተጨማሪ አዳዲስ ስራዎችን እንዲጀምሩም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርላቻው ይሆናል። እነዚህ ሂደቶች በሙሉ የሥራ እድል ለመፍጠርና የገንዘብ እንቅስቀሴ እንዲኖር በማድረግ እንደ ሀገር ያለውን ኢኮኖሚውን የሚደግፉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
በሌላ በኩል የአክሲዮን ገበያ መኖር በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገር እንዲመጡ በር የሚከፍት ይሆናል። ብዙ ጊዜ ከሀገራቸው ውጭ በኢንቨስትመንት የሚሳተፉ ባለሀብቶች እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጡት ነገር የተደራጀና ጠንካራ የአክሲዮን ገበያ መኖሩን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። የእነዚህ ባለሀብቶች በብዛት ወደ ሀገር ውስጥ መግባት በሌላ በኩል የራሳቸውን ካፒታልና ቴክኖሎጂ ይዘው የሚመጡ በመሆኑ ለሀገር ኢኮኖሚ የራሱ ፋይዳ እንደሚኖረው ነው አበራ (ዶ/ር) ያስረዱት።
በአክሲዮን የተቋቋሙ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ባለአክሲዮኖች አክሲዮናቸውን መሸጥ ወይንም ተጨማሪ መግዛት ይችላሉ። እነዚሁ ድርጅቶች ለማስፋፋት ወይንም አዳዲስ ኢንቨስትመንት ቢፈልጉ ተጨማሪ አዳዲስ አክሲዮኖችን ለገበያው ያቀርባሉ። እንደ አዲስ በተለያየየ መስክ ለመሳተፍ የአክሲዮን የሚቋቋሙ ድርጅቶችም አዳዲስ አክሲዮኖችን አቅርበው በመሸጥ ወደ ሥራ ሊገቡ ይችላሉ። የእነዚህ ኩባንያዎች መስፋፋትና አዳዲስ ስራዎችን መጀመር በቀጥታ ለዜጎች የሥራ እድል እንዲከፈት ባሉበት አካባቢ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቀሴው እንዲጨምር የሚያደርግ ይሆናል ነው ያሉት።
የአክሲዮን ገበያ ከመጀመሩ በፊት ዜጎች ያላቸውን ገንዘብ ጥቅም ላይ የሚያውሉበት መንገድ ቁጠባ ማስቀመጥ ወይንም መሬት ገዝቶ እንደማስቀመጥ የመሰሉ አማራጮችን መጠቀም ነበር። አሁን ግን በካፒታል ገበያው ውስጥ መሳተፍ ሲጀምሩ ከሌላው በተለየ የትርፍ ተካፋይ በመሆንና አክሲዮናቸውን አትርፈው በመሸጥ ጥቅም የሚያገኙበት አጋጣሚ ይፈጠራል። በዚህ አካሄድ የሚገኘው ትርፍ ዳጎስ ያለ ስለሚሆን ተጠቃሚነቱ የጎላ እንደሚሆን ምሁሩ አብራርተዋል።
ይህም ሆኖ እንደ ተግዳሮት የሚነሳው የአክሲዮን ገበያ አዲስ ጀማሪ እንደመሆናችን በተወሰነ ደረጃ የእውቀት ክፍተት ይኖራል ተብሎ ይታሰባል። ለዚህም በኩባንያዎች እና የኢትዮጵያ የመዋእለ ነዋዮች ገበያ በኩል ትምህርት መስጠት ይቻላል። የአክሲዮን ገበያ ተለዋወጭ ባህሪ አለው። የአክሲዮን ገበያ ዋጋ የሚወሰነው በተቋም፣ በሀገር አቀፍ ደረጃና በዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት የኢኮኖሚ መረጋጋት ላይፈጥር ይችላል። ይህ ባደጉት ሀገራትም የሚታይ ሲሆን እንደ አንድ ተግዳሮት የሚታይ እንደሆነ ነው የጠቀሱት።
ይህም የኢኮኖሚ ፖሊሲውን እያሳደጉ እያስተካከሉ በመሄድ፤ በየወቅቱ ጥሩ ጥሩ ህግ በማውጣትና ግንዛቤ በመፍጠር መቆጣጠር እንደሚችል ጠቁመዋል።
የአክሲዮን ገበያ ገንዘብን በሀገር ውስጥ ካሉ ብቻ ሳይሆን በሌላ ሀገር ካሉ ዜጎችም ጭምር መሰብሰብ የሚያስችል የገበያ ሥርዓት በመሆኑ ገበያው በሀገራችን መከፈቱ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ባለሀብቶችም ገንዘባቸውን በገበያው ላይ ፈሰስ እንዲያደርጉ እድል ይሰጣል። እንደ ሀገር የፋይናንስ እጥረት ያለብን እንደ መሆናችን ገበያው የተበጣጠሱ ገንዘቦች ተሰባስበው የተሻለ አቅም እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።ይህም የዜጎችንም ሆነ የሀገር ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ሲሉ ምሁራኑ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም