በአፋር ክልል በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች ድጋፍ እየተደረገ ነው

ሰመራ፡- በአፋር ክልል በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች የመከላከያ ሠራዊት እና የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገለጹ።

የዱለቻ ወረዳ ሰገንቶ ቀበሌ ሊቀመንበር ብቶ ፎንቴ እንደተናገሩት፤ ሀገር መከላከያ 10 ኦራሎችን መድቦ ከትናንት ጀምሮ የመሬት መንቀጥቀጡ አደጋ የደቀነባቸውን ወገኖች ወደ ሌሎች ቦታዎች በማጓጓዝ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው። በቦቴ መኪና የመጠጥ ውሃ በማቅረብ ላይም ይገኛል።

በመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተው ፍንዳታ ምክንያት የተፈናቀሉ ከአራት ሺህ በላይ የቀበሌው ነዋሪዎች በሁለት የመጠለያ ጣቢያዎች መስፈራቸውን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፤ በዳይኢዶ ጣቢያ ሁለት ሺህ 984 አባወራዎች እንዲሁም ፎሮይታ ጣቢያ አንድ ሺህ 400 አባወራዎች በአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን አስቸኳይ የነፍስ አድን እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የወታደራዊ ተሽከርካሪ አሽከርካሪ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አሰልጣኝ ሃምሳ አለቃ አባይነህ ባጬ የመሬት መንቀጥቀጡን ሸሽተው አካባቢያቸውን ለቅቀው ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያ ቦታ የሚጓዙ ሰዎችን ንብረትና ህይወት ለማዳን ርብርብ እያደረግን ነው ብለዋል።

አላማችን ሕዝብና ሀገርን ማገልገል ነው። በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት የተጎዱ እና ስጋት የተደቀነባቸውን ወገኖቻችንን በመርዳታችን ደስታ ይሰማናል ያሉት ሃምሳ አለቃ ዓባይነህ፤ ማህበረሰቡ መከላከያ እያደረገ ባለው ድጋፍ ደስተኛ መሆኑን እየገለፀልን ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።

የሀገር ሽማግሌ እና የጎሳ መሪው መሀመድ አህመድ በበኩላቸው፤ መከላከያ በኦራል መኪኖች ንብረታችንን ጭምር በማጓጓዝ ከአደጋው ቀጣና እንድንርቅ በማድረግ ታድጎናል ብለዋል።

በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተፈናቀልነው ወገኖች ተመዝግበን በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሸራ ምንጣፍ፣ ድንኳን የስንዴ ዱቄት፣ መኮሮኒ፣ የተለያዩ የምግብ አይነቶች ድጋፍ ተደርጎልናል ያሉት የጎሳ መሪው፤ “መንግሥት አስፈላጊውን ነገር እያደረገልን ነው። ወደፊትም ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

በተያያዘ ዜናም በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ መንገዶች እና የመኖሪያ መንደሮች የመሰንጠቅ አደጋ አጋጥሟቸዋል።ከአዋሽ አርባ ወደ ከሰም ስኳር ፋብሪካ የሚወስደው የአስፋልት መንገድ በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ዶሆ ቀበሌ በመሬት መንቀጥቀጡ ሰፋ ያለ ክፍተት ያለው መሰንጠቅ አጋጥሞቷል።

በመንገዱ የሚያልፉ ግመሎች እና ፍየሎች በመሰንጠቀ አደጋው የተፈጠረውን ክፍተት አይተው እንዳይደነብሩ በዛፍ ቅርንጫፍ የተሸፈነ ሲሆን፣ በመንገዱ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ክፍተቱ የሰፋውን የአስፋልቱን ስንጥቅ ክፍል በመሸሽ በዳር በኩል እያለፉ እንደሚገኙ ተመልክተናል።

ዋና መንገዱን የሚመግቡ የጠጠር መንገዶችም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሰፋፊ ስንጥቅ ይታይባቸዋል። ከመሬት መሰንጠቁ ጋር ተያይዞ የመሬት ስርገት በመኖሩም የተሰነጠቀው የመንገዶቹ ግራና ቀኝ ክፍል ከፍ እና ዝቅ ብሎ ይታያል።የመሬት መሰንጠቁ በመንደሮች ውስጥም በስፋት ተከስቷል። መኖሪያ ቤቶችም ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ቀበሌ አሊቤቴ መንደር ነዋሪ የሆኑት መንገሻ አሼቦ ሶስት ክፍል ያለው ቤታቸው ወለል ተሰነጣጥቋል፤ ግድግዳውም ፈራርሷል ብለዋል።

“26 ዓመታት ከባለቤቴ ጋር የኖርንበትና አምስት ልጆች የወለድንበት ቤቴ ታህሳስ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በጀመረውና ለአራት ቀናት በቀጠለው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ፈራርሷል” ያሉት አባወራው፣ የቤት ዕቃዎቻቸውን አውጥተው ኑሯቸውን ውጪ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የወረዳው አመራሮች መጥተው ጎብኝተውን ከጎናችሁ ነን ብለውናል ሲሉም አመልክተዋል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You