የቀጠርኳትን ወዳጄን ለመጠበቅ ከአንድ ካፌ ውስጥ ገብቼ ጥግ ተቀምጫለሁ። የምፈልገውን ነገር እንድታመጣልኝ አስተናጋጇን አዝዤ ከቦርሳዬ የሻጥኩትን የሥነ-ልቦና መጽሐፍ መቆያ እንዲሆነኝ ገለጥኩት።
“የሥነ ልቦና መጽሐፍትን ማንበብ ታዘወትራለህ ልበል?” አለች ሐረገወይን በስተጀርባዬ ቆማ በአለንጋ ጣቶቿ ፀጉሬን እያመሳቀለች። እኔን ምሰይ አልኳት ወንበር ከወሰደች በኋላ። እኔና ሐረገወይን ትውውቃችን የሚጀምረው ባስ ውስ ጥ ነው።
ሰዓት ደርሶ ከቢሮ ወጣሁና ወደ ፈረንሳይ በሚሄደው ባስ እንደገባሁ ከወንበር የተረፈው ሰው ሸንበቆ መስሎ ቆሟል። ከተሳፋሪው ጫጫታ ለመሸሽ የጆሮ ማዳመጫ ሰካሁና በእጅ ስልኬ የከፈትኩት ሬዲዮ ጣቢያ የማዲንጎ አፈወርቅን ‹አንች አይናማ› ዘፈን ያንቆረቁራል። ነፍስያዬ አብዝታ ትወደዋለችና ድምፄን ዘለግ አድርጌ ሙዚቃውን አብሬ አዜምኩት። ተሳፋሪው ከዳር እስከ ዳር ሲስቅብኝ ሐፍረት ተጭኖኝ በተለቀቀው ክፍት ወንበር ከጭልፊት እንዳመለጠች ጫጩት ተሸማቅቄ ቁጭ አልኩ። የዛሬዋ ወዳጄ ሐረገወይን ወንበር የተጋራኋት ተሳፋሪ እሷ ነበረችና “አሳፈሩህ አይደል? ግን እኮ ድምፅህ ያምራል” አለች ለሠላምታ በሚመስል ሁናቴ እጄን ይዛ። ይሄው ከዚያች ቀን ጀምሮ ትውውቃችን ጎምርቶ የልብ ወዳጅ ለመሆን በቃን።
የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችን ለመሳተፍ፣ ቴአትር ለማየት እልፍ መድረኮችን ታድመናል። አሁን ላይ ግን የተቀጣጠርነው ሲኒማ ቤት ለመሄድ ሳይሆን ‹የኖረ ምስጢሬን አጫውትሃለሁ› ስላለችኝ ምን ይሆን? የሚል ጥያቄ ሆዴን ሲቆርጠኝ ውሏል። ገና በትውውቃችን ማለዳ በውበቷ ተሸንፎ ልቤ ለትዳር ቢከጅላትም እሷ ግን እንደ በጋ ጉም ላይ ላዩን ታዘግማለች እንጂ ለትዝታ የሚተርፍ ለሕይወት የሚበጅ ማለፊያ ጊዜ አልሰጠችኝም።
እንዳው በደፈናው የልብ ወዳጅ ነን ልበል እንጂ እንደ አልፎ ሂያጅ ሰው ከቆጠርኳት ውዬ አድሬያለሁ። ይሁንና ‹ስትጠራኝ አቤት ስትልከኝ ወዴት› ማለቴ አልቀረም። ለመራቄ ምክንያት ስሜቴን ምን እንዳሻከረው ጠንቅቃ ታውቀዋለች። በጋራ ሕልም የምናይባቸው ምሽቶች አኩርፈው ፊት ሲነሱን ገላዋን እንዳላውቀው የሰፈረባት አይነ ቁራኛ አራስ ነብር ያደርጋታል። ችግሯን ደጋግሜ ብጠይቃትም በግልጽ ተወያይተን መፍትሔ ከመሻት ይልቅ እኔን መግፋት ምርጫዋ አድርጋ ለትዳር እንበቃ ዘንድ ያደረስነው ፀሎት ከደመና በታች ዋለ።
ታዲያ ዛሬ ‹የኖረ ምስጢሬን አጫውትሃለሁ› ስትል በፍቅራችን ዙሪያ ይሆን እንዴ?
አምሮብሻል ምን ተገኘ? አልኳት ጨዋታ ለመጀመር ያህል። “ትደርስበታለህ ምን አስቸኮለህ?” ብላ የያዘችውን ብርጭቆ ወደ አፏ እያስጠጋች በስስት አየችኝ። ሁለቴ ተጎንጭታ መልሳ እያኖረችው “ኩራት የሚያንቀው አንተን አየሁ፤ አሁንም ልብህ እንዳበጠ ነው አይደል?” አለችን። በነገር መርፌ ወግታ ስትይዘኝ ከመቅጽበት የትካዜ ውሽንፍር በአይኗ ስር ውልብ ሲል ተመለከትኩ። ዝምታዬ ንቀት እንደሚመስላት ባውቅም ይሁን ብዬ ተቀበልኩ እንጂ አልሞገትኳትም። ቁጣዋ ገንፍሎ ግንባሯ ላይ እየተነበበ “ላንተ ያለፈ ታሪክ ዋጋ የለውምን?” አለች እንደ ሽንኩርት በሚልጥ አስተያየት እየመረመረችኝ። ምን አድርግ ነው የምትይኝ? የማጠፋው ጊዜ አልተረፈኝምንና የምትነግሪኝ ሀሳብ ካለ ላድምጥሽ፣ አለበለዚያ ግን ብንሄድ ይሻላል አልኳት ንዴቴን ለመሸሸግ እየታገልኩ።
ዓመሌን ታውቀዋለችና እንደ እንዝርት ስትሾር ቆይታ የመጣችበትን ጉዳይ ለመናገር ከንፈሯን ስታላቅቅ እንባ ቀደማት። የቱንም ያህል ብታስከፊኝም ኀዘንሽን አልወድም ብያት ፍቃዷን ሳልጠይቅ ጉያዬ ውስጥ ቀበርኳት። ረጅም ደቂቃዎችን በመነፋረቅ ፈጀቻቸው። ወጀቡ ሲያልፍላት አይኖቿን አደራርቃ ከእቅፌ ሳትወጣ ተንሸራታ ተቀመጠች። ልቧን ልቤ እንዲያደምጠው ጋበዘችኝ። “ከመለያየታችን በፊት በነበረን የፍቅር ሕይወት ብዙ ጊዜ ስትቀጥረኝ እቀራለሁ። እራሴን በግድ አሳምኜ ብመጣም በልጅነት እድሜዬ የተፈጠረብኝ ጠባሳ መንፈሴን አጠልሽቶት አያሌ የፍቅር ሌሊቶችን ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሼባቸኋለሁ።
‹‹ምን እንደሆንኩ ልነግርህ አስብና ታሪኬን ሲያውቅ ቢተወኝስ? የሚለው ፍርሃቴ ሌላ ፍርሃት ወልዶ ለከፋ ጭንቀት ይዳርገኛል፤ አንተ ደግሞ ድብቅ ሴት ነሽ ካልወደድሽኝ ለምን ቀረብሽኝ? እያልክ ስትወቅሰኝ ከቀደመው በበለጠ በፀፀት ጅራፍ ተለበለብኩ። ይህን ጊዜ መላው ሲጠፋኝ የሥነ ልቦና ባለሙያ ሳማክር “ፓኒክ ዲስኦርደር” የሚባል በቀላሉ ሊድን የሚችል የሥነ ልቦና ችግር እንደያዘኝ ነገሩኝ። ምልክቱም አብሬህ ልተኛ ስል ፍርሀት ፍርሀት ይለኛል፣ ልቤን ይደክመኛል፣ ራሴን ያዞረኛል፣ ያቅለሸልሸኛል። ይህ ችግር የደረሰብኝን የመደፈር ሙከራ እያስታወሰ ሁሉንም ወንዶች አንድ አስመሰለብኝ። ዘመኔን በፀፀት አስገፋኝ፤ እናም ዛሬ የፈለኩህ ሐኪሞቹ “ጓደኛሽን ይዘሽው ነይ” ስላሉኝ አብረኸኝ እንድትሄድ ፍቃድህን ለመጠየቅ ነው›› ብላ ዓይን ዓይኔን አየችኝ።
“ከነፍሴ ታርቄ በፍቅር ልደር፣
ሰውኛ ጠባዬ በነበር ባይቀር። ”
እንዲል ጠቢቡ ከሰው ሚዛን ጎድዬ የተልባ ስፍር ሆኜ ባስቸግራት የኀዘኗን ፍም አምቃ ብቻዋን ከሰለች እንጂ እኔ ላይ ፊቷን አላጠቆረችም።
“ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” ሆነብኝና ሰው ለራበው ስሜቷ ቁብ ሳልሰጥ ለገዛ ፍላጎቴ ተገዝቼ በቁስሏ እንጨት እየሰደድኩ ችግራን አባስኩት። “አንድ ጊዜ ከመናገር ሦስት ጊዜ ማሰብ” የሚለውን ብሂል ስቼ ከወሰንኩ በኋላ እንወያይ በሚል፣ ጥያት ሄጄ እንድትመለስ የማባብል ግልብ ወዳጇ ወትሮስ ከፀፀት በቀር ምን ላተርፍ ኖሯል? ማሪኝ ሐረገወይን… ከደም የወፈረ እንባሽ መከራሽ ጥልቅ መሆኑን ይነግረኛል። ኀዘንሽ ሐፍረቴን አክብዶት እንደጎባጣ አሽከር አስጎንብሶኛልና ይቅርታሽን ሰጥተሽኝ ለዘላለም የፍቅርሽ ባሪያ እንድሆን ፍቀጅልኝ? ጉልበቷ ስር ተንበርክኬ እየተንሰቀሰቅሁ ስማፀናት በእጆቿ አንገቴን አቅፋ አቃናችኝ። ከምንጭ ውሃ የጠራ ምሕረቷን አላብሳኝ ከሠላም አዝመራ አቋደሰችኝ። ለካስ የይቅርታ ሸክም ክብደቱ የሚሰማው ሐፍረት ለተከናነበው በዳይ ነው፤ የተበደለማ ሕሊናው መልካም ፍሬ ተቀብላ በበረከት አትረፍርፋ እንደምትቸር ለምለም መሬት ነው። ውል አልባ እና ልጓሙ መረን የለቀቀ ስሜቴን አርቄ፣ ስክነት የራቀው ስህተቴን በንስሐ አጠብኩና እራሴን ልሰጣት ቃል ገብቼ ሂሳብ ከፍለን ወጣን። በቂ መረጃ ካለማግኘታቸው የተነሳ ስንት እህቶቻችን በዚህ የሥነ ልቦና ችግር (ፓኒክ ዲስኦርደር) ተጠቅተው ይሆን? ቤት ይቁጠራቸው…
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም