አዲስ አበባ፡- የሕክምና አገልግሎትን ለማዘመን በ110 የህክምና ተቋማት የዲጂታል የኤሌክትሮኒክስ ሜዲካል ሪከርድ ሥርዓት ትግበራ መጀመሩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የዲጂታል ጤና መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገመችስ መልካ እንደገለጹት፤ ይህን የዲጂታል ሥርዓት መተግበር ከጀመሩት 110 የመንግሥት ህክምና ተቋማት ውስጥ 20ዎቹ ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም ከወረቀት ነፃ የሆነ አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ተቋማትን ቁጥር ወደ መቶ ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በህክምና ተቋማቱ በተጀመረው አገልግሎትን በዲጂታል የመስጠት ሥርዓት ጥሩ ውጤት መታየቱን የገለጹት አቶ ገመችስ፤ በዚህም ተከታታይ ሕክምና ያላቸው ታካሚዎች መረጃቸው በተገቢው መልኩ መያዝ በመቻሉ የተሻለ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዲጂታል አገልግሎት መስጠት የጀመሩ የህክምና ተቋማትም የተሻለ ውጤት እያመስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በተለይም ከገቢ አንጻር ከዚህ በፊት ከሚያስገቡት የተሻለ እንደሆነና ከመድኃኒት አጠቃቀም አንጻርም መሻሻል መታየቱን ተናግረዋል።
እንደ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ሆስፒታሎች የቆዩ በመሆናቸው የኔትዎርክ መስመር አልተዘረጋላቸውም። በዚህም የውስጥ ኔትዎርክ መስመር ዝርጋታ ሥራ ለማከናወን በርካታ ግብአት በተጨማሪ ሥራው በርካታ ኮምፒውተር ስለሚፈልግ ሁሉንም ተቋማት ዲጂታላይዝ ማድረግ ከባድ ነው። ያም ሆኖ 110 የህክምና ተቋማትን በመለየት በቅድሚያ ዲጂታላይዝ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል።
አቶ ገመቺስ ሲያብራሩ፤ በቅርቡ ከወረቀት ነጻ አገልግሎት እንዲሰጡ የታሰቡት 80 የህክምና ተቋሞች ሲሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ነጻ አገልግሎት ከመስጠታቸው በፊት በውስጣቸው የሥራ ክፍሎችን በመለየት ከወረቀት ነጻ የሆነውን አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል። ለዚህም በሂደት የሥራ ክፍሎቹ ቁጥር እየጨመሩ ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ነጻ የሆነ አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል ብለዋል።
የተቋማቱ አገልግሎት ከሦስት ወር እስከ ስድስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ከወረቀት ነጻ ወደ መሆን እንደሚሸጋገር የጠቆሙት አቶ ገመቺስ፣ ቀድመው ከወረቀት ነጻ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት 20 የህክምና ተቋማት ለሌሎች ሞዴል በመሆን ልምድ እንደሚያጋሩ ተናግረዋል። ሁሉም ተቋማቱ አስፈላጊውን ግብአት ቢያሟላ በአጭር ጊዜ ከወረቅት ነጻ አገልግሎት መስጠት ይቻል እንደነበርም አብራርተዋል።
ሥራ አስፈፃሚው፤ አብዛኞቹ የህክምና ተቋማት ላይ በዘርፉ ከፍተኛ የሰው ኃይል ክፍተት በመኖሩ ችግሩን ለመቅረፍ የጤና ሚኒስቴርና የክልል ጤና ቢሮ ባለሙያዎች የህክምና ተቋማቱን እየደገፉ መሆኑንም ተናግረዋል። የሰው ኃይል እጥረት የግብአት አለመሟላት፣ የኮምፒውተሮች ዋጋ ውድ መሆንና የኔትዎርክ እቃዎች ዋጋ መጨመር በተፈለገው ፍጥነት ሥራው እንዳይቀላጠፍ አድርጓልም ብለዋል።
በጤና ተቋማት ዲጂታል አገልግሎት የመስጠት ሥራ ከሌሎች ተቋማት እንደሚለይ የሚናገሩት አቶ ገመችስ፤ በጤና ተቋማቱ በቁጥርና በባህሪ የተለያዩ በርካታ ማሽኖች መኖራቸው ሥራውን እንደሚያከብደው ጠቁመዋል። እያንዳንዱ ማሽን ላይ ጊዜ ተወስዶ ወደ ሥርዓቱ የማስገባት ሥራ እንደሚሰራ ገልጸውም፤ በተቋማቱ የሚገኙ የህሙማንን ካርድ ወደ ዲጂታል ሥርዓቱ ማምጣት ግን ጊዜ ይወስዳል ብለዋል።
እስካሁን በየህክምና ተቋማቱ የኔትዎርክ ሰርቨር እየተገዛ መረጃው ሲከማች እንደነበር የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፤ ሥርዓቱን ማእከላዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም ተቋማቱ የተሻለ ኔትወርክ ስለሚኖራቸው የመቆራረጡ ሁኔታ ይቀንሳል። የተሻለ የኔትዎርክ ጥራት ካለ ደግሞ አሁን ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙ የህክምና ተቋማት የሚታየውን የሲስተም መቆራረጥ እንደሚያሻሽል ገልጸዋል። ለዚህም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋርም በጋራ እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም