አዲስ አበባ ፦ ባለፉት አምስት ወራት ከዳያስፖራው ከሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ፡፡ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ያለፉት አምስት ወራት ከዲያስፖራው የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት ሆኗል።የዳያስፖራው ተሳትፎ እንዲያድግ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያደረገው ማሻሻያ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው። የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲመራ መደረጉ በአንድ በኩል የወጪ ንግድን አሻሽሏል። በሌላ በኩል በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ይገባ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በባንኮች በኩል እንዲመጣ ማስቻሉ ትልቅ ጥቅም እያስገኘ መሆኑን አመልክተዋል።
እስከ 100 ቢሊዮን ብር የሚገመት ለቤት ግንባታ የሚሆን ብድር በባንኮች መዘጋጀቱን ብሔራዊ ባንክ ማሳወቁ አውስተው፤ ይህን ተከትሎም ብድሩን ለማግኘት ቅድመ ቁጠባ ስለሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሬ አካውንት የሚከፍቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ በብር ሲመነዘር ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ እየሆነ ነው ያሉት አምባሳደር ፍጹም፤ በተጨማሪ በዶላር አስቀምጦ በዶላር ማውጣት የሚቻልበት ሥርዓት መዘርጋቱም ለውጤቱ አንዱ ማበረታቻ ሆኗል። ከዳያስፖራው የሚገኘው ገቢ ከመስከረም ወር ጀምሮ በወጪ ንግዱ ላይ እንደታየው ሁሉ ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበበት እንደሚገኘ ተናግረዋል።
በቀጣይ በተለይም በገናና በጥምቀት በዓላት ወደ ሀገር ቤት ከሚገቡት ሆነ ውጭ ሆነው ከሚልኩት ዳያስፖራዎችም ከፍተኛ ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በእነዚህና ተያያዥ ምክንያቶች አጠቃላይ የዳያስፖራው ኢንቨስትመንት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተው፤ ይህም ሆኖ ከዳያስፖራው የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ አቅም ያለ በመሆኑ በቀጣይ ብዙ የሚጠበቁ ስራዎች እንደሚኖሩም አመልክተዋል።
እንደ አምባሳደር ፍጹም ገለጻ፤ ከዚህ ቀደም በርካታ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ገንዘብ ወደ ሀገር ቤት በመላክ በጓደኛ፣ በቤተሰብና በወኪል ለማሰራት ሲሞክር ለተለያዩ ችግሮች ሲዳረግ ቆይቷል። የንግድ ሥርዓቱ ለዚህ አመቺ ስላልነበር በሀገር ውስጥ ኢንቨስት ከማድረግ የሚቆጠቡም ብዙዎች ነበሩ። አሁን ግን የካፒታል ገበያ ሊጀመር መሆኑም ዘርፉ በብዙዎች ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ሆኗል።
ለምሳሌ ዲያስፖራው በሀገር ቤት መኖሪያ ቤት ለማስገንባት በተለያዩ ሪል ስቴቶች መዋጮ ያወጡ ቢኖሩም፤ በወቅቱ የተወሰኑት ሪልስቴቶች ያስረከቡ እንዳሉ ሁሉ በርካቶችን ለችግር የዳረጉ ጉዳዮችም እንደነበር አምባሳደሩ አውስተው፤ አሁን የካፒታል ገበያ መቋቋም ተገማችና ታማኝ የሆነ ሥርዓት እንዲኖር ስለሚያስችል ዳያስፖራው ለራሱም ለሀገሪቷም እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግበት በር የሚከፍትለት ይሆናል ብለዋል።
ዳያስፖራው ማህበረሰብ ሀገሩን በልቡ ይዞ የሚኖር ነው ያሉት አምባሳደር ፍጹም፤ ባገኙት አጋጣሚ ወደ ሀገር ቤት በመምጣት ጊዜ የሚያሳልፉት በርካቶች ናቸው። በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀገር ቤት መምጣት ያልቻሉትም ቤተሰብ ከመርዳት ባለፈ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚደግፉት ብዙዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዲያስፖራው በሀገሩ ልማት ቀጥታ ከመሳተፍ ባለፈም በበጎ አድራጎት ስራም የሚሳተፍ መሆኑን አመልክተው፤ በቅርቡ ከአውሮፓ ዲያስፖራዎች ለመቄዶንያ ድጋፍ ማድረጋቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም