የኢትዮጵያ ክለቦች የአጭር፣ መካከለኛ፣ የ3000 ሜትር መሰናክል፣ የርምጃ እና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እየተካሄደ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዛል። የአትሌቲክስ ክለቦች በተለያዩ ውድድሮች አቋማቸውን የሚለኩበት ይህ ዓመታዊ ሻምፒዮና በፉክክር ታጅቦ የፍፃሜና የማጣሪያ ውድድሮችን እያስተናገደ የሚገኝ ሲሆን ነገ በሚደረጉ በርካታ የፍፃሜ ፉክክሮች ይጠናቀቃል፡፡
በሻምፒዮናው ሁለተኛ ቀኑ ውሎ በተለያዩ ፉክክሮች የፍፃሜ ውድድሮች የተከናወኑ ሲሆን፣ በወንዶች የዲስከስ ውርወራ ቴድሮስ ቦጋለ ከመቻል 44.80 ሜትር በመወርወር አሸናፊ ሆኗል። 44.79 ሜትር እና 44.04 ሜትር መወርወር የቻሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቶች ገበየሁ ገብረየስና ደሱ ወልደሰንበት ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል። በተመሳሳይ በሴቶች ዲስከስ ውርወራ የፍፃሜ ውድድር ዓለሚቱ ተክለሥላሴ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 44.12 ሜትር በመወርወር አሸናፊ ስትሆን፣ የኔሰው ያረጋል ከተመሳሳይ ክለብ 43.24 ሜትር ወርውራ ሁለተኛ ሆናለች። ዙርጋ ኡስማን ደግሞ ከመቻል 42.52 ሜትር ወርውራ የነሐስ ሜዳሊያውን ደረጃ ይዛለች፡፡
ሌላው ፍፃሜ ያገኘው ውድድር የወንዶች ርዝመት ዝላይ ሲሆን፣ ቡሌ መላኩ ከሸገር ከተማ 7.96 ሜትር በመዝለል ባለድል ሆኗል። 7.83 ሜትር መዝለል የቻለው የመቻል አትሌት ድሪባ ግርማ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ የአዳማ ከተማው በቀለ ጅሎ ሦስተኛ ሆኖ ፈፅሟል። የዘለለው ርዝመትም 7.46 ሜትር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በተለያዩ የአጭርና መካከለኛ ርቀት ውድድሮች የፍፃሜ ፉክክሮች የተከናወኑ ሲሆን በሴቶች 100 ሜትር መሰናክል እመቤት ተከተል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊ ያደረጋትን 13.95 ሰዓት አስመዝግባለች። የሸገር ከተማዋ መስከረም ግዛው ውድድሩን 14.26 ሰዓት በማጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ስኬት ጌታሁን ከመቻል በ14.55 ቀጣዩን ደረጃ ይዛ ፈፅማለች። በተመሳሳይ ፍፃሜ ባገኘው የወንዶች 110 ሜትር መሰናክል ውድድር ዮሐንስ ጎሹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 14.15 በማጠናቀቅ ሲያሸንፍ፣ ጌታሁን ታደሰ ከሸገር ከተማ በ14.30 ሰዓት ሁለተኛና ሚኪያስ ውቤ ከተንታ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ በ14.35 ሰዓት ሦስተኛ ሆናል፡፡
በ400 ሜትር የወንዶች ፍፃሜ ውድድር አዲሱ ዓለምነህ ከመቻል ፉክክሩን 47.05 ሰዓት በማጠናቀቅ ቀዳሚ ሲሆን፣ ኒያል ኛክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ47.30 ሁለተኛ፣ የሮሰን ግርማ ከሸገር ከተማ 47.62 ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል። በተመሳሳይ ርቀት በሴቶች የፍፃሜ ውድድር ራሔል ተስፋዬ ከመቻል 53.30 ሰዓት አስመዝግባ ስታሸንፍ፣ ዱርሲቲ በርማ ከሸገር ከተማ በ53.69 ሰዓት ሁለተኛና ሹሬ ጃርሶ ከአዳማ ከተማ በ54.02 ሰዓት ሦስተኛ ሆኗል።
በመካከለኛ ርቀት ፍፃሜ ባገኘው የሴቶች 800 ሜትር ውድድር የፓሪስ ኦሊምፒክ የርቀቱ የብር ሜዳሊያ አሸናፊና የወቅቱ የቤት ውስጥ የዓለም ሻምፒዮና ባለድሏ አትሌት ፅጌ ዱግማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊ ሆናለች። ርቀቱን ያጠናቀቀችበት ሰዓትም 1:59.60 ሆኖ ተመዝግቧል። ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ንግሥት ጌታቸው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 2:00.04 ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች። አስቴር አሬሬ ኦሮሚያ ኮንስትራክሽን በ2:02.42 ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያውን ወስዳለች። በተመሳሳይ በወንዶች 800 ሜትር ፍፃሜ ዮሐንስ ተፈሪ ኢኮስኮን ባለድል ሲያደርግ ያጠናቀቀበት ሰዓትም 1.47.79 ሆኖ ተመዝግቧል። ሞርሲሞድ ካሣሁን ደግሞ ለሸገር ከተማ በ1.47.99 ሰዓት የብር ሜዳሊያ አስመዝግቧል። የመቻሉ ዮብሰን ብሩ በ1.48.25 ሰዓት የነሐስ ባለቤት ነው፡፡
በውድድሩ 21 ክለቦች፣ 2 ከማሠልጠኛ ማዕከላት፣ 1 ከአካዳሚ በአጠቃላይ 24 ተቋማት 331 ሴት ፣416 ወንድ በድምሩ 747 አትሌቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ከታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮና ነገ በተለያዩ ውድድሮች በሚደረጉ የፍፃሜ ፉክክሮች እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም