የአፍሪካ የነጻነት ጉዞ ከ“ፓን አፍሪካ” እስከ “በቃ” የመላ አፍሪካ(ፓን አፍሪካኒዝም) ንቅናቄ ጥቁር የሰው ዘርን በተመለከተ በነጮች ዘንድ የነበረውን የተዛባ የበላይነት አስተሳሰብ ለመቀየር፣ ተፈጥሮ የነበረውን ኢፍትሐዊነት ለማስተካከልና በአጠቃላይ በመላው ዓለም በሚኖሩ ነጮችና ጥቁሮች መካከል እኩልነትን ለመፍጠር ያለመ የቀደምት አፍሪካውያን የፍትሕና የእኩልነት ሁለንተናዊ ትግል ነው::
በነጮች የተሳሳተ የበላይነት እሳቤና እብሪት ምክንያት ለዘመናት በቅኝ አገዛዝና በጭቆና መዳፍ ሥር ሆነው የኖሩት ጥቁሮች ጥንታዊ ሥልጣኔያቸውን መነጠቃቸው የገባቸው ቀደምት አፍሪካውያን አባቶች ከዚህ ቅኝ አገዛዝና ጭቆና ተላቀው ወደ ቀደመ ሥልጣኔያቸውና ማንነታቸው ለመመለስ በመላው ዓለም የሚኖሩ አፍሪካዊያንና ጥቁሮች አንድ መሆን አለባቸው በሚል መሪ ሃሳብ ነበር እንቅስቃሴውን የጀመሩት:: ለዚህም አፍሪካዊያን ከቅኝ ግዛት፣ ከጭቆናና ከባርነት ተላቀው ነጻነታቸውን መቀዳጀትና ችግሮቻቸውን ሁሉ አስወግደው በሚገባቸው ልክ ጥቅማቸውን አስከብረው መኖር የሚችሉት መከፋፈልንና መለያየትን አጥብበው አንድነት ሲፈጥሩ ብቻ ነው፤ ለዚህም የተባበረች አንዲት አፍሪካን መፍጠር አለባቸው በሚል ባደረጉት አስደናቂ ትግል በርካታ ድሎችን አስመዝግበዋል::
በመሆኑም ባለፉት መቶ ዓመታት የአፍሪካዊያንን ታሪክ፣ ባህል፣ መንፈሳዊና ሳይንሳዊ ግኝቶችን በማጣመር ፀረ ቅኝ አገዛዝ፣ በፀረ ባርነትና በፀረ ዘረኝነት ላይ የተደረጉ ተጋድሎዎችና የተመዘገቡ ድሎች የዚሁ የፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና ውጤቶች ናቸው:: የአፍሪካ ኅብረት፣ የፓን አፍሪካ ፓርላማና የፓን አፍሪካን ኮንግረስ የንቅናቄው ጉምቱ ተቋማዊ መገለጫዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው::
የአፍሪካዊ አንድነት፣ ድልና ነጻነት መሠረቱ ኢትዮጵያዊነት
የመጀመሪያው የጋና ፕሬዝዳንት ክዋሜ ንክሩማህ በአፍሪካ አንድነት ላይ ፅኑ ዕምነት የነበራቸውና በዚህም በመላው ዓለም የሚኖሩ አፍሪካውያን ቅኝ አገዛዝን እና ዘረኝነትን በመቃወም በጋራ በአንድነት እንዲቆሙና ለነጻነታቸው እንዲታገሉ በማድረግ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ ህያው አባት ተደርገው ይወሰዳሉ:: ንክሩማህን ጨምሮ ሌሎችም ቀደምት ፓን አፍሪካን አቀንቃኞች ነጻዋንና ታሪካዊቷን አገር የትግላቸው ሁሉ መነሻ አድርገው ይገልጻሉ::
በጣሊያን ከተደረገባት የአምስት ዓመታት ወረራ በቀር ለሦስት ሺዓመታት ነጻነቷን አስጠብቃ በክብር የኖረችው ኢትዮጵያ ለዓመታት በአውሮፓውያን ኢምፔሪያሊስቶች ቅኝ አገዛዝ ሥር ሆነው በባርነት ይማቅቁ ለነበሩ ሌሎች አፍሪካውን በጨለማው ዘመን ውስጥ አሾልከው መጭውን ብሩህ ዘመን የሚያጮልቁባት የነጻነታቸው የአጥቢያ ኮከብ ሆና አገልግላለች:: እንደነ ክዋሜ ንክሩማ ለመሳሰሉ ቀደምት የነጻነት ታጋዮችና የአፍሪካዊ አንድነት ጽንሰ ሃሳብ አቀንቃኞች የህልማቸው መጸነሻ ማኅፀን የዓላማቸው ማቀጣጠያ ቆስቋሽ ኃይል ሆናላቸዋለች::
የአፍሪካውያን የውጭ ፖሊሲ ከአፍሪካውያን ድል በስተጀርባ
በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አማካኝነት አፍሪካን ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ ለማላቀቅና ነጻ ለማውጣት በመላው አፍሪካ ሲደረግ የነበረው የነጻነት ትግል እስከ 1949 ዓ.ም ተጠናክሮ በመቀጠል ግብጽን፣ሱዳንን፣ ቱኒዝያን፣ ሞሮኮን፣ ሊቢያንና ላይቬሪያን ነጻ አውጥቷል:: የኛዋ ኢትዮጵያ ዕድሜ ሁሌም በነጻነት ለሚጠብቋት ልጆቿ በዘመቻ አፍሪካ ቅርምት የምዕራባውያን የቅኝ ግዛት ወረራ ዘመንም ነጻ ነበረች:: በመጋቢት መጀመሪያ 1949 ዓ.ም ደግሞ የክዋሜ ንክሩማዋ ጋና ነጻነቷን ተቀዳጀች:: እናም በአፍሪካ ፍቅር የተነደፉት ዝነኛው ፓን አፍሪካኒስት የጋና መሪ ክዋመሜ ንክሩማህ ከዓመት በኋላ በሚያዚያ 1950 ዓ.ም አክራ ላይ ነጻ የወጡ የአፍሪካ ወንድሞቻቸውን ስብሰባ ጠሩ::
በዚያም ንክሩማ የፓን አፍሪካን ንቅናቄ ከፍ ወዳለ ታሪክ ቀያሪ ምዕራፍ የሚያሸጋግር የአንድነት ሚሳኤልን አስወነጨፉ:: ነጻ ወጡ የአፍሪካ አገራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውን በድጋሜ እንዲያጤኑና ከአፍሪካውያን ጥቅም አንጻር መልሰው እንዲከልሱ ሃሳብ አቀረቡ::
አፍሪካውያንም ተስማሙ:: ነጻ ያልወጡ የአፍሪካ አገራትንም ነጻ እንዲወጡ ሁለንተናዊ ትብብር ለማድረግና አጠቃላይ የአፍሪካ አህጉርን ከምዕራባውያን ኢምፔሪያሊስቶች ቅኝ ግዛት ነጻ ለማውጣት በአፍሪካዊነት መንፈስ አንድ ላይ ለመቆም በድጋሚ ቃል ኪዳናቸውን ለማደስ ተማማሉ:: በዚህም የመጀመሪያው የመላ አፍሪካ ሕዝቦች ጉባኤ ተካሄደ::
የጉባኤው መሪ ሃሳብም እነሆ ዛሬ ከስድሳ አራት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያውያን የፀረ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ማቀጣጠያ ሆኖ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው አፍሪካ ነጻነቷን ማግኘት አለባት፤ “ከአፍሪካ ላይ እጃችሁን አንሱ” የሚል ሆነ:: በመሆኑም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን በተመለከተ የበለጠ ሥር ነቀል አካሄድን ይከተሉ የነበሩ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት በ1961 በሞሮኮዋ ካዛብላንካ ከተማ ተሰባስበው የካዛብላንካ ቻርተር የሚባለውን ስምምነት አጸደቁ::
ይህ ቡድን በዋነኝነት የክዋሜ ንክሩማዋን ጋና፣ በፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ የምትመራውን ጊኒንና የገማል አብዱልናስሯን ግብፅ ያቀፈ ነበር:: በሌላ በኩል በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የምዕራባውያን ደጋፊ የነበሩትና የአፍሪካ አንድነትን ጉዳይ በጥንቃቄ የሚመለቱት ወግ አጥባቂ የአፍሪካ አገራት ከግንቦት 8 እስከ 12 1961 በላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞኖሮቪያ ተሰብስበው የሞኖሮቪያ ቡድን መሰረቱ:: በመሆኑም የአፍሪካ አንድነትን በተመለከተ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ልዩነት ተፈጠረ::
የልዩነቱ ዋነኛ መንስኤም የመጀመሪያዎቹ የካዛብላንካ ቡድን አገራት ሁሉም አገራት ተዋህደው አንድ የአፍሪካ መንግስት ሊኖ ይገባል የሚል አቋም የሚያራምዱ ሲሆን በተቃራኒው የሞኖሮቪያ ቡድን አገራት ደግሞ እያንዳንዱ ሉዓላዊ አገር እንዳለ ሆኖ በጋራ ጉዳዮች ላይ ብቻ አብሮ መስራት ይገባል የሚል አቋም ያላቸው በመሆኑ ነበር:: የታንዛኒያውን ጁሊየስ ኔሬሬ የመሳሰሉ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ደግሞ ከሁለቱም ወገን ያልሆነ ገለልተኛ አቋምን ያራምዱ ነበር::
ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኒሬሬ ምንም እንኳን የአፍሪካን አንድነት በሚመለከት ባላቸው ስር ነቀል አቋም ከክዋሜ ንክሩማህ ጋር የሚመሳሰሉ ቢሆንም አንድ የአፍሪካ መንግስት ከመመስረቱ አስቀድሞ ግን በአገራት መካከል ቀጠናዊ አንድነት ሊኖር ይገባል የሚል ዕምነት ነበራቸው:: በመሆኑም አንድ የአፍሪካ መንግስትን ለማቋቋም በነ ንክሩማህ የቀረበው ጥሪ ገና ከመጀመሪያው ውድቅ ተደረገባቸው:: ከትንሽ ቆይታ በኋላ የንክሩማህ ሃሳብ ከአንዳንድ የካዛብላንካ ቡድን አባል አገራት ሳይቀር ተቃውሞ ገጠመው::
በመጨረሻም “ከተፈሪ መክረው” እንዲል ጉምቱው የጥበብ ሰው ክቡር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በሌላኛው ዕውቅ ፓን አፍሪካኒስት መሪና ለአፍሪካ አንድነት ባደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ “የአፍሪካ አባት” እስከመባል ድረስ በበቁት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አስታራቂ ሃሳብ አማካኝነት በሁለቱ ቡድኖች መካከል የነበረው ልዩነት ወደ አንድ መጥቶ የአፍሪካውያን አንድነት ድርጅት ተመሠረተ::
አፍሪካውያን መሪዎች ያሰቡትን ያሳኩበት የአንድነት መድረክ
ትብብርንና አንድነትን መርሁ አድርጎ የተመሠረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተንሰራፍቶ ሕዝቦቿን የበይ ተመልካች አድርጎ ጥቁሯን ወርቃማ አህጉር ሲበዘብዝ የቆየውን የኢምፔሪያሊስቶች የግፍ አገዛዝ ለማስወገድ በተደረገው መራር የነጻነት ትግል ጉዞ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል:: እንደተጠበቀውም ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ለአፍሪካ ነጻነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ከቅኝ ግዛት የመውጣትና ነጻነታቸውን የማስመለስ የዘወትር አፍሪካውንን ህልም አሳክቷል::
በተለይም የነጭ ሰፋሪዎች በብዛት በነበሩባቸው እንደነ ደቡብ አፍሪካ በመሳሰሉ አገራት የነጻነት ትግሉ እጅግ መራራ የነበረ በመሆኑ በራስ ትግል ብቻ ነጻ መውጣት የሚታሰብ አልነበረም:: በደቡብ አፍሪካ የነጮች የበላይነትና በጥቁሮች ላይ ከፍተኛ ግፍን ይፈፅም የነበረውን የአፓርታይድ የዘር አገዛዝ በማስወገድና አገሪቱን ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ አላቅቆ ነጻነትን በማስገኘቱ ሂደት የአፍሪካውያን አንድነት ድርጅት ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቷል::
በዚህም ደቡብ አፍሪካ ከረጅም ጊዜ እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በ1994 ነጻነቷን መቀዳጀት ችላለች:: በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ(በዛሬዋ ዚምባብዌ)፣ በአንጎላ፣ በሞዛምቢክ፣ በጊኒቢሳው፣ በኬፕቨርድና በሳኦቶሚና ፕሪንስፕ የነጭ ሰፋሪዎች በብዛት የሰፈሩባቸውና በነበራቸው የኃይል የበላይነት ምክንያት በሃገራቱ ለረጅም ዓመታት ገንግኖ የቆየው የቅኝ ግዛት የብረት መዳፍ በአፍሪካውያን የተባበረ ክንድ እንዲሰባበር ድርጅቱ የማይተካ ሚና ተጫውቷል:: ለመሆኑ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረትና በድርጅቱ አማካኝነት ለተገኘው ከዚህ ሁሉ ድል ያለው ሚስጥር ምንድነው?
ፓን አፍሪካ ከንቅናቄነት ወደነቅናቂነት
እርግጥ ነው የፓን አፍሪካ ንቅናቄ ከወጣቶች እስከ ሴቶች፣ ከምሁራንና ታዋቂ ሰዎች እስከ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የነበሩ መሪዎችና ፖለቲከኞች፤ ከአፍሪካ እስከ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ ካሪቢያንና ደቡብ አሜሪካ በመላው ዓለም የሚኖሩ የአፍሪካ ተቆርቋሪ አፍሪካውያን የመሩትና የተሳተፉበት ግሩም ድንቅ አፍሪካዊ የአንድነት የንቅናቄ መንፈስ ነው::
ጥቁር አፍሪካዊው ፈላስፋ ማርከስ ጋርቬይ፣ ጥቁር አሜሪካዊው ማልኮም ኤክስ፣ እንዲሁም ደግሞ ዊሊያም ኤድዋርድ ቡርግሃርድ ዱ ቦይስ ከአፍሪካ ውጭ ዝነኛው ፓን አፍሪካኒስት የመጀመሪያው የጋና ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴና ሌሎችም በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የንቅናቄው አመንጪዎች ተደርገው ይወሰዳሉ::
ንቅናቄው ከተጀመረ በኋላም በአህጉሪቱ ውስጥ ለተገኙ ሁለንተናዊ ድሎችም መሠረት ነው:: ይሁን እንጂ ጥቁር ሕዝቦች በሚገኙባቸው የዓለም ክፍሎች ሁሉ የተቀጣጠለው የአፍሪካውያን የአንድነት መንፈስና የነጻነት ትግል ማራመጃ የነበረው የፓን አፍሪካ ንቅናቄ አብቦና ጎምርቶ ጫፍ ላይ የደረሰውና ከንቅናቄነት ወደነቅናቂነት የተሸጋገረው እንደ አፍሪካውያን አቆጣጠር ከ1949 ዓ.ም በኋላ መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ:: ምክንያቱ ደግሞ አፍሪካውያን የአገር መሪዎች በስፋት በመቀላቀላቸውና ከዚያ በፊት ያደርጉት የነበረውን ያልተቀናጀና ኢመደበኛ በሆነ መንገድ ሲያደርጉት የነበረውን ተሳትፎ የበለጠ በማጠናከርና ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር ትግሉ ከሕዝባዊ ንቅናቄነት ወደ ፖለቲካ አቋምነትና መንግሥታዊ ተቋምነት እንዲሸጋገር ስላደረጉት ነው::
በዚህ ረገድ ስመ ጥሩው ፓን አፍሪካኒስት የመጀመሪያው የጋና ፕሬዚዳንት ኩዋሜ ንኩሩማህና የመጨረሻው የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የፓን አፍሪካን ንቅናቄ ታሪክ ከቀየሩት የአፍሪካ መሪዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ::
ለዚህ ደግሞ ሁለቱ የአፍሪካ መሪዎች፣ ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንኩሩማህ እና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መሪ ሚና የተጫወቱበትና እንደ አፍሪካውያን አቆጣጠር(አፍሪካውያን በኢትዮጵያውያን አማካኝነት የራሳቸው የሆነ ዘመን ኦቆጣጠር ስላላቸው ነው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ያላልኩት) ግንቦት 17 ቀን 1958 በአዲስ አበባ የተፈረመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር ህያው ምስክር ነው::
ይህ ዕለት በአፍሪካውን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበትና ሁሌም ሲታወስ የሚኖር ታላቅ የድል ቀን በመሆኑ ነው:: ምክንያቱም በተባበረ ክንድ እናት አፍሪካን ከምዕራባውያን ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት የሚያግዝ መተባበሪያ መድረክ ለመፍጠር የአፍሪካ መሪዎች ለዓመታት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ያፈራበት እና መላ አፍሪካውያንን የሚያስተባብር አንድ አህጉራዊ ድርጅት፤ የዛሬው የአፍሪካ ሕብረት የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ዕውን መሆን በመቻሉ ነው:: እናም ያች ቀን በሁሉም አፍሪካውያን ልብ ውስጥ በልዩ ፍቅር ተጽፋ ሁሌም በክብር ስትዘከር ትኖራለች::
ስለሆነም የአህጉሪቱን ህዝቦች በማስተባበር ቅኝ ግዛትን በማስወገድና ነጻነትን በማቀዳጀት ለአፍሪካያን ትልቅ ድልና ስኬት ያስመዘገበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዙፋን ወራሽ የሆነው የአፍሪካ ህብረትም ከነጻነት በኋላም ለዓመታት የቀጠለውን የአውሮፓውያን የእጅ ቅኝ ግዛት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ በማድረግና የእርስ በእርስ ትብብርን በማሳደግ ከዘመናዊ ቅኝ ግዛትና ከድህነት ነጻ የሆነች የበለጸገች አፍሪካን ዕውን በማድረግ የዙፋን አውራሹን ስኬት መድገም ይጠበቅበታል::
ለዚህ ደግሞ እንደጥንቱ ሁሉ ዛሬም አፍሪካውንንና መላ የጥቁር ሰው ዘሮችን ከምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ነጻ ለማውጣት “በቃ” ብላ ከተነሳችው የጥቁር ሕዝብ ነጻነት ፋና ወጊዋ ኢትዮጵያ ጋር አንድ ላይ አብሮ መቆም አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው::
አፍሪካውያን ይህን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ እንደ ሕዝብ በሚደረግ ኢመደበኛ ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን እንደ ቀደምቶቹ ፓን አፍሪካ አባቶቻቸውና የአፍሪካ አንድነት መሥራች አፍሪካዊ የነጻነት መሪዎቻቸው ዛሬም የአፍሪካ መሪዎች እንደ መንግሥት አንድ ላይ አብረው መቆምና መተባበር ሲችሉ ነው::
ሲቪል ተቆርቋሪዎችና የአፍሪካ ተሟጋቾች በተናጠል በሚያደርጉት ኢ መደበኛ ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን ልክ እንደ 1949ኙ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እንዳደረጉት ዛሬም የአፍሪካ መሪዎች በፖሊሲና በመንግሥታዊ ተቋሞቻቸው የእጅ አዙር ቅኝ ቅዛትን “በቃ” ማለት ሲችሉ ነው:: ያኔ ነው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አፍሪካ ከምዕራባውያን የዘመናት የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ነጻ የምትወጣው! እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና አፍሪካን ይባርክ!::
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26/2014