ብሔራዊ ምክክር ወይም ብሔራዊ መግባባት በኢትዮጵያ ዘመናትን ሲያስጠብቁ ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው ነው። በተለያየ መልኩ ተደጋግሞ የሚነሳው የብሔራዊ መግባባት ዓላማ የአገሪቷን ሠላም ለማረጋገጥ እና የሚፈለገውን ዕድገት ለመጎናፀፍ ዋነኛ መንገድ መሆኑ አያጠያይቅም። እንደኢትዮጵያ አይነት በብዙ ችግሮች የተተበተበች አገር እንቅፋቶቿን ለማለፍ በሰላማዊ መንገድ መነጋገር እና የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ባህል ማድረግ አማራጭ የሌለው ነው። አማራጭ የሌለው ብቻ ሳይሆን ኪሳራውም ምንም ሊባል የሚችል በመሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን አጥብቀው የሚሹት አጀንዳ ሆኗል። በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ በአገርም ሆነ በክልል፣ በዞንም ሆነ በወረዳ ደረጃ ሳይቀር ባለፉት ጊዜያት ለተፈጠሩት፤ አሁንም እየተፈጠሩ ላሉት ችግሮች ተነጋግሮ ለመፍታት እና ስምምነት ላይ ለመድረስ መድረክ ማመቻቸት የግድ ነው።
አገራዊ ምክክር ሲባል ሰፋፊ ጥያቄዎች የሚመለሱበት በዕለት ተነጋግሮ መፍታት ሳይሆን ወራትን የፈጀ ጥልቅ ውይይት የሚካሔድበት ነው። በተለያየ ጥግ ያሉ ግለሰቦች እና አስተሳሰቦች በአንድ መድረክ ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ ጉዳዮቻቸውን የሚያቀርቡበት እና ወደ አንድ አቅጣጫ የሚሄዱበት በመሆኑ ሂደቱ እጅግ ከባድ እና አካሄዱም ውስብስብ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ምክክሩን በብልሃት፣ በሰላም እና ብዙሃኑን ባሳተፈ ተቀባይነት ባለው መልኩ ማጠናቀቅ ከተቻለ ውጤቱ የኢትዮጵያን ቀጣይ የብልጽግና ራዕይ ለማሳካት እንደሚቻል አያጠራጥርም። በጋራ የምክክር መድረኩ ሰፊ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው ከሚታሰቡት መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች አንደኞቹ ናቸው። በዚሁ በአገራዊ ምክክር መድረኩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ የቀድሞ የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና አሁን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሻዶ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ባንተይገኝ ታምራት በአገራዊ ምክክር ላይ ያላቸውን እምነት አስመልክቶ የገለፁልንን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወቃል። የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ሲነሳ የሚግባባው ማን ከማን ጋር ነው? ማን ከማን ተጣላ የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ለመሆኑ የእዚህ ምክክር ዓላማና ግብ ምንድነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ባንተይገኝ፡- በቅድሚያ የእዚህ የብሔራዊ ምክክር ጉዳይ ሲነሳ ‹‹ብሔራዊ መግባባት የተመሠረተው ምን ላይ ነው? ›› የሚለውን ማየት ተገቢ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት 27 እና 28 ዓመታት እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ የሚያግባቡ ነገሮች እንዳሉን ሁሉ የማንግባባባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። እነዚህ ውለው አድረው በተለይ የብሔር አደረጃጀትን ተከትሎ ሁላችንም እንደዜጋ የማንቆጠርበት ከኢትዮጵያዊ ማንነት በላይ የብሔር ማንነት ልቆ የወጣበት ዘመን ነበር። ይህ ደግሞ እያደገ ሔዶ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ የአንድ አካባቢን ቋንቋ የማይናገርበት፤ ተንቀሳቅሶ የመኖር እና ሃብት ንብረት የማፍራት ሁኔታ ችግር ውስጥ የገባበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ይህ ደግሞ እንደ አገር በጣም አስቸጋሪ ነበር። በዚህ የተነሳ በአብዛኛው በግጭቶች የተሞላ ጊዜን ከማሳለፋችን አንፃር የብዙኃን ሕይወት ተቀጥፏል። ንብረት ወድሟል። ይሔ ሔዶ ሔዶ አንድ ቦታ መቆም ካልቻለ አገር እንደ አገር መቀጠል፤ ዜጎችም አገር አለን ብለን ህልውናችንን ማስጠበቅ የማንችልበት ደረጃ ላይ ልንደርስ እንችላለን። ስለዚህ ቢያንስ እስከ አሁን የተከፈለው ዋጋ በቂ ነው። ከዚህ በኋላ ተጨማሪ ዋጋ እንዳንከፍል እና እንደሌሎች አገር ዜጎች እንዳንሰደድ እና አገር አልባ እንዳንሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ልዩነት የፈጠሩ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አለብን ብለን እናስባለን። ይህ ሲሆን ደግሞ የእነዚህ ተዋናኝ መሆን ያለበት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፤ ስለኢትዮጵያ ጥሩ የሚያስብ አካል ሁሉ በየደረጃው መሳተፍ አለበት። ለመጥቀስ ያህል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም በአገር ጉዳይ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን እና አርሶ አደሮች፣ የመንግስት ሠራተኞች በአጠቃላይ ሕዝቡ መሳተፍ የሚችልበት መድረክ መኖር አለበት። ምክንያቱም በተለያየ ደረጃ አጀንዳ እየወሰዱ ማወያየት እና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሚገባው እና በሚችለው ልክ መወያየት እና ወደ መፍትሔ መሔድ ካልቻለ ችግር የሚመጣው በውስን ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ችግር ሁላችንንም የሚጎዳ ሆኖ ይገኛል። ስለዚህ ሁሉም ማህበረሰብ ተሳታፊ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡-የእዚህ ምክክር ዓላማና ግብ ምንድነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ባንተይገኝ፡- የመጨረሻ ግቡ መሆን ያለበት፤ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት አሁን የመጣንበት አጠቃላይ ሰላምን የማያሰፍን ከሆነ፤ የዜጎችን መብት በመጋፋት ዜጎች በፈለጉት ቦታ ተንቀሳቅሰው ሃብት ንብረት የማፍራትና የመኖር መብታቸውን የሚነካ ከሆነ፤ የአንደኛው ክልል ተወላጅ የሌላ ክልል ተወላጅን መጣብኝ ብሎ ወደ ማጥቃት የሚሄድበት ሁኔታ ካለ አገር እንደ አገር መቀጠል አትችልም። መሠረታዊ የሆነ ሰላም የማይገኝበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው። ስለዚህ ይነስም ይብዛ የተሻለች ሰላም ያላት አገር መፍጠር ለሁላችንም ተገቢ ነው። ስለዚህ ሰላም ማምጣት እና ዜጎች በነፃነት መኖር የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር የዚህ ምክክር የመጀመሪያው ዓላማ ነው።
አዲስ ዘመን፡-አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ አገራዊ ምክክሩ የሚኖረው ፋይዳ እንዴት ይታያል?
ዶክተር ባንተይገኝ፡- የፓርቲዬ አቋም እንደተጠበቀ ሆኖ በእኔ እምነት አገራዊ የምክክር መድረክ ከዚህ በፊትም ሲታሰብ የነበረ እና የሚፈለግ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ዞሮ ዞሮ አሁን ካለንበት ጦርነት አንፃር የብሔራዊ ወይም የአገራዊ መግባባት አጀንዳ መቅደም አለበት የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም አገራዊ የምክክር መድረክ በመሠረቱ ብዙሃንን ማሳተፍ አለበት ብለን ካመንን፤ እዚህ ጦርነት ውስጥ የገቡ አካላት ቢያንስ የውይይቱ አካል መሆን መቻል አለባቸው። ስለዚህ በከፍተኛ ሁኔታ ጦርነት ውስጥ ሆነን፤ ጦርነቱ በሚካሔድበት አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች በጣም ሞራላቸው በተነካበት፣ ከቀያቸው በተፈናቀሉበት እና ሃብት ንብረታቸውን ባጡበት፤ በየማቆያው ጣቢያ ውስጥ እያሉ አገራዊ መግባባት አጀንዳን ይዞ መምጣት ምናልባት መቅደም ያለበት ጉዳይ አይመስለኝም።
በእርግጥ በብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት ላይ እንተማመናለን። ነገር ግን በጊዜ ደረጃ አሁን መሆን አለበት ብለን አናምንም። አሁን ትልቁ አጀንዳችን መሆን ያለበት ጦርነት ውስጥ ነን። ጦርነቱ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎናል። ኢትዮጵያ በታሪኳ በመሯት በራሷ ልጆች የተወጋችበት፤ ሕዝብ ያለቀበት፤ ይህ በታሪክ የመጀመሪያ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ይሔ ሔዶ ሔዶ አንድ እልባት ማግኘት አለበት። ይሔ አንድ እልባት እስካላገኘ ድረስ ወደ ብሔራዊ መግባባት እና ወደ ውይይት ቢገባም የሚፈየድ ነገር የለም። ምክንያቱም በዚህ ብሔራዊ መግባባት ውስጥ መካተት ያለበት፤ ከጦርነቱ በኋላ የሚመጣ ውጤት አለ። ስለዚህ ያ ከጦርነት በኋላ የሚገኘው ውጤትም የብሔራዊ መግባባት አጀንዳችን አንድ አካል ተደርጎ መወሰድ አለበት። ስለዚህ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ኢትዮጵያ ጦርነቱን በድል አድራጊነት መቋጨት አለባት።
ጦርነቱን መቋጨት ብቻ ሳይሆን በዚህ ደረጃ የሰውን ሕይወት የቀጠፉ ሃብት ንብረት ያወደሙ ብዙ ጥፋት ያስከተሉ አካላት ለህግ መቅረብ አለባቸው። ከሕግ አግባብ ውጪ የታጠቁት መሣሪያንም በተቻለ አቅም እንዲፈቱ መደረግ አለበት የሚል እምነት አለኝ። ጠቅለል ሲደረግ ብሔራዊ መግባባቱ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ወቅታዊ አይደለም። ለዚህም መጣደፍ እና መቸኮል ያስፈልጋል የሚል እምነት የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- የብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል ብላችሁ ታምናላችሁ። ነገር ግን ፋይዳው ምንድን ነው? በእናንተ በኩልስ ለዚህ ዓላማ ስኬት ምን አስተዋፅዖ አለን ትላላችሁ?
ዶክተር ባንተይገኝ፡- ምናልባት ብሔራዊ መግባባት የምንለው አጀንዳ እንደተራ አጀንዳ መታየት ያለበት አይደለም። የብሔራዊ መግባባት ሲነሳ ኮሚሽን ከማቋቋም ጀምሮ ሰፋ ያለ የዝግጅት ጊዜ ይፈልጋል። ይህንን አገራዊ ምክክር ከምንም በላይ ለብዙ ዓመታት ስንጠይቅ የመጣን ከመሆናችን አንፃር በጣም በጥንቃቄ እና በጥሩ ዝግጅት መካሔድ እንዳለበት እናምናለን። ስለዚህ በዛ የዝግጅት ጊዜ እንደአንድ ፓርቲ ከኛ የሚጠበቅብንን እናደርጋለን። በግሌም እንደሌሎች የውይይት መድረኮች ተድበስብሶ የሚቀር ሳይሆን የሚዳሰስ ውጤት ማምጣት የሚቻልበት በሚሆን መልኩ መቃኘት አለበት የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ በዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ ከእኛ የሚጠበቀውን ሁሉ ለመፈፀም ዝግጁ ነን፤ በእኔ በኩልም ዝግጁ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በእዚህ የምክክር መድረክ ላይ እነማን ሊሳተፉ ይገባል? በተለይ በሽብርተኝት የተከሰሱ ቡድኖችስ ሁኔታ ላይ ያሎት አስተያየት ምንድን ነው?
ዶክተር ባንተይገኝ፡- እንግዲህ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀ አካል አለ። ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀ አካል ለድርድር መቅረብ አለበት ብዬ አላምንም። ይሔ ማለት ኢትዮጵያዊነታቸውን መንፈግ አይደለም። ኢትዮጵያዊነታቸውን መንፈግ ሳይሆን በተቻለ አቅም ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀ አካል ለህግ መቅረብ አለበት። ስለዚህ እንደዚህ አይነት ሃይሎች ለህግ ይቀርባሉ። በሕግ አግባብ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ተጠይቀው፤ በሕግ መሠረት ተዳኝተው፤ በእነርሱ ላይ የሚወሰን የቅጣት ውሳኔም ካለ የቅጣት ውሳኔውን በትክክል ከተወጡ በኋላ በየትኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረጉ ምክክሮች መሳተፍ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። አሁን ባለው ሁኔታ ግን በአንድ በኩል ሽብርተኛ ተብሎ ተፈርጆ በሌላ በኩል ከሽብርተኛ ጋር ቁጭ ብለን እንደራደራለን ማለት ተገቢነት የለውም። ስለዚህ በቅድሚያ ያ ችግር መፈታት አለበት የሚል እምነት አለኝ።
ሌላ ለመጨመር ያህል በዚህ የምክክር ሂደት ውስጥ ትልቁ ጉዳይ እኛም ራሳችን የምክክር አካል መሆን አለባቸው ብለን የምናስባቸው አንኳር አንኳር ነጥቦች አሉ። እነርሱም በዛ ውስጥ እንዲካተቱልን የራሳችንን በቂ ዝግጅት አድርገን፤ እነዚህን አጀንዳዎች ይዘን የምንቀርብ ይሆናል። ምክንያቱም ወደ ምክክር መድረኩ ሲገባ ወይም ስለብሔራዊ መግባባት ሲታሰብ የአጀንዳ ባለቤት መሆን አለብን ብለን እናስባለን። ስለዚህ ጊዜው ሲደርስ አጀንዳችንን ቀርፀን የምንገባ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የአስተሳሰብ ልዩነት የተራራቀ ከመሆኑ አንጻር ይህንን ለማቀራረብ ከባድ አይሆንም ? ከዚህ ጋር ተያይዞ ለማቀራረብ መሃከል የሚሆነው ማን ነው? ይህ አካል የሚለየውስ እንዴት ነው ?
ዶክተር ባንተይገኝ፡- እንግዲህ መሃከል ላይ ሆኖ ያቀራርባል ተብሎ የታሰበው የኮሚሽን ምስረታው ነው። ኮሚሽነሮች ይሾማሉ ተብሎ ይታሰባል። የኮሚሽነሮቹ አሿሿም ራሱን የቻለ ሂደት እና የአሠራር ሥርዓት ይኖረዋል ብለን እናስባለን። ስለዚህ በጥያቄው ላይ እንደቀረበው እኛ በቋንቋ ተከፋፍለን ለብዙ ዓመታት ሆድ እና ጀርባ ሆነን የቆየን ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን በዛው ልክ የሚያቀራርበን እና ይሄ ተገቢ አይደለም ብሎ ጉዳዮችን በደንብ አድርጎ የሚያቀርብ አካል መፈጠር ከቻለ በቀላሉ መግባባት የምንችል ኅብረተሰቦች ነን። ስለዚህ ኮሚሽኑ ከሚሠራው ሥራ ውስጥ አንደኛው ይህ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ለምክክር ስንቀርብ ቢያንስ እያንዳንዳችን መጀመሪያ ልንቀራረብ የምንችልበት ሥርዓት መፈጠር መቻል አለበት። ስለዚህ ይህንንም እግረ መንገዱን የመጀመሪያው የሥራው አካል አድርጎ ኮሚሽኑ ይወስዳል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከብሔራዊ መግባባት አንጻር ከዚህ ቀደም በሌሎች አገራት ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ አሰራር አለ? በተለይ በአፍሪካ ለኢትዮጵያ ሞዴል ሊሆን የሚችል ካለ ቢጠቅሱልኝ?
ዶክተር ባንተይገኝ፡- በእርግጥ በሩዋንዳ እና በሌሎችም አገሮች ከኢትዮጵያም በጣም በከፋ መልኩ እንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ የነበሩበት ሁኔታን ሊወጡ ችለዋል። እነርሱ የተወጡበት የራሳቸው ሁኔታ አለ። እኛ ደግሞ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል ብለን ስናስብ በተቻለ አቅም ማየት ያለብን፤ የእነርሱ ልምድ እና ተሞክሮ እንዳለ ሆኖ ወደ እኛ አገር ስንወስደው ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ከእኛ አገር ጋር ተቃኝቶ ሊሆን የሚችለው ብሔራዊ መግባባት አጀንዳ የትኛው ይሆናል የሚለውን በደንብ አድርጎ መለየት ተገቢ ነው። ከእዚህ አንፃር ይህንን ወደ ውጤት መቀየር ይቻላል። የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ አገራዊ መግባባት ኢትዮጵያ ምን ታተርፋለች ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ባንተይገኝ፡- ዘላቂ ሰላም በሌለበት ሁኔታ ምንም ያህል ሃብት ንብረት ማፍራት ቢቻል ዞሮ ዞሮ የሚፈየድ ነገር አይኖርም። ስለዚህ አገራችን ከአገራዊ ምክክሩ የምታተርፈው ትልቁ ነገር ሰላም ነው። በዚህም ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን ሰላምን እናረጋግጣለን። ዜጎች ሆድ እና ጀርባ ሆነን የምንተያይበት ወይም አንዳችን የሌላውን አስተሳሰብ እያናናቅን የመጣንበት ታሪክ ለአንድ አገር አደጋ ስለሚሆን ይህን ያስታርቃል፤ ያግባባል። ሕዝብ እንደ ሕዝብ አንድነቱን አጠናክሮ እንዲወጣ ያደርገዋል ብዬ አምናለው። ስለዚህ ብሔራዊ መግባባቱ ለአንድነታችን መጠናከር ተገቢውን ውጤት ያመጣል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በአገራዊ መግባባቱ ላይ ልዩነትን የሚያሰፉና ለመቀራረብ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ኃሎችን ለመከላከል እንዴት ይሠራል? ይህንን ለመከላከል በምን መልኩ መሠራት አለበት? በተለይ ማህበራዊ ሚዲያው የሚፈጥረው ጫና እና እርሱን ለመከላከል ምን ይሠራ?
ዶክተር ባንተይገኝ፡- ምናልባት የአገራዊ መግባባት አጀንዳ ሲነሳ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ብሎ ማሰብ ተገቢ አይደለም። እዛም እዚም ከውጪም ከውስጥም የሚፈጠሩ እንቅፋቶች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዞሮ ዞሮ ግን እነዚህን እንቅፋቶች ታሳቢ በማድረግ ቀድሞውንም ሥራ መሥራት ከተቻለ ከውጪም ሆነ ከውስጥ የሚኖሩ አፍራሽ አስተሳሰቦችን መመከት ይቻላል። ስለዚህ የሚያስፈልገው ጥንካሬ ነው። ሌላው ነገር ግን አሁን ኢትዮጵያ በጣም እየተጎዳች ያለችበት ትልቁ ነገር የዲፕሎማሲ ጉዳይ ነው። ቢያንስ እንደዚህ ዓይነት አገራዊ መግባባት ውስጥ ስንገባ የተለየ ወይም ተቃራኒ አስተሳሰብ ሊያራምዱ የሚችሉ አካሎችን መመከት ከምንችልባቸው መንገዶች መካከል አንደኛው የዲፕሎማሲ ሥርዓታችንን በደንብ አድርገን ማዘመን ነው። በዲፕሎማሲው መበለጥ የለብንም።
በዲፕሎማሲ በኩል በየትኛውም አካባቢ የአገሪቱን መንግስት ወክለው የሚሔዱ አካላት የተሻለ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት አለባቸው። ሚዲያው ደግሞ የብሔራዊ መግባባት ጥቅም ምን ያህል እኛን እንደ አገር እና እንደ ዜጋ ሊያስቀጥለን እንደሚችል የተሻሉ ዘገባዎችን በማስተላለፍ የራሱን ሚና መወጣት አለበት። ሚዲያው ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡም የእዚህን የብሔራዊ መግባባት ጠቀሜታ ከልብ ተረድቶ እያንዳንዱ ባለበት ቦታ በደንብ ትብብር ማድረግ መቻል አለበት። ይህን ለማድረግ በነቂስ መንቀሳቀስ ስንችል የፈለገውን ያህል አፍራሽ ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት እየተመናመኑ የሚሔዱበትን ሥርዓት መፍጠር እንችላለን። ስለዚህ በአንድነት ሁላችንም ለዚህ ለተቀደሰ ዓላማ አብረን በጋራ መቆም አለብን።
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ ተስፋ ማድረግ ተገቢ ነው። ነገር ግን ይህ ስራ እጅግ የውስብስብነት ባህርይ ያለውና ከባድ ከመሆኑ አንጻር የመሳካት እድሉ ምን ያህል ነው?
ዶክተር ባንተይገኝ፡- ትክክል ነው። ብሔራዊ መግባባት ሲነሳ እንደአገር ሲታይ በጣም ሥር የሰደዱ ችግሮች ውስጥ የገባንባቸው ሁኔታዎች አሉ። ይህንን በአንድ ጀንበር ወይም በመጀመሪያ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ውስጥ መፍታት ላይቻል ይችላል። ስለዚህ በሒደት ግን የመጀመሪያውን እያጎለበቱ በቅድሚያ ውጤት ማምጣት ይቻላል። ከዛም በሂደት ቀስ እያሉ ወጥ የሆነ ወይም የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ የሚቻልበት ሁኔታ አለ። አንዴ ግን ሙሉ ለሙሉ ይሳካል ብሎ ማሰብ ምኞት ብቻ ሊሆን ስለሚችል በተቻለ አቅም የምናደርገው አጠቃላይ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ውጤታማ እንዲሆን ከመጀመሪያው ጀምሮ ዕቅዱ ሲያዝ በደንብ በዚያ ላይ ንግግሮችን ማድረግ የትኛው አጀንዳ መቅደም አለበት የሚለውም ነገር ቅደም ተከተል መስጠት ተገቢ ነው። ስለዚህ በመጀመሪያው ዙር ፣ በሁለተኛ ዙር፣ በሶስተኛ ዙር እያልን አጀንዳዎቻችንን በቅደም ተከተል ካስቀመጥን በቀላሉ መፍታት የምንችልበት እና መድረስ የምንችልበት ግብ ላይ ልንደርስ የሚያስችለን ግብ ላይ እንደርሳለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ባንተይገኝ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 25 ቀን 2014 ዓ.ም