ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት እንዲኖር አይፈልጉም።ይህን ለማስፈጸም ደግሞ የተቀናጀ ዘመቻ እያካሄዱብን ይገኛሉ።ተንቤን በረሃ ላይ እንዳይወጣ እንዳይገባ አርገን ያስቀመጥነውን ትህነግን የመሰለ ሰይጣን ፈተው ለቀውብናል።ክህደት የእናት ያባቱ የሆነውን ይህ ቡድን ከጎናቸው ሲያሰልፉ ታሪካዊ ዳራ ሁሉ ሳይመለከቱ አይቀሩም፤ እነሱ ዳራ ያያሉ።እናም ለእኩይ ተግባራቸው አሰልፈው ቀብድ አስጨብጠው እየጋለቡት ናቸው።እሱ ክህደት ለመፈጸም ምንም የማያንገራገር መሆኑ እንዳለ ሆኖ ምዕራባውያን ከመቃብር አፋፍ እንዲመለስ ሲሉ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም ያቀረቡለት ድጋፍ ቀብድ ሆኖት ሀገሩን ኢትዮጵያን አሁንም በድጋሚ አንዲክድ አርገውታል።
አሜሪካኖቹ፣ እኛ የጦር መሳሪያ እንዳናገኝ አድርገዋል።ይህን በማድረግ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ያደረጉትን ደገሙት።የቀደሙት መሪዎቻቸው ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በዚያ ፍትሃዊ የጦርነት አጋጣሚ የገዛነውን፣ ለመግዛት የተዋዋልነውን የጦር መሳሪያ አስከልከለውናል፤ በአንጻሩ ለጠላቶቻችን መሳሪያ በገፍ በማቅረብ አስወግተውናል።በሁለተኛ የፋሽስት ጣልያን ወረራ ወቅት ንጉሰ ነገስቱ ለሊግ ኦፍ ኔሽን ጣልያን ኢትዮጵያን በድላለች፤ ከእናንተ ፍትህ አንፈልጋለን የሚል ሀሳብ ገና ሲያቀርቡ ነጮቹ ለጣልያን በማገዝ የማይገባ ድምጽ በማሰማት ንጉሰ ነገስቱን ከንግግራቸው አቋርጠዋቸዋል፡፡
በዚህ ዘመንም እኛ የጦር መሳሪያ አንዳንገዛ እገዳ ጥለውብናል፤ አስቀድመን ስምምነት ያደረግንባቸውን የጦር መሳሪያዎችና መለዋወጫዎች ማግኘት የምንችልበት ጊዜ ላይ አይደለንም፤ ለእዚህ ወሳኝ የህልውና ዘመቻ የሚያስፈልግንን የምንገዛበት የውጭ ምንዛሬ ልናገኝ የምንችልባቸውን መንገዶች ዘግተውብናል፤ አጎአ ለምን ታገደ? የመግዛት አቅማችንን ለመፈታተን ነው።
በአንጻሩ ለተላላኪያቸው ለአሸባሪው ትህነግ፤ የኢትዮጵያን የጦር ሀይል ከጀርባ ለወጋው ትህነግ፤ በሰብዓዊ እርዳታ ስም ብዙ አድርገውለታል፤ ስንቁ ከዚሁ ነው የሚሰፈረው።የጦር መረጃ ጭምር በሳተላይት በማቅረብ አስወጉን፤ በጠላት በኩል የውጭ ወታደሮች ተሰልፈው እንዲዋጉም አረጉ።
በፕሮፓጋንዳም መንግስታችንን ሊጥሉ ህዝባችንን ሊበትኑ ብዙ ሞከሩ።የዛሬ ሰላሳ አመት ያደረጉትን ዘመቻ ዘንድሮም ደገሙት።ትህነግና ሸኔ አዲስ አበባን ሊቆጣጠሩ ነው ብለው ሽብር ነዙ፤ አስነዙ።የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባዎችን የኢትዮጵያ መንግስትን የሚያብጠለጥሉበት አደረጓቸው። በጸጥታው ምክር ቤት የማይታይ ጉዳይን ሊታይ የሚችል አድርገው አቀረቡ።
ይህ ሁሉ የተቀናጀ ዘመቻ ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ ቢያስከፍላትም፣ ድሉ ግን የኢትዮጵያ ሆኗል። አዲስ አበባ ተከባለች የሚለው የአሜሪካ ኤምባሲና ምዕራባውያኑ የሚዘውሯቸው አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሟርት ከሸፈ።ፈረሳቸውን በላ።ይህ ዘመቻ በሚገርም ፍጥነት 360 ዲግሪ ዞሮ ትግራይ ክልል ገባ። የመንግስት ጦር ትህነግን እያሳደደ ከአማራና ከአፋር ሲያጸዳ ጦሩ ወደ ትግራይ ክልል ወደ መቀሌ እንዳይገባ አድርጉልን ወደሚል ጩኸት ተቀየረ።
አዲስ አበባ ተከባለች እያሉ የውጪ ዜጎች አዲስ አበባንና ሀገሪቱን ለቀው አንዲወጡ በተለይ አሜሪካ ያልነቀለችው ድንጋይ የለም፤ ምን ድንጋይ ቋጥኝ የለም።አውሮፓውያኑም የአለቃቸውን አሜሪካ ዘፈን ሲያቀነቅኑ ቆዩ።ዜጎቻቸውን አስወጡ።ዜጎቼ የሚሏቸውን ኢትዮጵያውያንም ካልወጣችሁ ብለው ሰቅዘው ያዙዋቸው።አንዳንዶች መልዕክቶቹን እንዳላየ አልፈው በሀገራቸውን የመጣውን ለመቀበል ሲቆዩ፣ አንዳንዶቹ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር ምልክት ባያዩም መውጣት ስላለባቸው በግድ ወጡ።
ያን ሰሞን አንድ ጎረቤት ሀገር መሳቂያ መሳለቂያ ሆና ነበር።‘ሲሉ ሰምታ ዶሮ ሞተች ከጭስ ገብታ’ ነው የተባለው።ሱዳን ናት።እሷም ዜጎቿ በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ እንዲወጡ አሳስባ ነበር።ያው ከእነ አሜሪካና አውሮፓውያኑ ጋር በኢትዮጵያ ላይ የተጣመረች አይደለች፤ እንደ አቅሟ የጥምረቱን ቃል መፈጸሟ ነበር።ዜጓቿን የሰላም አየር ከሚተነፍሱባት ኢትዮጵያ እሳት ወደሚንቀለቀልባት ካርቱም መጥራቷ ሌላ ምን ይባላል።
አንድ አባባል ታሰበኝ።‘ወፍራሟ ጊደር ስትቦርቅ ከሲታዋ ጭራዋን ታቆማለች’ የሚል ነው።እነ አሜሪካ የሚሰሩትን ሲያጡ ሱዳንም የማይሆነውን ሞከረች።ዋና ከተሞቿ አንዴ በመፈንቅለ መንግስት፣ ሌላ ጊዜ በሰላማዊ ሰልፍ እየተናወጡ ባሉበት ሁኔታ፤ ይህን ተከትሎ ዜጎች እያለቁ ባለበት ሁኔታ ኮሽታ ካልተሰማበት አዲስ አበባ ዜጎቿን ወደ ትኩስ ወደምትናወጠው ካርቱም መጥራቷ ከከንቱ ቂንቂን የሚቆጠር ነው።
ሁሉም የዘራውን እያጨደ ነው።የትህነግና ተባባሪዎቹ የተቀናጀ የተናበበ ዘመቻ በዜሮ ተባዝቷል።የአሜሪካ ሟርት ከሽፏል።አዲስ አበባ ገብቶ ስልጣን ለመያዝ ለሀጩ ይዝረበረብ የነበረው ትህነግ መቀሌ መመለሻ አጥቶ አሳሩን አይቷል።ዘሎ መግባት እንደ መውጣት አይቀልም፤ ትህነግ ከገባበት የአማራ እና አፋር ክልል እንዳይወጣ አርጎ መደምሰስ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ሀይሎች የገባባቸውን በሮች ክርችም አርገው ዘግተው ወቅጠውታል።የተራረፈው ታጣቂ የተፈጠረበትን ቀን እየረገመ ተራራ እየቧጠጠ፣ በየሰርጡ እየተሹለከለከ አምልጧል፤ ያምልጥ፤ ወሬ ነጋሪም ያስፈልጋል።ቢያንስ ለቤተሰብ ይነገራል፤ ትህነግ እንደሁ ቢነግሩት የሚሰማው የሚፈልገውን ብቻ ነው።
ከሀዲው ትህነግ አሁን እንኳ ጀግና ወጥቶት አሁን ቆጠራ ቢያካሂድ ጥሩ ነበር እላለሁ።ይህን ቢያደርግ ቡድኑ ክልሉን ባዶ ማስቀረቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ ይህ ወቅት ያስገነዝባል።በካሚዮን እያጨቀ ወደ አማራና አፋር ክልል የላካቸው ታጣቂዎቹ እዚያው ትግራይ አቅራቢያ ያሉት ካልሆኑ በቀር የተመለሱት በእግራቸው ነው።መኪናም ታጣቂም በገባበት ቀርቷል።ምርኮዎቹን ለቅመን መጨረስ አልቻልንም ነው ያሉት የጦር ሀይሎች ኤታ ማዦር ሹሙ ሌተናል ጀነራል ብርሃኑ ጁላ።ለእዚያውም በመጡበት አኳኋን በአውራ ጎዳናው ሳይሆን ጢሻ ለጢሻ፣ ገደል ለገደል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ እናቶች ልጆቻችን የት አሉ ብላችሁ ጠይቁ ሲሉ አስገንዝበዋል።የትግራይ እናቶች ይህን ጥያቄ ሲያነሱ አንዱ የቆጠራ ውጤት ይገኛል።የትህነግ መሪዎች የትግራይ አንድ ትውልድ እንደ ቅጠል አንዲረግፍ አርገዋልና።እናም ትህነግ ቆጠራ ቢያደርግ መልካም ነው።
ጦርነቱ አልቋል፣ እጃችሁን ስጡ፣ ሰው አታስጨርሱ ይሉ የነበሩት እነ ደብረጽዮን፤ ጦርነቱ አልቋል ምን የሚሉት ድርድር ነው ይሉ የነበሩት እነ ጻድቃን፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን አንወርዳለን ያሉት እነ ጌታቸው ረዳ፤ ሂሳብ ማወራረድ የሚያስፈልገው አሁን ነውና ለማወራረድ ተነሱ።በተረፈ እኛ ባወራረድነው መሰረት ውርደት ምን አንደሆን አታውቁትም እንጂ ትልቁን የአለማችን ውርደት ተከናንባችሁዋል።
የትግራይ ህዝብም አሁን ስትባል በነበረውና እየሆነ ባለው መካከል ቆመህ ሂሳብ ማወራረድ ይኖርብሃል።እነ ጌታቸው ረዳ ሂሳብ እናወራርዳለን ብለው ነው አማራ ክልልን የወረሩት።የሚወራረድ ሂሳብ በሌለበት።‘ሞኝ አይሙት’ ይባላል፤ የብልህ አጫዋች ነው በሚል እኮ ነው ይህን ያሉት።የጌታቸው ያየኔ አነጋጋር አሁን ትግራይ ላይ በትግራይ ህዝብ ቢተገበር ክልሉን እና ሀገርን ከሌላ ጥፋት መታደግ ይቻላል።የትግራይ ህዝብ ሆይ እወክልሃለሁ፤ ካለኔም ሌላ የለህ ሲሊህ ከቆየው ትህነግ ጋር ሂሳብ አወራርድ።ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት ቢያንስ ልጆቻችን የት አሉ ብለህ አጥብቀህ በመጠየቅ ከትህነግ ጋር ሂሳብ አወራርድ።
የትህነግ መሪዎች ጀግና አይደሉም እንጂ አሁን ሽጉጥ የመጠጫቸው ሰዓት ነው።የትግራይን ወጣቶች በከንቱ አስፈጅተው እንዴት አርገው ነው የትግራይ እናቶች ፊት የሚቆሙት።ለነገሩ እነሱ አያፍሩም፤ ይቆማሉ፤ ለዚያውም ኮራ ብለው።መግደል ማስፈጀት የተሰሩበት ድርና ማግ ነው።ታሪካቸው ነው፤ በተገደለው ቁጥር እንዲሁም ግድያው አረመኔአዊ አይደለም መሆን የነበረበት በሚለው ላይ ይነጋገሩ ይሆናል እንጂ በመግደል አስፈላጊነት ላይ ልዩነት አይኖራቸውም።ምንም እንዳልሆነ አርገው፣ ልጆቻችሁ በአዲስ አበባ ጥሩ ጥሩ ስራ ይዘዋል፤ በኛ ይሁንባችሁ አይሉም ተብሎ አይታሰብም።ስራ ሲሰሩ የሚያሳይ ፎቶ ሁሉ ለቤተሰብ ሊሰጡ ይችላሉ።በፎቶ ሾፕ።ቆርጦ ቀጥሎች አይደሉ።ይህ ቀልድ መቆም አለበት።የትግራይ ህዝብ አሁን ሂሳብ ማወራረዱ ላይ ጠበቅ አርገህ ያዝ፡፡
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 25 ቀን 2014 ዓ.ም