የስፖርት ውድድሮች (ጨዋታዎች) በተለይም አትሌቲክስና እግር ኳስ ውድድሮች የሚካሄዱበት፣ ሰዎች ቆመውና ተቀምጠው ውድድሮች የሚከታ ተሉበት፣ በክብ የታጠረ (የተገነባ) ሜዳ ስታዲየም ይባላል። በቀድሞው ጊዜ በስታዲየም ውስጥ የሚካሄደው አትሌቲክስ ብቻ እንደነበር ታሪክ ያወሳል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ስፖርት መለመድ፣ መዘውተር፣ መሠልጠንና ውድድር በፕሮግራም መካሔድ የተጀመረው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከወረረች በኋላ ነውና አንድ መቶ ዓመት እንኳን አልሞላውም። እግር ኳስን በጥንት ጊዜ ቻይናዎች፣ ትሱቹ፣ ግሪኮች፣ ኤፒስክይሮቭ፣ ሮማውያኖች፣ ሔርፓስተም በሚል ስያሜ ይጫወቱት ነበር።
ኤድዋርድ ሁለተኛ በ1324 እንዳይካሄድ እስካገደ ድረስ ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንግሊዞች ይጫወቱት እንደነበር ከድርሳናት መረዳት ይቻላል። በ1349፣በ1389፣ በ1401 እግር ኳስ በእንግሊዝ በተደጋጋሚ ታግዶ ነበር። አዋጆቹን ችላ በማለት በስውርና በገሃድ ውድድሮች አልፎ አልፎም ቢሆን ይካሄዱ ነበር።
በ15ኛው፣ በ16ኛው እንዲሁም በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ውድድሮችን እንደምንም ለማካሄድ ይሞከር እንጂ ከጅምራቸው በቀር ፍፃሜያቸው አላምር በማለቱ ውድድሮቹ ከጨዋታ ይልቅ ወደ ጦርነት እያመሩ ከፍተኛ ጥፋቶች ተፈፅመዋል። በ17ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የንጉሣውያን ቤተሰቦች ጭምር በጨዋታው ጥበብ ስለተማረኩና ስፖርቱ በሕዝብ ትምህርት ቤቶች በመስፋፋቱ (በመዘውተሩ) ተወዳጅነትን አተረፈ።
የመጀመሪያው የእግር ኳስ ጨዋታ ደንብ በሥራ ላይ የዋለው እ.ኤ.አ በ1862 ሲሆን፤ በ1863 ደንቡ ተሻሽሎና ተከልሶ እንዲወጣ ተደረገና “የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ደንብ” በሚል ስያሜ በተግባር ላይ ዋለ። የእንግሊዝ የእግር ኳስ ማኅበር በ1863 ቢመሰረትም የራሱን ደንብ ያወጣው በ1864 ነበር። የእንግሊዝ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜየተካሄደው በ1871-72 ሲሆን፣ የመጀመሪያው የእንግሊዝ እግር ኳስ ክለብ የተመሰረተው በ1855 በሼፊልድ ከተማ ነበር።
እግር ኳስና ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ መደበኛ ውድድር የተደረገው በእግር ኳስ ግጥሚያ ሲሆን፣ ይህንን ዕውነታ በትክክል ለማቅረብ የማስታወሻ ደብተሬን ማገላበጥ የግድ ብሎኛል። አዲስ አበባ አራዳ አካባቢ ተወልደው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እየተማሩ ለትምህርት ቤታቸው የእግር ኳስ ቡድን ይጫወቱ የነበሩ ጆርጅ ዱካስና አየለ አትናሽ የተባሉ ሁለት ወጣቶች የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድንን መሥርተው ከውጭ ሀገር ኮሚዩኒቲ ቡድን ጋር ይጫወቱ ጀመር። ጆርጅ ዱካስን በአካል አግኝቻቸው ስለነበር የነገሩኝን እንደ ወረደ እነሆ።
«ቡድኑን የመሠረትነው በታኅሣሥ ወር 1928 ዓ.ም ነበር። ግብ ጠባቂያችን ከአሥመራ የመጣ ተስፋዬ አክሎግ የተባለ ተጫዋች ነበር። ለግብ ጠባቂዎች መሬት ላይ ተወርውሮ በመውደቅ ኳስን መያዝ አልያም ግብ እንዳትሆን ማጨናገፍ እንደሚቻል ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳየና ያስተማረ እርሱ ነበር። ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተመዝግቦ መሰለፍ የቻለው ይድነቃቸው ስላመጣው ነበር። የ መ ጀ መ ሪ ያ ው ግ ጥ ሚ ያ ች ን ን ያ ደ ረ ግ ነ ው ከ አ ር መ ኖ ች ና ከግሪኮች ከተውጣጣ ቡድን ጋር እንደ ነበር ትዝ ይለኛል።
የዕለቱ አርቢትር ወፍራም ከመሆኑ የተነሣ ተሯሩጦ ማጫወት ስለማይችል ፈረስ እየጋለበ ነበር ያጫወተን ሁልጊዜ ጨዋታው እንደተጠናቀቀ ተጫዋቾች የግቦችን ቋሚዎችን አግዳሚ እንጨቶችን ነቅለንና ተሸክመን ወደ ሠፈራችን ማጓጓዝ የተለመደ የውዴታ ግዴታችን ነበር። የጆርጅ ዱካስ፣ የአየለ አትናሽ፣ የይድነቃቸው፣ የነመንግስቱ ወርቁ፣ የነ ሙሉጌታ ከበደ ሥም ከጊዮርጊስ ቡድን ጋር፣ የነሙሉጌታ ወልደየስ ከቡና ጋር፣ የእነ ከበደ መታፈሪያ ከመቻል ጋር ሲወሳ ኖሯል።
ዛሬ የነማን እንበል? ለመሆኑ ዛሬ በሀገራችን ራሱን ጠብቆ ለቡድኑ ውጤት በማሰብ ሌት ተቀን ሠርቶ በቴክኒክና ታክቲክ ችሎታው በትንፋሽና በሠውነት አቋም በአርአያነት ልንጠቅሰውና ወጣቶች እርሱን ሊከተሉት ይገባል የምንለው አንበሳ ተጫዋች አለን? የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከእሥራኤል ቡድን ጋር በተጋጠመበት ወቅት ከመሀል ሜዳ አክርሮ በመምታት ግብ በማስቆጠር ሁሉንም በማስገረም አድናቆትን ያተረፈው የመቻል እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አለኝታ የነበረው ከበደ መታፈሪያ የነበረውን አቋም ፎቶው ላይ ተመልከቱ።
ታሞ ለመሞት ጥቂት ጊዜ እስኪቀረው ድረስ ልጠይቀው እመላለስ ነበርና ራሱን የቻለ ትውስታ አለኝ። የተለያዩ ቡድኖችን አሠልጥኖ ነበርና በእነርሱ ጊዜና ከእርሱም ወዲህ ስላሉት ተጫዋቾች አንስቼበት «እኛ ከእግዚአብሔር በተፈጥሯችን የታደልን ነበርን!» በማለት ነበር በደፈናው የመለሰልኝ።
የከበደ መታፈሪያን ነገር ካነሣሁ ጋሼ ከበደ መታፈሪያን ኢንተርቪው ለማድረግ እቤት ስሔድ እሱ አንድ አልጋ ላይ ዐይነ ስውር ባለቤቱ ሌላ አልጋ ላይ ታመው ማዶና ማዶ ተኝተው ቤተሰቦቹ ደግሞ የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ተኮራምተውና አንገታቸውን ደፍተው ቀዝቃዛ ቤት ውስጥ ተቀምጠው ነበር ያገኘኋቸው። ከጋሼ ከበደ ጋር ብዙ አወጋን፤ ከንፈሬን በመምጠጥ ብቻ ልሰናበተው ስል እንዲህ አለኝ።
«ስማ የእኔ ልጅ እኔ እኮ የሚነግርልኝ ሰው አጥቼ ነው እንጂ አደራ የተባለ ሊያሳክመኝ የሚችል ሰው አለ» አለኝ። ማን ይባላሉ? አድራሻውን አጥቼና የሚነግርልኝ ሰው በማጣቴ ነው እንጂ እከሌ ያሳክመኝ ነበር! በአጋጣሚ የጠራልኝ ሰውዬ ስልክ ቁጥር ነበረኝና እርግጠኛ ነህ? ሰውየው አደራ ተብለዋል? አዎን! አደራ ያሉትም የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በክብር እንግድነት ጋብዞኝ ወደዚያው ሔጄ በነበረበት ወቅት በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ተጫዋቾች ናቸው።
የሰውየውን እጅ በመያዝ ከበደ መታፈሪያን በሚቸግረው ሁሉ እርዳልን አደራ! አደራ! ካስፈለገ ወጪውን እኛ እንከፍላለን ነበር ያሉት አለኝ። ስልኬን አወጣሁና ደወልኩኝ። የተባሉት ሰውዬ ስልኩን አነሱት። የስፖርት ጋዜጠኛ እከሌ እባላለሁ። በአጋጣሚ ያውቁኝ ይሆን? አልኳቸው፡ በሚገባ አውቅሀለሁ። ለምን ነበር የፈለከኝ? ለእርስዎ በአደራ የተሰጠ የቀድሞ ስፖርተኛ በጠና ስለታመመ አደራ ተብለዋልና ደውልልኝ ስላለኝ ነው የደወልኩልዎት። ለእኔ በአደራ … በአደራ የተሰጠ ስፖርተኛ? አዎን! ማነው እሱ? ከበደ መታፈሪያ በጠና ታሟል! ከቤ በጣም ታሟል? ሐኪሞች ምን አሉ? ምን ወሰኑ?ሀገር ውስጥ ነው ውጭ ሀገር ይታከም ያሉት? አሉኝ በድንጋጤ ተውጠው። ገንዘብ ስለሌለው ሐኪም ቤት ሄዶ አልተመ ረመረም አልኳቸው።
ከበደ የመታት ኳስ ግብ ሆናለች! የውጭ ሀገር ህክምናን ሲያነሱልኝ እንደ ሚያሳክሙት እርግጠኛ ሆንኩና ሰውነቴን ዘና፣ እግሬን ዘርጋ፣ ሞራሌን ጠንከር አደረግሁኝ። እባክህን የእኔ ወንድም እኔ በጣም ሥራ ስለሚበዛብኝ በድሉ ህንፃ ፊት ለፊት እሚገኘው ኖብል ከፍተኛ ክሊኒክ ይዘህልን መምጣት ትችላለህ? አቶ አባቡ የሚባል ሰው ይጠብቃችኋልና ለሕክምና ባለሙያዎች አስረክቡት አሉኝ። ላዳ ታክሲ ተኮናተርኩና የጋሼ ከበደን ወንድና ሴት ልጆች (ሥራ የላቸውም) ይዤ እክሊኒኩ ደረስን። የሕክምና ባለሙያዎቹ በር ላይ ጠብቀው ተቀበሉን።
ጋሼ ከበደ በስሜ ጠርቶ ከመረቀኝ በኋላ ሆስፒታል ገብቶ በሕክምና ላይ ሳለ ሞተ መባሉ ለእኔ ክብር ነውና ከእንግዲህ ብሞት ግድ የለኝም። ሒድ! አለኝ። ታላቁ የሀገር ባለውለታ! ተመላልሼ ጠየቅሁት ዕድሜ የተጫነው ከመሆኑ በተጨማሪ በሽታውም፣ ችግሩም ጎድቶት ነበርና በኢትዮጵያ ውስጥ ሊደረግ የሚገባው ሕክምና ሁሉ የተደረገለት ቢሆንም ማትረፍ አልተቻለምና አምላክ ባለው ቀን አረፈ። አደራ ለተባሉት ሰው ደወልኩኝ።
ለሕክምናው ብዙ ገንዘብ ያወጡ መሆኑን ባውቅም አማራጭ ስላጣሁ ነበር ወደ እርሳቸው የደወልኩት። ሕክምናውን ሲያስፈፅም የነበረው አቶ አባቡ፣ ከበደ መታፈሪያ የክብር አሸኛኘት እንዲደረግለት ከአስከሬን መጓጓዝ ጀምሮ ሁሉንም ወጪ ያለ መሰልቸት ከልጆቹ ጋር በመመካከር የቀብሩን ሥነ ሥርዓትና የለቅሶውን ሽኝትና አጠቃላይ ፍፃሜውን አሳመረው። የሕክምናውን ወጪ የሸፈኑት ሩኅሩኁ በጎ አድራጊ ናዝሬት ላይ የማይቀሩበት የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ስብሰባ ስላለ ወደዚያው ቢያመሩም ቤተሰቡን በስልክና በተወካያቸው አማካኝነት ሲያፅናኑ ቆዩ። ወገን ለወገን ደራሽነቱ በተግባር ታዬ። በመልካም አርአያነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ግለሰብ ለሀገር ባለውለታ ውለታ ዋሉ።
አሜሪካ የተሰጣቸውን አደራ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ አደረጉት ። ለመሆኑ ሰውዬው ማን ናቸው? የዚህ በጎ ተግባር ባለቤት አቶ አብነት ገብረ መስቀል ናቸው። አቦ እግዚአብሔር ይስጣቸው! ከዚያ ወዲህ የተቸገሩ ባለ ውለታ ስፖርተኞች አቶ አብነትን እንዳስቸግርላቸው ቢጠይቁኝም በድጋሚ ማስቸገሩን ፈርቼ ተውኩት። ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ። ወደ ርዕሴ ስመልሳችሁ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት አራት ስታዲየሞችን በአዲስ አበባ ከተማ ሠርታ በጥቅም ላይ እንዲውሉ አድርጋ ነበር።
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በፋንታሁን ኃይሌ