የንታ ፍሬው ከሰፈራችን ገበያ መካከል ከሚገኘው ትልቅ ዛፍ ስር የሰፈራችንን ሰዎች ሰብስብው «ነፍስ ሥጋን ካላሸነፈቻት ሥጋ ለነፍስ መቃብር ትሆናለች። » ይሉ ነበር። እነ አይተ ጭሬ ልድፋውም ስጋቸው ነፍሳቸውን በማሸነፏ ከህሊናቸው ይልቅ ለሆዳቸው አድረው ሰፈራችንን አጥፍተው ሊጠፉ ቆርጠው ተነስተዋል።
እንደሚታወቀው ሰፈራችን በአፍላ የለውጥ ትግል ውስጥ ናት። ነገር ግን እነ አይተ ጭሬ ልድፋው አፍላውን ለውጥ ለማኮላሸት እያደረጉት ያለው የተንኮል ሩጫ በባዕዳን እንጂ ሰፈራችን በፈጠረቻቸው ፍጥረታት የሚደረግ አይመስልም። አይተጭሬ ልድፋው እና ምዕራባዊያንን ጨምሮ ሌሎች የሰፈራችንን አፍላ የለውጥ ትግል ለመቀልበስ የሚራኮቱ ሃይላት የሰፈራችንን ህዝቦች አንድነት የሚጠሉ እና የሰፈራችንን የወደፊት እጣ ፋንታ በአጋም እሾክ ውስጥ የሚተክሉ ወይም ከገደል አፋፍ ላይ በተሰራ ቤት እንደሚኖር ሰው በጭንቀት በመወጠር የለውጡን ፍሬ መቅመስ እንዳንችል ለማድረግ እየተጋጋጡ ነው። ስለሆንም አይተ ጭሬ ልድፋውን እና የጥፋት ፈረሶቹን አምርሮ መታገል እንደሚገባ የንታ ፍሬው ደጋግመው ጮክ እያሉ በመናገር ለሰፋራችን ሰዎች ያስረዳሉ።
የንታ ፍሬው ይህንን ያሉበት ዋና ምክንያትም አይተ ጭሬ ልድፋው ከወንድሞቹ እና ከቤተሰቦቹ ይልቅ የባዕድ ምክር እየሰማ ሰፈራችንን አቃጥላለሁ፣ የክፍት መርዜን ተፍቼ የሰፈር ሰዎችን እገድላለሁ፣ የጥፋት ማዕበል በመፍጠር የሰፋራችንን ሰዎች እና ንብረት ጠራረጌ እንዳልነበር አደርጋቸዋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
አይተ ጭሬ ልድፋውም እንደፎከረ አልቀረም! ከህጻን እስከ ሽማግሌ፤ ነፍሰ ጡሮችን ሳይቀር ገዳይ እና ዘራፊ ቡድኖችን መለመለ። ምልምል ገዳይ እና ዘራፊ ቡድኑን ሰፈራችን ድረስ እንደጉንዳን አግተልትሎ ይዞ መጣ። ሰፈራችንን ለማፍረስ የሚችለውን አደረገ።
በዚህ ጊዜ የንታ ፍሬው መከረኞች ከመከራቸው ነጻ የሚወጡት ለመብታቸው መከበር ሲጥሩ ወይም ሲሞቱ ነው። «እንበለ መከራ፤ ኢይትረከብ ጸጋ ወይም ያለመከራ ጸጋ፤ ያለድካም ዋጋ አይገኝም። » እንዲሉ ማንኛውም የሰፈራችን ሰው በሚችለው ዋጋ ከፍሎ ሰፈራችንን ከአይተ ጭሬ ልድፋው ጥፋት ልንጠብቅ እንደሚገባ መልዕክት አስተላለፉ።
የንታ ፍሬው አክለውም «የጀግና ሰው መልኩ ሁለት ብቻ ነው፤ አንድም መስዋዕት መሆን ሌላኛው የወደ ፊት እድሉ ነው! የሌባም ሰው መልኩ እንደዚሁ ሁለት ብቻ ነው፤ አንድም ተቀጥቅጦ ተዋርዶ መሞት ሲሆን ሁለትም ተዋርዶ እና ተንቆ ቀማኛ! ሌባ! እየተባለ እየተሰደበ መኖር! ጀግና ቢሰዋም ታሪኩ በጥሩ ነገር እየተወሳ ለመልካም ነገር ምሳሌ ይሆናል። በሚደረገው ተጋድሎ ከሞት ከተረፈም በእሱ ልክ ለሃገር የሚጠቅሙ ሰዎች እያዘጋጀ ወገኖቹን ያጀግናል፤ ይመራል። ሌባ እና ዘራፊ ግን ሲሞትም የእርኩስ ሞት ነው የሚሞተው፤ ቀባሪ እንኳን አያገኝም! ሌባና ዘራፊ ሰፈራችሁን ሊያጠፋ በመጣ ጊዜ የማይከላከል ሰውም ከሌባው እና ከቀማኛው እኩል ነው! አንድም በዘራፊው በደል ይደርስበታል፣ ክብሩንም ከሰውነት ያወርዳል፤ ሁለትም ሰፈሩን ከቀማኞች እና ከገዳዮች መከላከል ያልቻለ ፈሪ እየተባለ ሲሰደብ ይኖራል!» ሲሉ የሰፈራችንን ሰዎች መከሩ።
የሰፈራችንም ሰዎች የየንታ ፍሬውን ምክር በመስማት አቅም ያለው ነፍጥ ይዞ ዘመተ። አቅም የሌለው በገንዘብ እና በፀሎት ድጋፍ አደረገ።
የሰፈራችን ጥምር የጸጥታ ሃይሎች በሚያስደንቅ መልኩ በመናበብ የአይተ ጭሬ ልድፋውን የጥፋት ቡድን ቀጠቀጡት። የጥፋት ሃይሉ አብዛኛው ተደምሶ ተበተነ። በወገን ጠንካራ ክንድ የተወቀጠው ጠላትም ቀበኛ ከብት እንደበላው ልብስ ሆኖ ወደ ፍርፋሪነት ተቀየረ። ከፍርፋሪነት የተረፉት የተወሰኑት አባላቶቹ ሲማረኩ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ደግሞ ወደ መጡበት ዋሻ ተመለሱ። በአጠቃላይ የጥፋት ማዕበል በመፍጠር ሰፈራችንን ሊያጠፋ የመጣው የአይተ ጭሬ ልድፋው የጥፋት ቡድን ራሱ በፈጠረው ማዕበል ተጠራርጎ ተበላ።
ይህን ተከትሎ አይኑን በጨው ያጠበው አይተ ጭሬ ልድፋው ልንሰርቅ እና ልንዘርፍ እንዲሁም ልንደፍር እና ንብረት ልናወድም በሄድንባቸው ሰፈሮች ለሞቱ ወገኖቻችን ሻማ እንዲበራላቸው የሚል ትዕዛዝ ሰጠ።
ከሞት የተረፉ የአይተ ጭሬ ልድፋው ገዳይ እና ዘራፊ ቡድን ዋይ! ሻማ ከየት አምጥተን ነው የምናበራው? “የዘረፍነው እኮ ኮምፒውተር እና ትላልቅ ማሽኖችን ነው። ለምን አሜሪካ የምናበራውን ሻማ እንኳን አትረዳንም?” ሲል ጠየቀ። አይተ ጭሬ ልድፋውም ተናዶ እና ጦፎ “ዋይ! ለአሜሪካ ስንት ነገር ትርዳን? ሰፈራችንን እንዴት ማጥፋት እንዳለብን በምክር የረዳችን አሜሪካ ናት። አሁን ላይ ደግሞ አሜሪካ እና ወዳጆቿ ሌላ ሰፈር ለማበጣበጥ በጣም አጣዳፊ ስራ ላይ ናቸው። ሁሉን ነገር ከአሜሪካ መጠበቅ አያስፈልግም። ስለዚህ ከዘረፍናቸው ኮምፒውተሮች እና ማሽኖች የተወሰኑትን ለዛሬ እንደ ሻማ እንጠቀም” ሲል ትዕዛዝ ሰጠ።
በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ የንታ ፍሬው ለአይተ ጭሬ ልድፋውን የሚሰጡት ስም አጥተው የተጨነቁት።
የንታ ፍሬው ለነገሮች ትርጉም በመስጠት እና በመተንተን የሚያክላቸው የለም። ይሁን እንጂ ለአይተ ጭሬ ልድፋው እና አይተ እኩይ ምግባሩ ግን ሁነኛ ስምያገኙላቸው አልመሰለኝም። እንዴትስ ስም ሊያገኙላቸው ይችላሉ?
ምክንያቱም ንጹሃንን እየገደሉ ለጅብ የሚሰጡ፣ ከህጻናት እስከ መነኮሳት የሚደፍሩ፣ የሃገርን ንብረት በማውደም ሃሴት የሚያደርጉ፤ ነገርግን አውዳሚዎቻቸው እና ደፋሪዎቻው ሲሞቱ ደግሞ ጥሩ ነገር ሲሰሩ እንደሞቱ ሁሉ ሙሾ እያስወረዱ ሻማ የሚያስበሩ ልዩ ፍጥረት ምን ሊባሉ ይችላሉ?
በእኔ በኩል እነዚህን ምን እንደምላቸሁ ስለተቸገርኩ የተከበራችሁ የሰፈራችን ሰዎች ለእነዚህ ፍጥረታት ስያሜ አጣሁላት፣ እስኪ ስም አውጡላት። ብያለሁ!
የንታ ፍሬው እና ደጋፊዎቹ ትልቁ ችግራቸው አይተ ጭሬ ልድፋውን እንደ ሰው መቁጠራቸው ነው። ለእኔ እነ አይተ ጭሬ ልድፋው ጉንዳን የያዘው ስጋ ናቸው፤ ሊበሉ የማይችሉ። ነገር ግን በእነሱ ሰበብ ጉዳንን የመሰለ ተናካሽ አውሬ ቤታችን በማምጣት የቤታችን ሰላም የሚያውኩ ናቸው። የራሳቸው መበላሸት ሳያንስ የሚያድሩበትና የሚውሉበትን እንዲሁም ሲያረጁ የሚጦሩበትን ቤታቸውን በጠላት እንዲወረር የሚፈቅዱ ልዩ ፍጥረታት ናቸው። ይህን ሲያደርጉ ብቻ ሃሴት በማድረግ እንቅልፍ የሚወስዳቸው ናቸው። እስኪ እነኝህን ፍጥረታት ምን ብለን እንጥራቸው? ምን ብለን እንደምንጠራቸውም እኮ ተቸገርን ጎበዝ! ለማንኛውም ማን እንበላት?
እስኪ ስም አውጡላት። ብያለሁ።
«በጽባሕ ዘተናገረ፤ ኢይደግም በሠርክ ወይም ጠዋት የተናገረውን ማታ አይደግመውም» እንዲሉ አይተ ጭሬ ልድፋው እና ግበረ አበሮቹ አሁን የተናገሩትን ቆይተው አይደግሙትም። ለምሳሌ ያሸነፉ ሲመስላቸው «እንቆርጣቸዋለን፤ እንፈልጣቸዋለን፤ እንደመስሳቸዋለን!» እያሉ ይደነፋሉ። የተሸነፉ ሲመስላቸው ደግሞ «የአለም ህዝብ ይድረስልን፤ ያደራድረን የዘር ማጥፋት ተፈጸመብን» በማለት ኡኡ ይላሉ።
የዘር ፍጅት እንዳይፈጸም በመከላከልና ሲፈጸምም በማስቆም ላይ እሰራለሁ እያለ መርጦ የሚያለቅሰው የጄኖሳይዶ ዎች የተባለው ተቋም ሊቀመንበር የሆኑት ግሪጎሪ ስታንተን በአንድ ወቅት ባቀረቡት ጥናት እንደገለጹት፤ የሰው ልጆች ልባቸው ሲደድር የሚጠናወታቸው የዘር ጭፍጨፋ አባዜ አስር የሚደርሱ ደረጃዎችን ሊሄድ ይችላል። እነዚህም የጥፋት ደራጃዎች በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንደሚፈጸሙ ጠቁመዋል።
ከአይተ ጭሬ ልድፋው ሰፈራችንን ለማጥፋት የሄደበትን ርቀት ለማየት ይረዳ ዘንድ በጥናቱ የተለዩ የዘር ማጥፋት ደረጃዎን አንድ በአንድ ማየቱ ተገቢ ነው። በጥናቱ መሰረት በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚቀመጠው መከፋፈል (Classification) የሚለው ነው። በዚህ ደረጃ ላይ አጥፊዎች እኛና እነርሱ ብሎ በመከፋፈል ለየት ይላሉ ተብለው የሚታሰቡትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀልድም ጭምር በማንቋሸሽ በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ያለማክበር ነገርን ይጀምራሉ።
አይተ ጭሬ ልድፋው እና ዘመዶቹም ይህን ደረጃ ሲጀምሩ ሰፈራችንን በዘውግ ከፋፈሉት። ህገ መንግስት አበጅተው እናንተ እስከፈለጋችሁ ድረስ መገንጠልም ትችላላችሁ አሉን። ነገር ግን የሚሰማቸው ጠፋ። የሚሰማቸው ሲያጡ ልዩነታችንን አጉልቶ ለማሳየት በማሰብ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ልዩነቱን ለማስፋት ጣሩ። አንዴ በሃውልት፣ ሌላ ጊዜ በታሪክ ሊያጋጩን ሞከሩ። አልጣላ አልናቸው፤ ተናደዱ!። በአደባባይ ሳይቀር እሳት እና ጭድ እንዴት አብረው ሊቆሙ ቻሉ ብለው ተዘባበቱብን።
ሁለተኛው የዘር ማጥፋት ደረጃ ደግሞ የሚታይ መገለጫ መስጠት (Symbolization) ነው። ይህ የጥላቻ ግልጽ መገለጫ ሲሆን ይሁዳዎች በናዚ ጀርመን ቢጫ ኮከብ ያለበት ልብስ እንዲለብሱ እንደተደረገው ነው። እነ አይተ ጭሬ ልድፋውም በእኛ ሰፈርም ያደረጉት ይሄንኑ ነው። ለእያንዳንዳችን ማልያ አለበሱን ። ከፊሉ ጠባብ፣ ከፊሉ ትምክህተኛ በማለት ሰየሙን። አንዳንዶቻችን እነ አይተ ጭሬ ልድፋው የሰጡንን መለያ በባህል አልባሶቶችችን ሳይቀር ለጥፈን መልበስ ጀመርን።
ሶስተኛው የዘር ማጥፋት ደረጃ ደግሞ ማግለል (Discrimination) የሚባለው ነው። በዚህ ደረጃ ደግሞ ጉልበት ያለው ሃያል ህጎችን፣ ልማዶችን እና የተለያዩ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ሽፋን በማድረግ ወቅቱ ጉልበት የነፈጋቸውን ሰዎች መብት መጣስ ነው። ወንጀለኞች በዚህ ደረጃ ህጎችን ተጠቅመው የመብት ተሟጋቾችን አሸባሪ፣ ሌቦችን ልማታዊ ባለሃብት፣ አብሮ የኖረን ህዝብ ለማፈናቀል ሲያስቡ ደግሞ የልማት ተነሽዎች ወዘተ እያሉ በረቀቀ መንገድ የዘር ማጽዳት ወንጀል ፈጸሙ።
አራተኛው የዘር ማጥፋት ደረጃ ደግሞ ከሰው ክብር ዝቅ ማድረግ (Dehumanization) የሚባለው ነው። ይህ ተግባር ወንጀል ፈጻሚዎች ከራሳቸው የተለዩትን ሰዎች ሰብዓዊ ክብርም ሆነ መብት በመንፈግ በእንሰሳት፣ ከበሽታ ወዘተ ጋር በማገናኘት የሰውን ክብር ዝቅ የሚደረግበት ደረጃ ነው። በሩዋንዳ አክራሪ ሁቱዎች የቱትሲ ዘውግ ተወላጆችን ‹በረሮ› ይሏቸው እንደነበረው መሆኑ ነው። ይህ ሂደት ገዳዮቹ ‹እየገደልን ያለነው ሰው አይደለም፤ ታዲያ ድርጊታችን ምኑ ላይ ነው ጥፋትነቱ?› እንዲሉ መንገዱን ይጠርግላቸዋል። አይተ ጭሬ ልድፋውም ለሰፈራችን ሰዎች የተለያዩ ስሞችን ከፊት እንደቀንድ ከኃላ እንደ ጅራት በመቀጠል ህግን ሽፋን አድረገው የሰፈራችንን ሰዎች በዘራቸው ለይተው ጨፍጭፏቸዋል።
ጥናቱ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠው ደግሞ ማደራጀት (Organization) የሚባለውን ነው። በዚህ ደረጃ ወንጀለኞች በጥላቻ ላይ የተመሠረቱ አንድን ሕዝብ ለማጥፋት የሚያስችሉ ኃይሎችን ያሰለጥናሉ። እነ አይተ ጭሬ ልድፋውም በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ይህን የሚያደርግላቸውን ቡድን በደህንነት ስም ከላይ እስከ ታች በመዋቅር ውስጥ በማደራጀት በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማሉ ተብሎ የማይገመቱ ጭካኔዎችን በግፍ ፈጸመዋል። ከስልጣን ከተባረሩ በኋላም ዋና ስራ አድርገው የያዙት ይሄንኑ ነው።
ጥናቱ በስድስተኛ ደረጃ ያስቀመጠው ደግሞ በተቃራኒ ጎራዎች ማሰለፍ (Polarization) የሚለውን ነው። በዚህ ደረጃ ጨፍጫፊውና ተጨፍጫፊው ወገን በዘውጉ ሚናውን እንዲለይ ይደረጋል። በብዛት ይህ የሚሆነው በጥላቻ ቡድኖች ውትወታና በመገናኛ ብዙኀን የጥላቻውን መርዝ በመርጨት ነው። ጀርመኖች ይሁዳዎችን ከመፍጀታቸው በፊት እና የሩዋንዳ አክራሪ ሁቱዎች ቱትሲዎችን ሲጨርሱ የገዳዩን ዘውግ አባላት በቀላሉ ለማሳመን መገናኛ ብዙኀንን በሰፊው ተጠቅመውበታል። በእኛ ሰፈርም እነ አይተ ጭሬ ልድፋው ያደረጉት ተመሳሳይ ነው።
ስምንተኛው ደረጃ ዝግጅት (Preparation) የሚባለው ነው። በዚህ ደረጃ ሰለባዎቹ በልዩነቶቻቸው ተለይተው ይፈረጃሉ።
ዘጠነኛው ደረጃ ፍጅት (Extermination) ነው። በዚህ ደረጃ በታቀደና ሆነ ተብሎ በተመቻቸ ዘመቻ የጥላቻ ቡድኖቹ ሰለባዎቻቸውን ይጨፈጭፋሉ። አይተ ጭሬ ልድፋው እና ግብረ አበሮቻቸው በማይካድራ፣ በአጣየ፣ በጭና፣ በወለጋ፣ በሶማሊያ፣ በአጋምሳ፣ በጭልጋ፣ በቤኒሻንጉል ወዘተ ሰዎች በማንነታቸው ተቧድነው እንዲጠፋፉ አደረጉ። ከዚህ የባሰው ደግሞ መከላከያ ውስጥ ያሉ ወታደሮች በማንነታቸው ተለይተው በተኙበት ተረሸኑ። አስከሬናቸው እንኳን ክብር አጥቶ ተጎተተ! ለጅብም ተሰጠ።
የዚህ ወንጀል የመጨረሻው ደረጃ ክህደት (Denial) ነው። በዚህ ደረጃ ግድያውን የፈጸሙት አካላት ለቀጣይ ትውልዶች ምንም ዓይነት ጥፋት ያልተፈጸመ በማስመሰል ክህደት ይፈጽማሉ። አይተ ጭሬ ልድፋው እና ግብረ አበሮቻቸው ሰዎችን በማንነታቸው እየተለዩ እንዲገደሉ ካደረጉ በኃላ፣ መከላከያን በተኛበት ካረዱ በኋላ እኛ አላደረግንም በማለት አይኔን ግንባር ያድርገው አሉ። ይባሱኑ ራሳቸው መከላከያን እና የሰፈራችንን ሰው በጭካኔ ገድለው ከጣሉ በኋላ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጸመብን ብለው ለአለም ህዝብ ከሰሱን።
ታዲያ እነኝህ ፍጥረታት ምን እንበላቸው? የንታ ፍሬውም ሆነ እኔ ስያሜ ልናገኝላቸው አልቻልንም። ውድ የሰፈራችን ነዋሪዎች፤ ለእነኝህ ፍጥረታት ለታሪካቸው መጠሪያ የሚሆን ስም አውጡላቸው ለማለት ፈልጌ ነበር። ነገርግን ለእነርሱ ስም ከማውጣት ይልቅ በጀግንነት ተፋልሞ ማጥፋት የተሻለ ነው ብዬ ስላመንኩ እነኝህ ልዩ ፍጥረታት ከዚህ በኋላ በታሪክ ብቻ እንዲታወሱ እናድርጋቸው እላለሁ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 21/2014