ዶክተር ጌታቸው ካሣ ንጉሴ የተወለዱት በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ጉጂ ዞን በሞያሌና ነገሌ መካከል በሚገኝ ዋጭሌ በሚባል አካባቢ ነው።በታሪክ ትምህርት በ1974 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ፤ ምእራብ ጀርመን ባይሮጅ ዩኒቨርሲቲ ለአምስት ዓመታት የአፍሪካ ታሪክ፤ ሶስዮሎጂ፤ አንትሮፖሎጂና ኢስላም በመማር በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል። በደቡብ ኢትዮጵያና ሶማሌ በሚገኘው ገሪ ብሔረሰብና በቦረና መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ሰፊ ጥናት አድርገዋል።በመቀጠል ለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን ተምረው ፒኤችዲ (ዶክትሬት) ዲግሪ አግኝተዋል።እንደገናም አፋር ላይ ጥናት ስለነበራቸው ስኩል ኦፍ ኦሪየንተል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ ተምረው ተመርቀዋል። በአብዛኛው የምስራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሮች ያላቸውን ግንኙነት ታሪክ እድገትና ተጽእኖ ያላቸውን ቁርኝት አጥንተዋል።
ሶማሌ፣አፋርና ቦረና ላይ ትኩረት በማድረግ ሰሜን ኬንያ፤ ደቡብ ሶማሊያና ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ሰፊ ጥናትና ምርምር አድርገዋል።በተጨማሪም ትንንሽ አርብቶ አደሮች የሚባሉት በተለይ ደቡብ ኦሞ ቦዲ አካባቢ በሚኖሩት ላይ ጥናት አካሂደዋል።በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው።የሶሻል አንትሮፖሎጂ።የኢትዮጵያ ጥናት (ኢትዮጵያን ስተዲስ) ዳይሬክተር ሆነው የማስተርስ ዲግሪ ፕሮግራም ለሚከታተሉ ተማሪዎች ሀገር በቀል የእውቀት ሥርዓትና፤ የግጭት አያያዝና አፈታትን አስተምረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አፍሪካን ስተዲይስ ዲፓርትመንት በመስራት ላይ ይገኛሉ።ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በተጨናነቀው የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲክስ፤ በአካባቢው በተከማቸው የተለያዩ ኃያላን ሀገራት ወታደራዊ ኃይል፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት፤ አፍሪካዊ ማንነትን በመደፍጠጥ የውጭ ማንነትን ለመጫን እየተሰራ የኖረው ደባና ሴራ ያስከተለውን መዘዝ እንዲሁም ወቅታዊ ሀገራዊ ለውጡን በተመለከተ ቃለ ምልልስ አድርገናል።ይከታተሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡-የምስራቅ አፍሪካ ጂኦ ፖለቲክስ በአሁኑ ሰዓት በፍጥነት በመለወጥ ላይ ይገኛል።እንዴት ያዩታል?
ዶ/ር ጌታቸው፡-ትንሽ የለውጥ ንፋስ አይነት አለ። የአፍሪካ ቀንድ በቀውስ ውስጥ የኖረና የከረመ ነው። በባሕል በኃይማኖት በኢኮኖሚ በንግድ ልውውጥ በዘመናት ታሪክ የተሳሰረ የተቆራኘ በብዙ መንገድ የተሳሰረ ሕዝብ የሚኖርበት አካባቢ ነው። በሁለት ክፍለ ዓለም መካከል ያለ መካከለኛውን ምስራቅና፤ ምስራቅ አፍሪካን የሚያገናኝ ነው።ቅኝ ግዛት እስከመጣበትና ጠረፎች(ድንበሮች) እስከተፈጠሩበት ግዜ ድረስ የተያያዘ የተቆራኘ ሕዝብ ነበር።በዘመናት አብሮነት እርስ በእርሱ እየተጋባ እየተዋለደ እየተጣላ እየታረቀ የኖረ ሕዝብ ነው።ከእኒህ መካከል በምስራቅ አፍሪካ ዋናዎቹ ቡድኖች ኩሼቲክ ግሩፕ ስለሆኑ ያው ኦሮሞና ሶማሌ አለ።ባንቱ ግሩፕስ አሉ።ሌሎቹም ቢሆኑ በጣም እርስ በእርሳቸው ተጋብተው ተዋልደው ተዛምደው ሳይለያዩ የኖሩ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቅኝ ግዛት ስር እስከወደቁበት ግዜ ድረስ ታላቅ ሕብረት በመፍጠር፤ እርስ በእርስ በመስራት በሰላም፤ በንግድ ጥበቃ፤ በሀብት ክፍፍል ላይ የላቀ ትብብር ነበራቸው።በነዚህ መሰረታዊ መነሻዎች ይሄ ሕዝብ አንድ አይነት ሕዝብ ነው ማለት እንችላለን።ብዙ የተሳሰሩ ባሕላዊ እሴቶች ያሉት ነው።የአፍሪካ ቀንድ እንደዚህ ነበር ፡፡
ከቅኝ ግዛት በኋላ ይሄ ሕዝብ በብዙ ምክንያቶች እንደ ቀድሞው አንድ ላይ ሊኖር አልቻለም፡፡አንደኛው በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ነው።ገለልተኝነትም ቢኖር በመሳተፍም ሆነ አንዱን በመደገፍ ቢቆም በውጭው ኃይልና በፖለቲካችንም ምክንያት አካባቢው በትርምስ እንዲኖር ተገዷል።በ1990ዎቹ ውስጥም አዲስ ነገር ይመጣል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።ምንም አልታየም።
በኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው ለውጥ ቀድሞ ያልነበረ ያልታየ አዲስ ክስተት ነው።በአፍሪካ ቀንድ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የለውጥ ንፋስ እያየን ነው።ይሄ ለውጥ የተከሰተው ባልተጠበቀ ሁኔታ ነው። ሁለተኛው ምክንያት መካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያለው ቀውስ ነው።ከቀድሞው በተለየ የኃይል ሚዛንን የመጠበቅ ነገር መጥቷል።በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሪጅናል ፓወርስ (አካባቢያዊ ኃይሎች) ናቸው የሚጫወቱት።እዚህ አካባቢ።ኢራን፤ ሳኡዲ አረቢያ፤ እነ ኩዋታር ገልፍ ስቴት የምንላቸው በጣም እያደጉ ያሉት አሉ።የነዚህም ተጽእኖ አለ።የእነኚህ ግጭቶችም ለእኛ አደጋ ነበሩ፡፡ ነገር ግን አሁን ስናየው እኛ ሀገር የተቀየረው ነገር ምንድነው ስንል የኤርትራና የኢትዮጵያ መታረቅ ትልቁ ቁልፍ ነው።ምክንያቱም ሶማሊያ ውስጥ ያለው ቀውስ እኛም ያለንበት ነው።ማለትም ኢትዮጵያና ኤርትራ።ደቡብ ሱዳንም ከተባለ ያው ነው።አካባቢያዊ (ሪጅናል) ነው ችግሩ።
ይሄን ችግር ለመፍታት ከተፈለገ አካባቢያዊ የሆነ መዋቅር ያስፈልጋል(ሪጅናል ፍሬም ወርክ)።ይሄን ነገር ስናየው ዶ/ር አቢይ ያመጣቸው ነገሮች አንደኛ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኤርትራ ጋር ያደረገው የሰላም ስምምነት በአካባቢው ያለውን ነገር ትንሽ አስተንፍሶታል ማለት ይቻላል። በአረቢያን ፔኒንሱላ በኩል የመንም ያለው ቀውስ አንዳንዶቹን ሀገሮች ኢትዮጵያ ገለልተኛም ሆና ከእነሱም ጋራ ያለውን ግንኙነት የማጠናከሩ ነገር ከሳኡዲ አረቢያና አረብ ኢምሬትስ ጋር የሚያደርጉትን ነገር ስናይ በእዚህ አካባቢ የኃይል ሚዛኑ እየተቀየረ ነው፡፡ በአረቦቹና በሌሎቹ መንግሥታት ቻይና ጭምር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወደቦችን የመያዝ ነገር እጅግ ያሰጋል።ምክንያቱም አሁን ሽሚያ ላይ ናቸው።ምንድነው የሚመጣው ነው ጥያቄው።የተለያየ ሀገር ሠራዊት ነው ያለው።ፈረንሳይ፤ አሜሪካ፤ ቻይና፤ ቱርክና ሌሎችም በቀንዱ አካባቢ የጦር መርከቦቻቸውን አከማችተዋል።የሌለው የለም።በአግባቡ ካልተያዘ ይሄን ስናይ ለእኛም አደጋ እንዳለ በገሀድ ያሳያል።
አዲስ ዘመን፡-የአፍሪካ ቀንድ ብዙ የውጭ ሀገራት ፍላጎቶች ያሉበት አካባቢ ስለሆነ እጣ ፈንታው ምን ሊሆን ይችላል ይላሉ ?
ዶ/ር ጌታቸው፡- በአካባቢው ያሉ ሀገራት የላቀ ትብብር ያስፈልጋል።የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ይሄንን የላቀ ትብብር የማያደርጉ ከሆነ ለእነሱም ለሕዝቡም ችግር ነው።የተለያዩ የውጭ ፍላጎቶች ስላሉ።እዚህ ላይ የበሰለ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተመሳሳይ አቋም ወስደው በሚመጡት ነገሮች ላይ እንደ በፊቱ ሳይከፋፈሉ ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ የግድ ያስፈልጋቸዋል።በጣም የጠነከረ የአፍሪካ ቀንድ የእርስ በእርስ ትብብርና ውህደት ያስፈልጋል።ቢቻልም በፖለቲካ ጭምር።
እነዚህን የሚታዩትን ያንዣበቡ አደጋዎችና በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችን ሊቀንስልን የሚችለው ይሄ ነው።ምክንያቱም አንድ ሀገር ያለው ሕዝብ ሌላም ጋ አለ።መሪዎቹ እርስ በእርስ የሚግባቡ አይነት ከሆኑ፤ ሕዝቡ ችግር የለበትም። መደበኛ ያልሆነ ንግድ አለ።ሌሎችም እየተካሄዱ ነው።እስከ አሁን ድረስ ያለው ችግር የመሪዎች ይመስለኛል።ጥገኝነቱ አለ።ጎራ ለይቶ የመሄድና ከፍተኛ የውጭ ተጽእኖ አለ።ችግር የሚፈጥረው መሪዎቻችን ጉዳዩን በአግባቡና በጥንቃቄ አለመያዛቸው ነው።የአካባቢው ሕዝቦች ችግር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡-በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የውጭ ኃይላት ተጽእኖ በብዛት አለ፤ ይሄንን እንዴት ያዩታል?
ዶ/ር ጌታቸው፡- ከፍተኛ ተጽእኖ አለ።መሪዎቹ እዚህ ላይ ጥሩ ዲፕሎማሲ ካላቸው ሕዝባቸው ችግር የለበትም።ተንቀሳቅሶ የሚኖር ነው።እያንዳንዱ ዘመድ አለው።ሶማሊያም ኬንያ… ዘመድ አለው።እንደዚህ እርስ በእርሱ በባሕል በቋንቋ የተሳሰረ አካባቢ መከፋፈል አልነበረበትም።ይሄ የተደረገው ወይንም የሆነው መጥፎ ፖለቲካ ስላለ ነው።
አዲስ ዘመን፡-የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ከአካባቢው አንጻር ሲታይ አሁን በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው ? ትላንትና ዛሬን እያነጻጸሩ ቢያስረዱን ?
ዶ/ር ጌታቸው፡- እኔ ፖለቲካል ሳይንስ አይደለም ያጠናሁት።ግጭቶቹን ከሕዝብ አንጻር ስናይ ለምሳሌ አፋር ምንድነው ጥቅሙ ካልን አፋር ላይ ስላጠናሁ የምለው አለኝ።ይሄ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው።አፋር እንደምታውቁት የራሱ የሆኑ መሪዎች አሉት።በሁሉም መንገድ የተባበረ በአንድ የቆመ ሕዝብ ነው።በኃይማኖት በአገዛዝና በአስተዳደርም።ነገር ግን የአፋርን ሕዝብ የከፋፈለው ፖለቲካው ነው።በቱሪዝም በኩል እዛ አካባቢ የሚሄድ ሰው የለም፡፡ይጠለፋል።እነኚህን ነገሮች ሁሉ ሊቀንስ ይችላል።ሕዝቡ መንቀሳቀስ ከቻለ፤ በንግድ ከብቶቹን ይዞ ከአንድ ቦታ ወደሌላ የሚሄድ ከሆነ እነኚህ ግንኙነቶች ከጠነከሩ ችግሮች አይኖሩም፡፡
አፋር ድንበር አካባቢ ያሉትን ሰዎች በተመለከተ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላም ይሄንን ማእከል ማድረግ አለበት።ምክንያቱም እነሱ ናቸው መጠቀሚያ የሚሆኑት።ለውጭ ኃይልም ሽፍታም ለሚባለው ሌላም ነገር የሚመጣው በዚያው ነገር ነው።ይሄንን እንቅስቃሴና እርስ በእርስ የመገናኘት ጉዳይ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ከንግድና ከመሳሰለው ጋር ከማጠናከሩ ጋር ሌሎቹ ነገሮች የሚስተካከሉ ይመስለኛል።ለምሳሌ በጋራ ከቆሙ አረቦቹ እነሱን አይከፋፍሏቸውም።አንዱ ይሄ ነው።እንደሚታወቀው እነ ግብጽ ሁሉ የራሳቸው ፍላጎት አላቸው።ለዛ ነው ግብጽ እዚህ አካባቢ ሁልግዜ የምትሯሯጠው፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ሰመረ ማለት ሰላማዊ የሆነው የሕዝብ ለሕዝብና የመሪዎች ግንኙነት ከጠነከረ አንደኛ ለእድገታቸው ጥሩ ነው ፡፡የተቀዛቀዘው ንግድ ገበያው ይሞቃል፡፡ ትንንሾቹ ግጭቶች ሁሉ በቀላሉ የሚፈቱበት ሁኔታ ይኖራል።ይፈጠራል።ለዚህ ሁሉ ይጠቅማል። የኤርትራው በተለይ ለአፍሪካ ቀንድ ጭምር ማለት ነው።በእነሱ ምክንያት ሶማሊያም ሰላም ይመጣል ብለን እናስባለን።ደቡብ ሱዳን አሁን ያለው ግጭት እንደዚህ ነው፡፡እነኚህን ሁሉ ሊያሳካ ይችላል።ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መጥተው ችግሮቻቸውን በመወያየትና በመነጋገር የሚፈቱበት አካሄድ ሕዝቦቻቸው የሚገናኙበትን እድል ይፈጥራል ብዬ ነው የማስበው።ትልቁ ለውጥ የምለው ይሄ ነው።እሱም ደግሞ ቀይሮታል።ለምሳሌ ከአረቦቹ ጋር ብዙ ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረው ግንኙነት በዚሁ ምክንያት ቀዝቃዛ ነበር።አሁን ግን እኛም አንበላም ማለት ነው።ሕዝቡም ለብዙ ነገሮች አይጋለጥም።እርስ በእርስ ተመካክረው የሚሰሩ ከሆነ የጸጥታ ችግሮች ይቀንሳል ብዬ ነው የማምነው፡፡
ሌላው ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው የሚነሱ ትንንሽ ነጻ አውጪ ነኝ የሚሉ ቡድኖች ቦታ አይኖራቸውም።ምክንያቱም ችግሮችን በጋራ ልንፈታ ስለምንችል።ሶማሊያ ውስጥ ያለው ችግር የኢትዮጵያ ችግር ነው።እዛ ያሉት ሰዎች እዚህ ካሉ ሰዎች ጋር የተገናኙ ናቸው።ኬንያ ያለባት ችግር የእኛም ጭምር ነው ብለን ከወሰድን እነዚህን ችግሮች በጋራ መፍታቱ ላይ በተለይ ኢጋድ አሁን ባለበት ሁኔታ ላይ ቢጠነክር ሕዝቦቹ ላይም መሰረት ያደርጋል፡፡ሕጋዊ የሆኑ መሪዎች ሕዝብ የሚፈልጋቸው መሪዎችም ከሌሉ ችግር ነው።የውጭ ኃይል የሚያስመጣው መሪ የሆነው ምሁር ነው።እነዚህ ነገሮች በተባለው መንገድ የሚሰራባቸው ከሆነ አሁን በሀገራችን የምናየው የለውጥ ንፋስ ለአፍሪካ ቀንድ በጣም ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ። እንግዲህ ይሄ የመሪዎችን ጥንካሬ ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡-አፍሪካም እኛም ወደ ጥንታዊ ማንነታችን ባሕላችን እውቀታችን ለመመለስ ምን መደረግ አለበት ብለው ያምናሉ ?
ዶ/ር ጌታቸው፡- ምስራቅ አፍሪካንም ሆነ ሌሎች አፍሪካ ሀገራትን ከወሰድናቸው የሰዎችና የሀሳቦች መንቀሳቀስ መኖር አለበት።ከዚህ በፊት የነበረው እንደዛ ነው።ድንበሮች ተብሎ የማይነኩ ድንበሮች አልነበሩም።ብዙ ግዜ እነዚህ ድንበሮች ይለዋወጣሉ።አንዱ ሰው ከአንዱ አካባቢ ወደቤተሰብ ወደ ሌላኛው ቢሄድ ድሮም ተቀባይነት የሚያገኝበት ባሕል አለ።ይህም ማለት ጦርነትም ቢኖር የተሸነፈውን ወደራስህ ታደርጋለህ ታስገባዋለህ እንጂ አታስወጣውም፡፡
አታገለውም።ይሄ ሰብአዊነት ወንድማማችነት የሚለው መርህ አፍሪካ ውስጥ ትልቁ ባሕል ነው።ትልቁ መሰረታችን ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ያለው ሌላው ትልቁ ባሕል ያለውን የመካፈል የጋርዮሽ ባሕል ነው።አንዱ በተቸገረበት ግዜ ሌላውን የማስጠለልና ያለህን ነገር የመካፈሉ ባሕል ትልቁ ነው።ባሕል ላይ ሰው ላይ ማእከሉን ያደረገ አስተሳሰብ ነው መኖር ያለበት።ካፒታሊዝም ከቅኝ ግዛት ጋ የመጣ የምእራባውያን ባሕል ነው።ግለኝነት ላይ ያተኩራል።የእኛ የጋራ የሆነ ባሕል ነው። ስለተፈጥሮ ስለዩኒቨርስቲ ስናስብ ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘ እንጂ ሰው ብቻውን ሆኖ የሚያደርገው የለውም።የአየር ንብረቱ አካባቢው መጠበቅ አለበት።የሞራልና የመንፈስ ዓለም የምንለው ነገር በአፍሪካ ባሕል እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
በአፍሪካ መንፈሳዊነት አለ።በአፍሪካ ግለኝነት በአብዛኛው ይወገዛል።መሪም ሀብታምም ቢሆን ግለኛና ለሌላው የማያካፍል ከሆነ ጥሩ ስላልሆነ ታወግዘዋለህ።ጥሩ መሪ ሆኖ የማይመራ ከሆነ ችግር ነው።ያ ማለት በዛ ግዜ ገዢዎች ሳይሆኑ መሪዎች ነበሩ።ከሕብረተሰቡ የተዋሀዱ የተቀላቀሉ ሌላውን ገለልተኛ የማያደርጉ መሪዎች ነበሩ።አሁን ለምሳሌ ምዕራባዊ ዲሞክራሲ ሀምሳ ለአንድ የሚባለው ሌላውን የሚያገል ሳይሆን ተግባብተህ አሳታፊ ሁነህ ብዙ ግዜ ስምምነትን /ኮንሴንሰስ ቤዝድ/ በሆነ መልኩ ነው የሚሰራው።እኛም ዘንድ እንደዛ አለ፡፡
ሽምግልና ላይ የምናየው ነው። መጨረሻው ድረስ ሄደን አሳምነን ያጠፋው ሰው ይቅር ብሎ ኃይማኖትን ተጠቅመን ከዛ በኋላ አናስወጣውም።ድሮም የነበረ ነው።ማግለል ሳይሆን ማስገባት ማቀፍ ነው የሚባለው አፍሪካዊ ባሕል ነው፡፡ አንዱ ሌላውን የመማር(ይቅር የማለት) ባህልን ካጠፋ ደግሞ ጥፋቱን በትክክል ነግረሀው ቅጣት ሲቀጣ እንዲጠፋ ሳይሆን እንዲማር ነው የሚደረገው። እነዚህ ባሕሎች ኬርና፤ ገዳ ሥርዓት ላይ አሉ።
ምዕራብ አፍሪካ ብንሄድ እንደዛው ነው።አፍሪካዊ ነው።አንዱ ሌላው ጋ ከመጣ ያለው ነገር አይከለከልም።መሬት የአያት ቅድመ አያቶች፤ የእግዚአብሄር፤ ከዛ ውጭም አሁን ያሉት ሰዎች የሚጠቀሙበት ነው።ድሮም የኖሩት አያቶቻችን ተጠቅመውበታል።ወደፊት ደግሞ ለሚወልዱትም ጭምር ነው።መሬት የማንም አይደለም።ይሄ ጽንሰ ሀሳብ ራሱ አፍሪካዊ ነው።ለዛ ነው አሁን ከሌሎቹ ጋር የማይሄደው፡፡ በአፍሪካዊ እሳቤ ስትሄድ ለትምህርቱ ዋናው ሲስተም መሰረቱ ቤተሰብ ነው።ቤተሰብ ብዙ ነው የሚያስተምርህ።አንተ ገበሬ ከሆንክ ስለግብርናው የሚያስተምርህ ቤተሰብ ነው።አንተ አርብቶ አደር ከሆንክ የሚያስተምርህ ቤተሰብህ ነው።የምትማረው ነገር ደግሞ ከመሬት ጋር ተያይዞ ነው።የት የት እንደምትሄድ፤ የትጋ ጥሩ ግጦሽ እንዳለ ከልጅነትህ ጀምሮ ነው የሚያስተምሩህ። ይሄ ትልቅ ትምህርት ነው።ከባቢ አየሩን ታውቃለህ፤ የት የት መሄድ እንደሌለብህ ታውቃለህ።
ከተግባራዊ እውቀት ጋር የተያያዘ ነገር ነው፣ በእድሜህ የምትማረው ማለት ነው። ስለዚህ አንደኛ ሀገርህን ሁለተኛ ባህልህን አውቀህ ነው የምታድገው ማለት ነው።ስታገባ እውቀቱ አለህ። ከ12 ወይንም ከ15 ዓመት በኋላ ስታገባ አንተ ትምህርትህን ጨርሰሀል ተመርቀህ ነው የወጣሀው ከቤተሰብ የተማርከውን በተግባር መስራት ችለሀል ማለት ነው።እነኚህን ነገሮች በምናይበት ግዜ ይሄ ባህላዊ የሆነው እውቀት ወይም የትምህርት ሥርዓት የምንለው አለ።እንደገናም ማሕበረሰቡ ጋ ስትሄድ የምትማረው አለ፡፡
በሀይማኖት በኩል በሌሎችም።ስትሄድ ሰው ሁነህ ትወጣለህ ማለት ነው። አሁን እኛ እያወጣነው ያለው ሥርዓት ትምህርቱ ላይ መጀመሪያውኑ ኋላቀር ነን ብለን ነው የምንጀምረው።የምናስተምረው።የእኛ ባህል ዋጋ የለውም ብለን ራሳችን ስለምንጀምር ማንነታችንን ክደን ቅድመ አያቶቻችን የኖሩበትን ሁሉ ስተን፤ አሁን የሌላ ባሕል ነው የምንማረው።በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ቀውስ ያመጣው አንዱ የትምህርት ሥርዓቱ ብልሹነትና በራስ ማንነት ላይ ያልተመሰረተ መሆኑ ነው።ሁሉ ቦታ ስንሄድ ግጭቶች ነው የምናየው።ምክንያቱም የተማርነው ነገር ከሕብረተሰብ ፍላጎት ጋር በፍጹም አይሄድም።ስለ እርሻ የምንማረው ሌላ ነገር ነው።
እዚህ ግን የገበሬ ልጅ የሚማረው እያንዳንዷን ሰብል መቼ እንደሚተክል፤ ምን ያህል ግዜ እንደሚፈጅ ወቅቶቹን ይማራል።ምን መትከል እንዳለበት ያውቃል።ይሄን እውቀት ከግብርና ኮሌጅ የምታገኘው አይደለም።ልትንቀው ልታጣጥለውም አትችልም።ያ ማለት ፒኤችዲ አግኝተህ ስትመጣ አባትህን ለማጥፋት ነው የምትመጣው ማለት ነው። በሀገር ውስጥ ለዘመናት የኖረውን በባህል ውስጥ የቆየውን አሰራርና ሥርዓት ለመንቀል ነው።ስለዚህ አሁን ወደቀድሞው ወደራሳችን ተመልሰን እንዴት ነበረ እነዚህ ሰዎች ሰርቫይቭ ያደረጉት፤ ምን አይነት ቴክኖሎጂ ብናመጣ ይሄን ያሻሽላል የሚል ከእኛ ጋር የሚዋሀድ ነገር አላመጣንም።በትምህርትም ብንሄድ።ለዚህ ነው የቅኝ አገዛዝ መምጣት እኛ ራሳችንን እንድንክድ አድርጎን ችግር መፍቻ የምትላቸው ነገሮች ችግር መፍቻ ሳይሆኑ ችግሩን ለማባዛት የሰሩበት።መጀመሪውያንም እነሱን ከጠየቅን ምክንያቱን እነሱም አያውቁትም።በእነሱ መሪነት የተቀረጸው የትምህርት ሥርዓት ራሱ ልጆቼን ከሕብረተሰቡ አውጥቷል።
አግልሏል።ተመለስ ብትለው አይሄድም።ያ ባሕላዊ ትምህርት ላይ የተማረው ግን ይመለሳል።ምክንያቱም መኖሪያው ስለሆነ፡፡ያንን አይነት ትምህርት ነው ማምጣት ያለብን።ለዛ ነው የእኛ የትምህርት ስርአትና ጭንቅላታችንም የነጭ ባሪያ ቅኝ ግዛታዊ አይነት ስለሆነ በአካል ቅኝ ባንገዛም ፤ የባርነት እሳቤ (ሜንታሊቲ)፤ ራሳችንን የመናቅ አስተሳሰብ ስላለ በዛ ነው የምንሄደው። ፈረንጅ ምናምን እንላለን።የፈረንጅ ሀሳብን አድናቂ አጨብጫቢ በመሆን የፈረንጅ እኮ ነው እንላለን።ፒኤችዲ (ዶክተር) እንዲሁም ፕሮፌሰር የምትለው ነጮችን ፈረንጆችን ሳይጠቅስ አያወራም።ስንትና ስንት ታላላቅ ቀደምት የነበሩ በብዙ ዘርፍ የተመራመሩ ዓለምን ቀድመው የነበሩ ያስደመሙ የእኛዎች ነበሩ።እሱ የት እንዳደገ ስለማያውቀው ነው እንጂ እዚሁ ከእኛ ሀገር የምትጠቅሳቸው በርካታ ነገሮች አሉ።አካባቢ ጥበቃ፤ ልጆች አስተዳደግ፤ ሌሎችም ፍርድና አስተዳደር ላይ የምናያቸውን ነገሮች ማንሳት ይቻላል።
ሌብነትን የምንጸየፈውና መጸየፍ አለብን የምንላቸው ነገሮች ሁሉ የመጡት በዛ ምክንያት ነው።ዋናው ምክንያት ከውጭ የመጣው ሥርዓት የእኛ ሥርዓት ስላልሆነ እኛን ሊቀይር አልቻለም።200 ዓመት አስተምረውናል።ለምን አንቀየርም? በፍጹም ባሕላዊ መሰረት ስለሌለውና የበቀለበትም ቦታ ሌላ የሆነን ነገር አምጥተን ስለተከልን ነው አልበቅልም ያለው።ስለዚህ አሁን መፍቻችን የሚሆነው ጥሩ መፍትሄ እናምጣ ካልን እዚህ ሆኖ ሕብረተሰቡ መካከል የሚማር ይሄን አድንቆ ሌላ የሚጨምር ካልሆነ በስተቀር ጥሩ መሪም ልታመጣ አትችልም።ምክንያቱም የሚነግርህ ነገር ከአንተ ጋር አይሄድም።ለዛ ነው የአፍሪካ ትልቁ ችግር የሆነው፡፡ ኤሽያ ውስጥ ለውጥ ያመጡት የተሳካላቸው ለምንድነው ከተባለ ቅድመ አያቶቻቸውን ያከብራሉ።
ግን ሳይንስ ተምረዋል።በፊት ያለውን ጭራሽ አላጠፉትም።እንዳለ ነው።አለባበሳቸውን አበላላቸውን አልቀየሩም። ጨምረውበት ቴክኖ ሎጂ አስገብተዋል። ጃፓንም ብትሄድ በራሱ ቋንቋ ነው የሚሰራው።ግን ደግሞ እንግሊዝኛ እኩል ነው የሚናገሩት።አንደኛ ቋንቋ ማለት ባህልህ ነው። ባህልህ ደግሞ ያገኘኸውን ስልጣኔ ሁሉ የያዘ ነው።ቋንቋው ጠፋ ማለት አልቆልሀል፤ ያው አንድ ትልቅ ስልጣኔ እንደገደልክ ነው የሚቆጠረው።ትንሽም ቋንቋ ብትሆን እዛ ውስጥ ያሉ እውቀቶች አሉ።ስለሞራሊቲና እግዚአብሄርን ስለመፍራት፤ ይሉኝታ፤ ታላቅን የማክበሩ፤ እነዚህ አሁን ወጣቱን ትውልድ ማስተማር አለብን የሚባለው ድሮም አለ።እነሱን አላሳደግንም።ቻይና ገዝፋ እንደዚህ ስትገዳደር የምናየው የራሷን ባሕል መሰረት አድርጋ የሚጠቅመውን ብቻ ቀድታ ስለተጠቀመች ነው።ለእዛ ነው አሁን አሜሪካንን እየበለጠች ያለችው።አፍሪካ ውስጥ ምዕራባዊ ስልጣኔ ማለት እራስህን ማጥፋት፤ እራስህን መሳት ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን፡፡
ዶ/ር ጌታቸው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በወንድወሰን መኮንን