ፍሬ ነገሩ
ኢል-ናንሲ አስመጪ የሚሰኝ ድርጅት እና ቫዮ አውቶሞቢል ማኑፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መካከል ሥምምነት ነበረ። ነገር ግን ሥምምነቱ ሳይከበር ቀርቶ መካካድ እና ቃል አለማክበር ተፈጠረ የሚል እሰጣ ገባ መጣ። በዚህ እሰጣ ገባ ውስጥ ኢል- ናንሲ አስመጪ የሚባለው ድርጅት “ለቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር 836 የሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) የፊት መስታወት ከውጭ ሀገር አምጥተናል። በውላችን መሰረት ካስረከብን በኋላ ክፍያ አንፈጽምም ብለውናል። ይህ ድርጊት ደግሞ ዓይን ያወጣ ክህደት ከመሆኑም በላይ ሀገሪቱንም ማግኘት የሚጠበቅባትን ጥቅም እንድታጣ የሚያደርግ ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።
ቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እያንዳንዳቸውን ንብረቶች በባለሙያዎቹ በኩል ቆሞ ቆጥሮ ተረክቧል። መረከባቸውንም በፊርማቸው ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በርክክቡ ወቅት የዓይን እማኞች እና በቂ የምስል ማስረጃዎች አሉ ብለዋል። ታዲያ ይህ ሁሉ ግልጽነት የተሞላው ርክክብ ከተፈፀመ በኋላ ክፍያው ላይ ወገቤን የሚለው አካሄድ አግራሞት የሚጭርና አግባብነት የሌለው ስለመሆኑ ያብራራሉ። ሥራው እንዲፋጠን ሲያጣድፉ እንደነበርና በክፍያ ላይ ግን ማጭበርበር የተሞላው አካሄድ መከተላቸው እጅግ አሳዛኝ ስለመሆኑ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።
ከሥምምነቱ ተፈፃሚ የሆነው ምን ነበር?
ኢል-ናንሲ አስመጪ ድርጅት እና ቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መካከል በተደረገው ሥምምነት መሠረት የተወሰኑ ውሎች መስመር ይዘዋል። በውሉ መሠረት ክፍያዎች የተፈፀሙ ቢሆንም በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ክፍያ አለመፈፀም ይስተዋላል። በዚህም መሠረት ኢል-ናንሲ አስመጪ ድርጅት ውል ከተዋዋለ በኋላ ድርጅቱ ግማሽ ሚሊዮን ብር ብቻ መቀበሉን ይገልፃል።
ቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር የግል ማህበር ይህን ክፍያ ከፈፀመ በኋላ ግን ቀሪውን 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ለመክፍል ፈቃደኛ አልሆነም። ለዚህም ደግሞ የተለያዩ ምክንያችን የሚጠቅስ ሲሆን በውላችን ወይንም በሥምምነታችን መሠረት ለመክፈል ተጨማሪ ወጪዎች አውጥተናል፤ እነዚህ ነገሮች በደንብ ሊጤኑ ይገባል የሚለው የመጀመሪው የመከራከሪያ ነጥብ አድርጎታል ቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር። ነገር ግን ወጪው ለምን እንደወጣ እና ስንት እንደሆነም በግልጽ ለማሳወቅ አልፈቀደም።
ኢል-ናንሲ አስመጪ በበኩሉ፤ በውላችን መሰረት ከውጪ የሚመጡ ንብረቶችን በሙሉ በማምጣት በህጋዊ መንገድ ርክክብ መፈፀሙን እና ለዚህም ደግሞ በፊርማ የተረጋጋጠ መረጃ እንዳለው ያብራራል። ይሁንና በክፍያ ሂደቱ ላይ ግን የተወሰነ ገንዘብ ከተከፈለ በኋላ ሌላው ለመክፈል የተለያዩ ሰበቦችን መፍጠር እንደተጀመረ ይናገራሉ። ለአብነትም ሥራ አስኪያጁ ከውጭ ሀገር አልመጣም፤ ቼክ ላይ የሚፈርመው አካል ዛሬ ቢሮ አልገባም፤ ሌላ ቦታ ስብሰባ ሄደዋል የሚሉና ሌሎች ሰበቦችን ሲደረድሩ መቆየታቸውን ሌሎች የማይዋጡ ምክንያችን ማስቀመጣቸውን ያነሳሉ።
ቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃ/የተ/የግ/ማህበር ምን ፈለገ?
በመጀመሪያው ዙር ከከፈለው 500ሺ ብር ውጪ ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለማጭበርበርም ሌሎች ዘዴዎችን ስለመጠቀሙ የኢል-ናንሲ አስመጪ ሥራ አስኪያጅ ኤልሳቤት ፋንታሁን ይናገራሉ። ከእነዚህም የማዘናጊያ መንገዶች መካከል ንብረቱን የተረካከብንበት ደረሰኝ ከሰጣችሁን በኋላ ክፍያ እንፈፅማለን የሚል ሲሆን፤ ኢል-ናንሲ አስመጪ ግን ደረሰኙን የምንሰጠው ሙሉ ክፍያ ሲፈፀም አሊያም ደግሞ እጅ በእጅ ክፍያ ሲፈፀም እንጂ 500ሺ ብር ብቻ ተከፍሎ ቀሪው 1ነጥብ8 ሚሊዮን ብር እያለ ደረሰኝ አንሰጥም የሚል ምላሽ ሰጥቷል። ታዲያ ደረሰኙን ቀድሞ ለመቀበል መቻኮሉ አንዱ ክፍያ ላለመፈፀም የነበረ የማጭበርበሪያ መንገድ መሆኑን ያመለክታሉ።
ኢል-ናንሲ አስመጪ ምን ይላል?
ኢል-ናንሲ አስመጪ እንደሚያብራራው፤ ቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሥምምነቱ መሰረት ክፍያ ለመፈፀም ፈቃደኛ ያልሆነው ከማጭበርበር የመነጨ ጥልቅ ፍላጎት እንጂ ሌሎች በቂ ምክንያቶች እንደሌሉ የሚናገሩት የኢል-ናንሲ አስመጪ ዋና ሥራ አስኪጇ ኤልሳቤት ፋንታሁን ናቸው። በተደጋጋሚ ደብዳቤዎች ቢፃፍላቸውም ጉዳዩን ቸል ብለውታል። ሌላው ቀርቶ በአካል ሄደው ሲያነጋግሩ እንኳን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም ሲሉም ይወቅሳሉ።
ደብዳቤዎች ምን አሉ?
በዚህ የሃሳብ አለመግባባቶች ውስጥ ኢል-ናንሲ አስመጪ የተባለው ድርጅት በርካታ ደብዳቤዎችን እና ማስጠንቀቂያዎችን ለቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፅፈዋል። በደብዳቤዎቹም ውስጥ ተደጋጋሚ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን ሁለቱም እንደ ቢዝነስ ሰዎች አቀራራቢ ሃሳቦችን ለማሳየት አልሞከሩም። ለአብነት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዝግጅት ክፍል ከደረሱ መረጃዎችና ደብዳቤዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
የመጀመሪያው ደብዳቤ
ኢል-ናንሲ አስመጪ 06/01/2014 ዓ.ም በቁጥር ኢልህ7/2014 ለቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ‹‹ጉዳዩ፡- ክፍያ እንዲፈፀምልን ስለመጠየቅ›› በሚል የተፃፈ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው ድርጅታችን ኢል-ናንሲ አስመጪ ለድርጅታችሁ ቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃ/የተ/የግ/ማህበር 38 ሳጥን እያንዳንዱ 22 ፍሬ በጠቅላላ 836 (ስምንት መቶ ሰላሳ ስድስት) (WINDSHIED GLASS) በ26/08/2021 ዱከም በሚገኘው መጋዘናችሁ መረከባችሁ ይታወቃል። በውላችን መሰረት ዕቃው መጋዘን እንደተራገፈ ክፍያ እንደምትፈፅሙ በተዋዋልነው መሰረት የሙሉ ክፍያ ደረሰኝ እንዲቆረጥላችሁ በጠየቃችሁን መሰረት በደረሰኝ ቁጥር 00000015 ከተቆረጥላችሁ በኋላ ግን ሙሉ ክፍያውን ለመክፈል የገንዘብ እጥረት እንዳለባችሁ አሳውቃችሁናል።
የተቆረጠው ደረሰኝ የሙሉ ክፍያ ስለሆነ፤ የደረሰኝ ቁጥር 00000015 ቮይድ (void) ሆኖ ቅድመ ክፍያ የከፈላችሁት ገንዘብ 528,000 (አምስት መቶ ሃያ ስምንት ሺ) ሆኖ ጭማሪ በምትከፍሉት ገንዘብ ልክ ደረሰኝ እንዲቆረጥላችሁና ያልከፈላችሁበትን ዕቃ ወደ ድርጅታችን ተመላሽ እንድታደርጉ ብንጠይቅም መልሳችሁ ግን እቃውን ከተረከባችሁበት ቀን ጀምሮ እስከ 15 ቀን እንከፍላለን ብላችሁ በሰጣችሁን ቃል መሰረት ብንጠብቅም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም።
አሁንም ክፍያውን እያዘገያችሁ ስለሆነ መልሳችሁን በሁለት ቀን ውስጥ ማለትም እስከ 08-01/2014 ዓ.ም እንድታሳወቁን ወይንም ክፍያውን ብር 1,590,118.02 (አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ዘጠና ሺህ አንድ መቶ አስራ ስምንት ብር 02%) በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000256056457 ኤልሳቤጥ ፋንታሁን እንድትፈፅሙልን እያሳወቅን
ከዚህ ቀን ካለፈ ግን ወደ ህግ ለመሄድ እንገደዳለን ሲል የማሳሰቢያ ደብዳቤ ለቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፅፏል። ግልባጩም ለቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፋይናንስ ክፍልም እንዲደርስ መደረጉን ከደብዳቤው መረዳት እንችላለን።
ምላሽ ያዘለው ደብዳቤ
ለኢል- ናንሲ አስመጪ መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥር ቫዮ/ጀነ/001/14 ዮናስ ገብረእግዚአብሄር ምክትል ሥራ አስኪያጅ የተፃፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል። ለድርጅታችን ላቀረቡት 836 የሦስት እግር ተሽከርካሪ የፊት መስታወት ያቀረቡትን ክፍያ በተመለከተ በደብዳቤ ቁጥር ኤል/17/2014 መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ መጠየቅዎ ይታወሳል። ሆኖም የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ባለመኖራቸው በወቅቱ መመለስ አልቻልንም። ባለፈው ሳምንት ባደረግነው ስብሰባ እና ጥልቅ ጥናት መሰረት ባቀረቡት የክፍያ ጥያቄ በሚከተለው መሰረት እንዲያስተካክሉ አናስታውቃለን።
አንደኛ፤ ባቀረቡት የክፍያ ጥያቄ ውስጥ
እንዳካተቱት በቅድሚያ ክፍያ ብር 528.000.00 (አምስት መቶ ሃያ ስምንት ሺህ ብር) የከፈልንዎት ሲሆን በተጨማሪ ያቀረቡት ዕቃዎች ድርጅታችን መጋዝን ከመድረሳቸው በፊት ድርጅታችን ያወጣቸውን ወጪዎች አላካተቱም።
ሁለተኛ፤ እንዲከፈልዎት የጠየቁት ክፍያ ከድርጅታችን ስሌት ጋር ያልተጣጣመ ከመሆኑም በላይ የእቃዎቹ ዋጋ ትክክል ባለመሆኑ የጠየቁት ክፍያ አልተቀበልነውም።
ሦስተኛ፤ ላቀረቡት ዕቃ ደረሰኝ ያዘጋጁ መሆኑን ቢገልፁም ለድርጅታችን ካለማቅረብዎም በላይ እቃውን ለድርጅታችን ገቢ ያደረጉበት ሰነድ አላቀረቡም እንዲሁም ደረሰኝ መዘጋጀት ያለበት በጋራ በተሰላ ስሌት መሰረት መሆን አለበት።
አራተኛ፤ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነው የተዘጋጀው ደረሰኝ ተስተካክሎ ለድርጅታችን ባለማቅረብዎ ተገቢውን የግዥ ወጭ በወሩ ባለማሳወቃችን ለሚደርስብን ኪሣራ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ ለመጠየቅ የማያስችለን መሆኑ እያስታወቅን ለሚደርሰው ኪሣራ ኃላፊነቱን የሚወስዱ መሆኑን እንገልፃለን ሲል ነገሮችን ውድቅ ለማድረግና ህጋዊ አሰራሮችን ያልተከተለ ስለመሆኑም ያስረዳል።
ኢል-ናንሲ የፃፈው ሁለተኛው ደብዳቤ
ለቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግልማህበር‹‹ምላሽ ስለመስጠት›› በሚል የተፃፈ ደብዳቤ ድርጅታችሁ ቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የየግል ማህበር በቀን መስከረም 25 ቀን 2014 በደብዳቤ ቁጥር ቫዮ/ጀነ/001/14 በላኩልን ደብዳቤ መሰረት ክፍያ እንደገና ይስተካከልልን ጥያቄ መላካችሁ ይታወቃል። ስለሆነም እንዲስተካከልላችሁ ካቀረባችሁት ጥያቄ መካከል ለሚለው በሰጡት ምላሽ፤ አንደኛ ከ528,000 (አምስት መቶ ሃያ ስምንት ሺህ ብር) በላይ በተጨማሪ ድርጅታችሁ ያወጣውን ወጪ እንዳለ እስካሁን ያላሳወቃችሁን በመሆኑ አሁንም አለን ካላችሁም በደረሰኝ እንድታሳውቁን የሚል ነው።
ሁለተኛ፤ የእቃዎቹን ዋጋ ከራሳችሁ ደርጅት የተሰጠን የዋጋ ተመን በመሆኑ የዋጋ ቅያሪ በማድረጋችሁ ድርጅታችሁን ተጠያቂ ያደርጋል።
ሦስተኛ በ26/08/2021 ቀን እቃውን ለድርጅታችሁ ያስገባንበትን እና የተቆረጠውን ደረሰኝ ቢሮ ድረስ አምጥተን በሰዓቱ የድርጅታችሁ ምላሽ ግን የሙሉ ክፍያ ደረሰኝ ወስዳችሁ ግማሽ ክፍያ ብቻ ለመክፈል ነው የምንችለው ማለታችሁ የታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 149/2011 መሰረት ሙሉውን ክፍያ ሳትከፍሉ ደረሰኝ መስጠት እንደማንችል ተደንግጓል። ስለዚህ ደርጅታችን የዱቤ ሽያጭ ያልተዋዋለ በመሆኑ ሙሉ ክፍያ ሳይፈፀም የሙሉ ክፍያ ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ የለብንም። በተጨማሪም ከላይ የዘረዘሩትን ችግሮች ለመወያየት በቢሮአችሁ ብንገኝም ተገቢውን ምላሽ የሚሰጠን አካል ስላለገኘን የሚደረስባችሁ ማንኛውም ኪሣራ ድርጅታችን ተጠያቂ እንደማንሆን ከወዲሁ እንገልፃለን ሲል ሃሳቡን ይቋጫል።
ለቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለዝግጅት ክፍሉ የሰጠው ምላሽ
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ስለጉዳዩ በሚገባ ለመረዳትና በተደጋጋሚ ለቫዮ አውቶሞቢል ማንፋክቸረር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተለያዩ ኃላፊዎች በተለያዩ ወቅቶች ስልክ የደወለ ሲሆን በእነዚህ ወቅቶች በዝግጅት ክፍሉ ቀርቦ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛም አልሆኑም።
በስልክ መረጃ እንዲሰጡ ቢጠየቁም ለዚህ ፈቃደኛ አለመሆን ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ጉዳዩ ሲነሳባቸው ስልኮችን በጆሮ ላይ ዘግተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የዝግጅት ክፍሉ ሚዛናዊ የሆነ ሥራ መሥራት አለበት መረጃ ስጡን ለሚለው የማይገናኙ ምክንያቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል። በርከት ላሉ ወቅቶች ደግሞ ስልክ ባለማንሳት ለመረጃ ተባባሪ ሊሆኑ እንዳልቻሉ እንዲታወቅ እንፈልጋለን።
ከዚህም በዘለለ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ሲደወልላቸው ጉዳዩ እኔን አይመለከተኝም ከማለት ውጭ በግልፅ ማንን እንደሚመለከት መግለፅ መናገር አልፈቀዱም። የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ናቸው የተባሉት ህንዳዊ ግለሰብም በተደጋጋሚ ሲደወልላቸው እኔን አይመለከተኝም ‹‹ኢትዮጵያዊ ሠው›› ወክያለሁ በማለት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በተደጋጋሚ ሃሳባቸውን ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ከዚህም በተጨማሪ የድርጅቱ የበላይ ኃላፊዎች ናቸው የተባሉት ግለሰብ ጋር በተደጋጋሚ ሲደወልም ስልክ የማያነሱ መሆኑን መግለፅ እንፈልጋለን።
ህጉ ምን ይላል?
አቶ በፍርዴ ጥላሁን የህግ ባለሙያና ጠበቃ ሲሆኑ በጉዳዩ ላይ በሰጡን ሐሳብና ማብራሪያ መሰረት በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የተደረጉ ሥምምነቶች በራሳቸው ህጋዊ ውል ናቸው ይላሉ። ተንቀሳቃሽ ንብረት ከሆነ የግድ በወረቀት ላይ የሰፈረ ውል ያስፈልጋል የሚሉት አቶ በፍርዴ በመሰል ጉዳዮች ግን የቃል ሥምምቶች፣ የተወራረሱ አሊያም ደግሞ በድምጽ በምስል፣ በፅሁፍ፣ በኢ-ሜል እና ሌሎች መሰል የመግባቢያ መንገዶች የተለዋወጡት መረጃዎችና መልዕክቶች በራሳቸው ከወረቀት ላይ ውል ባልተናነሰ መንገድ ጥቅምና ትርጉም አላቸው ይላሉ።
መሰል ሥምምነቶች በጽሁፍ ውል ቢደገፉ ኖሮ የሚመረጥ ሲሆን ይህም ባይሆን በቃላት ልውውጥ ደረጃ ምስክሮች ባሉበት ቦታ መነጋገራቸው በራሱ በቂ ስምምነት ወይንም ውል ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህም አልፎ በተግባር ዕቃው ወይንም ንብረቱን መለዋወጥ መጀመራቸው እንደ ህጋዊ ውልና በጉዳዩ ላይ ስለመስማማታቸው ይቆጠራል። ይህ ማለት ደግሞ ሁለቱ ድርጅቶች አብሮ ለመሥራት እንደተስማሙ የሚያሳይ ሲሆን ሰነዶችን መለዋወጥ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ህጋዊ ያደርገዋል። ከቃላት ልውውጥ ባለፈም ውል በተጨማሪም በኢ-ሜል እና በደብዳቤ የተለዋወጡት መረጃዎችም ሥራውን አብረው ሥለመስራታቸው የሚያመላክት ነው፤ መረጃዎችም በራሳቸው ምስክር ናቸው።
በዚህም ህግ ትርጉም የሚሰጠው እና ሥምምነቱን ያፈረሰ ወይንም ህጉን ያልተገበረ ሰው በህግ ተጠያቂ ከመሆን አይድንም ባይ ናቸው። በዚህ ውስጥ ሁለቱ ድርጅቶች በተለያዩ ወቅቶች ጉዳዩን አስመልክቶ የተለዋወጧው መረጃዎች ወይንም እያንዳንዱ ሰነድም ዋጋ የሚሰጠውና በፍርድ ቤቶችም እንደ ማስረጃ እና መረጃ የሚያገለግሉ ስለመሆናቸው ይናገራሉ። ይህም በፍትሃብሄር ህጉ አንቀፆች እና ቁጥሮች ተቀምጠውለት የሚዳኝ እንደሆንም ያብራራሉ።
በፍትሃብሄር ህጉ ከአንቀጽ 1665 ጀምሮ ባሉት እነዚህ መዘርዝሮች መቀመጣቸውን ይናገራሉ። ለአብነትም በአንቀፅ 1682፣ በአንቀፅ 1683፣ በአንቀፅ 1684 በአንቀፅ 1687፣ ጉዳዮን በሚገባ የሚተነትነውና መሰል ሥምምነቶች ተቀባይነት እንዳላቸው የሚያሳይ ነው ብለዋል። በአንቀፅ 1725 ጀምሮ የፅሁፍ ውል ግዴታ አለመሆኑን የሚያብራራ ስለመሆኑም ይጠቅሳሉ- የህግ ባለሙያው አቶ በፍርዴ ጥላሁን።
ከዚህም በተጨማሪ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በመሰል ጉዳዮች ላይ የወሰነው ጉዳይ መኖሩን እና ይህም ውሳኔ እንደ ህግ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑንም ያብራራሉ። በተለይም ደግሞ ቅጽ 13 ላይ በመዝገብ ቁጥር 71375 ላይ መሰል ጉዳይ በሰፊው የተብራራ ጉዳይ ሲሆን መፍትሄው የተሰጠው እንደሆነ ይገልፃሉ።
በኢ-ሜል፣ በስልክ የተለዋወጡት አጭር ፅሁፍ መልዕክት፣ የክፍያ ሰነዶች እና በመሃል ላይ ሲያደርጓቸው የገንዘብና ሰነድ ልውውጦች በሙሉ ሥራው በጋራ እየሠሩ እንደነበርና ውል ስለመኖሩ የሚያሳይ ሲሆን ይህን አፍርሶ የተገኘ ወይንም ደግሞ በቢዝነሱ ላይ እክል የፈጠረው ድርጅት በማናቸውም ጊዜ እና ቦታ ተጠያቂ እንደሚሆንም አብራርተዋል።
ከእነዚህ ህጎችና ውሎች በተጨማሪ ሁለቱን ድርጅቶች በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሆን ብለው አሳጥተው ከሆነ ከተጠያቂነት እንደማያመልጡም ይናገራሉ። በተለይም ውሉን ያልፈፀሙት ሆን ብለው ሀገርና መንግስትን ጥቅም ለማሳጣት ወይንም ደግሞ ሌሎች ህጋዊ አሰራሮችን በህገ ወጥ መንገድ ለማለፍ የሞከሩ እንደሆንም ሁለቱም በህግ ዓይን እኩል የሚጠየቁ መሆኑንም ያብራራሉ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 20/2021