እ.አ.አ ከ2010 እስከ 2012 ለሁለት ዓመታት ከታየው መጠነኛ ተቃውሞ ውጪ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የአልጄሪያ መንግሥትና መሪ ይህ ነው የሚባል ከባድ ህዝባዊ ተቃውሞ አጋጥሟቸው አያውቅም፡፡ አብዛኞቹን የመካከለኛ ምስራቅና የሰሜን አፍሪቃ ሀገራትን ያፈራረሰውና መሪዎችን ከመንበራቸው አሽቀንጥሮ የጣለው የ2011ዱ የአረብ አብዮት ከመንበራቸው ሳያሽቀነጥራቸው ማለፍ ከቻሉት ጥቂት የአረብ ሀገራት መሪዎች አንዱ የአልጄሪያው ፕሬዝደንት አብዱላዚዚ ቡተፍሊካ ነበሩ፡፡ ሰሞኑን ግን በፕሬዝደንት ቡተፍሊካ ላይ ከባድ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡
ከአንድ ወር በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ ፓርቲያቸውን ናሽናል ሊብሬሽን ፍሮንት (ኤፍ ኤን ኤልን) ወክለው ለአምስተኛ ጊዜ ለፕሬዝደንትነት ለመወዳደር መዘጋጀታቸውን ማሳወቃቸው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ አልጄሪያዊያንና ትውልደ አልጄሪያዊያን ዘንድ ቁጣ ቀስቅሶ አደባባይ እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል፡፡
ተቃውሞው ከዚህ ቀደም የአመጽ እንቅስቃሴ ተደርጎባቸው በማይታወቅባቸውና እንዳይካሄድባቸው ተብሎ በተከለከሉ አካባቢዎች ጭምር ከመቀስቀሱ ባሻገር በየእለቱ የሚነሱ ጥያቄዎች ብዛት እየጨመረ መምጣቱ የተቃውሞውን ክብደት አመላካች ነው እየተባለ ነው፡፡ አልጄዚራ እንደዘገበው፤ ላለፉት 18 ዓመታት ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ተከልክሎ በነበረባቸው የሀገሪቱ መዲና አካባቢዎች ጭምር ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ተማሪዎች የተለያዩ መፈክሮች አሰምተዋል፡፡
በከተማዋ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ፊት ለፊት በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ‹‹ቡተፍሊካ ይበቀሃል፤ ውረድ›› የሚሉ መፈክሮች ተደምጠዋል፤ ታይተዋልም፡፡ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ከመዲናዋ በተጨማሪ በተለያዩ ግዛቶች ቅሬታቸውን በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡ ተቃውሞው ከሀገር ውስጥ አልፎ አልጄራዊያንና ትውልደ አልጄራዊያን በብዛት በሚኖሩባቸው ፈረንሳይና ዩናይቲድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካም በመሳሰሉ ሀገራት አደባባዮችም ተካሂደዋል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች አጋዥነት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት እየተካሄደ ባለው የተቃውሞ ሰልፍ ተመሳሳይ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡
መልዕክቱም ፕሬዝደንት አብዱላዚዚ ቡተፍሊካ መንበራቸውን እንዲለቁ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ተቃውሞን በዋናነት እያካሄዱ ያሉት ወጣቶች መሆናቸውን የዘገበው ሮይተርስ ደግሞ የሀገሪቱ ወጣቶች በመንግሥታቸው ላይ የተለያየ ቅሬታ አላቸው ይላል፡፡ ስራ አጥነትና የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለወጣቶቹ ቁጣ መቀስቀስ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከዚያ ባሻገር በአህጉሩ ከፍተኛ ነዳጅ አምራች በሆነችው ሀገራቸው የተንሰራፈው ሙስና ወጣቶችን ለተቃውሞ አነሳስቷቸዋል፡፡
በመሆኑም ወጣቶቹ ሀገሪቷ አሁን ካለችበት ችግር በመላቀቅ ለዘመኑ የሚመጥን አዲስ አስተሳሰብ ባላቸው አዲስ ትውልዶች እንድትመራ ፍላጎት አላቸው፡፡ በመካሄድ ላይ ያለው የተቃውሞ ሰልፍ በፕሬዝደንትነት ለመወዳደር መዘጋጀታቸውን ባሳወቁት ቡተፍሊካ ላይ ጫና ከመፍጠሩም ባሻገር ገዢው ፓርቲ ኤፍ ኤን ኤልና ከመንግሥት ጀርባ ሆነው የሀገሪቱን ፖለቲካ ይዘውሩታል ተብለው በሚታሙት የቢዝነስ፣ የመከላከያና የደህንነት ዘርፍ ላይ ከባድ ጫና ያሳድራል፡፡ የቡተፍሊካ ተቀናቃኞች በበኩላቸው ቡተፍሊካ ሀገራቸውን ለመምራት ብቁ አይደሉም ብለዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ሀገሪቱን ለመምራት ብቁ ላለመሆናቸው ማሳያ ብለው ከሚያነሷቸው ነጥቦች መካከል ፕሬዝደንቱ በሀገራቸው ከሚያሳልፉት ጊዜ በላይ በአውሮፓ ሀኪም ቤቶች የሚያሳልፉት ጊዜ መብለጡ ነው፡፡ በአውሮፓ ሀኪም ቤት ውስጥ ሆኖ ሀገርን መምራት ሊያበቃ ይገባል ብለዋል፡ ፡
ከዚያ ባሻገር ሀገሪቱ የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ የሚያስፈልጋት ቢሆንም እስካሁን ድረስ ምጣኔ ሃብታዊ ማሻሻያ ማካሄድ አለመቻላቸው የአመራር ብቃታቸውን አጠያያቂ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ከዕለት ወደ ዕለተ እየተጠናከረ፣ አድማሱን እያሰፋና የሚሳተፈው የህብረተሰብ ቁጥርና ስብጥር እየጨመረ መምጣቱን የዘገበው ደግሞ ቢቢሲ ነው፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ በአንዳንድ አካባቢዎች በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ጋዜጠኞች ጭምር ተሳትፈዋል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ሳንሱር እንዳንገሸገሻቸው በመግለጽ ሳንሱር እንዲቆም የሚል መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፎቹ በአንዳንድ አካባቢዎች የተለያዩ ትውልዶች ለአንድ ዓላማ በጋራ እንዲቆሙ አድርጓል፡፡ በጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ከእነ አብዱላዚዚ ቡተፍሊካ ጋር በመሆን ሲታገሉ የነበሩ እድሜ ጠገብ አዛውንቶች ጭምር ከወጣቶች ጋር በመሆን ቡተፍሊካን ሲቃወሙ ታይተዋል፡፡ አህመድ ረኣኡባ ለቢቢሲ በጻፈው ሀተታው በአብዛኞቹ የአረብ ሀገራት ተቃውሞዎች ከረገቡ በኋላ በአልጄሪያ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ነው ያለውን ጉዳይ ያነሳል፡፡
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የነበረው የነዳጅ ዋጋ በነዳጅ ላይ የተመሰረተው የአልጄሪያ ኢኮኖሚ የተረጋጋ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ሀገሪቷ ትላልቅ መሰረተ ልማቶችን እንድትዘረጋና ቤቶችን ገንብታ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝቡ እንድታቀርብ አስችሏታል፡፡ በተጨማሪም ከነዳጅ ከተገኘው ገቢ በመበደር በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ራሳቸውን የሚለውጡበት ሁኔታዎች መመቻቸቱ፤ አነስተኛ የቢዝነስ ስራዎች ላይ የሚሳተፉ ወጣቶችም ያለ ዋስትና የብድር ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ መመቻቸቱ፣ ሀገሪቱ ላለፉት ዓመታት የተረጋጋ ምጣኔ ሃብት እንዲኖራት ረድቷታል፡፡ ዜጎችም ለተቃውሞ እንዳይወጡ አፍ አስይዟቸው ነበር፡ ፡ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የነዳጅ ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲንገዳገድ ምክንያት ሆኗል፡፡ መንግሥት እንዳለፉት ጊዜያት ለወጣቶችና ለአነስተኛ ቢዝነስ አንቀሳቃሾች ፈንድ የማድረግ አቅሙ እየተዳከመ መጥቷል፡፡ በሀገሪቱ የስራ አጦች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ላለውየህዝብ ቅሬታ ብሎም ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከቦታው የዘገቡ የብዙሃን መገናኛዎች የተቃውሞ ሰልፉ እጅግ ሰላማዊ እንደሆነ ዘግበዋል፡፡
በአንዳንድ ቦታዎች የተቃውሞ ሰልፎቹ ተሳታፊዎች ለፖሊሶች የፍቅር መግለጫ የሆነውን አበባ ሲሰጡ ጭምር ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፈኞችን ለመበተን ውሃና አስለቃሽ ጭስ ሲጠቀም ታይቷል፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ኦሃይአ የተቃውሞ ሰልፍ ተሳታፊዎች እያካሄዱት ላለው ሰላማዊ ሰልፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና በማቅረብ ብቻ አላለፉም፡፡ ስጋታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በሶሪያ ቀስ በቀስ የተጀመረው ተቃውሞ ሰልፍ መልኩን ቀይሮ ወደ ውጊያ በመሻገር ሀገሪቷ እስከዛሬ ልትወጣው ወዳልቻለችው አዘቅት ውስጥ እንደከተታት በማስታወስ አልጄሪያዊያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
የፓርቲያቸው ናሽናል ሊብሬሽን ፍሮንት (ኤፍ ኤን ኤል) ባወጠው መግለጫ በሀገሪቱ ውስጥ የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል ቡተፍሊካ ሀገሪቱን መምራት አስፈላጊ ነው ተብሎ በመታመኑ ለአምስተኛ ዙሪ እንዲወዳደሩ መወሰኑን አብራርቷል፡፡ ከኢኮኖሚ ልማት በተጨማሪ ከአብዛኞቹ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛ ምስራቅ ሀገራት በተለየ ሁኔታ በአልጄሪያ የሚታየውን መረጋጋት ለማስቀጠል የእድሜ ባለጸጋው አብዱላዚዚ ቡተፍሊካ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ሀገሪቷን ለመምራት እንዲወዳደሩ ተወስኗል ብለዋል፡፡
ሀገሪቱን ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻ ለማውጣት እ.አ.አ ከ1954 እስከ 1960 የተደረገውን ጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ከመሩት ግለሰቦች አንዱ የሆኑት ቡተፍሊካ ላለፉት 20 ዓመታት ሀገራቸውን በፕሬዝደንትነት ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ የ81 ዓመት እድሜ ባለጸጋው ቡተፍሊካ፤ እ.አ.አ በ2013 በስትሮክ ተጠቅተው በዊልቸር መንቀሳቀስ ከጀመሩበት ጊዜ ወዲህ በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት ለህዝባቸው የታዩት በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ሲሆን ባለፉት ስድስት ዓመታት አንድም ቀን ለህዝባቸው ንግግር አላደረጉም፡፡ ምንም እንኳ የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ቢሆንም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች እጅግ ደካማና የተፈረካከሱ በመሆናቸው ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው ምርጫ ቡተፍሊካ የሚሳተፉ ከሆነ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በመላኩ ኤሮሴ