በየዕለቱ በከተሞቻችን የሕንጻዎች ቁጥር መጨመር ይስተዋላል፡፡ የኢትዮጵያ ከተሞች የማደጋቸው ማሳያ የህንጻዎች ቁጥር መጨመር ይሆን? ወይስ የሕንጻዎች ጥራት መሻሻል? ሕንጻዎቹ የዘርፉ መሰረታዊ እውቀት አርፎባቸዋልን? መልሱን ለጊዜው ወደጎን እንተወውና የሆነው ሆኖ የግንባታው ዘርፍ ማለትም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ማደግ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የማይተካ ሚና ያበረክታል፡፡
ከላይ ከጠቀስናቸው ጉዳዮች አለፍ ስንል፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚፈልግ መሆኑና ከዚህ ጋር ተያይዞ ዘርፉ የሚፈጥረው ከፍተኛ መጠን ያለው የሥራ ዕድል ወጣቶች የዕለት ጉርሳቸውን ከመሸፈን አልፈው ጥሪት እንዲቋጥሩ በማድረግ በኩል የማይናቅ ሚና አበርክቷል፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲዘምን፣ እድገት እንዲያሳይ፣ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ መታነጽ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን ለነዋሪዎቻቸው ከሚያተርፉት ምቾት ባሻገር የአልፎ ሂያጅ ጎብኚዎችን ዓይንና ቀልብ በመግዛት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚያበረክት ይነገራል፡፡
የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ እና ከግ ብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የሚደረገውን ሽግግር የተሟላና የተሳካ ለማድረግ ብቃት ያለው እና ተወዳዳሪ የሆነ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ምርምር እና አቅም ግንባታ ሥራዎች ማካሄድ ቅድሚያ የሚሰ ጣቸው ተግባራት መሆናቸው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እና ዩኒቨርሲቲ- ኢንዱስትሪ ትስስር ፍኖተ ካርታ ላይ ተመላክቷል። በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር በእኛ አገር የተጀመረ ጉዳይ አይደለም፡፡ በተለያዩ አገራት በተለያየ ወቅት እንደተጀመረ ሰነዶች ያመላክታሉ፡፡ ቴክኖሎጂን ግብዓት ለሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል፡፡
ለኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ትስስሩ ከቴክኖሎጂ ምርትባሻገር ብቃት ያለው፣ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ማፍለቂያ እና ውጤታማ ዜጋ የሚፈጠርበት ሆኗል፡፡ በትስስሩ መሰረት ኢንዱስትሪዎቹ በዩኒቨርሲቲዎቹ የምርምር ውጤቶች ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ዩኒቨርሲቲዎቹም ለምርምር ሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከኢንዱስትሪዎቹ ያገኛሉ፡፡
ከዚህ በዘለለም የገበያ ፍላጎቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ሥርዓተ- ትምህርታቸውን እንዲከልሱ የሚያደርግ መሆኑን የትስስር ሰነዱ ፍኖተ ካርታ ያስረዳል፡፡ በፍኖተ ካርታው ላይ እንደተመላከተው አገሪቱቅድሚያ ትኩረት በሰጠቻቸው መስኮች የእሴት ሰንሰለቱን ተከትሎ ቴክኒካዊ ችግሮች በመለየትና በጋራ ምርምር አድርጎ መፍትሄ በማስገኘት በኩል በትስ ስሩ ያሉ ባለድርሻ አካላት ያላቸው ሚና ውስንነት ይታይበታል፡፡
በተጨማሪም ተፈላጊ የሆነ ቴክኖሎጂን መርጦ በመለየት፣ በመትከል፣ በመጠቀም፣በማላመድ እና በማስወገድ ረገድ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ምሁራን ኢንዱ ስትሪውን በማማከር ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ክፍተት የሚስተዋልበት ነው፡፡ በርካታ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ቢኖሩም በዚህ ጽሁፍ ሊዳሰስ የሚሞከረው ግን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል አገር አቀፍ ትምህርት፣ ሥልጠና እና የምርምር ተቋማት ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አማካኝነት ሰሞኑን ምክክር አድርጓል፡፡
በዚህ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አርጋው አሻ እንዳስታወቁት፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ነው። የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እና የምርምር ማዕከላት ከኢንዱስትሪዎች ጋር ተቀናጅተው ተግባር ተኮር ምርምር በማካሄድ የዘርፉን ችግር በጥናት መፍታት ይገባቸዋል፡፡ በዚህ ሂደትም ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱ ስትሪዎች ጥብቅ ቁርኝት መፍጠር ይችላሉ፡፡
ይህ ሲሆን የኮንስትራክሽኑ ዕድገት ይወለዳል ብለዋል፡፡ እንደ ዶክተሩ ገለፃ፤ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከላት እና ኢንዱስትሪዎች ተደምረው ለአገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዕድገት ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ ተደጋግፎ መስራት አለባቸው፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በግብዓት የጥራት ችግር፣ በባለሙያዎች የክህሎት ጉድለት እና ሌሎች ብዙ ተያያዥ ችግሮች የተነሳ በከፍተኛ አዙሪት ውስጥ እንደሚገኝ ያብራሩት ምክትል ዳይሬክተሩ በዚህ የተነሳም አገሪቱ ከዘርፉ የምትጠብቀውን ያህል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማግኘት እንዳትችል አድርጓታል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይም ዩኒቨርሲቲዎች፣ ጥናትና ምርምር ማዕከላት እና ኢንዱስትሪው ተናቦ፣ ተሳስሮ እና በአንድ ዘምቶ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር የማድ ረግ ውስንነት እንዳለበትም አክለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ትውውቅ ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ፋናኤል ንጉሴ እንደገለጹት፣ የትምህርትና ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪው ቅንጅታዊ ትስስር መኖሩ ከሚያስገኛቸው ፋይዳዎች መካከል በኢንዱስትሪ ፣ በትምህርት ተቋማት እና በምርምር ማዕከላት መካከል የተጠናከረ ትስስርን በመፍጠር የኢንዱስትሪውን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ጥናት እና ምርምሮች ማካሄድ ያስችላል፡፡
በቀጣይም የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራትን በማከናወን የኢንዱ ስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ የተናጠል ጥረቶችን በማቀናጀት ያለውን ውስን ሀብት (ገንዘብ እና የሰው ኃይል) በመጠቀም አገራዊ ፋይዳ ያለው ውጤት ማስመዝገብ ያስችላል፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ አዳዲስ እውቀቶችና የምርምር ውጤቶች በኢንዱስትሪ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ወይዘሮ ፋናኤል አብራርተዋል፡፡ በደቡብ ክልል ኮንስትራክሽን ቢሮ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ባለሙያ አቶ ዘርፉ ዘውዴ በበኩ ላቸው አራተኛው የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር የምክክር መሪ ቃል ‹የዘመነ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እና ቅንጅታዊ አሰራር ለዘላቂ አገራዊ ልማት› የሚል መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
እውቀቱ፣ ልምዱ፣ ጥናቱና ምርምሩ ያለው ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ዘንድ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት የኮንስትራክሽኑ ኢንዱስትሪ ዕድገት የሚረጋገጠው በዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር አማካኝነት ነው የሚል ጽኑ እምነት አለው፡፡ አሁን በፍጥነት እያደገ በሚገኘው ኢንዱስትሪ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በጥናትና ምርምር መጠ ናከር አለበት፡፡
ይህን ማድረግ የማንችል ከሆነ ዘርፉ በውስብስብ ችግር ውስጥ ያለ ኢንዱስትሪ በመሆኑ በጥናትና ምርምር ችግሩን ለይተን ካልቀረፍን ወደ ፊት መራመድ አዳጋች ይሆናል ብለዋል፡፡ አቶ ዘርፉ ፤ ትስስሩ የግድ አስፈላጊና አስገዳጅም እንደሆነ ጠቅሰው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ካሉት የሥራ ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል ፈጠራ ያለበት ነው፡፡
ድርሻውን እየተወጣ ቢሆንም ያለበት የአቅም ውስንነት፣ ዝቅተኛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ፣ ዝቅተኛ የፕሮጀክት አፈጻጸም፣ከፍተኛ የሃብት ብክነት፣ከፍተኛ የጥራት መጓደል እና ለሌብነት ተጋላጭ መሆኑ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ሊሻገራቸው ያልቻሉ ማነቆዎች መሆናቸውን ዘርዝረዋል፡፡ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ሽመልስ ረጋሳ እንደተናገሩት ‹‹ኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስሮች ሲባል ብዙ ናቸው፡፡
ለምሳሌ ያህል ምግብ፣ መጠጥና ፋርማስቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት፣ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እና ሌሎችንም የሚያካትት ነው። ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር፡፡ የእኛ የመስራት ተነሣሽነት ማጣት እንጂ የበጀትና ሌሎች መሰል ችግሮች ይገጥሙናል ብዬ አላስብም፡፡
ኢንዱስትሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር መስራት ያለመፈለግ አይደለም፡፡ ‹‹ኢንዱስትሪዎችን እኛ ዩኒቨርሲቲዎች ተጭነን ከእኛ ጋር በተገቢው እንዲሰሩ ማድረግ እንችላለን። ወደ ኢንዱስትሪው ሄዶ ችግሮችን የመለየትና በጥናትና ምርምር የመፍታት እንዲሁም የማማከር ፍላጎቱ መጀመሪያ አለን ወይ? ዝም ብለን ተማሪ ዎቻችንን ከመላክና ለተግባር ልምምድ ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የሚመጡትን ተቀብሎ ከመሸኘት ባለፈ ተቀራርበን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ለመስራት ብዙ ጥረት እያደረግን አይደለም፡፡›› ብለዋል፡፡
ኃላፊነት እንደተጣለበት አንድ አካል አለያም እንደ እዚች አገር አንድ ዜጋ የሀገሪቱ ችግር የኔም ችግር ነው፤ ያገባኛል የሚል ስሜት አልፈጠርንም የሚሉት ዶክተር ሽመልስ በሀገሪቱ የሚጠፉት ነገሮችም ሆነ የሚለሙት ነገሮች ይመለከቱኛል የሚል ጠንካራ አገራዊ አቋም ሊኖር ይገባል ባይ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ሲባል ቴክኒክና ሙያ ተቋማትንም የሚያስተሳስር ነው፡፡ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ከቴክኒክና ሙያ ጋር አብሮ ይሰራል።
‹‹ቴክኖሎጂ ያመጣሉ እንገመግምላቸዋለን፡፡ ከሦስት ጊዜ በላይ ገምግመንላቸዋል፡፡ ተገምግሞ ያለፉ ወደ አምስት የሚደርሱ ቴክኖሎጂዎች ወደ ማህበረሰቡ እንዲተላለፉ ተደርገዋል፡፡ ለዚህ ተግባር እኔ በምመራው ዳይሬክቶሬት በጀት ይዣለሁ፡፡ ወደ ማህበረሰቡ እንዲተላለፉ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ማከናወን ያስችለኛል ማለት ነው፡፡›› ሲሉ ሂደቱን አስታውሰዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹ የተለያዩ ሲሆኑ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ኮንክሬት ሲሞላ የሚፈጠረውን ብክነት ማስ ቀረት የሚችል ቴክኖሎጂ ተካትቶበታል፡፡ብረትን በቀላሉ ማጠፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂም በዚሁ ዘርፍ ቀርቧል፡፡ በራሳችን በኩል የሚስተዋለውን ችግር መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡ አሁን ላይ በወሬ መተላለፍ አይቻልም፡፡
‹‹ያ ወቅት ማለፉን መረዳት አለብን፡፡ ጊዜው ለሚሰራ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት ነው፡፡ ስለዚህ በሥራ፣በተግባር፣ውጤት በማሳየት፣አርአያ በመሆን የምንሰራበት እንጂ የፖለቲካ ጨዋታ የምንጫወትበት ጊዜ አይደለም፡፡ ያ ጊዜ አብቅቷል›› በማለት ዶክተር ሽመልስ ረጋሳ በሰፊው አብራርተዋል፡፡ በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኢንዱስትሪዎች እና የምርምር ተቋማት ተቀናጅተው የሚሰሩበትን ሥልት መቀየስ፣ባለድርሻ አካላት በተጠያቂነት መንፈስ ተግባራቸውን እንዲወጡ ማስቻል ለኢኮኖ ሚው ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ ትስስሩን የሚፈጥሩት ባለድርሻ አካላት በመተማመን ላይ ተመስርተው ተግባሮቻቸውን እንዲወጡ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ይመክራሉ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2011
በሙሀመድ ሁሴን