የመኸር ግብርናን በጥራትና በስፋት – በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል

በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፤ ዜጎችን ከድህነት ለማላቀቅ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ስራዎች አበረታች ውጤቶች እያስመዘገቡ ናቸው። በተለይም ግብርና የሀገሪቱና የሕዝቡ የኢኮኖሚ መሰረት እንደመሆኑ ምርታማነት በተጨባጭና በሚታይ መልኩ እንዲጨምር ለማድረግ ክልሎችም ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነቱን ወስደው በመስራታቸው እምርታ ማምጣት እየቻለ ነው።

በዘርፉ ፈጣንና ተስፋ ሰጪ ለውጥ እያሳዩ ካሉ ክልሎች መካከል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ነው። ክልሉ የክልሉን ሕዝብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መርሀ-ግብሮችን ነድፎ ተግባራዊ በማድረጉ በምርትና ምርታማነት ማሳደግ በኩል ለውጦችን ማስመዝገብ እንደቻለ ይገልጻል።

ክልሉ በአዲስ ክልልነት ከተቋቋመ ገና የአንድ ዓመት እድሜ ብቻ ያለው ቢሆንም፣ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ‘በአዲስ ምዕራፍ፣ አዲስ ተስፋ፣ ለአዲስ ክልል’ በሚል እሳቤ ሕዝቡን ከተረጂነትና ከድህነት ለማላቀቅ በጀመራቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ኢኒሼቲቮች እንዲሁም የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የላቀ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ክልሉ ይገልጻል። በዘንድሮው የመኸር ግብርና ወቅትም በተለይም ከተለመዱት በተጨማሪ በርካታ ሰብሎችን በክላስተር እንዲመረቱ በማድረግ ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጎለብት ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና እና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ሰሞኑን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የዘንድሮውን የግብርና ልማት ስራ ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ የክልሉን ሕዝብ የኢኮኖሚ ልማት ተጠቃሚነት መሰረት አድርጎ ባስቀመጣቸው አቅጣጫ መሰረት እንዲከናወን ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶታል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የበጋ መስኖ ልማት፣ የበልግ ልማት እንዲሁም የመኸር ንቅናቄ ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል።

በክልሉ የመኸር ወቅት ከተቀመጡ ጉዳዮች መካከልም ስድስት የግብርና ዘርፉ የተለዩ ምሰሶዎች መቀመጣቸውን የቢሮ ኃላፊው ይጠቅሳሉ። ‹‹ምሰሶዎቹ በተለይም ግብርናው አጠቃላይ የሕዝባችንን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፤ የስራ እድልና የገበያ ችግርንም ለመፍታት የተቀመጡ ናቸው›› ይላሉ። የምግብና ስነ- ምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ማረጋገጥ፤ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት፣ የወጪ ምርቶችን በብዛትና በአይነት ማምረት ዋና ዋናዎቹ ምሶሶች መሆናቸውን ያስረዳሉ። በዚህም ለአምራቹ የተሻለ ገቢ ማግኘት፤ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ልማት ላይ ክልሉ የድርሻውን ማበርከት በሚችልበት መልኩ እየተሠራ ስለመሆኑም ያብራራሉ።

ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን በቂ ምርት በብዛትና በጥራት ማምረት፤ የግብርናው ዘርፍ የስራ እድል ምንጭ እንዲሆን ማድረግና እነኚህን ነገሮች በብቃት በመከወን የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነትን ያረጋገጠ ፣ ከድህነት የተላቀቀ ፣ ድህነትን ቀድሞ ያሸነፈ ቤተሰብ፣ ማህብረሰብና ክልል መፍጠር የሚሉት ጉዳዮችም በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት የተሰጣቸው የልማት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አቶ ኡስማን ያስገነዝባሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህ መነሻ በመኸር ወቅት ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ መላውን አመራር፣ ሙያተኛ፣ ህብረተሰብ ያሳተፈ ህብረተሰብ አቀፍ ንቅናቄ ተካሂዷል። ንቅናቄው የክልሉ ፕሬዚዳንትና አብይ ፓርቲ የሚመራው ሆኖ ከክልል እስከ ህብረተሰቡ ድረስ የሚያሳትፍ ስራ ተከናውኖበታል።

በዚህም ንቅናቄ አጠቃላይ በስድስቱ ምሰሶዎች ላይ የጋራ መግባባት መፈጠሩን የቢሮ ኃላፊው ያመለክታሉ። እነዚህን ለማሳካት የተቀመጡ ግቦች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ‹‹ በዋናነትም 540 ሺ ሄክታር መሬት በማልማት 49 ነጥብ 89 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እናመርታለን ብለን ግብ አስቀምጠናል፤ ይህንን ግብ ለማሳካትም አስፈላጊዎቹን የምርት ማሳደጊያና ግብርናን ለማዘመን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በወቅቱ በማቅረብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሰፊ ርብርብ ተደርጓል›› በማለት ያብራራሉ።

እንደ አቶ ኡስማን ማብራሪያ፤ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት አስቀድሞ ሁሉንም አካል ባለቤት፣ አጋዥና አጋር የማድረግ ስራ ተሰርቶ ነው ወደ ተግባር የተገባው። በዚህም በርካታ ውጤቶች ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን እስከአሁን ባለው ግምገማም ከ545 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ተሸፍኗል። በአብዛኞቹ ማሳዎችም በሚባል ደረጃ የተሻለ የማሳ ዝግጅት የነበረበት፣ የተሻለ ክላስተር መፍጠር የተቻለ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ሜጋ ክላስተሮች ሆነው ለሀገርም በተምሳሌት የሚጠቀሱ ናቸው። ዘንድሮ ከአምናው በተለየ መልኩ በቆሎ ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ በርበሬ ፣ አተር፣ ባቄላና ሌሎች ሰብሎች ሰፋፊ ክላስተሮችን መፍጠር ተችሏል።

ዘንድሮ በተለያዩ የሰብል አይነቶች ክላስተር እንዲለማ መደረጉ፤ ቴክኖሎጂ፣ ግብዓት አጠቃቀም ከማሳደግ ባሻገር የአመራራት ሂደቱ ዘመናዊና ከብክነት የፀዳ በመደረጉ ምርታማነቱ በእጅጉ እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል። ‹‹አምና በቆሎና ስንዴ ብቻ ነው በክላስተር ያረስነው፤ ዘንድሮ ግን በሁሉም ሰብሎቻችን በሚባል ደረጃ በስንዴ፣ በገብስ፣ በዳጉሳ፣ በጤፍ፣ በድንችና በሌሎችም ሰብሎች ነው እያለማን ያለነው›› ይላሉ።

የእርሻ ሂደቱን በክላስተር ማከናወን በመቻሉም ምርት በጥራት፣ በመጠንና በወቅቱ እንዲሰበሰብ አቅም መፍጠሩን አቶ ኡስማን ያስረዳሉ። ‹‹የክላስተር እርሻን ማስፋፋት በመቻላችን ምርት በመጠንም ሆነ ጥራት እንዲጎለብት ያደርግልናል›› ይላሉ። በቀጣይም ለገበያ ተመራጭ በመሆኑ ዘንድሮ በተሻለ መልኩ አምራቹንም ሆነ ሸማቹን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያመለክታሉ። ይህም በክላስተር የመስራቱ ውጤት አርሶአደሩ ራሱ በተጨባጭ አይቶ የመሰከረው ከመሆኑም ባሻገር ወጣቶች በዘር ማባዛት፣ እንዲሁም ባለሀብቱ በስፋት በግብርናው ዘርፍ እንዲሰማራ ተስፋ የሚሰንቅ፣ የሚያነሳሳ እንደሆነም ነው ያስረዱት።

በዘንድሮ የምርት ዘመን በክልሉ ምርታማነትን ለማጎልበት ከተሰሩ በርካታ ስራዎች መካከልም የአፈር አሲዳማነትን የመከላከል ስራ ተጠቃሽ እንደሆነ አቶ ኡስማን ያመለክታሉ። በተለይም ‘የአፈር ጤና ለሀገር ህልውና’ በሚል ሀገራዊ ንቅናቄ መካሄዱን ጠቅሰው፤ በክልሉም አሲዳማነት ባጠቃባቸው አካባቢዎች ህብረተሰብ አቀፍ ንቅናቄ መካሄዱን አስታውቀዋል። ህብረተሰቡን ባለቤት በማድረግ መሬቱን በማከም ምርታማነት መጨመር የሚያስችል ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።

‹‹በአጠቃላይ የግብርና ልማት ስራችንን ለማሳለጥ በፈጠርናቸው ሕዝብ ተኮር ንቅናቄዎቻችንን ተስፋ የሚሰጡ ውጤት እየመጡ ናቸው፤ ይሁንና ይሄ ውጤት መጣ ብለን አልቆምንም፤ ምክንያቱ ደግሞ ትክክለኛ ውጤት መጣ የምንለው ድህረ ምርት ላይ ያለውን ብክነት ተከላክለን የመጨረሻውን ምርት ከማሳ ሰብስበን ጎተራ ማስገባት የሚጠበቅብን ስናከናውን በመሆኑ ነው›› ሲሉም ያብራራሉ። አሁን ባለው የማሳው ነባራዊ ሁኔታ ግን ከእቅዱም በላይ ምርት መሰብሰብ እንደሚቻል እንደሚጠበቅ ይጠቁማሉ።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ፣ ከልመና ወደ ሀገራዊና የሕዝብ ክብርና ልዕልና በሚል መርህ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን የቢሮ ኃላፊው ያመለክታሉ። ይህንን ለማምጣት ደግሞ የክልሉ መንግሥት ያሉትን የተፈጥሮ ፀጋዎችና አማራጮች በሙሉ መጠቀምና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ያስረዳሉ። አሁን ላይ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የለሙ ማሳዎች አጓጊና ብዙ ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። በቀጣይም የአረም፣ የበሽታ መከላከልና ተባይ ክትትል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፤ ምርቱ ከማሳ ወደ ጎተራ እስከሚገባ ድረስ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

እንደ አቶ ኡስማን ገለጻ፤ ከግሪሳ ወፍ ወረርሽኝና ከድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ ጋር ተያይዞ እስከአሁን ባለው ሂደት የጎላ ችግር አላገጠመም። ይሁንና አንዳንድ ቦታዎች የዋግ በሽታዎች የታዩ ሲሆን፣ ለዚያ ደግሞ በተደረገው ቅድመ ዝግጅት መሰረት መድኃኒት የመርጨት፤ ህብረተሰቡ ክትትል እንዲያደርግ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በተደረገው ግምገማ አጠቃለይ የክልሉ የግብርና ልማት ስራ ተስፋ የሚሰጥ፣ ህብረተሰቡ ውስጥ መነሳሳትና ቁጭት የሚፈጥር የሰብል ቁመና ነው ያለው። ይሁንና አበረታች ውጤት እስከመጨረሻ ማስቀጠል ይጠይቃል።

ባለፈው የምርት ዘመን የአቅርቦት ችግር እንደነበር አቶ ኡስማን ጠቅሰው፤ በተለይም ሕገወጦች እጃቸውን አስገብተው የነበረበት ሁኔታ ምርታማነት እድገት ላይ የራሱ አሉታዊ ሚና ማሳደሩን ገልጸዋል። ‹‹ያ ወቅት ክልሉ በአዲስ መልክ የተደራጀበትና የሽግግር ጊዜ ስለነበር፤ ሕገወጦችም ጭምር በተለይ ማዳበሪያ ላይ እጃቸውን አስገብተው በደላሎች ምዝበራ የተከሰተበት ሁኔታ ነበር›› ይላሉ። ዘንድሮ ግን እነዚህን ነገሮች የመከላከል ስራ መሰራቱን፣ በክልል ደረጃ ሕግ መውጣቱ፣ ማዳበሪያ በህብረት ስራ ማህበራት ብቻ እንዲሰራጭ በመደረጉ ምርታማነቱ እንዲጎለብትና እምርታ እንዲመዘገብ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

‹‹አምና ግን በርካታ ተዋናዮች ስለነበሩ ለሕገወጥነት ሰፊ እድል ነበር፤ የክልሉ መንግሥት ዘንድሮ በተለየ መልኩ ምርታማነትን የሚጎዳ ማንኛውንም ነገር አንታገስም ብሎ ባስቀመጠው ግልፅ አቅጣጫ ምክንያት የማዳበሪያ ችግር ለመፍታት ጥረት ተደርጓል›› ይላሉ። ያም ሆኖ ግን ሙሉ ለሙሉ ከችግር የፀዳ ነው ለማለት እንደማይቻል ያነሳሉ። አሁንም በርካቶች እጃቸውን ለማስገባት እንደሚሞክሩ ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግሥት ግብርና ቢሮ የሚመራው ግብረ-ኃይል አደራጅቶ ሰላምና ፀጥታ፣ፖሊስና የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት ስራ ተሰርቶ በርካታ ሕገወጦች ላይ እርምጃ መወሰዱን ነው ያመለከቱት። በተጨማሪም ሕገወጥነትን ለመከላከል ሲባል የክልሉ መንግሥት ከህብረተሰቡ መካከል ሕገወጦችን ለሚጠቁም 20 በመቶ፣ ይዘው ለሚያቀርቡ 20 በመቶ የተቀረውን ደግሞ የመንግሥት መዋቅር እንዲጠቀምበት የማድረግ ስራ መስራቱን ይናገራሉ።

በቀጣይም የግሪሳ ወፍ ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁመው፤ እስከመጨረሻ ድረስ ነቅቶ መጠበቅ የግድ እንደሚል ገልጸዋል፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ፀረ-አረምና ተባይ መድኃኒት የሚረጩ አውሮፕላኖች ማረፊያ በክልሉ ስልጤ ዞን ላይ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ይጠቁማሉ። ግንባታውን በተያዘው በፍጥነት ማጠናቀቅ ከተቻለ ለዘንድሮው የመኸር ምርት ውጤታማነት የራሱ አወንታዊ ሚና ይኖረዋል ተብሎ እንደሚታመን ነው አቶ ኡስማን ያስገነዘቡት።

በተጨማሪም ከመስከረም ወር በኋላ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል አመልክተው፤ ይህ ሊያደርስ የሚችለውን ችግር ከወዲሁ ለመፍታት እንደክልል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያመለክታሉ። ‹‹ ወቅቱን ያልተጠበቀ ዝናብ የደረሱ ሰብሎችን እንዳያበላሽ ለማድረግ ሕዝባዊ የንቅናቄ ስራ በመላው የክልሉ መዋቅር የሚሰራ ይሆናል›› ይላሉ። ‹‹ይህም ንቅናቄ ብዙ የደከምንበትን የእርሻ ስራ ከብክነት በፀዳና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሰበሰብ የሚያደርግ ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ። በዘንድሮ የመኸር ምርት የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በመቀመር በቀጣዩ በጋ ላይ የሚሰሩ የመስኖ ልማት ስራዎች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥና ዝግጅት የማድረግ ስራ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You