የተወለዱት አዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም ያደጉትም ሆነ የተማሩት በቢሾፍቱ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸው እዛው ከተማ በሚገኘው ከታ በተባለ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን በቀድሞ ስሙ ልዕልት ተናኘወርቅ፣ በኋላ ደግሞ ደግሞ ደብረዘይት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ በሚባለው ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረዋል። ከልጅነታቸው ጀምሮ ከቤተሰባቸውም ሆነ ከጎረቤቶቻቸው የአየር ኃይሉን ዝና እየሰሙ ያደጉት የዛሬው የዘመን እንግዳችን ተዋጊ አብራሪ የመሆን ፍቅራቸው አብሮ አድጎ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በቀጥታ ተቋሙን ተቀላቀሉ። መጀመሪያ በአጠቃላይ ኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ ስልጠና ወሰዱ። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ለበረራ ስልጠና ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት አቀኑ። ለሶስት ዓመት ተዋጊ አብራሪነት ከፍተኛ ስልጠና አግኝተውም ወደ አገራቸው ተመለሱ። በቀጥታ ግን በተዋጊ አብራሪነት ሥራ ላይ አልተመደቡም፤ ተጨማሪ ሥልጠና እና በዲስፒሊን የታነፀ ትምህርት ወስዱ።
በተቋሙ የሚሰጠውን ከባድ የተግባር ፈተና አልፈው በአስመራና በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ልምምድ እንደጀመሩ ደግሞ በአገሪቱ የሥርዓት ለውጥ መጣና ትህነግ መራሹ መንግሥት አገሪቱን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠረ፤ አየር ኃይሉንም አፈረሰው። እሳቸውም ልክ እንደሌሎቹ አባላት ሁሉ የመታሰር ዕጣ ደረሳቸውና ለአንድ ዓመት ያህል ወህኒ ቤት ከረሙ። በኋላም ከእስር ተፈቱና በተቋሙ አብራሪዎችን እንዲ ያሰለጥኑ ተመደቡ። ይሁንና አጠቃላይ የፖለቲካው አካሄድና የሕወሓቶች አገርን የማፍረስ ሴራ አልጥም ይላቸዋል። በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሳሉ ደግሞ በማያውቁት ነገር ታፍነው ይወሰዱና በጨለማ ክፍል ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል ከፍተኛ ድብደባና እንግልት ደረሰባቸው።
ከሁለት ዓመት እንግልትና ስቃይ በኋላም ከእስር ተፈቱና ዳግመኛ አገራቸውን እንዲያገለግሉ ተጠሩ። አሁንም በሚወዷት አገር ላይ ፊታቸውን አላዞሩም፤ ውስጣቸው የሚብላላውን ቅሬታና ቂም እንደያዙም ዳግመኛ ተማሪዎችን ማሰልጠን ጀመሩ። ይሁንና ብዙም አልቆዩም። በአንድ ብሔር የበላይነት የሚመራው የፖለቲካ ስሪት እንዳሰቡት አገራቸውን በቅንነት ለማገልገል እንደማያስችላቸው በመገንዘባቸው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የፈጠረላቸውን ዕድል በመጠቀም ከአንድ ጓደኛቸው ጋር በመሆን የሚያበሩትን አውሮፕላን ይዘው ኤርትራ ገቡ። ከኤርትራ የአንድ አመት የስደት ቆይታ በኋላ ደግሞ በዓለም አቀፉ ቀይመስቀል ድርጅት አማካኝነት ካናዳ የመግባት እድሉን አገኙ። ባለፉት 20 ዓመታትም በሚኖሩበት አገር ሆነው የአገር አፍራሹን መንግሥት ሴራ ሲያጋልጡ የኖሩት እኚሁ እንግዳችን የለውጡን መምጣት ተከትሎ ደግሞ መንግሥትን በሙያቸው በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ እየተፋለመች ያለችውን የሕልውና ጦርነት ለመደገፍም ከሰሞኑ ወደ አገራቸው ገብተዋል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ የቀድሞ አየር ኃይል አባል ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጓቸዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- አየር ኃይል የተቀላቀሉበትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
ካፒቴን ተሾመ፡- እንደምታውቂው ደብረዘይት የወታደር አገር ናት። በርካታ ወታደራዊ ተቋማት ያሉበት በተለይም ደግሞ አየር ኃይል የሚገኝባት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአየር ኃይሉና የነዋሪው ሕይወት የተሳሳረ ነው። ከእኔ ብቻ ሳልሆን ሁለት ወንድሞቼ የአየር ኃይል አባል ናቸው። በአየር ኃይሉ የሚደረገው በረራ አብዛኞቻችንን ይስብ ስለነበር ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል ብዬ አስባለሁ። በዚህ መሠረት እኔም በ1973 ዓ.ም አካባቢ ነው አየር ኃይሉን የተቀላቀልኩት።
መጀመሪያ እንደገባሁ በአጠቃላይ ኤሌክትሮኒክስ ጨረስኩኝ። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ለበረራ ስልጠና ወደቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ሄድኩኝ። ለሶስት ዓመት ተዋጊ አብራሪነት ከፍተኛ ስልጠና አግኝቼ ወደ አገሬ ተመልሻለሁ።
በነገራችን ላይ ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ በቀጥታ ወደ ሥራ አልገባንም። የኢትዮጵያ አየር ኃይል የራሱ ስታንዳርድ አለው፤ ሲጀመር ከአፍሪካም ሆነ ከአንዳንንድ የአውሮፖ አገሮች ሳይቀር ቀደምትነት ቴክኖሎጂ የተቀበለች እና በጣም ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የአቬየሽን ቴክኖሎጂ ባለቤት ናት። እናም ከውጭ ሰልጥነሽ ስለመጣሽ ዝም ብሎ የሚቀበል አየር ኃይል አይደለም። በተጨማሪ በራሱ ስታንዳርድ ይፈትንሻል። የሚገርምሽ ራሺያ ስንሄድ ከ 60 በላይ የነበርን ቢሆንም ስንመለስ በአጠቃላይ 13 ሆነን ነው የመጣነው። እንደመጣንም ዳግመኛ ወደ ስልጠና ገባንና ብዙዎቹ ፈተናውን ማለፍ ተስኗቸው እየተንጠባጠቡ ሶስት ሰዎች ቀረን። ከሁሉም በላይ ስልጠናውና ዲሲፒሊን በጣም ከባድ ነው። በተለይ ደግሞ ተዋጊ አብራሪ መሆን ከፍተኛ የሆነ ዲስፒሊንና ለአገር ያለሽን ታማኝነት ይጠይቃል። በዚያ መሠረት ነው ወደ ሥራ የገባሁት።
አዲስ ዘመን፡- ሥራ እንደጀመሩ መታሰርዎትን ሰምቻለሁ፤ ለመሆኑ የታሰሩበት ምክንያት ምን ነበር?
ካፒቴን ተሾመ፡– ልክ ነሽ ፤ ገና ሥራ እንደጀመርን የመንግሥት ለውጥ መጣ፤ ወያኔ ሙሉ ለሙሉ አገሪቱን ተቆጣጠረና አየር ኃይሉን አፈረሰው። እናም ሁላችንም ወደ እስር ቤት ተጋዝን። ያለምንም ምክንያት ለአንድ ዓመት ካሰሩን በኋላ ሰዎች እየመረጡ መውሰድ ጀመሩ። ከተመረጡት ሰዎች መካከል እኔ ነበርኩኝ። የሚያሳዝነው ግን በአየር ኃይሉ ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ ልምድ ያላቸው አብራሪዎችን ግን እዛው እስርቤት እንዲማቅቁ አድርገዋቸው ነበር። እነዚያ አብራሪዎች ኢትዮጵያ የተቃጣበትን ወረራ ሁሉ እንደጨዋታ አድርገው አሳፍረው የሚመልሱ ነበሩ። የኢትዮጵያን የአየር ክልል አንድ ጊዜም ተደፍሮ አያውቅም። የሱማሌን ወራሪ ኃይል አሳፍረው የመለሱ፤ በኮንጎና በኮሪያ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው የተመለሱ ገናና ታሪክ ያላቸው ናቸው። ይሁንና ከተወሰኑት ነባር አብራሪዎች በስተቀር ሌሎቹ እስር ቤት እንዲቆዩ ተደረገ።
አዲስ ዘመን፡-በወቅቱ ወጣትና ጀማሪ ሆነው ሳለ እንዴት ሊመረጡ ቻሉ?
ካፒቴን ተሾመ፡- እነዚህ ሰዎች ገና ሲመጡም ኢትዮጵያን የማፍረስ እንጂ የማስቀጠል እቅድ አልነበራቸውም። ኢትዮጵያን የማጥፋት ዓላማቸው እንዲሳካ ደግሞ አገሪቷን ያለጠባቂ ማስቀረት ይገባቸዋል። እነዚያ አብራሪዎች የአገር ጠባቂዎች ናቸው። ኢትዮጵያ የተቃጣባትን ወረራ ሁሉ ሲመልሱ ነው የኖሩት። ከሕወሓቶች ጋርም ቢሆን አንገት ለአንገት ተናንቀው የቆዩ አብራሪዎች ናቸው። ከዚያ በመነሳት ሕወሓቶች ሊበቀሏቸው ይፈልጉ ነበር። በሁለተኛ እኛን ከእስር ፈተው ዳግም አየር ኃይሉን እንድናገለገል የመረጡን እኛ ስለወደዱን አልነበረም። በተወሰነ ደረጃ የራሳቸውን ኃይል የማደራጀትና የማስተማር ፍላጎትም ነበራቸው። ይህ እቅዳቸው ግን ለእኛ ድብቅ ነበር። እኛ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች የሚል መንፈስ ነበረን። የአገራችንን ሉዓላዊነት በተመለከተ አንደራደርም።
አየር ኃይል ያለነዚያ ጀግና አብራሪዎች ይቀጥላል ብሎ ማሰብ ከባድ ነበር። እኛም ተመልሰን የገባነው ተቋሙንና ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ነበር። ሲታይ ግን ታሪኩ ሌላ ሆኖ ነው ያገኘነው። ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ትግርኛ ተናጋሪዎችን ሰብስበው አመጡ። በጣም የሚያሳዝነው ከምልመላው ጀምሮ ስታንዳርዱንም የጠበቀ አልነበረም። ዝም ብሎ ታንክ መንዳት ስለቻሉ ብቻ ነበር ሰብስበው ያመጧቸው። ሌላው ይቅርና የጤና፤ የአካል ብቃትና የእድሜ መስፈርትን እንኳን ያላሟሉ ነበሩ። ልክ እነሱን ሲመጡ ትንሽ ስሜት የመደፍረስ ነገር ተፈጥሮብን ነበር። የሚገርመው ደግሞ እኛን አሰልጣኝና ኃላፊ አድርገው ቢመድቡንም ከነሙሉሥልጣናችን ኃላፊነት አልሰጡንም ነበር። እንደባዕድ ሙያሽን ብቻ እንድንሸጥላቸው ነበር የሚፈለጉት። እንደባይተዋር ስለአገርም ሆነ ስታንዳርዱ እንደማያገባን ተደርገን ነው የተቆጠርነው። ያም ደግሞ አንድ ላይ ለመጓዝ አያስችለንም። እንዲህ አይነቱ ነገር ነው ኢትዮጵያ እየቀጠለች ነው ወይ? የሚለው ነገር ሁሉ ጥያቄ የፈጠረብን። በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብቻ ያንን የሚያህል ተቋም መገንባት አይቻልም። በዚያ ምክንያት ትንሽ የተራራቀ ግንኙነት መፈጠር ጀመረ፤ ግምገማ የሚሉት ነገር አመጡ። ይህ ተቋም የሙያ እንጂ የካድሬ ቤት አልነበረም።
የሚገርምሽ ከትግራይ ተወላጆች በተጨማሪ ኤርትራውያንን እንድናሰለጥን ተደርገን ነበር። የኢትዮጵያ ጠላቶች ከሚባሉ ሁሉ ከእነሱ ጋር በጣም የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ነበሩ። የቀደመውን ወታደራዊ ሥርዓት እንደጭራቅ እንደሌላ አይነት ፍጡር የማድረግ ሁኔታን ተከተሉ። አየር ኃይሉ ምንም እንኳን የፖለቲካ ተሳትፎ ባይኖረውም የደርግ ተቋም አድርገው እንደነበር በማንሳት መወንጀል ጀመሩ። በድንገት ግን ሻዕቢያ ኢትዮጵያን ስለወረረ ተዘጋጁ አሉን። ከነበራቸው ቅርበት የተነሳ የእነሱ መጣላት ለእኔ ተዓምር ነው የሆነብኝ። ለማመን ተቸግሬ ነበር። ያም ሆኖ እነሱ ባድመ ተወረረች ቢሉም እኛ የምናስበው ሙሉ ኤርትራን ዳግም ወደ አንድነት መመለስ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ኢትዮጵያውያን ደም የፈሰሰበት፤ ብዙ ሕይወት የተከፈለበት ሁኔታ በመሆኑ ከኢትዮጵያ የመገንጠሉ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ አልተዋጠልንም ነበር። ደግሞም ኤርትራውያኖች ወንድሞቻችን ናቸው፤ ተዋልደናል፤ በደም ተገናኝተናል። በመሆኑም እንደገና ሌላ ግጭት ለመቀበል ከባድ ነበር የሆነብን።
አዲስ ዘመን፡- እስቲ አሁን ደግሞ ዳግመኛ ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ ያስረዱን?
ካፒቴን ተሾመ፡- አይደለም እኔ እነሱ ራሳቸው ያውቁታል ብዬ አላስብም። ግን አስቀድሜ እንዳልኩሽ ኤርትራ ሰብራ ገብታለች የሚል ነገር ስለመጣ ለመብረር ዝግጅት ማድረግ ጀምሬ ነበር። አንድ ቀን አመሻሽ ላይ በድንገት ለፖለቲካው ቅርብ የሆነና ከማስተምራቸው የእነሱ ሰዎች አንዱ ይመጣና ‹‹ኤርትራ ወራናለች፤ ከሱዳን ጋር እየተጋገዙ ስለሆነ አንተ ቢሮ ያለውን ካርታ ሥጠኝ›› አለኝ። ይሄ ልጅ በመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዬ ነው ፤ ሁለተኛ ካርታ የሚፈልግ ከሆነ አየር ኃይሉ የሚያመርትበት የፎቶ ክፍል መውሰድ ሲገባው ለምን እኔን ጠየቀኝ የሚል ጥርጣሬ ፈጥሮብኝ ነው።
ግን ደግሞ ባለስልጣን ስለሆነ እምቢ ማለት አልቻልኩም። ተስማምቼ ወደ እኔ ቢሮ ተያይዘን ሄድን። እዚያ ስንደርስ አንድ ሌላ የእነሱ ሰው መጣ። ይሄኛው ደግሞ የባሰ በግልፅ የደህንነት ሠራተኛ ነው። ካርታውን ልሰጣቸው ተዘጋጅቼ ሳለ ትተውት አዋክበውኝ ይዘውኝ ወጡ። ቀጠሉናም በመኪና ከደብረዘይት ወደ ዱከም ሄደን ሻይ እንጠጣ አሉኝ። እኔ ግን ከእነሱ ጋር ሻይ የሚያስጠጣኝ ግንኙነት ስለሌለኝ ደስ ሳይለኝ ተከተልኳቸው።
ከደብረዘይት ከተማ ወጥተን ወደ ዱከም ጨለም ያለ ስፍራ ስንደርስ ለካ ሌላ መኪና ከኋላችን እየተከተለን ነበር። ብቻዬን ነኝ፤ መሐል ሜዳ ነው፤ ሰዓቱም እየመሸ ነበር። ድንገት መኪናውን አቆመ። ምንእንዳረጉኝ አላውቅም አሁን የማላስታውሰው ነገር ተፈጠረ። ብቻ የተከተሉን ሰዎች የደህንነት ሠራተኞች እንደመሆናቸው የሆነ ቦታዬን መተውኝ ራሴን ሳትኩኝ። ከብዙ ቆይታ በኋላ ስነቃ ከመኪናው ጀርባ ባለው የእቃ ማስቀመጫ ውስጥ አስገብተው ሸራ አልብሰውኛል።
ያንን ሸራ ከላዬ ላይ ላነሳ ስል በውሻ ሰንሰለት እግሬም እጄም ታስሯል። እናም መጮህ ጀመርኩኝ። በቃ ዝም በል አሉኝ። የት እንደሚወስዱኝ አላውቅም፤ ብቻ አንድ ቦታ ወስደው አሳደሩኝ። በማግስቱ ሌላ ቦታ ወሰዱኝ። እናም የሆነ ጥያቄ ሊጠይቁኝ ሞከሩ። ግን ደግሞ ይሄነው ብለው የሚነግሩኝ ጥፋት አላገኙብኝም። ግን ደግሞ ዝም ብዬ ለማቆየት ሲሉ እንዳወራላቸው ይወተውቱኝ ነበር። ስለጦርነቱ ያለኝን ሃሳብ ይጠይቁኝ ነበር። እኔ የምትሉን ሁሉ ለመመለስ ዝግጁ ነኝ ፤ ግን እኔ ከሙያዬ ውጭ ለፖለቲካው ባዕድ ነኝ አልኳቸው። ከዚያ በኋላ እጅ እግሬን በሰንሰለት እንዳሰሩኝ ምንም የማይታይበት ጨለማ ክፍል ከተቱኝ።
በነገራችን ላይ ከቦታ ቦታ ሲያንቀሳቅሱኝ ፊቴን ይሸፍኑት ነበር። ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ ቶርች ያደርጉኝ ጀመር። ደግሞም ይዘውኝ የወጡት ያንኑ የበረራ ቱታ እንደለበስኩ ነው። በቃ ቱታው እስከሚበጫጨቅ ድረስ ነበር ሲቀጠቅጡኝ የነበረው። እኔን ብዙ ቢደበድቡኝም ምንም ነገር ሲያጡ መጨረሻ ላይ ጨለማና በጣም ትንሽ ክፍል ውስጥ ወስደው ጣሉኝ። እዛም ሆኜም እጅና እግሬ በውሻ ሰንሰለት እንደታሰረ ነው። አሁን ድረስ የት አካባቢ አስረውኝ እንደነበር አላውቅም። ሁለት ዓመት ሊሞላ ሲል ሲፈቱኝ በፈጣሪ ተዓምር ነፍሴ ትትረፍ እንጂ በጣም ተዳክሜ ነበር። የለበስኩት የበረራ ልብስ እላዬ ላይ አልቆ ነበር። የሚጠይቀኝም ስላልነበርም እጅግ ተስፋ ቆርጬ ነበር። በአጠቃላይ እዛ ጨለማ ክፍል ውስጥ በቆየሁባቸው ጊዜያት በጣም ብዙ ፈተናዎች ነው ያሳለፍኩት።
አዲስ ዘመን፡-ታዲያ እንዴት ሊፈቱ ቻሉ?
ካፒቴን ተሾመ፡- እዚያ ጨለማ ቤት ውስጥ አስቀምጠውኝ በአካልም በመንፈስም እጅግ ተዳክሜ ሳለሁ አንድ ቀን አንድ ሰው መጣና ‹‹ምንም ልናገኝብህ አልቻልንም፤ ከሁሉ በላይ ግን ኢትዮጵያ ዛሬ ትፈልግሃለች›› አለኝ። እኔ እየሞትኩኝ ያለሁ ሰው እንዴት ኢትዮጵያ ትፈልገኛለች የሚል ጥያቄ ተፈጠረብኝ። ምንም ነገር ስላላገኘነብህ ወደ ክፍልህ ተመልሰህ ትነጋገራለህ አሉኝ። እንግዲህ ከዚህ ሁሉ ቆይታ በኋላ እንደዚህ አይነት ንግግር እሰማለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። እጅና እግሬ እንደታሰረና ፊቴ እንደተሸፈነ ከሞቃት አካባቢ ያመጡኝ ይመስለኛል፤ ብቻ ረጅም ሰዓት ከነዱ በኋላ በቅሎ ቤት አካባቢ አንድ አዲስ የተሰራ ሕንፃ ውስጥ አስገቡኝ። እዚያ ስንደርስ መሽቶ ስለነበረና ራቁቴንም ስለነበርኩኝ በጣም በረደኝ። የሆነ ጥግ ላይ አስቀመጡኝ። አንድ ሌላ የእነሱ ሻለቃ ሲያስጠራኝ እንደበረደኝ ተገነዘበና ሰንሰለቴ እንዲፈታልኝ አዘዘ፤ ልብስ እንዲሰጡኝ ነገራቸውና የሴት ሱሪና ሸሚዝ ሰጡኝና ለበስኩኝ።
ቀጠለናም ‹‹እስቲ ያንንም ጥሩት አለ››፤ ከሩቅ ይዘውት ሲመጡ እንደእኔ አስረው ያሰቃዩትና አብሮኝ ይበር የነበረ የማውቀው ልጅ ነው። ልክ ሳየው ያሳሰረኝ እሱ እንደሆነ ሊመሰክርብኝ እንደሆነ አሰብኩኝ። ከዚያ መጀመሪያ ያመጣኝ የነበረው የደህንነት ሰው ‹‹አትተዋወቁም እንዴ?›› ብሎ ጠየቀኝ፤ እኔ ግን ከዚያ ሁሉ ድብደባ በኋላ አዕምሮዬ ማሰብ የቻለው ሰውዬው ሊመሰክርብኝ እንደሆነ ብቻ ነው። እናም እኔ ሊመሰክርብኝ ከሆነ እኔ ለማዳመጥ ዝግጁ ነኝ ብዬ ተናገርኩኝ። እሱ ግን በጣም አዝኖ ጭንቅላቱን ወዘወዘ። ይሄን ጊዜ ሻለቃው ግራና ቀኝ አስቀመጠን መሐላችን ቁጭ አለ። አሁንም ‹‹አገራችሁ ትፈልጋችኋለች›› የሚል ነገር ተናገረ። ከኤርትራ ጋር ይደረግ የነበረው ጦርነት አላለቀም ነበር፤ ስለዚህ ወደ ክፍላችሁ ሄዳችሁ ሪፖርት አድርጉ አሉን። እኔም ያንን ሲሉኝ እኛ? ብዬ ጠየኳቸው። ታምሜና ተዳክሜ የነበርኩት ሰው መነቃቃት ጀመርኩኝ። ለእኔ ተዓምር ነው የመሰለኝ። ጓደኛዬም ከወዲያው ጫፍ ቁጭ ቢልም ምንም መነጋገር አልቻልንም።
አመሻሽ ላይ ደብረዘይት አየር ኃይል ጊቢ ወሰዱንና የጠፉ ሰዎች የሚቆዩበት ክፍል ወስደው ከሌሎች እስረኞች ጋር ቀላቀሉን። ለእኔ ያ ራሱ ተዓምር ነው የሆነብኝ። ምክንያቱም ከሁለት ዓመት በኋላ ከሰው ጋር ስቀላቀል የመጀመሪያዬ በመሆኑ ነው። እየዳንኩኝ ነው ብዬ ማሰብ ጀመርኩኝ። ከዚያ አብሮኝ ከታሰረው ጋር የሆነብንን ተመሳሳይ ነገር አወራን። በማግስቱ ምሽት ላይ እኔን ኮሎኔል ተመስገን የተባለ ሰው አስጠራኝና ከአየር ኃይሉ አዛዥ አበበ ተክለሃይማኖት ተልኮ ስለመምጣቱ ነገረኝ። ‹‹ወደ ሥራ እንድትመለስ ይፈልጋሉ›› ብሎ ምን እንደሆነ ሃሳቤን ጠየቀኝ። እምቢ ብል ተመልሰው እስር ቤት ሊከቱኝ ስለሆነ ያለኝ አማራጭ መስማማት ስለሆነ ይችላል ብላችሁ ካሰባችሁ ደስ ይለኛል፤ ስለጓደኛዬም እኔ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ አልኩት። ይሁንና እኔ በወቅቱ የማስበው ከዚህ በላይ ከእነሱ ጋር አብሮ መሥራትም ሆነ መኖር እንደማይቻል ነበር።
በመሆኑም እጄ ላይ አውሮፕላን ስለሚሰጠኝ አማራጭ እንደሚኖረኝ አሰብኩኝ። ጓደኛዬ የእነሱን ፍላጎት ስነግረው በጣም ተናደደ፤ ከእነሱ ጋር አብሮ መስራት እንደማይፈልግ ነገረኝ። ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ አሳመንኩት። በማግስቱ ኮሎኔሉ ዳግመኛ አስጠራኝና ‹‹እስካዛሬ የቆየህበት ሁኔታ ለማንም ላለመናገር መስማማትህን ፈርምልኝ›› አለና አንዳች ወረቀት ሰጠኝ። እኔም ሳላነብ ዝም ብዬ ፈረምኩት። ወደ ምሽት ላይ ሂዱ ብለው ሸኙን። በር ላይ ቤተሰቦቻችን ተቀበሉን። እኔ ወደ እናቴ ቤት ልሄድ ስል ወንድሜ እናታችን ከከተማ ስለወጣች እሱ ቤት እንድሄድ ጠየቀኝ። ብዙም ደስ ሳይለኝ ተስማምቼ አብረን ሄድን። በማግስቱ ሌሊት የወንድሜ ባለቤት እናቴ ማረፏን አረዳችኝ። እናቴ ቤት ስገባ ደግሞ ያሳደጉኝ ጎረቤት ሁሉ ተሰብስቦ ጠበቀኝ። እናቴ እኔን ፍለጋ ብዙ ተንገላታ ነው የሞተችው። ከጠፋሁ ዕለት ጀምሮ አየር ኃይል በር ላይ ቆማ ልጄን አምጡ እያለች ትጮህ እንደነበር ነገሩኝ። እለት በእለት ሳታገኘኝ ስትቀር እያበደች መጣች። የአየር ኃይል አዛዡ አበበ ተክለሃይማኖት ሲገባም ሲወጣም መኪናው ሥር ወድቃ ትማፀነው እንደነበር፤ ጠባቂዎች እየወጡ ይገፈትሯት እንደነበር ነገሩኝ። በዚህ ሁኔታ ሶስት አራት ወር መቆየት አለመቻሏን ስሰማ በጣም ተረበሽኩኝ። በቃ ከዚህ በኋላ ከእነሱ ጋር መቀጠል ከባድ ሆነብኝ። ‹‹አገርህ ትፈልጋሃለች›› የሚለው ነገር ቀልድ መሰለኝ።
ይሁንና ቁጭ ብዬ ማዘንም አልፈለኩም፤ ሶስት ቀን ቆየሁና አየር ኃይል ተቀላቀልኩኝ። ስደርስ ፈረንጆች ብቻ ነበሩ እዛ ክፍል ውስጥ ይሰሩ የነበሩት። አየሽ፤ በቂ የሰው ኃይል ስላልነበራቸው ጦርነቱ የተካሄደው በፈረንጆች ነበር። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸው ነበሩ። በመሆኑም አገሪቱ ያንን መሸከም ስለከበዳት እኛን ማስገባት ፈለጉ። የሚገርምሽ አንድ የቀድሞ አባል የነበሩ ጀነራል መስፍን ተጫነ የተባሉ አስተማሪዬ በዚያ እድሜያቸው እንዲያበሩ ተደርገው ነበር። ነገር ግን ከእሳቸው የተሻሉ ወጣቶች እስር ቤት አጉረው እሳቸውን በስተርጅና እንዲህ አይነት ግዳጅ መስጠታቸው በጣም ግራ አጋባኝ። እኚህ ሰው አስተዳደራዊ ሥራውን ቢሰሩ የበለጠ ለአገር ይጠቅሙ ነበር። እኚህ ሰው ቢሯቸው ወስደው ሰባት ዓመት አስረዋቸው ለጦርነቱ ሲሉ እንደፈቷቸው ነገሩኝ። እንዲህ አድርገዋቸው እንኳን ‹‹አገር ላይ አይኮረፍም›› ብለው እኔንም መከሩኝ። ሥራውን ከፈረንጆቹ እንድረከብ ስለመጠራቴም ነገሩኝ። እኔ ግን ሰውን ሁሉ የምጠራበት ቁጭትና በቀል ስነልቦና ነበር የነበረኝ። ያ ሁሉ በደል ደርሶብኝ እናቴን በዚህ ምክንያት አጥቼ እንኳን ምንም እንዳልተፈጠረ ከእነሱ ጋር በሰላም እንደምሠራ ነበር ያሰቡት። ከሙያው ባሻገር አብሮ የስነልቦና ሜካፕ ሊኖር ይገባ ነበር።
ወዲያውኑ ደግሞ አየር ኃይሉን ነቀሉና መቀሌ ወሰዱትና እኔም እዛው ሄድኩኝ። ተማሪዎች ይዘን የበረራ ልምምድ እናደርግ የነበረ ቢሆንም አካባቢው የጦርነት ቀጠና በመሆኑ ብዙ ርቆ ለመሄድ አይቻልም ነበር። አካባቢው በራዳርና በሚሳኤል የታጠረ በመሆኑ መመታት ሊኖር ይችላል። ከሁሉ በላይ ደመወዝ መቀበል ቀፈፈኝ። ምክንያቱም ይህ ደመወዝ የእኔ የደም ዋጋ ያለበት ነው። እናቴን ከገደሏት ሰዎች ገንዘብ የምቀበል መሰለኝ። በፍፁም ራሴን ማስተካከል አቃተኝ። ይህ ከሆነ በቃ አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ብዬ ማሰብ ጀመርኩኝ። ጎረቤት አገሮችን ሁሉ አጤንኩኝ። ነገር ግን ከኤርትራ በስተቀር ከሁሉም ጋር ስለሚቀራረቡ ወደዚያ ብሸሽ አሳልፈው ይሰጡኛል የሚል ስጋት አደረብኝ። ስለሆነም ወደ ኤርትራ መሄድ አንድም እነሱን ለመቅጣት እድል ይሰጠኛል፤ ሁለትም ለእኔ አስተማማኝ ሆኖ አገኘሁት። ግን ደግሞ ከኤርትራ ጋር የሚያገናኘን ድንበር በራዳር አጥረውታል። ቢመቱኝም ኃላፊነቱን ወስጄ መሄድ እንዳለብኝ ወሰንኩኝ። ስለዚህ አንድ ጠዋት ተነስቼ አንድ ሌላ እንደእኔ በእስር የተሰቃየ ጓደኛዬን ይዤ አዲስ የነበረች አውሮፕላን ለመፈተሽ በሚል በዚያው ነው ወደ ኤርትራ የሄድኩት።
አዲስ ዘመን፡-ግን የኤርትራ መንግሥት እንዴት ሳይጠራጠር ተቀበላችሁ?
ካፒቴን ተሾመ፡– አስቀድሜ እንደነገርኩሽ የኤርትራ ሰዎች የሩቅ ሰዎች አይደሉም። አብዛኞቹ የምናውቃቸው ሰዎች ናቸው። ኮማንደር ሃብተፂዮን ሃድጉ የተባለ ሰው ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ ይሰራ ስለነበር እንተዋወቅ ነበር። ሁለተኛ ግን እኛ እናስብ የነበረው እዛ ደርሰን የሚደርስብንን ሳይሆን ከዚህ ማምለጣችንን ነው። ያንን የጦርነት ቀጠና አልፌ ከሄድኩ ነው ወያኔዎቹን የምቀጣው ብዬ ነው ያሰብኩት። ስለዚህ ተደብቄ ነው የሄድኩት። በእርግጥ በቀጥታ ከመቀሌ አስመራ ብሄድ ሩቅ አይደለም፤ እኔ ግን ወደዚያ አልሄድኩም፤ በአፋር ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ዝቅ ብዬ መሬት ለመሬት በሚባል ደረጃ እያበረርኩኝ ነው የሄድኩት። ወደ መሬት ዝቅ ባልሽ ቁጥር ደግሞ ከራዳር እይታ ውጪ ትሆኛለሽ። እናም መሬት ለመሬት ሄጄ ቀይ ባሕር ላይ አረፍኩኝ። በአጋጣሚ ደግሞ እንደገና ከምስራቅ ወደ ሰሜን ስበር በተመሳሳይ ሰዓት ከምፅዋ አሰብን የሚገጥም መንገድ ኤርትራውያኖቹ ሰርተው ነበርና ያንን ለማሳየት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋዳፊን እያስጎበኘ ነበር። እኔ በእነሱ ላይ ነበር የበረርኩት። ያ ሁሉ ሲሆን ግን እኔ የማውቀው ነገር አልነበረም።
በኋላ ተሸሽጌ እንደሄድኩ አስመራ ከተማ ገባሁኝ። ከተማ ላይ አንዴ ከደረስኩኝ ሊመቱኝ አይችሉም የሚል ሃሳብ ነበረኝ። እኔ ምንም መሳሪያ አልያዝኩም፤ ስለራሴ ሁኔታ በሬድዮ እየገለፅኩኝ ነው ያስረዳኋቸው። አየር ላይ ሆኜ መጣራት ጀመርኩኝ። እየተጣራሁ ሳለ አንድ ከላይ የሚበር የኤርትራ አውሮፕላን አብራሪ እነሱ እየሰሙኝ እንዳልሆነ እኔ ምን እንደፈለኩኝ ጠየቀኝ። ማንነቴንና የመጣሁበትን ምክንያት ነገርኩት። እንደ ዕድል ሆኖ አብራሪው እኔ ካስተማርኳቸው የኤርትራ ተማሪዎች አንዱ ነበር። ‘ሚግ 29’ ይዞ አየር ላይ ነበርና ማንነቴን ሲያውቅ አማርኛ ትግርኛ እየቀላቀለ ማንነቴን አጣራ። እኔም በአየር ላይ የምንጠራራበት ስም ማንነቴን ስገልፅለት አወቀኝ። እናም በእኔ ጉዳይ ከዋናው ጣቢያ ሰዎች ጋር መጨቃጨቅ ያዘ። እሱ እንደሚያውቀኝና ኃላፊነት እንደሚወስድ ነገራቸው። በዚህ መሐል እኔ አረፍኩኝ።
ይህንን ሲያዩ ‹‹ተመለስና ወደ መጨረሻ ሂድ›› አሉኝ። እኔ ግን ሰው እንዲያየኝ ስለፈለኩኝ እንዳልሰማሁ ዝም አልኳቸው። ሚሊተሪ ተርሚናል አልፌ ሲቪል ተርሚናል ገባሁና አቆምኩኝ። ራቅ ብሎ ሉፍታንዛ አለ፤ በጎን ደግሞ የኬኒያ አውሮፕላን አጠገብ ነው ያቆምኩት። የእኔ አውሮፕላን የኢትዮጵያ ባንዲራ አለበት። ከተርሚናሉ ነጮችና ሌሎች ሰዎችም መውጣት ጀመሩ። በመቀጠልም መትረየስ የያዙ አራት ፒካፖች ከበቡኝ። ሞተሩን አጥፍቼ ሄልሜቴን እንዳደረኩኝ አንድ ሰው ወደ እኔ መምጣት ጀመረ። ሰውየው እየቀረበ ሲመጣ ደግሞ ድሮ አየር ኃይል የነበሩ ካፒቴን አብረሃም እንቁበስላሴ የተባለ የማውቃቸው ሰው ሆኖ አገኘሁት። እሳቸው መሆናቸውን ሳውቅ የአውሮፕላኑን መስኮት ከፈትኩና ሄልሜቴን አወጣሁኝ። ጤና ይስጥልኝ ካፒቴን አብርሃም አልኩት። ጠጋ አለና ረጅም ደቂቃ ካየኝ በኋላ ‹‹ግድ የለም፤ ከቤት ወደቤት ነው የመጣችሁት ይሁን፤ አይዞህ!›› አለኝ። በሌላ መኪና ደግሞ ያ አውቀው ነበር ያልኩሽ ሃብተፂዮን የተባለው የአየር ኃይሉ አዛዥ መጣ። እሱም በደስታ ተቀበለኝና አቀፈኝ።
ይሁን እንጂ ለወር ያክል ግን ብዙ ጥያቄዎች ሲጠይቁኝ ነበር። ምክንያቱም እኔ የበረርኩት በእነኢሳያስና ጋዳፊ ላይ መሆኑ ጥያቄ ፈጥሮባቸው ስለነበር ነው። እንዳውም በዚያ ምክንያት ብዙ ሰዎች ታስረው ነበር። ያንን መስመር መጠበቅ ነበረባቸው። እኔ ዝቅ ብዬ እበር የነበረው ከራዳሩ ለመሸሸግ እንጂ እነሱ መኖራቸውን የማውቀው ነገር አልነበረም። ግን ደግሞ ስለእኔ የተፃፉ ጋዜጦችን ይዤ ስለነበር ሰጥቻቸው ታሪኬን አነበቡና እውነታውን ተገነዘቡ። ለሚዲያ ሳይናገሩ ዝም አሉ። ግን በአጋጣሚ ከኬንያ አውሮፕላን አጠገብ ስቆም ያዩኝ ሰዎች ነበሩ። በኋላ ላይ እንደሰማሁት በኤርትራ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኃላፊ የሆነች ፈረንጅ አይታኝ ነበር። ‹‹በመሐል ጉዳት እንዳይደርስበት›› በሚል በአስቸኳይ ወደ ሌላ አገር እንድሄድ ጥረት አደረገች። ካናዳ ስዊድንና አሜሪካ ሊቀበሉኝ እንደሚችሉ አሳወቁና ከአንድ ዓመት በኋላ ካናዳ ገባሁኝ።
ካናዳ በቆየሁባቸው ላለፉት 20 ዓመታት ካናዳ ጥሩ ኑሮ ባገኝም አርፌ አልተቀመጥኩም። እንደነገርኩሽ ስወጣ በቁጭት እንጂ አገር ጥሎ ለመክዳት አልነበረም የወጣሁት። ካናዳ ተመችቶኛል፤ ዝም ብዬ ቁጭ ማለት እችል ነበር። ግን መቀመጥ አልቻልኩም። ስለዚህ 33 ገፅ የሚሆን ወረቀት በሕይወቴ ያጋጠመኝን አስከፊ ሁኔታ ፃፍኩት። በተጨማሪም ኢሳት ላይ ቀርቤ የእነሱን ማንነት ማጋለጥ በቋሚነት ስለአየር ኃይል ሙያዊ አስተያየት በመስጠት ሕዝቡ እውነታውን እንዲገነዘብ አድርጌያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ወያኔን ያኔ ከጅምሩ መቅጨት ቢቻል አሁን ላይ የተከሰተው ችግር ይፈጠራል ብለው ያምናሉ?
ካፒቴን ተሾመ፡- አስቀድሜ የነገርኩሽ አብሮኝ ታስሮ የነበረው ዳንኤል የተባለው ልጅ እንሂድ ስለው ‹‹እምቢ›› ብሎ ቀርቶ በድንገት መኪና ተገልብጦ ሞተ ተባለ። ግን እውነታው በጥይት ጭንቅላቱ ተመቶ ነበር። ይህንን ልጅ አጥፍተውታል። እናቱም ልክ እንደእኔ እናት እንዲሁ እንደተቃጠሉ አረፉ። ይህንን ሁሉ ስታዪ ዝም ብሎ በየዋህነት የሚፈፀም ነገር አይደለም። ሰዎችን ብቻ አይደለም እያጠፉ የነበረው፤ የኢትዮጵያን ጠባቂዎች ጭምር እንጂ!። እኔ የነገርኩሽ ታሪክ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ አይደለም፤ እኔን በዚያ መልኩ ከምወደው ሙያ ሲያገሉኝ የአገርንም ተስፋ ጭምር ነው የቆረጡት። ወያኔዎች የተወሰነ ያህል እውቀትሽን ከወሰዱ በኋላ ያስወግዱሻል። በምትኩ ደግሞ የራሳቸውን ሰዎች ብቻ እየሰበሰቡ ሲያስገቡ ነበር። ዝም ብሎ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብቻ ይህንን ሙያ ማስተማር አደገኛ ነው። በወቅቱ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ከተፈለገ ይህ አሠራር መስተካከል አለበት የሚል ሃሳብ አነሳ ነበር።
የሚገርምሽ ከእስር ከወጣሁ በኋላ ያለ በቂ መስፈርት ሲያስገቧቸው የነበሩ የእነሱ ሰዎች በሙሉ አልቀዋል። የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት የነበሩ በርካታ አውሮፕላኖችም ወድመው ነበር። መጀመሪያ ላይ ያሳፈነኝ ሰው ራሱ ሳይቀር ሞቷል። እግዚአብሄር አስቀድሞ ፍርዱን ቢሰጥም ኢትዮጵያ እንደ አገር፤ አየር ኃይሉ እንደተቋም ስጋት ውስጥ ወድቆ ነበር። ይህንን እውነታ ቆይተውም ቢሆን ሲገነዘቡ የተወሰኑ ሰዎችን ለመቀላቀል ሞከሩ። በተለይ ደግሞ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ተከትሎ የአንድ ብሔር የበላይነት ነገር ብዙ ጩኸት በዛባቸው። ስለሆነም አስር ሰው ሲያመጡ አንድ አማራ አንድ ኦሮሞ መቀላቀል ጀመሩ። ግን የሚቀላቅሏቸው ከእነሱ የባሱ ሰዎችን ነው። እነዚህ ሰዎች አንካሳ ወይም የአቅም ችግር ያለባቸው ነበሩ። ይህንን የሚያደርጉት ሆን ብለው ሰዎቹን እንድትጠያቸው አስበው ነው ። እንደዚህ አይነት በጣም የረቀቀ ሥራ ነው የሚሰሩት። እንደዚህም ሆኖ ነገሮች መሆን አልቻሉም። በኋላ ላይ ከዩኒቨርሲቲ ወጣቶች መቀላቀል ሲጀምሩ አሁን ያሉት እነ ይልማ መርዳሳ የመሳሰሉ ሰዎች መግባት ጀመሩ። ይሁንና ዋናዋና ቦታ ላይ የራሳቸውን ሰዎች አስቀምጠው እነይልማን የማይገባቸውና ከሙያቸው ውጭ የሆነ ስፍራ ሰጧቸው።
እኔ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አገር በጣም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባቷን ፤ በተለይም በተቋሙ የኃይል አለመመጣጠን መኖሩ በአገር ላይ የሚያመጣው ችግር ያሳስበኝ ነበር። በዚያ ሁኔታ እስከቀጠለ ድረስ አሁን ወደደረስንበት ቦታ መድረሳችን አይቀርም ነበር። ያም ቢሆን ከጠበቅነው ስጋት አንፃር የሚነፃፀር አይደለም። ምክንያቱም የለውጡ ኃይል ጉዳዩን በጥበብ በመያዙ እንደሆነ አስባለሁ። አሁንም ቢሆን አገሪቷን የያዟት እጆች ቢለቀቅ ሊፈርስ የሚችል ቋፍ ላይ ያለ ነው የሚመስለኝ። በተለይም ዶክተር አቢይ ጉዳዩን የያዘበት ሁኔታ ለእኔ አስገራሚ ነው። አሁን አሁን የምናየው ጦርነት እንደኛ ከምንም ለተነሳ አገር ከባድ ነበር። እነሱ ወደዚህ ጦርነት ሲገቡ መቶ በመቶ የታጠቀ ኃይልና ቴክኖሎጂ ይዘው ነው። 300 ኪሎ ሜትር የሚሄድ ሮኬት ሁሉ ነበራቸው። እኛ ግን ምንም አልነበረንም። የሚገርምሽ ድሮኑን መቀሌ ሊወስዱት ነበር። ያንን ሊቆጣጠር የሚችል ሙሉ ሙያተኛ አላቸው። ይህ ሆኖ ሳለ እነ ዶክተር አብይ ያ ሁሉ መሳሪያ እንዴት አድርገው እንዲከሽፍ እንዳደረጉባቸው ሳስብ ዛሬም ድረስ እንደተዓምር ነው የሚታየኝ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ባሉበት አገር ሆነውም ለአየር ኃይሉ ቀጥተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር ሰምቻለሁ። እስቲ አሁን ደግሞ ስለዚህ ሁኔታ ያስረዱን?
ካፒቴን ተሾመ፡– እኛ ውጭ ሆነን የምንሰራው ትልቁ ሥራ አየር ኃይልን ማዳከም ነበር። ምክንያቱም እዚያ ተቋም ውስጥ ኢትዮጵያ የለችም ነበር። ሁሉንም ዜጋ የሚያሳትፍ ስፍራ አልነበረም። ስለዚህ ባይተዋር ሆነሽ በዚህ ሙያ መቀጠልና ኃላፊነት ሊኖርሽ አይችልም። የሠራዊቱ አባል ስትሆኚ ደግሞ ከራስሽ አልፈሽ ስለአገር ነው የምታስቢው። እይታሽ ይሰፋል። በቀጠናው ስላሉ ጠላቶቻችን በማሰብ ነው የምትጠመጂው። ለነገሩ ኢትዮጵያ እንደጠላቶቿ ብዛት ዛሬ አልነበረም መጥፋት የነበረባት። ምክንያቱም ኢትዮጵያን ለማጥፋት ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል። እነዚህ ወጣት ተማሪዎች ያንን ሥርዓት የሚያገለግሉ ከሆነ ነገሮች እየተበላሹ እንደሚሄዱ ነበር የማየው። ስለዚህ በተቻለ መጠን እነዚህ ልጆች ከዚህ ተቋም ራሳቸውን የሚያገሉበት እና ወደ ውጭም ወጥተው ቢሆን ትግሉን እንዲቀላቀሉ ነበር የምናደርገው። ምክንያቱም ወያኔ መላውን ሕዝብ እስከመጨረሻ ቅኝ ገዝቶ ሊቀጥል አይችልም። ነገሮች ይቀየራሉ። እኛ ደግሞ አየር ኃይሉ ጠቅላላ ወደ መቀሌ የመውሰድ ነገር ምን ሊያመጣ እንደሚችል እንገምት ነበር። በተቻለ መጠን ራሳችንን ስናዘጋጅ ነበር። በአገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ድጋፍ ስናደርግ ነበር። ፈጣሪ ይመስገን ተሳክቶልን ለውጥ መጥቷል።
ለውጡ የመጣበት ሁኔታ ግን ከዚያው ከኢህአዴግ ውስጥ መሆኑ ያለውን ኃይል መጠቀም ተችሏል። ለውጡ ከውጭ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ትገባ ነበር። ከውስጥ ስለሆነ ግን መዋቅሩን ራሱ እየተጠቀምሽ ነው ቀስ እያለ እንዲለወጥ ለማድረግ የሚቻለው። ያ መሆኑ ኢትዮጵያን የጠቀማት ይመስለኛል። እነዚህ የለውጥ ኃይሎች ውስጥ ያለውን ብቻ ሳይሆን ውጭ ያለውን ኃይል የመጠቀም ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ብዙ እገዛ አድርገንላቸዋል። እኔ ለውጡ እንደመጣ ጀኔራል አለምሸት ወዲያው ነው ያገኘኝ። በነገራችን ላይ የቀድሞ አየር ኃይል ሠራዊቱ አሁንም ድረስ በኔትወርክ የተሳሰረ ነው። የትም አገር ይኑር በኔትወርክ ይገናኛል፤ ውይይት በአገራችን ጉዳይ እናደርጋለን።
በተለይም ለውጡ እንደመጣ ለመንግሥት ፕሮፖዛል ከማቅረብና ከማማከር ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎች እናደርጋለን። እነዚህ ሰዎች አውሮፕላን በእጃቸው ቢሆን ኖሮ የመጀመሪው ጦርነት ራሱ ለኢትዮጵያ መንግሥት ከባድ ነው የሚሆነው። አይተሽ ከሆነ እነዶክተር አብይ እስከመጨረሻው ድረስ ታግሰው ነበር። የሚታገሱት ግን አቅም ስላልነበራቸው ነበር። አውዳሚ የሆኑ መሳሪያዎችን በተቻለ መጠን ከትግራይ እንዲያወጡ ፕሮጀክት ነድፈን ሰጥተናቸው ነበር። አብረን እየተጋገዝን ነበር የምናደርገው። በዚያ መሠረት ቶሎ እነዚያን መሣሪያዎች ወደመሐል አገር ባያመጡት ሁኔታው ከባድ ነበር የሚሆነው። አሁን ከገጠመን ችግር የበለጠ ይሆን ነበር።
አዲስ ዘመን፡-ኢትዮጵያ በአሸባሪው ቡድን ከገባችበት ችግር ውስጥ መውጣት የምትችልበት ተስፋ ምንድነው ብለው ያምናሉ?
ካፒቴን ተሾመ፡- እየተዋጋን ያለነው እኮ ከወያኔ ጋር ብቻ አይደለም። ሕወሓት የነጮቹ መሳሪያ ሆኖ ነው እየተዋጋን ያለው። ከሕወሓት ጀርባ አጠቃላይ የምዕራባውያን ስትራቴጂክ ዲዛይን አለ። ኢትዮጵያ በቀጠናው የምትጫወተውን ሚና ለመቆጣጠር ሲባል ዘመናት ያስቆጠረ ሥራ ሲሠራ ነበር የቆየው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አገር ወዳድነት ለአፍሪካ የሚወደድ አይደለም። ኢትዮጵያ ላይ እያጠላ ያለው ነገር ዛሬ የጀመረ አይደለም። ምዕራባውያኑ በተለይ ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ጫና ለመፍጠር ይሞክሩ ነበር። ንጉሡም ወደው አልነበረም መከላከያቸውን ጠንካራ ለማድረግ ሲሠሩ የነበሩት። ኢትዮጵያ በነገራችን ላይ እነዚህ ሰዎች እስከሚመጡ ድረስ ጠንካራ የምትፈራ አገር ነበረች። አየር ኃይሉ፤ የምድር ጦሩም ሆነ ባህር ኃይሉ በከፍተኛ ብቃት ላይ የነበረ ነው።
ሱዳንን በአንድ ቀን ሄዶ የፈለግነውን ማድረግ የምንችልበት አቅም ላይ ነበርን። እኔ አሁን የተፈጠረውን ነገር ከሕወሓት በላይ ነው የማየው። እርስ በርስ በሚመስል ደረጃ የአንድ እናት ልጆች እንዲህ መጨራረሳችን ያሳዝነኛል። ከሁሉ በላይ ሕወሓቶች የፈለጉትን ቢያደርጉ እንኳን የፖለቲካ ግብ ስላላቸው እንደሆነ አስባለሁ። የትግራይ ሕዝብ ለምን ይህንን ሊቀበል እንደቻለ አይገባኝም። ቅር የሚያሰኘውም የትግራይ ሕዝብ እንዴት ‹‹ተዉ!›› አይልም ብዬ ነው። ምክንያቱም አብረን የኖርነው ከአክሱማዊት ሥርወ መንግሥት በፊትም ነው። ታዲያ አብሮ የኖረ ሰው እንዴት ይህ ሁሉ ነገር ወያኔዎች ግፍ ሲፈፅሙ ዝም ይላል?። ደግሞም እኮ እርስበርስ ያልተጋባና በደም ያልተሳሰረ የለም። የትግራይ ተወላጆች ኢትዮጵያውያኖች ሆነው ሳለ ለምን በዚህ ደረጃ አማራንም ሆነ ሌላውን ማኅበረሰብ እንደጠላት ማየት እንደፈለጉ ለእኔ ግልፅ ሊሆን አይችልም።
በመሰረቱ ወያኔዎች በዕብሪቱ የጀመሩት ጦርነት መጨረሻ ያውቁታል ብዬ አላስብም። ከሌላው ኅብረተሰብ ተገንጥለው መኖራቸው የሚያመጣባቸውን የባሰ ችግር አስበውታል ብዬም አልገምትም። ዝም ብሎ የልህ ነገር ሆነና አብሯቸው የኖረውን ንፁሕ ሕዝብ ጨፈጨፉ፤ ንብረት አወደሙ። በድሃ አቅማችን ይህንን ሁሉ የምናደርግበት ነገር ያሳዝነኛል። አሁን የገባንበት ነገር የባሰ እንዳውም ሁለተኛ እንዳንተያይ የሚያደርገን ነው። ግን እንደመንግሥት ነው ማሰብ ያለብን።
እንደመንግስት ስታስቢ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ያስፈልጋል። በተቻለ መጠን ትግራይንም የጨመረች ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ነው መድኃኒት መፈለግ ያለብን። እንደሽፍታ ብናስብ ኖሮ እነሱ የሚደርጉትን ማድረግ ከባድ አይደለም። ግን መንግሥት ስትሆኚ በጣም ኃላፊነት ይኖርብሻል። ከኃላፊነት ስሜት ውጭ በመንቀሳቀሰ ከወያኔዎቹ ጀርባ ላለው ትልቁ ኢትዮጵያን የማፍረስ ስትራቴጂ ስኬት እንዳንተባበር ነው የምፈራው። ጥፋት ጠፍቷል። ይህ ልንክደው የምንችለው ሐቅ አይደለም። ግን ‹‹ሄደን እንበቀል›› የሚለው ነገር ከባድ ነው። ከዚያ ይልቅ መፍትሔ ነው ማበጀት ያለብን። ምክንያቱም ጉዳቱ የሁላችንም ነው። ኪሳራው በጣም አሳዛኝ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምዕራባውያኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እያደረጉት በአንድ ጎን ያመዘነ፤ እውነታውን ያላገናዘበ ጫና እንዴት ያዩታል? ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው የዲፕሎማሲ አካሄድ ምንያህል አዋጭ ነው ይላሉ?
ካፒቴን ተሾመ፡-የመንግሥትን የዲፕሎማሲ አካሄድ እኔ እንዳውም በጣም እድለኞች ነን ብዬ ነው የማስበው። ለመንግሥት ቀላሉ ነገር አሜሪካኖቹ የሚሉትን መቀበል ነው። አሁን የእነሱ ፍላጎት ደግሞ እኛን ትናንሽ አገር ማድረግ ነው። እንደዩጎዝላቪያ ተለያይተን ሁሉንም በቀላሉ የሚያዙበትን ሁኔታ መፍጠር ነው የእነሱ ትልቁ ፍላጎት። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከግድቡ አንፃር ያላትን ነፃ አገር የመሆን ስነልቦና የማፍረስ፤ አፍሪካን ሙሉ ለሙሉ የመቀራመት፤ ሃብቷን ለመበዝበዝ ሲሉ ነው። ይህንን ለማድረግ በሕብረት ከሆንን አይመቻቸውም። ስለዚህ አፍሪካን ሙሉ ለሙሉ የማዳከም፤ እርስበርስ እንድንለያይ የማድረግ እቅድ ነድፈው ነው የሚንቀሳቀሱት።
በተለይም አሜሪካኖቹ ትልቁ ችግር ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ብቻቸውን መጠቀም እንጂ አፍሪካ እንድትጠቀም አይፈልጉም። ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚያደርጉት በዓለም ላይ የነበራቸው የበላይነት እንዳያከትም በመስጋት ነው። ግን ደግሞ በተቃራኒው ጎልቶ እየወጣ ያለው የእነቻይናና ራሺያ ኃይል ነው። ስለሆነም እነዚህን አገራት ለማጥቃትና አፍሪካን ከእነሱ ለመለየት የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው። ዋናው በር ደግሞ ኢትዮጵያ በመሆንዋ ነው ጫናው የበረታብን። ኢትዮጵያን ከተቆጣጠሩ ሌላውንም ይቆጣጠራሉ።
በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንዳትሆን የማድረግ ሴራ ነው ሲሰሩ የነበሩት። እሷ ተጠቃሚ ከሆነች በአካባቢው ላይ አቅም ትፈጥራለች የሚል ከባድ ስጋት አላቸው። አሁንም ማድረግ የሚገባው ከነጮቹ ጥገኝነት መላቀቅ ነው። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እየበለፀገች ከሄደች ስለብሔራዊ አንድነት ታስባለች። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ደግሞ አሁን ባለው ሥርዓት እድለኞች ጭምር ነን። የፈጣሪም ድጋፍ ያለበት ነው። ምክንያቱም ሕወሓት እንድትፈርስ አድርጎ ነው ገደል አፋፍ ላይ ያስቀመጣት። ለዚህም ነው በሰብ ባስባቡ የመበተን ስጋት ያጠላብን። ባለፉት 27 ዓመታት የተሠራው ስራ አማራ ብቻ ወይም ኦሮሞ ብቻ እንድንሆን ነው። ኢትዮጵዊነትን ወይም አንድነት ከአዕምሯችን እንዲወጣ ብዙ ተሠርቷል። ወያኔ ሕዝቡ ላይ የክፋት ሴራውን ለመሥራት ብዙ ዓመት ዕድል አግኝቷል። ባያገኝ ጥሩ ነበር። እንደእኔ እምነት 1997 ምርጫ እነቅንጅት እንዳሸነፉ ስልጣኑን ተረክበው ቢሆን ኖሮ ጥገናው ቀላል ነበር የሚሆነው። ረጅም ዓመት በዚህ ጉዳይ ላይ ሠሩና ብዙ ተጎድተናል። አሁን በጣም በጥበብ ነው መመለስ ያለብን። አሁን ላይ አንድነትን ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ሊበረታታ ነው የሚገባው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ካፒቴን ተሾመ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 16/2014 ዓ.ም