የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ነባር አመራሮችን በወጣቶች ተክቶ በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ወደ ክልሉ በማውረድ ለማሳካት እንደሚሰራ የድርጅቱ ሊቀመንበር አስታወቁ፡፡
በሰመራ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአብዴፓ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ተጠናቋል፡፡
በማጠቃለያው ወቅት የአብዴፓ ሊቀመንበር አቶ ስዩም አወል እንደተናገሩት ኮንፈረንሱ የፓርቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለአባላቱ በግልጽ በማሳወቅ በቀጣይም በሚካሄደው ሰባተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ አቅጣጫዎች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በዚህም የጋራ አቋም ለመወሰድ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ባለፉት ሁለት አሰርተ ዓመታት የፓርቲው ነባር አመራሮች አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ክልሉ አሁን ላለበት ደረጃ ማድረሳቸውን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም አሁን ወቅቱ የሚፈልገውን የሰለጠነ አመራርነት በመስጠት ከብልሹ አሰራር የጸዱና እውነተኛ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ የተላበሱ አዳዲስና የተማሩ ወጣቶችን በማምጣት በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ወደ ክልሉ በማውረድ ለማሳካት ፓርቲው ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የድርጅቱ ሊቀመንበር እንዳመለከቱት በሰባተኛው መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የፓርቲውን የመተካካት መርህ መሰረት ያደረገና በክልሉ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በመልካም ጎኑ ሊወሳ የሚችል የአመራር መተካካት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡
በሀገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታ ወደፊት ለማራማድ የሚደረገውን ጥረት ፓርቲው በመደገፍ የድርሻውን ለመወጣት የሚየስችለውን እርምጃ በጉባኤው እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ጉባኤው ግልጽነት የተሞላበትና ዴሞኪራሲያዊ በሆነ አግባብ ተካሂዶ በስኬት እንዲጠናቀቅ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የሚገኙ የፓርቲው አባላት ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አቶ ስዩም አስታውቀዋል፡፡
በተለይም ጥያቄያቸውን ሊመልሱ የሚችሉ የጉባኤ ተሳታፊዎችን በጥራት በመመልመል በቀጣይ የተሻለ ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የሚያበቁ ተተኪ አመራሮች እንዲመጡ ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ባወጡት የጋራ አቋም መግለጫ በቀጣዩ ሰባተኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ነባር የፓርቲው አመራሮችን በክብር በመሸኘት በክልሉ ልማትና መልካም አስተዳደር መረጋገጥ ፣ ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ሊሰሩ በሚችሉ ለመተካት በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ የህግ የበላይነት እንዲከበር ፣ ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ የህዝብንና የመንግስት ሃብትን ለግል ጥቅማቸዉ አላግባብ ያዋሉ አካላትን በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡
በኮንፍረንሱ በክልሉ በየደረጃው ከሚገኙ መዋቅሮች የተወጣጡ ከ1ሺህ በላይ አመራሮችና አባላት ተሳትፈዋል፡፡
የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ ህዳር 24/2011ዓ.ም. በሰመራ ከተማ እንደሚጀመር ታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡