በኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን በባለቤትነት የሚመራው ስፖርታዊ ክንውን ባህላዊ ስፖርቶችን ከማጉላት በተጓዳኝ፣ በሀገር አንድነትና ሰላም ላይ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በርካቶች ሲናገሩ ይደመጣሉ።የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማንነታቸው መገለጫ የሆነውን ባህላዊ ስፖርት አንዱ ክልል ከሌላኛው ክልል፣ አንዱ ከተማ አስተዳደር ከሌላው ክልል እና ከተማ አስተዳደር የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት አውድ መሆኑን ይገልጻሉ።
በአምቦ ከተማ ለአንድ ሳምንት የተካሄደው 16ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድርና 12 ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ይሄንኑ ያሳየ መድረክ እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል። በመድረክ ተሳታፊ የነበሩና ከተለያዩ ክልሎች የመጡትን ተወዳዳሪዎች የባህል ስፖርት ውድድሩ ለሀገር አንድነትና ሰላም ያለው ሚና ጉልህ መሆኑን ለአዲስ ዘመን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ወክሎ በኩርቦ የባህል ስፖርት የተወዳደረው አብተው ይርጋ ፤የባህል ስፖርት ውድድሩና ፌስቲቫሉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና አለው ይላል።በተለይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር የእርስ በርስ ቅርርብን ይፈጥራል።
በአምቦ ከተማ በነበረው መድረክም ይሄንኑ በሚገባ መመልከቱን ምስክርነት ሰጥቷል። በውድድሩ ፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት መታየቱን የምትገልጸው ደቡብ ክልልን በመወከልኩርቦ የባህል ስፖርት ተወዳዳሪ የነበረችው ብርሀኔ ብሬ በበኩሏ፣በስፖርታዊ ውድድሩም ሆነ በባህል ፌስቲቫሉ ላይ አንዱ ክልል የሌላውን ባህል በሚገባ እንዲያውቅና ልምድን እንዲቀስም የማድረግ አጋጣሚን ሲፈጥር ለመመልከት መቻሏን ትናገራለች። እርሷ የመጣችበት ክልል በሌላ አካባቢ ያለውን የባህልና ሌሎች ልምዶችን በአንድነት መንፈስ እንዲለዋወጡ ያደረገ መልካም አጋጣሚ ሆኖ እንደተሰማት ገልጻለች። የባህል ስፖርት ውድድሩ ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ ተጀምሮ መጠናቀቁ ደግሞ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከምንም ጊዜው በላይ ጥሩ ነበር ብላለች።
የአማራ ክልልን በባህል ስፖርት ወክሎ የመጣው ወርቅነህ አገኘሁ በተመሳሳይ በአምቦ ከተማ ለአንድ ሳምንት የነበረው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርት ውድድር መድረክ ኢትዮጵያዊነት ስሜትን በመቀስቀስ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ያስፈነጠዘ እንደነበር ይገልጻል። በደጋፊዎች በኩል ይሰሙ የነበሩ ዜማዎችም የልዩነት ነጋሪት ጉሰማውን ድምጽ የዋጠና፣ የአንድነቱን ድምጸት ያጎላም ጭምር መሆኑን ይገልጻል።
በሀገራችን ያለውን የእርስ በርስ መቀራረብ ስሜት በአምቦ ከተማ በነበረው የውድድር መድረክ ላይ በሚገባ እንደተንጸባረቀ ይናገራል። ከስፖርታዊ ፉክክሩ በተለየ መልኩ ሰላምና አንድነት መንጸባረቁ ደግሞ ከውድድሩ አላማ ጋር የተጣጣመ ክንውን እንደሆነ በሙሉ ልብ መናገር ያስችላል ይላል ። ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር አልነበረም።ለዚህ ደግሞ የአምቦ ከተማ ህዝብና አስተዳደር ከፍተኛ የሆነ አድናቆት የሚቸረው መሆኑን በመግለጽ ንግግሩን ይቋጫል። የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ሰለሞን አስፋው በበኩላቸው፣ የስፖርት ውድድሩ ዓላማ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ቱባ ባህሎቻቸውን ለማስተዋወቅና ልምድ ለመለዋወጥ መሆኑን ይናገራሉ።
በመድረኩም ላይ ፍጹም የሆነ ስፖርታዊ ጨዋነትና የእርስ በርስ ግንኙነት የተጠናከረበት መድረክ እንደነበረም ተናግረዋል።የባህል ስፖርት ውድድሩና ፌስቲቫሉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከር አስችሏል:: በቀጣይም የውድድር አውዶች ይኸው መልካም የአምቦ ስታዲየም ግንባታ፤ የከተማዋ የልማት ረሀብ ማስታገሻ ዳንኤል ዘነበ ዳንኤል ዘነበ የውድድር መንፈስ ይበልጥ ይንጸባረቃል ተብሎ ይጠበቃል። «የባህል ስፖርት ተሳትፏችን ለሰላምና ለአንድነታችን» በሚል መሪ ቃል በኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ ከየካቲት 16 እስከ 23 ቀን 2011 ዓ.ም በድምቀት ሲካሄድ የሰነበተው 16ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድርና 12 ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ሰላምና አንድነት በጋራ ተጣመረው የታዩበት መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።
በመድረኩ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ተሳታፊ ያደረገ ነበር። በ13 የስፖርት ዓይነቶች ከፍተኛ ፉክክር በታየበት ሁኔታ ተጀምሮ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በባህል ስፖርቶች ውድድር አማራ ክልል አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ሲያጠናቅቅ አዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ከ2 እስከ 3 ያለውን ደረጃ ይዘው ነበር ያጠናቀቁት:: የብዙዎችን ትኩረት የሳበው 12 ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ደቡብ ክልል አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን ኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ከ2 እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። አዲስ አበባ የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
በዳንኤል ዘነበ