አምቦ ከተማ ዓለም አቀፍ ደረጃን የተላበሰና ዘመናዊ ስታዲየም ባለቤት የምትሆነው መቼ ነው? የሚል ጥያቄ እንቆቅልሽ ሆኖ ቆይቷል። በ1888 ዓ.ም መመስረቷ በታሪክ የተጻፈላት ቢሆንም ከልማት ርቃና ተገላ እንደኖረች ተደጋግሞ ይገለጻል። የአምቦ ህዝብ ከትናንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያ አንድነት፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የተሟገተ ህዝብ ባለቤት ናት።የህዝቧ ለውጥን መሻት፣ ልዩነትን መርሳት ደግሞ በሦስት መንግሥታት ከልማት እንድትርቅ መደረጓን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። የአምቦ ከልማት ውጪ የመሆኑን እውነታ ምስክርነት «በከተማዋ ይሄነው የሚባል ዓለም አቀፍ ስታዲየም ራሱ የለም » ሲሉ ያነሳሉ።
የአምቦ ከተማ ከልማት የመገፋትን ሀቅ ከየካቲት 16 እስከ 24 ቀን 2011 ዓ.ም 16ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 12ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ለመዘገብ ከሥፍራው በተገኘንበት ወቅት ይሄንኑ እውነታ ለመታዘብ ችለናል። ሀገራዊ ስፖርታዊ ክንውኑ መክፈቻው ሆነ መዝጊያውን ያስተናገደው የአምቦ ስታዲየም ለዚሁ ቋሙ ምስክር የሆነ ተናጋሪ ቅርስ ነበር።
የእግር ኳስ ሜዳው ሳሩ እምጥ ይግባ ስምጥ ባይታወቅም ሙሉ ለሙሉ በአፈር ተሸፍኖ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውን በአቧራ የታጀበ እንዲሆን አስገድዶታል። የአምቦ ስታዲየምን የሜዳላይ እንቅስቃሴውን በበጋ ወቅት አዋራ በክረምት ደግሞ የቦካ ጭቃው የሜዳላይ ቆይታን ከአዝናኝነት ወደ ዘግናኝነት እንደሚያሸጋግረው አይን አይቶ ይፈርዳል። የመሮጫው ትራክም ቢሆን አይደለም ለመሮጥ ለመራመድ ራሱ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ነው። በስሙ ብቻ የመሮጫ ትራክ ለመባል ያህል ቀይ አሸዋ የለበሰ ነው።
ይህ የመሮጫ ሜዳው «ፀረ ሩጫ እንጂ የመሮጫ ሜዳ ነው» ብሎ መናገር እጅጉን አሳፋሪ ይሆናል።ይሄን የተመለከተው ዓይኔ በእርግጥም ከአምቦ አብራክ የወጡ እነ ፊጣ ባይሳ፣ ዮሚፍ ቀጀልቻ ………. ሌሎች የአገር ኩራት የሆኑ አትሌቶች የፈሩባት ሆና ስለምን በስታዲየሟ አትሌቶችን የሚያፈራ የማዘውተሪያ ስፍራ እንድታጣ ተፈረደባት ? ሲል ጥያቄውን ለሚመለከተው አሻግሬ ከስታዲየሙ ገጽታ ውጣሁ።
አምቦ ከተማ ከሰው ቀድማ ነቅታ ከሰው በታች ሆና ለምትታወቅ ለከተማዋ አንድ ለእናቱ በመሆን ለዘመናት ሲያገለግል እንደኖረ የከተማዋ ነዋሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተውኛል። ስታዲ የሙ በጊዜው ጥሩ የሚባልና ከጊዜው ጋር አብሮ ይራመዳል። የስፖርቱ እንቅስቃሴም ቢሆን ተመሳሳይ መልክ የተላበሰ ነበር። በከተማዋ መሰረቱን ያደረገው የሙገር ሲሚንቶ ክለብ በሀገርአቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ያሳረፈም ጭምር ነው። የክለቡ መኖር ደግሞ በከተማዋን ስፖርት ላይ የራሱ የሆነ ጉልህ ድርሻን ሲጫወት ቆይቷል።
የእግር ኳሱ ቁመና ይህን መስሎ ጉዞውን ሲያደርግ ቆይቶ ሆን ተብሎ ሙገር ሲሚንቶ መቀመጫውን ወደ ሌላ ቦታ እንዲያሸጋገር መደረጉን ያስታውሳሉ። በዚህ ምክንያት በአምቦ የነበረው የስፖርት እንቅስቃሴ ሆነ የአምቦ ስታዲየም በነበረበት ቆሞ መቅረቱን ይናገራሉ። ስታዲየሙ ምንም አይነት እድሳት ሳይደረግለት የድሮ መልኩን በመያዝ ዛሬ ላይ መድረሱን በቁጭት የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። ከዚህ ቁጭት ጀርባ ከአብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አምቦ ዩኒቨርሲቲ ይሄንኑ ቁጭት ያበረደ ተግባር መፈጸሙን ከመናገር አያመነቱም። የአምቦን የልማት ረሀብ የተመለከተው አምቦ ዩኒቨርሲቲ ከተማዋን ወደኋላ ከቀረችበትን ልማት ፎቀቅ እንድትል ጥረቱን ማድረጉም አልቀረም።
ዩኒቨርሲቲው ከያዘው የመማር ማስተማር ራዕይው እኩል ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ከዚሁ ትይዩ አስፍሮታል። በዚህ መሰረትም ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የልማት ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ተግባሩን ያልዘነጋው ተቋሙ ከዓመት በፊት ያስቀመጠላቸው የመሰረት ድንጋይ ደግሞ ለዓመታት አንድ ለናቱ የነበረውን የአምቦ ስታዲየም የሚያስረሳ ስታዲየም ለመገንባት ውጥን መያዙን ይፋ ማድረጉ ነበር።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሙሉ ወጪ በመሸፈን የከተማዋን ህብረተሰብና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ስታዲየም መሆኑ ደግሞ ድርብ ደስታን የፈጠረ እንደነበር ያነጋገርኳቸው ነዋሪዎች ሳይደብቁ ስሜታቸውን አጋርተውኛል። የአምቦን የልማት ረሀብ የተመለከተው አምቦ ዩኒቨርሲቲ በአዋሮ ካምፓስ እያስገነባ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ግንባታ ሂደትን ለመመልከት ሞክረናል።
የአምቦ ከተማ የዓመታትን ቁጭት ታሪክ ያደርጋል የሚል ተስፋ የተጣለበትን የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ግንባታ በቦታ በመገኘት ጉብኝት ባደረግንበት ወቅት ያነጋገርናቸው በቲኤንቲ ኮንስትራክሽንና ንግድ ድርጅት የአምቦ ስታዲየም ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር አብነት ፊጣ፤ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የግንባታ ሂደት በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘ መሆኑን በመግለጽ ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት።እንደ ኢንጂነር አብነት ገለጻ፤ የግንባታው ኮንትራት ውሉ ስምምነት በ2009 ዓ.ም ግንቦት ወር የተፈረመ ሲሆን፤ በተለያዩ ምክንያቶች ከተባለበት ጊዜ በጥ ቂት ወራት በመዘግየትም ህዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም ሊጀመር መቻሉን ያስታወሳል።
በዚህ መልኩ የተጀመረው የግንባታው ሂደት በከፍተኛ ፍጥነት እየተጓዘ ይገኛል ያለው ኢንጂነሩ፤ በአሁኑ ወቅት የግንባታው ዋናው ተግባር የሚባለው የኮንክሪት ሥራው መጠናቀቁንና ቀሪው ሥራ የፊኒሺንግ ሥራና የኤሌክትሮ መካኒክ ሥራው እንደሚቀር ይገልጻሉ። በግንባታ ሂደቱ ውስጥ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት የተከናወነው ሥራ ከ50 በመቶ በላይ ሥራ ማከናወን መቻሉን ይገልጻሉ ።በዚህም መሰረት ቀሪውን የግንባታ 50 ከመቶ የሚይዙትን የፊኒሽንግና የኤሌክትሮ መካኒክ መሆኑን ገልጿል።
ኢንጂነር አብነት የኤሌክትሮ መካኒክ ሥራ ማለትም እንደ ጄኔሬተር፣ በስታዲየሙ ውጭም ውስጥም ክፍል የሚተከሉት ስትሬት ላይት ሥራዎች በቀጣይ የሚሰሩ መሆናቸውን ነበር ያብራሩት። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አልሰም ፊሮምሳ በተመሳሳይ፤ በ3 መቶ 19 ሚሊዮን ብር አምቦ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ በጥሩ ፍጥነት እየሄደ መሆኑን በማረጋገጥ ሃሳባቸውን ይጀምራሉ። ስታዲየሙ 30 ሺህ ተመልካች እንደሚያስተናግድ ገልጸው፤ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ከስፖርታዊ ክንውኖች በተጓዳኝ ለሌሎች አገልግሎቶች የሚ ውሉ 252 ክፍሎችን ይዟል። በዚህም ሱቆች፣ ስብሰባ አዳራሽ፣ የተወዳዳሪዎች ማደሪያም ያካተተ ስታዲየም ነው።
ለህብረተሰቡ የገቢ ምንጭ መፍጠሪያ የሚያስችል መሆኑን አክለው ይገልጻሉ። « ይህን መልክ የተጎናጸፈው ስታዲየም የግንባታው ሂደት ፍጥነት ደግሞ የጥራቱን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ይታወቃል ። የእኛ ተቋራጭ ይሄንኑ ጥያቄ በመለሰ መልኩ እየተጓዘ እንደሆነ እናምናለን።
ለዚህ ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ያቆመው ኮንሰልታንት ይገኛል። የግንባታው ሂደት በምን ዓይነት ጥራት እየሄደ ይገኛል የሚለውን በሚገባ ማረጋገጫ እየሰጠ መሆኑ ለዚህ ምስክር ይሆናል»ሲሉ ይናገራሉ። ኢንጂነር አልሰም በስተመጨረሻም፤ ስታዲ የሙ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለከተማው ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጓዳኝ አገራዊ ፋይዳው የጎላ ነው። ከዚህ አኳያ የስታዲየሙ የግንባታ ሂደት ከምንም በላይ ህብረተሰቡ በንቃት ሲከታተል ቆይቷል።
በዚህ የስሜት እርካብ የተጫነው የስታዲየም ግንባታ በአሁኑ ወቅት ሀምሳ በመቶ መጠናቀቁን ገልጸው፣ ቀሪው ደግሞ በ2012 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ መታቀዱን በመግ ለጽ ሀሳባቸውን ይቋጫሉ። በሀገሪቱ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ ስታዲየሞች እየገነቡ ይገኛሉ ።በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ዩኒቨርሲቲዎች ትኩረት ሰጥተው እየሰሩበት ይገኛል።በመንግሥት ከፍተኛ ተቋማት ውስጥ ዓለም አቀፍ ስታዲየሞች መበራከት ያላቸው ፋይዳ ሰፊ እንደሆነ ይናገራል።
በከተማ የስፖርት እንቅስቃሴን ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲጓዝ ከማድረግ አኳያ፤ በሀገሪቱ በቀጣይ በዓለም አቀፍም ሆነ አህጉር አቀፍ የውድድር መድረኮችን ለማዘጋጀት ዕድሉን እንድታገኝ ያስችላል። በመሆኑም የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መገንባቱ የሚሰጠው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ እንደሚሆን እሙን ነው። ከዚህ ሀቅ በመነሳት የአምቦ ስታዲየም ግንባታ የአምቦ ከተማ ሀዝብ የልማት ረሀብ የሚያስታግስ ጅምር ተግባር ይሆናል። አምቦ ከተማ ከአዲስ አበባ 114 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝ መሆኑ ሀገሪቱ ኢንተርናሽናል ውድድሮች በቅርብ ርቀት ለማከናወን አጋዥ ይሆናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
በዳንኤል ዘነበ