እግር ኳስ ይወዳል፡፡ ከአገር ውስጥ ይልቅ የውጭ አገር ጨዋታዎች ቢያስደስቱትም፤ የአገር ውስጡንም ችላ አይለውም፡፡ ከአገር ውስጥ የቡና እግር ኳስ ቡድንን ይደግፋል። ያደንቃልም፤ ከውጭ አገር ደግሞ የአርሴናል ቡድን ደጋፊ ነው፡፡ የስድስተኛ ክፍል ተማሪው አብነት አለነ መስማት የተሳነው ነው፡፡
እኔ እና እርሱ እንደልብ ለመግባባት አልቻልንም፡፡ በመሆኑም አብራው የምትማረው የክፍል ጓደኛው ተማሪ ጽዮን አንዱዓለም በምልክት ቋንቋ እያግባባችን መነጋገራችንን ቀጥለናል፡፡ አብነት የሞባይል ጥገና ባለሙያ ለመሆን ይፈልጋል፡፡ ገንዘብ የሚገኝበት መሆኑን ከመገንዘቡም ባሻገር፤ ለሙያው ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው ነግሮኛል፡፡
እቤት ውስጥ የተጣሉ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን መፈታታት እንደሚያስደስተውም ነው የገለጸለኝ፤ አንድ ወንድም ያለው ሲሆን፤ ‹‹ሲያድግ የምልክት ቋንቋ አስለምደዋለሁ›› ብሎኛል፡፡ የአካትቶ ትምህርት ዓላማው ልዩ ፍላጎትን ለይቶ ማብቃትን መሰረት ያደርጋል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎችም በዚሁ ይስማማሉ፡፡ ልዩ ፍላጎትን በሁለት ከፍሎ መግለጽ የሚቻል ሲሆን፤ ተሰጥኦን ወይንም ልዩ ችሎታን የሚያማክለው በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ያጋጠማቸው ተማሪዎች የሚረዱበት ደግሞ ሁለተኛው መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ አካሄድ አሁን ካለበት የበለጠ ተጠናክሮ ውጤት ተኮር እንዲሆን መስራት አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ጥሩ ሁኔታ እንዳለ ማየት ቢቻልም በቂ ነው ብሎ ለመደምደም ግን አዳጋች ይሆናል፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዋ ጽዮን የ13 ዓመት ዕድሜ ያላት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ በአካትቶ ትምህርት በመማሯ የምልክት ቋንቋ ችላለች፡፡ የምልክት ቋንቋ መልመዷ መስማት ከማይችሉት የክፍል ጓደኞቿ ጋርለመግባባት አስችሏታል፡፡
ከነርሱ ጋር በእረፍት ሰዓት በሚኖራት ቆይታ ተግባብታ በመነጋገሯ በጣም ደስ እንደሚላት እና መስማት ከማይችሉት ጓደኞቿ ጋርም ጥሩ ፍቅር እንዳላቸው ነው ያጫወተችኝ፤ የእረፍት ጊዜ ከሴት ጓደኞቿ ጋር የተለያዩ ጨዋታዎች በመጫወትም እንደምታሳልፍ ነግራኛለች፡፡ ከጓደኞቿ ጋር የምታሳልፈው ጊዜ ደስ እንደሚላት ፈገግታ በሞላ ፊቷ ደስታ ባዘሉ ቃላቶች ነው ያጫወተችኝ፡፡
መስማት ከተሳናቸው ጓደኞቿ ጋር በምልክት ቋንቋ እንደሚግባቡ የምትናገረው ተማሪ ጺዮን፤ ትምህርት እንደጀመረች ለመግባባት ትቸገር እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ሁለተኛ ክፍል ከገባች በኋላ ግን በደንብ መግባባት መቻሏን ነው የነገረችኝ፤ ወደፊት የህክምና ዶክተር ለመሆን እንደምትፈልግ እና በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት አንደኛ ደረጃ እንደያዘች፣እንዲሁም ይህንን ውጤት አስጠብቃ ለመቀጠል ተግታ እያጠናች መሆኑን ትናገራለች፡፡ ሌሎች ጓደኞቿንም ታግዛቸዋለች።
ስዕል እንደምትወድ፣ በትርፍ ሰዓቷም የመኖሪያ አካባቢዋን የሚያሳይ እና የተለያዩ ስዕሎችን እንደምትስልም ገልጻልኛለች፡፡ ተማሪ አብነት ዕድሜው 12 ሲሆን፤ በአካትቶ ትምህርት ከተማሪ ጺዮን ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ይማራሉ፡፡ በመጀመሪያው ሴሚስተር አምስተኛ ደረጃ ይዟል፡፡ በቀጣይ ግን ደረጃውን ማሻሻል እንደሚፈልግ ገልጾልኛል፡፡
የሞባይል ጥገና ባለሙያ መሆን እንደሚፈልግ፤ ከዚህ ባሻገርም ነጋዴ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ጠቁሞኛል፡፡ የሞባይል ጥገና ባለሙያ ለመሆን የፈለገው ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ መሆኑንም ነው የነገረኝ፤ ከጓደኞቹ ጋር በክፍል ውስጥም ሆነ በጨዋታ ቦታ ለመግባባት እንደማይቸገር የሚናገረው ተማሪ አብነት፤ ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር ተግባብቶ ይማራል፤ ይጫወታል። ሆኖም፤ አንዳንዴ አንብቦ ለመረዳት እንደሚቸገር እና ማንበብ ጀምሮ እንደሚያቋርጥ ገልጾልኛል፡፡ ቤተሰቦቹ በቤት ውስጥ በማስጠናት ቢረዱት የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችልም ያምናል፡፡ ቀደም ሲል አባቱ በማስጠናት ይረዳው እንደነበር በመጠቆምም፤ አባቱ ከቤት በመውጣቱ የሚረዳው ሰው ማጣቱን ነግሮኛል፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የልዩ ፍላጎት መምህርት ሳራ መብራቱ፤ ሁሉም ሰው ልዩ ፍላጎት እንዳለው ይጠቅሳሉ። ይሁን እንጂ፤ በትኩረት የሚታይ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ ሰው የመናገር ብቃት ማነስ፤ ሌላው ደግሞ ሌላ አይነት ክፍተት ሊኖርበት ይችላል በማለት ይጠቁሙና፤ ተከታትሎ የመናገር ችሎታው ወይም ክፍተቱ እንዲዳብር ቢደረግ ክፍተቱ ሊሞላለት ይችላል ባይ ናቸው፡፡
እንደ መምህርት ሳራ ማብራሪያ፤ መስማት የተሳናቸው መስማት ከሚችሉ ሰዎች የሚለያቸው ነገር ቢኖር የምልክት ቋንቋ ተጠቃሚ መሆናቸው ነው፡፡ ማየት የተሳናቸውም ልዩ ፍላጎት አላቸው ስንል ብሬል ተጠቃሚ መሆናቸው ነው፡፡ የመማር ችግር አለባቸው ብለን በልዩ ፍላጎት የምንይዛቸው በሆነ ቦታ ላይ ተክተን የምንደግፍ ሲሆን ነው ይላሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የልዩ ፍላጎት እንደሌለው ማህበረሰብ እኩል ተደራሽ ይደረጋል የሚሉት መምህርቷ፤ እነርሱም ለአገር እኩል ድጋፍ የሚያደርጉ፣ የሚንቀሳቀሱ እና የሥራ ዕድልም የሚያገኙ መሆናቸውን በበጎነት ያነሳሉ፡፡ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ማብቃት ከተፈለገ መስማት ለተሳናቸው ትክክለኛውን የምልክት ቋንቋ የሚችል፣ በምልክት ቋንቋ የተመረቀ መምህር በሁሉም ዘርፍ እንዲኖር ማድረግ ይገባል፤ ይላሉ፡፡
ባብዛኛው በልዩ ፍላጎት የተመረቁ መምህራን ሁሉንም የትምህርት ዓይነት እንዲያስተምሩ ሲደረግ፤ በመማር ማስተማሩ ሥራም ክፍተት ሊፈጥር እንደሚችል ይገልጻሉ። መስማት ለተሳናቸው ብቻ ሳይሆን በሌላውም ዘርፍ እንደየአስፈላጊነቱ ብቁ መምህራን እንዲኖሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት መቶ በመቶ ጥሩ ነው ባይባልም መልካም ነገር አለው የሚሉት መምህርት ሳራ፤ ልጆቹ ትምህርት ቤት መጥተው መማራቸው፣ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባት መቻላቸው፤ እንዲሁም በሥራ መሰማራታቸውን በስኬት ያነሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ አሁንም መምህራን በበቂ ሁኔታ ሰልጥነው መቀላቀል ይገባቸዋል። ትክክለኛ ድጋፍ መሰጠትም አለበት ሲሉ ነው የሚገልጹት፤ አካትቶ የትምህርት አሰጣጡ አካታች ማህበረሰብ ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ያመለክታሉ፡ ፡
እንዲሁም ትምህርት መስማት የማይችሉት ከእኩዮቻቸው ጋር ጥሩ ተግባቦት እንዲፈጥሩም ይረዳቸዋል፡፡ የልዩ ፍላጎት መምህርቷ ራሄል ወልደ ስላሴም ሁሉም ተማሪ ልዩ ፍላጎት እንዳለው በመጠቆም፤ ተማሪዎች ያላቸውን ዕምቅ ችሎታ እንዲያወጡ መደረግ አለበት ባይ ናቸው፡፡ ውጤታማ ተማሪዎችን ማፍራት ካስፈለገ የተለየ ትምህርት አሰጣጥ አስፈላጊ መሆኑን ይስማሙበታል፡፡
መምህራን የተማሪዎቻቸውን ፍላጎት ለይተው መከታተልም አለባቸው ይላሉ፡፡ በልዩ ፍላጎት ትምህርት ስር የሚጠቃለሉት አካል ጉዳተኞች መስማት የተሳናቸው፣ ማየት የተሳናቸው፣ የእጅ ወይም የእግር ጉዳት ያለባቸው፣ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት፣ የሚጥል በሽታ፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም፣ ኤች አይ ቪ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ልዩ ፍላጎት የተለየ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች መደበኛ ከሆነው የተለየ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ የሚሰለጥኑበት መንገድ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በምሳሌነት ሲያነሱም፣ መስማት የተሳናቸውን ከመደበኛው በልሳን ከሚማሩት በተለየ መስማት ከሚችሉት ጋር በኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ እንደሚሰጥ ነው የሚናገሩት፡፡ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ለማብቃት መጀመሪያ መምህሩ መብቃት አለበት የሚሉት መምህርት ራሄል፣ መምህራንን የማብቃት ተግባር ቀዳሚ ሊሆን ይገባዋል የሚል አቋምም አላቸው፡፡
እንዴት አድርጎ ተማሪዎችን እንደሚያግዝ የተገነዘበ መምህር ተማሪዎቹን ማብቃት ይቻለዋል ይላሉ፡፡ የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል አለመኖር ዘርፉን እየፈተነው መሆኑን የሚናገሩት መምህርቷ፤ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን በትምህርታቸው ብቁ ሊያደርጋቸው እና ሊያግዛቸው የሚያስችል የመርጃ መሳሪያ የማሟላቱ ሥራ ትኩረት የሚገባው ነው ይላሉ መምህርት ራሄል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 27
በዘላለም ግዛው