ከአምስት ዓመት በፊት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዜጎች ብሄራዊ መታወቂያ እንዲሰጥ አዋጅ ቢያጸድቅም እስካሁን ድረስ ሥራ ላይ አልዋለም፡፡ በዚሁ ወቅትም የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በ2005 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ሰነድ ላይ ለብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት 3 ሚሊዮን 773 ሺህ 271 ብር በጀት መድቦ ነበር። በአሁኑ ጊዜም ይህ ብሄራዊ መታወቂያ የመስጠት ስልጣንም አዲስ ለተቋቋመው ሰላም ሚኒስቴር ተሰጥቷል።
በአዋጁ መሰረት አዲስ ይወጣል የተባለው ብሄራዊ መታወቂያ የግለሰቦችን ማንነት
በቀላሉ መለየት የሚያስችል ምስጢራዊ ቁጥር ያለው ነው፡፡ የአዋጁ መውጣት የብሄራዊ መታወ ቂያ በተለያዩ ስሞችና ማንነቶች በህገወጥ
መንገድ መታወቂያዎችን የማውጣት የወንጀል ድርጊ ቶች እንዳይፈጸሙ ይከላከላል ተብሏል፡፡
ረቂቅ አዋጁ እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መታወቂያ የማውጣት ግዴታ እንዳለበት ሲያመላክት፤ ይህንን ግዴታ
ውን ያላከበረም በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ እስከ ስድስት ወር በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል። በተጨማሪም በምዝገባ ወቅት ሐሰተኛ
መረጃ የሚሰጡ ሰዎች ከአንድ እስከ አምስት ዓመት እስራት ይከናነባሉ።
መታወቂያው የግለሰቦችን ሙሉ አድራሻና ማንነት የሚገልፅ መረጃ የሚይዝ ሲሆን፤ ለአሥር ዓመትም ፀንቶ እንደሚቆይ ረቂቅ አዋጁ አመልክቷል፡፡ በቀድሞው በፍትህ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ ሕግ በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የሆነ፣ የራሱ ምስጢራዊ ኮድ ያለው መታወቂያ በብሔራዊ ደረጃ ማዘጋጀት ያስፈለገው ሽብርና ወንጀልን ለመከላከል፣ ለግብር አከፋፈል፣ ለፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት ጥቅም እንዲሰጥ ታስቦ ነው ይላል፡፡ሆኖም በአገሪቱ ብሄራዊ መታወቂያ ሥራ ላይ አለመዋሉም ባንኮች ለመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ብድር እንዳይሰጡ ችግር ፈጥሮባቸዋል።
የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ አለመኖሩ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መልኩ እንዳይሰጡ ማድረጉን ያረጋግጣሉ፡፡ የብድር አገልግሎት ለመስጠት ከሚያስፈልጉት አንዱ የደንበኛን ታሪክ በእርግጠኝነት ማወቅ ይጠይቃል፡፡ የደንበኛን የግል ታሪክ በደንብ ማወቅ ሲቻል፤ ማለትም ምን ገቢና ወጪ እንዳለው፤ ምን ወንጀልና መልካም ነገር እንደሰራ ዝርዝር ታሪኩ ከታወቀ ወደ ባንክ ቤት ሳይመጣ ባለበት ቦታ የተቀላጠፈ የብድር አገልግሎት መስጠት ይቻላል። ይህ መረጃ ሊገኝ የሚችለው ደግሞ የዜግነት ቁጥር ያለው ብሄራዊ መታወቂያ (ናይሽናል አይዲ) ሲኖር ነው ፡፡
በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ብሄራዊ መታወቂያ አሰጣጥ ስርዓት ቢኖር እያንዳንዱ ዜጋ ማንነቱ በአሻራና በዓይኑ ብሌን ተለይቶ ይታወቃል፡፡ የትም ቦታ ቢሄድ መቀየር የማይችል ብሄራዊ መታወቂያ ይኖረዋል። ብድር ባይመልስ፣ ግብር ባይከፍል፣ ወንጀል ቢሰራ፣ ቢያጭበረብር ሁሉም ታሪኩ በኤሌክ ትሮኒክስ መታወቂያ ሥርዓቱ ሰፍሮ ይገኛል። ይህ መረጃ ለባንኮችም ሆነ ለመሰል ተቋማት ተደራሽ ስለሚሆን የደንበኛውን ማንነት አውቆ ያለ ስጋት ማንኛውንም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የባንክ አገልግሎቶች መስጠት ይቻላል የሚል ሃሳብ አላቸው። አቶ አቤ።
ሌሎች አገሮች ብሄራዊ መታወቂያ በመኖሩ ባንኮች የተቀላጠፈ አገልግሎታቸውን በቴክ ኖሎጂ ስለሚሰጡ ደንበኞችና ባንኮቹ በአካል የማይገናኙበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በአንጻሩ በኢ ትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ ባለመኖሩ ባንኮች ደንበኞቻቸውን የሚያገለግሉት በጣም ውድ በሆነ ዋጋ ነው፡፡ ምክንያቱም፤ በቴክኖሎጂ በቀ ላሉ የሚሰጠውን አገልግሎት በሰው ኃይል ነው እየሰጡ ያሉት፤ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ አንድ ሰው መታወቂያው መቶ ሊሆን ስለሚችል ትክክለኛው ሰው በመታወቂያው አይታወቅም፡፡ ለማጭበርበርም የተጋለጠ ነው፡፡
በቂ ገንዘብ በባንኮች ውስጥ እያለ ስጋቱን በመፍራት ብቻ የብድር አገልግሎት ሥራ ላይ አይውልም፡፡ የዜጎችን ትክክለኛ መረጃ የሚገኝበት በኮምፒዩተር የታገዘ ብሄራዊ መታወቂያ ስለሌለ የሚበደር ሰው መምረጥ ድካሙና ወጪው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ከሙያተኞቹ ጋር የጥቅም ትስስር ሊኖር ይችላል በሚል ሙሉ እምነት የለም፡፡ ለደንበኞችም በቴክኖሎጂ የታገዙ የባንክ አገልግሎቶችን ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በጥቅሉ የብሄራዊ መታወቂያ አለመኖር ባንኮች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በጣም ውስን እንዲሆኑ አድርጓል ሲሉ አቶ አቤ ችግሩን አሳይተዋል።
የዳሸን ባንክ የማርኬቲንግና ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ሙሉጌታ አለባቸው በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ብሄራዊ መታወቂያ አለመኖር ባንኮች የተቀላጠፈና ከስጋት ነጻ የሆነ አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል የሚለውን የአቶ አቤ ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ በተለይ ብሄራዊ መታወቂያ አለመኖር በባንኮች የብድር አቅርቦት ተደራሽነት ላይ ትልቅ ችግር ፈጥሯል ይላሉ። ባንኮች ለመካከለኛና ለዝቅተኛ ገቢ ላለው የህብረተሰብ ክፍል በስፋት ብድር ለማቅረብ አንዱ መሰረታዊ ችግር ኤሌክትሮኒክስ የሆነ ብሄራዊ መታወቂያ (ብሄራዊ አይዲንቲፊኬሽን ሲስተም) አለመኖሩ ነው።
ሰዎች በየትኛውም የአገሪቷ ጫፍ ቢኖሩ በተለየ መልኩ የሚታወቁበት መታወቂያ ስለሌለ እዚህም እዚያም ከአንድ በላይ መታወቂያ ማውጣት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች አሉ። ሰዎች በተለየ መልኩ የሚታወቁበት ስርዓት ከሌለ ደግሞ ከማስያዥያ ውጭ ብድር ማበደር ስጋት አለው። በአንጻሩ መታወቂያ ቢኖር ኖሮ ተበዳሪዎች ከየትኛው ባንክ ብድር መውሰዳቸውና የብድር አመላለስ ታሪካቸው በቀላሉ ስለሚታወቅ የብድር ተጠቃሚ ለማድ ረግ የሚፈጥረው ስጋት አይኖርም፡፡
በተቃራኒው ብሄራዊ መታወቂያ አለመኖር የባንኮችን የብድር አቅርቦት ውስን አድርጎታል። በተለይ መካከለኛና አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዳይሆኑ አድርጓል፡፡ ለምሳሌ፤ የዳሸን ባንክ የመኪና ብድር ለተወሰኑ ትልልቅ ተቋማትና ግብረሰናይ ድርጅት ሠራተኞች ይሰጣል፡፡ ተቋማቱ ኃላፊነት ወስደው፣ ማስያዥያ አስይዘው፣ ብድሩን በየወሩም ከደመወዛቸው እየቆረጡ ለባንኩ ገቢ ለማድረግ ስምምነት በማድረጋቸው ሠራተኞቻቸው ከባንኩ የመኪና መግዥ ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ መኖሩን አቶ ሙሉጌታ ያነሳሉ።
በአገሪቱ ብሄራዊ መታወቂያ ቢኖር ግን፤ ይህ የብድር አቅርቦት በዚህ ደረጃ ሳይወሰን አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ጭምር የአቅርቦቱ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻል ነበር። በተለይ፤ በአሁኑ ጊዜ ባንኮች በኤሌክትሮኒክስ በታገዙ የግብይት ስርዓቶች ውስጥ እየገቡ በመሆኑ የብሄራዊ መታወቂያው አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ ስለዚህ፤ ለዘርፉ ዕድገትና ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት አስፈላጊነቱ የጎላ በመሆኑ መንግሥት ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ይሳቅ መንገሻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቢዝነስ ዲቨሎፕመንት ክፍል ኃላፊ ደግሞ፤ ባንኮች ለደበኞቻቸው ሂሳብ ሲከፍቱ፣ የሀዋላና የብድር አገልግሎት ሲሰጡ ሥራቸው ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ስለሆነ የእያንዳንዱን ሰው መረጃ ለማወቅና ለማረጋገጥ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ምክንያቱም አንድ ሰው ብዙ መታወቂያዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ በቴክኖሎጂ የታገዘ ወጥ አገራዊ መታወቂያ ካለ ግን ማንነቱ በቀላሉ ይታወቃል፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴውም ከዚህ ስርዓት ጋር የተቆራኘ ስለሚሆንና የሁሉም መረጃዎች መነሻ መታወቂያ ስለሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ መታወቂያ መኖሩ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ወደፊት ሁሉም ሰው ብሄራዊ መታወቂያ እንዲኖረው ሁሉም በኮምፒዩተር ተመዝግቦና ማንነቱ ታውቆ የትም ቢሄድ በዚህ በመታወቂያ የሚለይበት ሁኔታ ቢፈጠር ለባንኮች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ተቋማትም በጣም ጠቃሚ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
የብሄራዊ መታወቂያ አለመኖር በተጭበረበረ መልኩ ብዙ መታወቂያዎች ለማውጣት ስለሚ ያስችል የደንበኞችን ማንነት ለማወቅ ረጅም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ስጋቱም ከፍተኛ በመሆኑ የባንኮች አገልግሎቶች በዓይነት ውስን ናቸው። ብሄራዊ መታወቂያ ቢጀመር ግን የግለሰቦች ትክክለኛ መረጃ ስለሚኖር ባንኮች ከስጋት ነጻ ሆነው የተለያዩ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈና ተደራሽ በሆነ መልኩ ለሁሉን የህብረተሰብ ክፍሎች መስጠት ያስችላቸዋል፡፡ ወጪያቸውንም ይቀን ስላቸዋል፡፡ ጊዜያቸውን ይቆጥብላቸዋል። በጥቅሉ የተቀላጠፈ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
ብሄራዊ የመታወቂያ ሥርዓት በሰለጠኑ አገሮች ብቻ ሳይወሰን በአፍሪካም ተግባራዊ ተደርጎ አገሮች የፋይናንስ ሥርዓታቸውን እያቀላጠፉበት ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋምቢያ፣ ቦትስዋና፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ ይገኙበታል። ኢትዮጵያ ግን ትልቅ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቀስ ቢሆንም የብሄራዊ መታወቂያ ሥርዓት እስካሁን ድረስ መዘርጋት ተስኗታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2011
ጌትነት ምህረቴ