የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራ ሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሆነ ይገለፃል። ፓርቲው አዲስ የመዋቅርና የፖለቲካ አካሄድም ለመከተል እየሰራ መሆኑ ይሰማል። ለመሆኑ ድርጅቱ እየሰራቸው ያላ ቸው ሥራዎች ምንድናቸው? በሚለው ዙሪያ ከድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገን ለአንባቢዎቻችን እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ መኖሩን የሚጠራጠሩ አሉ። ኢህአዴግ አለ?
አቶ መለሰ፡- ጥያቄውን በሁለት መልኩ ማየት ይገባል። ድርጅታዊ ህልውናን በሚመለከት አንድ ፓርቲ ሊኖር የሚገባው ተቋማዊ አቋም አለው። ምክር ቤት፣ ጉባዔ፣ ሥራ አስፈፃሚና ሌሎች ነገሮች ሁሉ አለው። በአገሪቱም እንደ ፓርቲ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ሲታገልና ሲያታግል የቆየ፤ አሁንም በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ የሚመራ ነው። በህዝብ የተመረጠና አገር የሚያስተዳድር መሪ ፓርቲ ነው። እነዚህን ሁኔታዎች ወስዶ ድርጅቱ አለወይ? ከተባለ መልሱ አለ ነው።
ሁለተኛው ሁኔታ ኢህአዴግ በተልዕኮና በይዘት ምን ይመስላል? ከሆነ ጥያቄው ኢህአዴግ በባህሪው፣ በዓላማው እና በተልዕኮው ተራማጅ ፓርቲ ነው። ተራማጅ ፓርቲዎች በባህሪይ ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ የሚታገሉ ናቸው። ኢህአዴግም የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት በተለያዩ ስልቶች የሚታገል ነው። በዚህም የተለያዩ ለውጦችንም ሲመራ ነበር። አሁንም ከተራማጅ ባህሪው ተነስቶ በአገራችን በህዝብ ተገፋፍቶ የመጣውን ለውጥ እየመራና እያስተባበረ ነው። የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ተረድቶ የለውጡን ዓላማ ለማሳካት እየመራ ራሱንም እያስተካከለ ያለ ፓርቲ ነው። ኢህአዴግ አለ? ወይስ የለም? ለሚለው ጥያቄ ከዚህ ውጭ መልስ የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- «ኢህአዴግ አለ። ከተራማጅ ባሕሪው ተነስቶ ወቅቱን የሚመጥን ማሻሻያ እያደረገ ነው፤» ነው የሚሉኝ? አቶ መለሰ፡- ኢህአዴግ አለ። እንደተራማጅ ፓርቲ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ራሱን እያስተካከለ ወደፊትም ይቀጥላል። አዲስ ዘመን፡- ቀደም ባለው ኢህአዴግና በአሁኑ ኢህአዴግ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
አቶ መለሰ፡- ከህብረተሰቡ የለውጥ ፍላጎት ተነስቶና በተራማጅ ባህሪው ምክንያት ኢህአዴግ ራሱን እየለወጠ ነው። ለውጡ የህብረተሰቡን ፍላጎት ከመምራት ጋር የሚያያዝ ነው። ድርጅቱ ከአሁን በፊት ለበርካታ ለውጦች ምላሽ እየሰጠ ነው የመጣው። አሁንም የደረስንበትን የህብረተሰብ ዕድገትና ትግሉ የሚጠይቀውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለውጡ ከህዝብ ቢመጣም ተቀብሎ እየመራ ነው። ከአሁን በፊት ለውጥ ሲታሰብ ኢህአዴግ ራሱ ቀድሞ አቅዶ ይመራው ነበር። አሁን ግን ለውጡ ኢህአዴግ አቅዶት ሳይሆን በህብረተሰብ ግፊት የመጣ ነው። መለያ ባህሪው ይህ ነው። የለውጡ ዋና ዋና ምክንያቶችም ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተካሄደው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች የፈጠሯቸው ተጨማሪ ፍላጎቶች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በለውጡ ሂደት በአራቱ ግንባር ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?
አቶ መለሰ፡- የፓርቲዎቹ ግንኙነት የሚወሰነው በአሰራራቸውና አደረጃጀታቸው ነው። አራቱም ብሄራዊ ድርጅቶች የለውጡ መነሻ የሆነውን የጥልቅ ተሀድሶ በጋራ በመገምገም አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በ17ቱ ቀናት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ግምገማ አመራር መቀየር እንዳለበት ተስማምተዋል። ከአመራር ለውጥ በኋላ በተወሰዱ ርምጃዎች አገሪቱ ከነበረችበት የሰላም ችግር ወጥታ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል። በርካታ ውጤቶችም ተመዝግበዋል። ለውጡ በመልካም ዕድልና በስጋት ታጅቦ ቢሄድም ተስፋው የሚያመዝን እንዲሆን አድርጎታል። በሂደት አራቱ ድርጅቶች በአሰራሮቻቸው በጋራ በሚያስቀምጡት አቅጣጫ እና በየራሳቸው አመራር በሚሰጡባቸው ክልሎች ለውጡን ሲመሩ ቆይተዋል።
ድርጅቶቹ ጉባዔ አካሂደው ተቋማዊ እንዲሆንም አድርገዋል። የፖለቲካ ማስተካከያም እየተደረገ ነው። የኢኮኖሚ ማስተካከያውም እየቀጠለ ነው። አስተዳደራዊና ህጋዊ ማሻሻያዎችም እየተሰሩ ናቸው። እነዚህም በጉባዔው የተቀመጠውን አቅጣጫ ተከትለው እየተሰሩ፤ በተቀመጠላቸው ጊዜ መሰረት እየተካሄዱ ናቸው። በምክር ቤት ደረጃ በየስድስት ወራት፤ በአስፈፃሚ ደረጃ በየሦስት ወራት በህገ ደንባቸው መሰረት ጉባኤ እየተካሄደ ነው። አራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች በተቀመጠው አቅጣጫና አሰራር መሰረት ለውጡን እየመሩት ነው። ግንኙነታቸውን በሚመለከትም በዚህ መንገድ የሚገለጽ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በህዝብ ዘንድ ኦዴፓና አዴፓ የለውጥ ኃይሎች፤ ደኢህዴን የዳር ተመልካች፤ እንዲሁም ህወሓት ፀረ ለውጥ ሲባል ይሰማል። ለዚህ መልስዎ ምንድን ነው?
አቶ መለሰ፡- በህብረተሰቡና በማህበራዊ ሚዲያ ይህ ጉዳይ ይነሳል። ይህ በሃሳብ ደረጃ ሊነሳ ይችላል። በግንባሮቹ መካከል በተደረገው ግምገማ እንዲህ ዓይነት ነገር አለ ተብሎ አልተወሰደም። በኢህአዴግ ውስጥ በርካታ ለውጦች ተደርገዋል። ከዛሬ 16 ዓመት በፊት ለውጥ ተደርጓል። ያኔም በለውጡ ወቅት የተለያዩ ሃሳቦች ተራምደዋል።
በሂደት ግን ሃሳቦቹ እየጠሩ ሄደዋል። ለውጥ በሚካሄድበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት እሳቤ የሚጠበቅ ነው። በድርጅቶቹ ውስጥ ግን አንዱ የለውጥ ኃይል ሌላው አደናቃፊ ተብሎ በጥቅል ሊቀመጥ አይገባም። በግለሰብ ደረጃ ግን በለውጡ ላይ ሁሉም ሰው እኩል አቋም አለው ተብሎ ሊወሰድ አይችልም። ግለሰቦች በውስጠ ዴሞክራሲ ነፃ ሆነው ሃሳባቸውን አቅርበው ይከራከራሉ። አብዛኛው ለወሰነው ተገዥ በመሆንም የተወሰነውን ተቀብለው ይተገብራሉ። በሂደት ልዩነት ካላቸው ልዩነታቸውን እያቀረቡ በጉዳዮቹ ላይ ፍጭት እያደረጉ ጠንካራው እየቀጠለ ደከም የሚለው እየታረመ ይቀጥላል። ፓርቲዎቹ የየራሳቸው ህልውና አላቸው።
የራሳቸው ምክር ቤት፤ ጉባዔ፤ ማዕከላዊ ኮሚቴ፤ ሥራ አስፈፃሚ እና ጽሕፈት ቤት አላቸው። ስለዚህ በሁሉም ደረጃ ባላቸው መዋቅር ያሉት አባሎቻቸው በአንድ ጉዳይ ላይ በአንድ ጊዜ አኩል እምነትና አስተሳሰብ ሊኖራቸው አይችልም። ይህ የተለመደና ወደፊትም የሚቀጥል ነው። ይህ ማለት ግን አንድ ፓርቲ እንደፓርቲ ልዩነት አለው ማለት አይደለም። ደኢህዴንን ብንወስድ «ለለውጡ ሚና የለውም» ይባላል። ግን ይህ ሊሆን አይችልም። ደኢህዴን በለውጡ ሚና የለውም ከተባለ 45 ድምጽ ኢህአዴግ አይኖረውም ማለት ነው። ይህ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም።
ደኢህዴን ሚና የለውም ከተባለ፤ በጥልቅ ተሀድሶው ውስጥ ሚና የለውም ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ከስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ የግለሰብ ሳይሆን የፓርቲ ስለሆነ ፓርቲው አይወስንም ማለት ነው። በአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶችም ተመሳሳይ ነው። ሁሉም ለለውጡ አስተዋጽዖ አላቸው። ይህ ማለት እንደድርጅት የራሳቸው ጥንካሬና ጉድለቶች የሏቸውም ማለት አይደለም። ይህ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚለያይ ነው። በአንድ ጊዜ ጠንካራ የሆነው በሌላ ጊዜ ሊደክም ይችላል። ከለውጡ ጋር ተያይዞ ግን ምንም ልዩነት የለም፤ የተፋዘዘ ነው ሊባል ግን አይችልም።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ይህ አስተሳሰብ እንዴት ሊፈጠር ቻለ?
አቶ መለሰ፡- ለሰዎች አስተሳሰብ ምላሽ መስጠት አልችልም። ምላሽ መስጠት ያለባቸው ይህን ያሰቡ ሰዎች ናቸው። በውስጥም በውጭም ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በውስጥ ያሉ ሰዎች ይህ አስተሳሰብ ካላቸው ማንጸባረቅ ያለባቸው በፓርቲው ውስጥ ነው። ሃሳብ አንጸባርቀው ሃሳባቸው በብዙሃኑ ከተሸነፈ ለዚያ መገዛት ግድ ነው። ብዙሃኑም የነሱን ሃሳብ ያከብራል። ይህ ማለት ግን፤ በኢህአዴግ ውስጥ ልዩነት አለ ማለት አይደለም። በኢህአዴግ ውስጥ ልዩነት አለ የሚባለው የአቋም ልዩነት ሲኖር ነው። እያንዳንዱ ፓርቲ በሚመራው ክልል ያለው ነባራዊ ሁኔታና የሚሰጠው ምላሽ ህሊናዊ ሁኔታ ልዩነት ሊኖረው ይችላል። በዚህም ሰዎች በለውጡ ልዩነት እንዳለ እንዲገምቱ ሊያደርጋቸው ይችላል። ይህ ግን የፓርቲው ሊሆን አይችልም።
አዲስ ዘመን፡- በሀዋሳው ጉባዔ ኢህአዴግ ተስማምቶ መውጣቱን ገልጿል። ከጉባዔው በኋላ ብሄራዊ ድርጅቶች የሚሰጧቸው መግለጫዎች፤ መሪዎችም የሚያነሷቸው ሃሳቦች መስማማታችሁን አያሳዩም። ተስማምተናል ብላችሁ ህዝቡን ዋሽታችሁታል?
አቶ መለሰ፡- በጉባዔው መገናኛ ብዙሃን፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ የሲቪክ ተቋማት ተገኝተዋል። በሂደቱም ኢህአዴግ ግልጽ ውይይት በማካሄድ የውስጥ ዴሞክራሲ አሳይቷል። በርካታ ጉዳዮችም በጉባዔው ተነስተዋል። መሰረታዊ የማስተካከያ ውሳኔ የሚያሳልፈው ይህ ጉባዔ በመሆኑ የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ክርክር ተደርጓል። በመጨረሻም፤ የጋራ የሚያደርጉን በርካታ ጉዳዮች ስለነበሩ ጉባዔው ለውጡን፣ የለውጡን መርሆዎችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክቶ መግባባት ላይ ተደርሶ ጉባዔው ውሳኔ አሳልፏል። በጉባዔው ነፃ ሆነው ሃሳብ በማንሳት የተከራከሩት ፓርቲዎቹ በማመንና በማሳመን የጋራ አድርገው በመወሰን ውሳኔውን እስከቀጣዩ ጉባዔ ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ ወስነዋል። ይህን ውሳኔ ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ ፓርቲዎቹ ወስደዋል። ይህ ደግሞ በኢህአዴግ የተለመደ ነው። በየትኞቹም ጉባዔዎች የትኛውም ጉዳይ ይነሳል፤ የጋራ መግባባት ተይዞ ይወጣል። በዚህ ጉባዔም የነበረው ይህ ነው። ከዚያ ውጭ አንዱን ለማስደሰት ሌላውን ለማስቀየም ተብሎ ኢህአዴግ ህዝብን አይዋሽም። እንዲህ አይነት ተቋማዊ እምነት የለውም። እንደዚያ ሊያደርግም አይችልም።
አዲስ ዘመን፡- ስምምነት የደረሳችሁባቸው ጉዳዮች በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ እየሆኑ ነው?
አቶ መለሰ፡- በጉባዔ የተቀመጠውን አቅጣጫ ለመፈጸም በመጀመሪያ እቅድ ነው የሚዘጋጀው፤ እቅዱ ከተዘጋጀ በኋላም የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር፤ እቅዱ ተግባራዊ መሆኑን ማረጋገጥ፤ የስምሪት፤ የዝግጅት፤ የክትትል እና የድጋፍ ሥራዎች ይሰራሉ። ከዚህ አንፃር የጉባዔውን ውሳኔ የሚመጥን እቅድ በኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ተዘጋጅቶና በሥራ አስፈፃሚ ታይቶ፤ ሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶችና የሚመለከታቸው ሁሉ ከተሳተፉበት በኋላ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ስድስት ወራት በመሆኑ ስለውጤታማነቱ ክትትል እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከአጋር ድርጅቶች ጋር ለመዋሀድ ጥናት አጥንታችኋል። ከጥናቱ የተገኘው ፍሬ ነገር ምንድን ነው?
አቶ መለሰ፡- የጥናቱ መነሻ ጥልቅ ተሀድሶውና አጠቃላይ አገራዊ ግምገማው ነው። በግምገማው የተቀመጠው አቅጣጫ አሁን በደረስንበት ነባራዊ ሁኔታ የትግል ስልታችን ከህብረተሰብ የዕድገት ፍላጎት ጋር የሚመጥን መሆን አለበት የሚል ነው። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ፓርቲዎቹ የሚታገሉበት አካሄድ ምን መሆን አለበት? የሚለው ከፓርቲዎቹ ከራሳቸው የመሳተፍ ጥያቄ ተነስቷል። እነዚህ ጉዳዮች በጥናት መመለስ አለባቸው። በአስረኛው የድርጅት ጉባዔ መታየት አለበት ተብሎ አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር። ባለፈው የድርጅት ጉባዔ ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ተጠንቶ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ መሳተፍ አለባቸው የሚል ውሳኔም ተላልፏል። የአጋር ድርጅቶች ሥራ አስፈጻሚዎች በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ውሳኔዎች ላይ እየተሳተፉ ነው።
ጥናቱ የተጀመረው ሂደቱን ወደ ተግባር ለመቀየር ነው። የጥናቱ ዋና ጉዳይም ፓርቲዎቹ ሲዋሀዱ ከፕሮግራም፤ ከአመራር ስምሪት፤ ከአባላት መብትና ግዴታ፤ ከተልዕኮና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሉ ጥያቄዎች እንዴት ምላሽ ማግኘት አለባቸው የሚሉትን ነው ያጠናው፤ በጥናቱም ፓርቲዎቹ ሲዋሀዱ ኢህአዴግ ምን አይነት ቅርጽ መያዝ አለበት? ከኢህአዴግ ጋር ተዋህደው የሚታገሉ ፓርቲዎች በዓላማና በትግል ስልቱ ላይ ምን ድርሻ እንደሚኖራቸው የሚያይና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች የሚመለሱበት ነው ጥናቱ፤ ጥናቱ ይህን ብቻ ሳይሆን፤ በአገሪቱ ከፖለቲካዊው ለውጥ ጋር ፓርቲውም ራሱን እየለወጠ ለመሄድም ነው። ፓርቲው ከለውጡ ጋር ራሱን እንዴት እያጣጣመ ይሄዳል? የሚለውን ጭምር የሚመልስ ነው። በውህደቱ ሂደት የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለማለፍ፤ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የሚያስችልም ነው። ጥናቱ የሌሎችን አገራት ተሞክሮዎችና የእኛን አገር ተጨባጭ ሁኔታዎች የዳሰሰ ነው። ጥናቱ የተጠናቀቀ ሲሆን በፓርቲዎቹ ውይይት ተደርጎ የጋራ ስምምነት ሲደረስ ይፋ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የኢህአዴግ አራቱ ፓርቲዎች ግንባር ናቸው። አሁን በተደረገው ጥናት ግንባር ወይስ ውህድ ፓርቲ ነው የምትሆኑት? አቶ መለሰ፡- አሁን ላይ ግንባር ወይም ውህድ ፓርቲ ለማለት አይቻልም። ለፓርቲዎቹ ቀርቦ ውይይት ከተደረገና ውሳኔ ሲያገኝ ነው ይህ የሚታወቀው፤ ጥናቱ እየተጠናቀቀ ነው። ኢህአዴግ የአራት ግንባርና የአጋር ፓርቲዎች ድርጅት ነበር። አሁን ግን ይህ ይቀየራል። በመጀመሪያ የሚፈጸመው የኢህአዴግና የአጋር ድርጅቶች ውህደት ነው። የተቀራረበ ርዕዮተ ዓለም ያላቸው ፓርቲዎች እንደአገር ሰብሰብ ብለን መስራት ስላለብን እየጠበብን በመጣን ቁጥር ለትግል ይመቻል። ይህን ታሳቢ ያደረገ የፖለቲካ ማሻሻያ አቅጣጫ ነው የምንከተለው።
አዲስ ዘመን፡- ለሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እንዲቀላቀሉ ክፍት ታደርጋላችሁ?
አቶ መለሰ፡- ኢህአዴግ የህዝብ ድርጅት ነው። የተወሰኑ ግለሰቦች አይደለም። ተራማጅም ነው። ዓላማው ኋላ ቀርነትን ከማጥፋት እስከዳበረ ዴሞክራሲ አገሪቱን ማድረስ ነው። ከድህነት ወጥታ የበለጸገች አገር መገንባት ነው። ይህ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነው። ትግሉ በኢህአዴግ ብቻ የሚያልቅ አይደለም። እንደአንድ ፓርቲ ይታገልለታል እንጂ፤ ኢህአዴግ የሚታገልለት ዓላማ የተለያዩ ፓርቲዎችን ትግል የሚጠይቅ ነው። የፓርቲዎችን ብቻ ሳይሆን የትውልዶችን ትግል ይጠይቃል። ከዚህ አንፃር ተመሳሳይ ዓላማ ያለው ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ካለ ኢህአዴግ የእኔ ብቻ የሚልበት ምንም ምክንያት የለውም። ተፎካካሪዎችም ቢሆኑ ኢህአዴግ ማሻሻያ ሲያደርግ በሩን ዘግቶ አይደለም። የሚወሰነው ግን በተፎካካሪ ፓርቲዎች ፍላጎት ነው። ኢህአዴግ ከማንም ጋር አልገናኝም ብሎ በሩን የዘጋ አይደለም። ሊዘጋም አይችልም። ግን ደግሞ አብረን እንሁን ብሎ አያስገድድም።
አዲስ ዘመን፡- ከአጋሮች ጋርም ሆነ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ግንባር ብትፈጥሩ ማዋቅሩ ይፈቅድላችኋል። ምክንያቱም በእያንዳንዱ የግንባር ፓርቲ 45 የምክር ቤት አባል፣ 9 ስራ አስፈፃሚ ነው ያላችሁ፤ ይህ በፓርቲዎች ብዛት ልክ የሚጨምር ከሆነ አስቸጋሪ ይሆናል። ስለዚህ ምን ይላሉ? ውህደት ብትፈጽሙ አሁን በአገሪቱ ያለው የብሄር ፖለቲካ ያዋጣችኋል?
አቶ መለሰ፡- ለዚህ ነው ጥናትና ውይይት የሚካሄደው፤ የሚያስቸግሩ ነገሮች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። እነዚህን እንዴት እንለፋቸው? ውህደት ሲፈጠር ምን ስጋቶችና ዕድሎች ይመጣሉ? ብሎ በመለየት፤ ዕድሎቹን እንዴት እንጠቀማለን? ስጋቶችን እንዴት እንገራቸዋለን? የሚለውን ለማስቀመጥ ነው። እንደአገር ያለንን ዓላማ ማሳካት በጥናቱ የሚመለሱ ናቸው። በመሆኑም ግንባር ወይም ውህደት የሚፈጸመው ጥናቱን መሰረት በማድረግ ነው። ዋናው ዓላማ አንድ ጠንካራ፤ ተፎካካሪና አገሪቱ አሁን በደረሰችበት ደረጃ ሊያታግል የሚችል ፓርቲ መፍጠር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ የጽሕፈት ቤቱን መዋቅርም እያሰራ ነው። የዚህ ፋይዳው ምንድነው? አቶ መለሰ፡- ከአገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ ማስተካከያ የሚደረግባቸው አቅጣጫዎች ተለይተዋል። አንዱ አገራዊ የፖለቲካ ሪፎርም ማድረግ ነው። የዚህ ማስተካከያ ባለፉት ወራት በተወሰዱት እርምጃዎች ይገለፃል። በሰብዓዊ መብት፤ በፓርቲዎች አያያዝ፤ በዳያስፖራ ዲፕሎማሲና በሌሎች ሁኔታዎችም ይገለፃል። ከዚህ በመነሳትም ኢህአዴግ በህዝብ ውስጥ ያለውን የለውጥ ሚና መወጣት አለበት። የፓርቲ የውስጥም ይሁን የውጭ ዴሞክራሲ ትግሉ በደረሰበት ደረጃ መሆን አለበት።
በጽሕፈት ቤት ደረጃ የሚደረገው ማሻሻያም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሻሻያ ለማሳለጥ እንዲረዳ ለማድረግ ነው። ይህን የሚመራበት ቁመና መያዝ አለበት። የተጀመረው ለውጥ ህጋዊና አስተዳደራዊ አመራር ያስፈልገዋል። ይህን የሚመራ ኃይል መፍጠር አለበት። በጽሕፈት ቤት ደረጃ የሚደረገው ማሻሻያና ለውጥ ውጤታማ የሚያደርግ የማዕከል ግንባታ ነው። የአደረጃጀት፤ የአሰራር፤ የሰው ኃይል አደረጃጀት ለውጡ ይህን የሚሸከም ማዕከል ለመገንባት ነው። አዲስ ዘመን፡- መዋቅሩ ግለሰቦችን ማዕከል ያደረገ ነው የሚሉ አሉ። ስለዚህ ምን ይላሉ? አቶ መለሰ፡- ማሻሻያ ግለሰቦችን ማዕከል ሊያደርግ አይችልም። ግለሰቦችን ማዕከል ካደረገ ሪፎርም ሊሆን አይችልም። የማሻሻያው ዓላማ ለውጡ ውጤት እንዲያመጣ ማድረግ ነው። ይህን ያሳካል አያሳካም የሚለው በሂደት የሚታይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረቱን እየረሳ ነው የሚሉ አሉ። መልስዎ ምንድን ነው?
አቶ መለሰ፡- የድርጅቱ ማህበራዊ መሰረቱ ከለውጡ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ፤ የከተማው ነዋሪ፤ ወጣቱ፤ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። የለውጡ መነሻም የተለያዩ የህብረተሰብ ቅሬታዎች ናቸው። ወጣቱን ለማስተማር ከፍተኛ ወጪ ወጥቷል። አሁን ላለው ለውጥ የምትጠቀምበት ነው። ይህን ያለመጠቀም ችግር እንደነበርና አኩራፊ መሆኑ ተገምግሟል። የለውጡም አካል ነው። ወጣቱን አንዱ መሰረት አለማድረግ ወላጆችን የሚያስከፋ ነው። በዚህም የተነሳ ማህበራዊ መሰረታችን ሰፍቷል። ወጣቱ፣ ሴቶች፣ አርሶና አርብቶ አደሩ፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶችና ምሁራን የኢህአዴግ መሰረት ናቸው። ሲደመር ልማት ሁሉንም በተመጣጠነና በአቅም ልክ ማልማት ነው። ወደዚህ ለመግባት ግን የመጀመሪያው ሥራ ሰላምን ማረጋገጥ ነው። የሰላም እጦት እየቀነሰ ቢሆንም፤ አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮች አሉ። ይህን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ያስፈልጋል። ባለፉት ወራት በስፋት የተሰራው እዚህ ላይ ነው። ሰላምን ማረጋገጥ ለሁሉም መሰረት ነው።
አዲስ ዘመን፡- አብዮታዊ ዴሞክራሲን መስመራችሁን ትታችኋል በሚል ትታማላችሁ። ለዚህ ምንድን ነው የሚሉት?
አቶ መለሰ፡- አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማለት ልማትና ዴሞክራሲ ማለት ነው። ይህን መስመር አልለቀቅንም። በዚህ አገር መሰረታዊ ችግር የሚባለው የድህነትና የዴሞክራሲ ችግር ነው። ድርጅታችን በነዚህ ላይ አትኩሮ የሚሰራ ነው። ከዚህ በፊትም እንደተገለጸው ልማታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራሙ መሆኑ ግልጽ ነው። ተራማጅ ከመሆኑ አንፃር በቀጣይ ማስተካከል ሲኖርበት የሚስተካከል ይሆናል። ከለውጡ ጋር ተያይዞ መደናገር እንዳለ እናውቃለን። እስካሁን የቀየርነው ፕሮግራም የለም። ለውጥን የሚመሩ፣ የሚከተሉና የሚያደናቅፉ ሁሌም በለውጥ ውስጥ አሉ። በለውጡ ወቅትም የሚደናገሩ ይኖራሉ እንጂ እኛ እስካሁን የቀየርነው የለም።
አዲስ ዘመን፡- የኢህአዴግ ባህል እየተሸረሸረ እንደሆነ የሚያነሱ አሉ። በተለይም ከአመራሮች መግነንና ክህዝባዊነት ይልቅ መሬት የመቀራመት አባዜ ተጠናውቷቸዋል ይባላል። ስለዚህስ ምን ይላሉ?
አቶ መለሰ፡- የመሬትን ሌብነት በሚመለከት ድርጅቱ ግልጽ አቋም አለው። ወሰንን በሚመለከት ከሆነም በመርህና በተቋማዊ አሰራር ይመለሳል የሚል አቋም ነው ያለን፤ ከዚያ ውጭ ፍላጎት አለ የለም የሚለው በተለያየ መልኩ ይነሳል። የወሰን ጥያቄ የህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ስለሆነ ህዝቦችን በማቀራረብ ይፈታል ብሎ ኢህአዴግ ያምናል። ከጉባዔው ውሳኔ በመነሳትም የእርቅና የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በግለሰብ ደረጃ የተለያየ ፍላጎት ቢንፀባረቅም የፓርቲ ሊሆን ግን አይችልም። ክልሎች ካላቸው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተው የተለያየ ሃሳብ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። በኢህአዴግ ደረጃ ውይይት ሲደረግ እየተፈታ የሚሄድ ነው። ኢትዮጵያ ሁሉም ህዝቦች የሚወዷት አገር ትሆናለች። ስርዓት ባለው መንገድ ችግሮች ይፈታሉ።
የተቀመጠው አቅጣጫ ችግሮቹን የሚፈታ ነው። በለውጥ ወቅት የተለያየ እሳቤ ስለሚኖርና ይህንንም የተለያዩ አካላት ለተለያየ ዓላማ ለመጠቀም ስለሚጎትቱት መደናገር ቢኖርም በይዘቱ ግን ችግር የለም፤ በተቀመጠው አቅጣጫም ይፈታል። በህብረተሰቡ መለወጥና በነባራዊ ሁኔታዎች መቀየር የኢህአዴግ ባህልም ይለወጣል። ከአመራሩ ጎልቶ መውጣት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ያልተማረ ሰው ይበዛ ነበር። አሁን የተማረ ሰው ቁጥሩ ጨምሯል። የነበረው አስተሳሰብ ተለውጧል። ይህ ብቻ አይደለም፤ አሁን የመረጃ ዘመን ነው። የሰው የንቃት ደረጃም ጨምሯል። ቀደም ሲል የነበረውን የኢህአዴግ የግንኙነት ስልት ዛሬ ሊጠቀምበት አይችልም። የዛሬውንም በቀጣይ ሊቀጠምበት አይችልም። ከጊዜውና ከሁኔታዎች ጋር አብሮ ይቀያየራል።
አዲስ ዘመን፡- በሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ አገርን ሊበትን የሚችል አደጋ መኖሩን፣ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እንዳለ፤ እንዲሁም እርስ በርስ መጠራጠር እንዳለ ተማምናችኋል። ለዚህ ማንን ተጠያቂ አደረጋችሁ?
አቶ መለሰ፡- የአገሪቱን ሁኔታ በሚመለከት በለውጥ ውስጥ ናት። በዚህ ምክንያት ለውጡን የሚመራና ለውጡን ለመቀልብስ የሚፈልግ፤ እንዲሁም በነበረው ፍላጎትና አስተሳሰብ ለመቀጠል የሚፈልግ አለ። እነዚህ በማንኛውም ለውጥ ውስጥ የማይቀሩ ናቸው። ይህ የሚለየው በአቅጣጫዎችና በውሳኔዎች ላይ ተመስርቶ ነው። ለውጡ በራሱ ጥርጣሬ የሚፈጥር ነው። አንዳንድ ጊዜ የለውጡ ኃይል እንዲበዛ ማቀዝቀዝም ያስፈልግ ነበር። በሂደቱ የተለያዩ ግለሰቦች የተለያየ አቋም ይይዛሉ። እንደኢህአዴግ ለውጡን የሚመራው ባላደራ ነው። ከዚህ የተነሳ ሁልጊዜም ትግል ይፈልጋል። በለውጥ ሂደት ውስጥ ያለ ነው።
እርምጃ በመውሰድም ሂደት ፊትና ኋላ የመሆን ሁኔታ አለ። ይህ እየተገመገመ እየተስተካከለ የመጣና ወደፊት የሚሄድ ነው። በሂደቱ ግን በአመራሩ፤ በድርጅቱ ውስጥና በህብረተሰቡም ጭምር መጠራጠር ይኖራል። ይህ ግን በኢህአዴግና በውጭ የተለያየ እሳቤ ነው። ኢህአዴግ በለውጥ ሂደት ችግሮች እንደሚፈጠሩና እየተገማገሙ፤ እየተስተካከሉ እንደሚሄዱ ያውቃል። እየተስተካከለም መጥቷል። ልዩነቶች ካሉም በቀጣይ ውይይት ይደረጋል። በተግባቦት ይፈጸማል። መጠራጠር ከሌለ ግን አደገኛ ነው። በመሆኑም ችግሩ ለእከሌ ተብሎ የሚሰጥ አይደለም። የሁሉም ነው። እየተተጋገለ ችግሮችን እየፈታ ይመጣል። አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ በአንባቢዎች ስም አመሰግናለሁ! አቶ መለሰ፡- እኔም አመሰግናለሁ!