የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ ደጉን እና ፈጣሪውን አብዝቶ የሚያከብረውን አጼ ዮሃንስ አንደኛን የወለደች እናት በማህጸኗ ራስ ሚካኤል ስሁልን ጸንሳ ወለደች:: ብዙ ተባዙ በተባለው የፈጣሪ ህግ መሰረት ትንሿ ትንኝስ ራሷን ተትካ አይደል፤ ራስ ሚካኤል ስሁልም ለአካለ መጠን በደረሰ ጊዜ ቢጤውን አግብቶ ተካነን ወለደ:: ተካነ የታበለው ልጁም ጥላቻ የተባለች ሴትን አግብቶ በተንኮል እና በውሸትን ወለደ:: ስምን መላዕክ ያወጣዋል እንዲሉ በውሸት ተካነ እና በተንኮል ተካነ ምግባራቸውም እንደስማቸው ሆነ:: እንደውም የሰፈራችን ሰዎች የተካነን ልጆች ገብረ ተንኮል እና ገብረ ውሸት እያሉ ይጠሯቸዋል:: የተንኮል ባሪያ እና የውሸት ባሪያ እንደማለት ነው ::
የሚገርመው ነገር ራስ ሚካኤል ስሁል በክፋትም፣ በተንኮል እና በውሸትም ራሱን አስመስሎ መውለዱ ነው:: እነኝህ የራስ ሚካኤል ልጆች ባልና ልጅን አስቀምጠው እናትን ይደፍራሉ:: በልጅ ፊት አባትን ይደበድባሉ:: ሃጢያት ነው የተባለን ነገር በሙሉ ይፈጽማሉ:: ለዚህ አይደል የእድራችን አባላት የራስ ሚካኤልን ልጆች ከየት እንደሚመድቧቸው የተቸገሩት:: ምክንያቱም “ሰው” እንዳይሏቸው የትኛው ሰው ነው ባል እና ልጆች ፊት እናቶችን የሚደፍር ? “አውሬ” እንዳይሏቸው የትኛው አውሬ ነው ባል እና ልጆች ፊት እናቶችን የሚደፍር ? ማን ብለን ለመጥራት ተቸገርን እኮ ጎበዝ!
በነገራችን ላይ ገብረ ተንኮል እና ገብረ ውሸት ለእናታቸው ሌላው ጎረቤት የሚያከብራትን ያህል አንድ አስረኛውን ክብር አይሰጧትም:: ይልቁንም እናታቸውን ክፉ ከሚመኟት ባላጋራዎቿ ጋር ወግነው እናታቸውን በከፋት መርዛቸው እየነደፉ እና በውሸት ትርክታቸው እየተበተቡ ለመግደል ይጣጣራሉ:: ይህን የተመለከቱ እናቶች ልጅ እንዲህ ከሆነ ልጅ እንዳትሰጠኝ ብለው ፈጣሪያቸውን ሲለምኑ አይቻለሁ::
በውሸት እና በተንኮል ተካነ የራሳቸው የ”መ” ህጎች አሏቸው:: የ“መ” ህጎቻቸውም መዝረፍ ፣መስረቅ፣ መድፈር ፣ መዋሸት፣ መግደል ፣ መምሰል ፣ በአጠቃላይ መርከስ የሚለውን የያዘ ነው::
አሁን ላይ እድራችንን እያስተዳደረ ያለው የደጉ የአጼ ዮሃንስ አንደኛ ሶስተኛ የልጅ ልጅ አቶ ቁም ነገር ነው:: አቶ ቁም ነገርን የሰፈራችን ሰው አስናቀ እያለ ይጠራዋል:: እኔም አቶ ቁም ነገርን አስናቀ እያልኩ ስጠራው ነው ደስ የሚለኝ:: ስንቱን አዋቂ ነኝ ባይ ፈረንጅ በአመራር ጥበቡ አስከንድቶት የለም እንዴ!
አስናቀ እንደአባቱ ፈጣሪውን የፈራ እና አገሩንም አጥብቆ የሚወድ ነው :: የራስ ሚካኤል ስሁል ልጆች ግን ደግ የሚሰራ ሰው አጥብቀው ስለሚጠሉ ከአጼ ዮሃንስ የልጅ ልጅ አስናቀ ጋር አይን እና ናጫ ናቸው::
የራስ ሚካኤል ልጆች አሁን ላይ አስናቀ የሚመራውን እድር በሚመሩበት ጊዜ የእድሩን ገንዘብ እንደፈለጉ መዝበራዋል:: እንዴት የእድራችን ብር ይመዘበራል ብለው የጠየቁ ሰዎችንም ገለዋል::
እድሩን መመዝበራቸው አልበቃ ብሏቸው፣ የእድሩ አባላትን በመግደላቸው እና በማሳደዳቸው መጸጸት ሲገባቸው «ነፍስ ጽግብት ጻቃውዓ መዓር ትሜንን / የጠገበች ነፍስ የማር ወለላ ትረግጣለች» እንዲሉ ይባስኑ ብለው የእድሩን ህልውና ያስጠብቃሉ የተባሉ ወታደሮችን በተኙበት አርደው ጣሉ:: ለምን ቢባሉ ምን አገባችሁ አይነት መለስ መለሱ::
አባቶች ጠብቀው ያስረከቡኝን እድርማ ሲፈርስ ዝምብዬ አላይም ያለው የእድራችን መሪ አስናቀ ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ›› ብሎ ወደ እነ ገብረ ተንኮል ሰፈር ሠራዊቱን አዘመተ:: በጥቂት ቀናትም እነገብረ ተንኮልን ልክ አስገባቸው:: የሰፋራችን ሰዎችም እጅጉን ደስ አላቸው::
የእድራችን መሪ አስናቀ ጊዜ ሳያጣፋ «ጠቡን ትተን እድራችንን እናልማ » ብሎ ከእነ ገብረ ተንኮል መንደር ወታደሩን አስወጣ :: በዚህ ጊዜ ጥጋብ የማይችሉት እነገብረ ተንኮል እና ገብረ ውሸት የአስናቀን ወታደር አሸነፍን ሲሉ ተንጫጩ:: ይህን የእነ ገብረ ተንኮል ውሸት እና ጉራ በሰማሁ ጊዜ አንዲት ሰካራም ጦጣ ያለችው ትዝ አለኝ ::
አንድ ጦጣ ጥንብዝ ብላ ሰክራ እየተወላገደች እየሄደች ሳለ በአጋጣሚ ከየት መጡ ያልተባሉ አንበሳ እና ነብር ከጦጣዋ ከግራ እና ከቀኝ ተከሰቱ:: አንበሳ እና ነብርም እኔ እበላ እኔ እበላ ፊት ለፊት ተፋጠጡ:: ተፋጠውም አልቀሩ ግብግብ ገጠሙ:: በግብግቡም የሰከረችውን ጦጣ በትንሹ ገፋ አደረጓት::
የተገፋችው ጦጣም በጣም ሰክራ ስለነበር ወዲያውኑ ወደቀች :: ከስካሯ ብዛትም ጦጣዋ በወደቀችበት አደረች :: ጠዋት ላይ ጦጣዋ ከስካሯ ስትነቃ አንበሳ እና ነብር ሞተው አገኘቻቸው:: ከወደቀችበት ተነስታ አቧራዋን እያራገፈች እና እስከምትችለው ድረስ ወደ ላይ እና ወደ ጎን እየተንጠራራች ምን ብትል ጥሩ ነው ፡- «እኔ እኮ ስሰክር የማደርገውን አላውቀውም :: ሁለቱንም ገደልኳቸው ! አይ የኔ ነገር ብላ ደሰኮረች:: » ነገር ግን ጦጣዋ እሷ እንዳልገደለቻቸው ልቧ በደንብ ያውቅ ነበር::
ገብረ ተንኮል እና ገብረ ውሸት ያደረጉትም የጦጣዋ አይነት ነው :: የአስናቀ ወታደሮች በእነ ገብረ ተንኮል እና ገብረ ውሸት ሰፈር ገብተው ሳለ ገብረ ተንኮል እና ገብረ ውሸት እንደ አይጥ በየጉድጓዱ እና ጥሻው ይሽሎከለኩ ስለነበር የሚበሉት እና የሚጠጡት ለማግኘት ተቸግረው ነበር:: በዚህ ወቅት እነ ገብረ ተንኮል እና ገብረ ውሸት ረሀባቸውን ለመርሳት ሃሺሽ አብዝተው ይመጉ ነበር :: በሃሺሽ ናውዘው እና ሰክረው የነበሩት የራስ ሚካኤል ልጆች በአጋጣሚ ከተደበቁበት ዋሻ ሲወጡ እና የሃሽሽ ስካራቸው ሲለቃቸው የእድሩ ጠባቂዎች ከሰፈራቸው ወጥተው አገኟቸው:: የእድሩ ጠባቂ ወታደሮች ከሰፈራቸው አለመኖራቸውንም ያዩት እነ ገብረ ተንኮል እና ገብረ ውሸት «የአስናቀን ወታደሮች » አሸነፍን ሲሉ ታበዩ::
ከሰፈራቸው የወጣውን ወታደርም ለመምታት ተከተሉ:: ተመለሱ! ቢባሉ ማንንም አንሰማም አሉ:: የእድሩ ጠባቂ ወታደሮችም ከዛሬ ነገ ይማሩ ይሆን በማለት ሸሹላቸው :: ነገር ግን ሲያዙ ጭብጥ ሙሉ ፤ ሲለቀቁ ጥጋብ የማያስችላቸው የራስ ሚካኤል ልጆች በሄዱበት ሰፈር ሁሉ የህዝብ መገልገያዎችን አወደሙ፤ ሴቶችን ደፈሩ፤ ወንዶችን ገደሉ :: በአጠቃለይ የፖለቲካ መርሃቸው የሆነውን መዝረፍ ፣መስረቅ፣ መድፈር ፣ መዋሸት፣ መግደል ፣ መምሰል ፣ መርከስ የሚለውን የ“መ” ህጎቻቸውን በደረሱበት በሙሉ ተገበሩ:: የአሪዎሳዊ ምግባርን በአደባባይ ፈጸሙ::
ይባሱኑ ብለው የእድሩ መሪ ተሸንፏል:: ከእድሩ መሪ መናገሻ ከተማ ልንገባ ነው :: ስለሆነም የእድሩ መሪ እና ወታደሮች “እጃችሁን ስጡ” ሲሉ ታበዩ :: የእድሩ መሪ የሆነውን አስናቀን ኤርዶጋን ሆነ ቪላድሚር ፑቲንም አያድነውም ሲል ተዘባበቱ:: ጦርነቱ በእኛ አሸናፊነት ስለተጠናቀቀ ከእንግዲህ በኋላ ድርድር የሚባለው ጉዳይ ተዘግቷል:: እንደራደር ቢባልስ የምንደራደረው ከማን ጋር ነው? ሲሉ የሰሚ ጆሮ እስኪደነቁር ለፈፉ::
የራስ ሚካኤል ልጆች ለጥፋት ጌቶቻቸው ምዕራባዊያንን ለማስደሰት የእድሩን መሪ አሸንፈነዋል ሲሉ ለጌቶቻቸው ሪፖርት አደረጉ :: የጥፋት ጌቶች ምዕራባዊያንም የራስ ሚካኤል ልጆችን ውሸት አምነው “አስናቀ የሚመራው እድር ሊፈርስ ነው!” ሲሉ 360 ዲግሪ በሚያሽከረክሯቸው መገናኛ ብዙኃኖቻቸው ለአለም ህዝብ አስተጋቡ:: ዜጎቻቸውን እና ዲፕሎማቶቻቸውንም አስናቀ ከሚመራው እድር መገኛ እንዲወጡ ወተወቱ:: በራስ ሚካኤል ልጆች እና በምዕራባዊያን ሰፈር «የቀበሮ ደስታ በዛ :: »
ምዕራባዊያን ይህን ባሉ በቀናት ውስጥ የእድራችን መሪ አስናቀም ትግስቱ ተሟጦ በባህሩ ቃኘው ፉከራ እና ሽለላ እንዲህ ሲል ሸለለ፡-«ስጋዬን ብሉ አጥንቴንም እንኩ፣በምንም በምንም አገሬን አትንኩ:: » «በእድሬ ስር ያለህ ህዝቤ ተከተለኝ» ሲልም አወጀ :: ህዝቡም ከሊቅ እስከ ደቂቅ በመውጣት ለእድራችን መሪ አጋርነቱን አሳየ:: ሁሉም ነገር በቅፅበት ተለወጠ::
የእድራችን አባላት መሪያቸውን ተከትለው ወደ ጦር ግንባር ተመሙ:: መሪያቸው ወደ ጦር ግንባር መሄዱን የሰሙ መጀመሪያውኑ ጦር ግንባር የከተሙ የነበሩ ጥምር የጸጥታ ኃይላትም ሞራላቸው በከፍተኛ ደረጃ ተነሳሳ:: ሞራሉ የተነሳሳው የወገን ጦር የሽብር ቡድኑን ይወቃው ያዘ:: የሽብር ቡድኑም ተፍረከረከ:: ብርክ ያዘው :: ወደ ኋላ ለመውጣት ሞከረ :: ወደ መሃል አገር እየዘለሉ እንደገቡ ሁሉ ከመሃል አገር እየዘለሉ መውጣት እንደእናት እቅፍ ናፈቁ :: የእናት እቅፍ ጊዜው ካለፈ በኋላ የት ይገኛል? አሁን የመውጫው ጊዜ አልፏል :: መሞት ወይም እጅ መስጠት ብቸኛው አማራጭ ነው !
የሽብር ቡድኑ መሪዎች የራስ ሚካኤል ልጆች ከሰፈራቸው እስከመሀል አገር ሲገቡ እዚህ ግባ የሚባል ውጊያ አላደረጉም:: ውጊያው ከባድ መሆኑን አልተረዱም :: በውጊያው ወቅት በጣም የተከፉት የእድራችን ሰዎች ቀጭኑ በንዴት ወፈረ፣ ወፍራሙ በንዴት ተንተክትኮ ቀጨጨ:: በእልህ የገባው የወገን ጦር የሽብር ቡድኑን ጉሮሯቸውን እያነቀ እስከ ወዲኛው ሸኛቸው::
ባህሩ ቃኘውን ፉከራ እና ሽለላም ፡-
ሰርጎ ገቡን አስሮ አፈር አለበሰው ፣
ሰርጎ ገቡን አስሮ ደሙን አፈሰሰው ፣
ወንበዴውን ገድሎ አፈር አለበሰው ፣
ሄደ ግብር ኃይሉ እየደመሰሰው:: እንዳለው የወገን ጦር ሰርገው የገቡ የራስ ሚካኤል ልጆችን በገቡበት እየገባ ደመሰሳቸው:: በቆፈሩት ምሽግ ፣ በቆለሉት ድንጋይ ፣ እንደዝንጀሮ በወጡበት ተራራ፣ በዘረፉት እና በአፈራረሱት የመንግሥት እና የግል ተቋማት ውስጥ ከነጥፋታቸው እና ሃሽሻቸው ላይመለሱ ወደ ተመኙት ሲኦል ተሸኙ:: የተረፉትም እግሬ አውጭኝ ብለው ሲሸሹ:: የወገን ጦር ፈርጣጮችን እየተከተለ ወቃቸው::
በእነ ራስ ሚካኤል ልጆች እና በምዕራባዊን ሰፈር የነበረው ደስታ የቀበሮ ደስታ ብቻ ሆኖ ቀረ:: የቀበሮ ደስታ ምንድን ነው? ይባል ይሆናል:: መልሱ ወዲህ ነው:: ቀበሮ ምግቧን ለመፈለግ ከተደበቀችበት ጉድጓድ በሌሊት ትወጣለች:: እንዳጋጣሚ ሆኖ የጣዝማ ማር ታገኛለች:: የጣዝማ ማር በማግኘቷ ደስታዋ ልክ ያጣል:: የጣዝማ ማሩን አውጥታ ከመብላቷ በፊት ሃሺሽ እንደማገ ሰው በደስታ ሰክራ ከወዲያ ወዲህ በደስታ ትፈነጥዛለች :: ደስታዋ ልክ አጥቶ የጣዝማ ማሩን ካየችበት ቦታ ርቃ እየፈነጠዘች ትሄዳለች:: በመጨረሻም ፈንጠዝያዋን ጨርሳ ስትመለስ የጣዝማ ማሩን ታጣዋለች:: ምክንያቱም ደስታዋ ያለመጠን ሆኖ ማሩን ካገኘችበት ቦታ በጣም ርቃ ሂዳ ስለነበር ነው:: በዚህም የቀበሮዋ ደስታ ጊዜያዊ ሆነ:: በአገራችንም ጊዜያዊ ደስታን ለመግለጽ አባቶቻችን “የቀበሮ ደስታ” እያሉ ይጠሩታል::
ይህን ተከትሎ “እጃችሁን ስጡ፤ የእድሩ መሪ የሆነውን አስናቀን ኤርዶጋን ሆነ ቪላድሚር ፑቲንም አያድኑትም፤ ጦርነቱ በእኛ አሸናፊነት ስለተጠናቀቀ ከእንግዲህ በኋላ ድርድር የሚባለው ርዕስ ተዘግቷል፤ እንደራደር ቢባልስ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው ?” ሲሉ ሲዘባበቱ የነበሩት የራስ ሚካኤል ልጆች አሁን ላይ ተደራደሩ የሚለውን ምዕራባዊያን ከንቱ ምክር ይዘው ጉዳዩን በሰላም ለመቋጨት በማሰብ ለመደራደር ነው እንጂ ከአማራ እና ከአፋር ክልል የወጣነው አሁንም እድሩን የማጥፋት አቅሙ አለን ሲሉ ደሰኮሩ::
ይህንን በሰዎች ተጽዕኖ ያልፈለጉት ለማድረግ የሚታገሉትን የራስ ሚካኤል ልጆች ስመለከት አንድ ሚስቱን ይጠላ የነበረ ሰው ታሪክ ትዝ አለኝ :: አንድ ሰው ሚስቱን አብዝቶ ይጠላት ነበር :: ከሚስቱ ጋር አብሮ ይኑር እንጂ ሚስቱን እንደጠላት ይቆጥራት ነበር:: ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ቤቱ ሲገባ ሚስቱን ባልተለመደ አኳኋን የእኔ ቆንጆ እወድሻለሁ እያለ ግንባሯን ይስማታል፤ ይደባብሳታል:: ሚስትም በባሏ ያልተለመደ ባህሪ ተገርማ «ምነው ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው እንዲህ የምትንከባከበኝ?» አለችው:: ባልም አሁን የመጣሁት ከቤተ ክርስቲያን ነው :: ቤተክርስቲያንም ሲሰበክ «ጠላታችሁን እንደራሳችሁ አድርጋችሁ ውደዱ የሚል ስብከት ሰማሁ:: ለዚያ ነው ዛሬ እንዲህ የተንከባከብኩሽ» ብሏት አረፈው::
የራስ ሚካኤል ልጆችም እንደራደር ያሉት ምዕራባዊያን በቀጣናው የሚያጡትን ጥቅም አስልተው ጥቅማቸውን እንዳያጡ በሰላም ቢፈታ ይሻላል ስላሏቸው እንጂ የራስ ሚካኤል ልጆች ድርድርን የሚያክል የጤነኞች መግባቢያ መርህ የሚያስብ ጭንቅላት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ አይተናቸዋል::
ለማንኛውም መደራደር ከፈለጋችሁ የመደራደሪያ ቦታ ከተመኛችሁት ሲኦል ውስጥ ተዘጋጅቶላችኋል:: ከሲኦል ጌቶች ከምዕራባዊያን ጋርም በሰላም በሲኦል ያገናኛችሁ!
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2014