የገና በዓል የስጦታ በዓል ነው። በተለይ በፍቅረኛሞች መካከል የሚደረግ የስጦታ ልውውጥ በእጅጉ ይታወቃል። ‹‹የገና ስጦታ›› መለዋወጡ በፍቅረኛሞች ዘንድ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ከፍቅረኞችም አልፎ ከግለሰብ እስከ ተቋማት ድረስ ዘልቋል። በሥራ ባልደረባነት፣ በጓደኛነት፣ በአብሮ አደግነት፣ ወዘተ. መካከል የሚደረግ የስጦታ ለውውጥ የገናን በዓል በጉጉት እንዲጠበቅ አድርገውታል።
የዘንድሮውን ገና በዚህ ዓይነት መልኩ የደስታና የፌሽታ ስጦታዎች መለዋወጫ አድርጎ ማክበር ብዙም የሚታሰብ ይሆናል ብዬ አላምንም። ምክንያቱ ደግሞ አገራችን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ እርዳታና ድጋፍ ማድረግን የሚጠይቅ መሆኑ ነው።
ኢትዮጵያውያን በዓላትን አብረው የሚያከብሩ እንደመሆናቸው ባለፉት ዓመታት ከበርካታ ወገኖቻቸው ጋር በዓላትን አብረው አክብረዋል። ለበርካታ ወገኖችም አሉበት ድረስ በመሄድ እንዲሁም በአደባባይ ሥርዓት ድጋፎችን አድርገዋል።
ዘንድሮ ደግሞ ይህን ድጋፍ በብዙ እጅ ማሳደግ የሚያስፈልግበት ሁኔታ ተከስቷል። ከሀዲው ትህነግ በአማራና አፋር ክልል ወረራ በመፈጸም ሚሊዮኖችን እርዳታ ፈላጊ አድርጓልና። የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ።
በየአደባባዩ ለተፈናቀሉ ዜጎች ያላችሁን ለግሱ የሚሉ ጥሪዎች ይሰማሉ። ይህን ሁሉ በእጅጉ ልብን ይሰብራል፤ አንጀት ያላውሳል። የሰው ልጅ ይፈጽመዋል ተብሎ የማይታሰብ ግፍ በዜጎቻችን ላይ በትህነግ ተፈጽሟል። እናም የዘንድሮውን የገና በዓል በተለመደው የስጦታ በዓል ድባብ ማክበር የማያስችል የሥነ ልቦና ችግር ውስጥ ገብተናል። የዘንድሮውን የገና ስጦታ ለእነዚህ ዜጎች የበዓል መዋያ ብቻ ሳይሆን መደገፊያና መልሶ ማቋቋሚያ ማዋል መንፈሳዊና ባህላዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን፣ ለወገን ደራሽ በመሆን አገራዊ ኃላፊነትን የመውጣት ፋይዳም አለው።
እነዚህ ዜጎች የኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የመላ ዓለምን ልዩ ድጋፍ ይፈልጋሉ። እርግጥ ነው ኢትዮጵያውያን ከመንግሥት ጋር በመሆን ድጋፋቸውን እያደረጉ ናቸው። ይህ ወቅት የኢትዮጵያውያን መተሳሰብ በእጅጉ ጎልቶ የወጣበትም ነው። ድጋፉ ወራትን የዘለቀና መጠናከር ያለበትም ነው። ስጦታውን ለድጋፍ ማሰባሰቢያ በማዋል ይህን ርብርብ ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ባይ ነኝ። አሁን ካለው ሰፊ ችግር አኳያ ሌሎች አዳዲስ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መንገዶችንም ማሰብ ያስፈልጋል።
የዘንድሮው የገና በዓል እንዴት ይከበር? ይህን የገና በዓል ‹‹ገናን ለወገኔ›› በሚል የገና ስጦታ ንቅናቄ ለማክበር አንዳንድ ግለሰቦች በማህበራዊ ገፆች እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረው ተመልክቻለሁ። እንዲህ ዓይነቱን ቅዱስ ተግባር ማበረታታትና ሽፋን መስጠት ደግሞ ከዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ይጠበቃል። አስታውሳለሁ ከሁለት ይሁን ሦስት ወራት በፊት ‹‹ቻሌንጅ›› በሚባል የማህበራዊ ገፆች ጨዋታ ለተቸገሩ ወገኖች ብዙ እርዳታ ተደርጓል። እንዲያውም አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር በዚሁ ጉዳይ ላይ ጽፈው አንብቤያለሁ፤ በእነርሱም ታይቷል ማለት ነው። ጨዋታው እንዲህ ነው። ሰዎች የሆነ ፎቶ ይለጥፋሉ።
በለጠፉት ፎቶ ‹‹በላይክ ይህን ያህል ብር፣ በአስተያየት ይህን ያህል ብር፣ በመጋራት (ሼር) ይህን ያህል ብር እከፍላለሁ›› ብለው ቃል ይገባሉ። ለምሳሌ፤ በትንሹ እንኳን በላይክ አንድ ብር፣ በአስተያየት ሁለት ብር እና በመጋራት (ሼር) ሦስት ብር ሊባል ይችላል።
ይህን ያለው ሰው 200 ላይክ፣ 100 አስተያየት እና 50 ሼር ቢያገኝ 550 ብር ድጋፍ አደረገ ማለት ነው። ለታማኝነቱም ያስገቡበትን የባንክ ደረሰኝ እዚያው ላይ ይለጥፋሉ። እየተጫወቱ በጎ ማድረግ ትልቅ ተግባር ነው። አብዛኛው ወጣት ደግሞ የማህበራዊ ገጾች ተጠቃሚ እንደመሆኑ ወጣቱ በእዚህ ዓይነቱ በጎ ተግባር እንዲሳተፍ ለማድረግ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው። እነዚህን ገጾች ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ታዋቂ ሰዎችም ይሳተፉባቸው እንደነበር አውቃለሁ።
የዘንድሮው የገና በዓልም አንድም በዚህ መልኩ መከበር አለበት፤ እየተዝናኑና እየተጫወቱ ለወገን መድረስ! ከሚበሉት ማካፈል። ወቅቱ የምንዝናናበት፣ የምንጫወትበት ባይሆንም፣ እንዲህ ቀለል ባሉ መንገዶች በመጠቀም ሁሉንም በማሳተፍ በዓሉንም እርዳታ ማሰባሰቡንም ማስኬድ ይቻላል።
የማህበራዊ ገፆችን ያነሳሁት እንደ ምሳሌ እንጂ ቅስቀሳው ግን በዚያ ብቻ መወሰን የለበትም። በአብዛኛው አዋቂዎች የማህበራዊ ገፆች ተጠቃሚ እንዳለመሆናቸው እነሱ ላይ በዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን በኩል ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል። ገናን ለወገን ስጦታ በማበርከት ማክበር ቀላሉ መንገድ ነው። ሌሎች ብዙ ዓይነት መንገዶችም አሉ። አቅም ላለው በተለያዩ አካላት የተከፈቱ የባንክ አካውንቶች፣ በተለያዩ ተቋማት የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴዎች በኩል ድጋፉን ማድረግ ይቻላል፤ በግለሰብ ደረጃም የሚያሰባስቡ አሉ።
ለእነዚህ አካላት የቻልነውን ያህል ማድረግ የህሊና እርካታን ይሰጣል፤ ወገኖቻችንን ይጠግናል። ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሠራው ዘገባ ላይ ሁለት ግለሰቦች ያደረጉትን የቁሳቁስ ድጋፍ አይተናል። እንዲህም በግለሰብ ደረጃ ይቻላል ማለት ነው። ብዙ ሰዎች ድጋፍ ሲባል የግድ በሚሊዮን ወይም በሺዎች የሚቆጠር ነገር ያስባል። ስጦታ ያለንን ማድረግ ነው።
ሰው ስጦታን የሚያከብረው በስጦታነቱ እንጂ በብዛቱ አይደለም። ‹‹ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም፣ የስጦታ ትንሽ የለውም፣ የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም…›› የሚሉት ምሳሌያዊ ንግግሮችም የሚያመለክቱት ይህንኑ ነው። የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም ማለት፤ ልክ እንደገዛኸው ዕቃ እያገላበጥክ እያየህ ‹‹ይሄ እንዲህ ሆኗል፣ ይሄ እንዲህ ነው›› አይባልም ማለት ነው።
ሰውየው ያለውን ነው አክብሮ የሰጠው። ኢትዮጵያውያን በእነዚህ በጎ እሴቶች የታነጹ ናቸው። ስለዚህ ‹‹እኔ ምን አለኝና ነው የምረዳው፣ እኔም ባገኝ እፈልጋለሁ›› የሚሉ አስተያየቶች ተገቢ አይደሉም። ተፈናቃዮቹ ምንም የላቸውም።
እኔ ጋ ያለች ቲሸርት ለእነርሱ ትጠቅማለች። ስጦታ ማለት ሲተርፈን የምንሰጠው አይደለም። ካለን ላይ የምናካፍለው ነው። ሦስት ወይም አራት ሸሚዝ ያለው አንዱን መስጠት ማለት እንጂ የግድ ጠቦን ወይም ሰፍቶን የተውነውን የምንሰጥበት አይደለም። እርግጥ ነው አልሆነን ብሎ የተውነውም ይሆናል፤ ለእኛ ያልሆነ ለሌላው ስለሚሆን፤ የግድ እሱን አጋጣሚ ብቻ መጠበቅ ግን የለብንም። የገና በዓል ምግብ መጠጥ በሰፊው የሚዘጋጅበት ነው። በተለይ አርሶ አደሩ በሚገባ ያከብረዋል። ወቅቱ የአዝመራና የጥጋብ እንደመሆኑ በልዩ ዝግጅት ያከብረዋል። ዘንድሮ ግን ተፈናቃዮችንና ችግረኞችን በማሰብ በልኩ ቢከበር መልካም ነው እላለሁ። በእያንዳንዱ የበዓል ዝግጅት ውስጥ ለተፈናቃዮች ማድረግ የሚገባውን ማሰብ ያስፈልጋል። በዚህ የገና በዓል በተለይ ምግብ ነክ ነገሮችን ድጋፍ ማድረግ የበለጠ ያስፈልጋል። የቱንም ዓይነት ቢለበስ፣ ጎዳና ላይም ቢታደር ዋናው ጉዳይ ምግብ ነው። የሰው ልጅ ምግብ ሲያጣ ሁሉንም ነገር ያጣል፤ የምግብ ነገር ጊዜ አይሰጥም፤ የማያልፍ ህመም ላይ ይጥላል።
ለእነዚህ ወገኖች ምግብ በማቅረብ መድረስ የምንችለው ዛሬ ነው። ስለዚህ፤ ለእዚህ በዓል በግ መግዛት የለመደ ካለ ዘንድሮ ወገኑ ሰብአዊ ድጋፍ /ምግብ/ ይፈልጋልና የሚገዛውን በግ በልኩ አድርጎ የተወሰነ ገንዘብ ለወገኑ የበዓል መዋያ ቢያደርግ በሕይወቱ ትልቅ ታሪክ ይሠራል። ከበግ መግዣው አካፈለ ማለት ነው። በየሆቴል ቤቶቹና መሰል ተቋማት በዓላትን የሚያሳልፉም ለመዝናኛ ከመደቡት ገንዘብ የተወሰነውን ለተፈናቃዮች በዓል መዋያ ቢያደርጉ በዓልን ተካፍለው አሳለፉ ማለት ነው። በቅርቡ የቀን ወጪዬን ለተፈናቃዮች የሚል ማስታወቂያ የተመለከትኩ መሰለኝ።
ይህም ጥሩ መንገድ ነው። እስቲ የቀን ወጪያችን መለስ ብለን እናስብ። የአንድ ቀን ወጪ ቢለገስ ተሰባስቦ ሊሆን የሚችለውን እናስብ። ይህ ጥሩ የእርዳታ ማሰባሰቢያ መንገድ ነው። ስለዚህ ለወገን ደራሹ ወገን ነውና የገና በዓልን በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች የድጋፍ ስጦታ በማበርከት እናክብር!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2014