ቅድመ ነገር፤
የጽሑፌን ርዕስ ለማጎላመስ የመረጥኩት የረቀቁና የመጠቁ መንፈሳዊ ምሥጢራት በተሸከሙ ሁለት ቃላት አማካይነት ቢሆንም የትርጉማቸውን ይዘት ጠልቆ ለመተንተኑ ግን ዐውዱ አይፈቅድልኝም። ማንኛውም ቃል ከተለመደው የላይ ላይ ትርጉሙ ከፍ ያለ ፍቺም እንደሚኖረው ይታወቃል።
እማሬያዊ ፍቺ የተለመደና በስፋት አገልግሎት ላይ የሚውልን ትርጉም የሚወክል ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ ፍካሬያዊ ትርጉሙ በተለምዶ አገልግሎት ላይ ከዋለው ላቅ የሚለው መልዕክቱ ነው።
ከዕብራይስጥ ቋንቋ በውሰት ተዳብለው ቤትኛ የሆኑት “ኤሎሄና ሃሌ ሉያ” የተሰኙት እነዚህ ሁለት ቃላት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የተመረጡት ማንኛውም ሰው በሚግባባባቸው የተለምዶ እማሬያዊ ፍቺያቸው እንጂ በፍካሬያቸው ብቃት አይደለም። ሥነ መለኮታዊ ትርጉማቸውን በተመለከተ ግን ለጊዜው ከጽሑፉ ዓላማ ላለማፈንገጥ በማሰብ ትንተናውን ማቅረቡ አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም።
“ኤሎሄ” መከራ ሲበረታ ወደ ፈጣሪ የሚያስቃትት የጭንቀት መግለጫና የመማጸኛ ቃል ሲሆን፤ “ሃሌ ሉያ” ደግሞ ደስታን፣ ሃሴትን፣ ፍስሃንና ፍንደቃን ለመግለጽ ግልጋሎት ላይ የሚውል ቃል ነው። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ “ኤሎሄና ሃሌ ሉያ” በሚል ርዕስ በዘመነ ደርግ ላይ ያተኮረ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ በ1992 ዓ.ም ለንባብ ማብቃቱን በማስታወስም “ከራስ ለራስ የተወሰደ የርዕስ ውሰት” መሆኑን መጠቆሙ አይከፋም።
አገሬ የተፈተነችባቸው የኤሎሄ ታሪኮች፤
በጄኔራል ናፒየር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት አጤ ቴዎድሮስን አድኖ ለመያዝ ከየአቅጣጫው ያደረገው የእብሪት ወረራ የተጠናቀቀው ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም ንጉሡ ራሳቸውን በራሳቸው እጅ ካጠፉ በኋላ መሆኑ በሁሉም ዘንድ የታወቀ የታሪካችን አንዱ ምዕራፍ ነው።
”እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ፤ እጅ ተይዞ ሊወሰድ፣ ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ፣ አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ?‘
በብዙ አቅጣጫ ሊተረጎሙ የሚችሉት እነዚህ ጥቂት ስንኞች በውሰት የተወሰዱት ከጸሐፌ ተውኔት ጸጋዬ ገብረ መድኅን “የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ” ከሚለው ዘለግ ያለ ግጥም መካከል ተቆንጥረው ነው። ቆራጡ አጤ ቴዎድሮስ በራሳቸው እጅ በጀግንነት እርምጃ ከወሰዱ በኋላ ነፍሳቸው ፈጥና አልወጣች ኖሮ ለመሞት እያጣጣሩ ባለበት ቅጽበት ወራሪዎቹ የእንግሊዝ ወታደሮች ፈጥነው በመድረስ በቀኝ እጃቸው አቅጣጫ የወደቀውን ሽጉጣቸውን፣ የጣታቸውን የወርቅ ቀለበት፣ የአንገታቸውን የወርቅ መስቀልና የለበሱትን ልብስ ሳይቀር ገፍፈው ለመውሰድ መሽቀዳደማቸው በበርካታ የታሪክ መዛግብት ተሰንዷል። ወራሪዎቹ ይህን መሰሉን ኢሰብዓዊ ድርጊት ከፈጸሙ በኋላ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ የማዕድ ቤት በመግባት ወደ ሃያ እንሥራ የሚገመት የተጠመቀ ጠጅና የእህል አረቄ ዘርፈው ከመጠን በላይ በመስከር ይፈነጥዙ እንደነበር የራሳቸው የታሪክ ጸሐፊ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ከዚያ በኋላማ ምን ይጠየቃል። ቴዎድሮስ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም በማሰብ የሰበሰቧቸውን እጅግ በርካታ መጻሕፍት፣ ሰነዶችና ከ500 በላይ የሚገመቱ የብራና ጽሑፎች እንደ እብድ አቅላቸውን ስተው ለሸክም እስከሚቸገሩ ድረስ መቀርቀቡን ተያያዙት። ጎን ለጎንም ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶችንም እየተናጠቁ ተቃረጧቸው። የንጉሡን የወርቅ አክሊል፣ የወርቅ ጽዋ፣ ልዩ ልዩ ጌጣጌጦችንና አልባሳትን ተሽቀዳድሞ ለመውሰድ እየተራኮቱ
ብዝበዛውን አጧጧፉት። ከፊሉ ጨረታ እዚያው መቅደላ፣ የሚበዛውን ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች በማድረግ “ምርኳቸውን” መሬት ላይ እየዘረጉ እንደ ተራ ሸቀጥ እርስ በእርስ እየተቸራቸሩ ተቀራመቷቸው። ለዘረፋ ያልተመቿቸውን የወግ ዕቃዎች፣ የንጉሡን ግምጃ ቤቶችና በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን አቃጥለውና አውድመው በመፈንጠዝ ደስታቸውን ገለጡ።
በግፍ ተግባር አጨማልቀው የሰበሰቧቸውን የከበሩ ቅርሶችና አሥራ አንድ ያህል ታቦታትም ወደ አገራቸው ለማጓጓዝ አሥራ አምስት ዝኆኖችንና ከሁለት መቶ በላይ የጭነት አጋሰሶችን መጠቀማቸውን በርካታ የአገር ውስጥና ባዕዳን ምሁራን ለታሪክ ምስክርነት እውነቱን ጽፈው አስተላልፈውልናል።
በዘረፋ የተወሰዱት ከላይ የተዘረዘሩት ቅርሶች አብዛኞቹ ዛሬም ድረስ በለንደኑ ቪክቶሪያና አልበርታ ሙዚዬሞች ውስጥ እንደሚገኙ ተረጋግጧል። (ለተጨማሪ ንባብ፤ KASA AND KASA – IES, Addis Ababa University 1990)።
ኢትዮጵያ በኤሎሄ ጣር የቃተተችባቸውን እኒህን መሰል በርካታ ዘግናኝ ታሪኮች ተቋቁማ አልፋለች። የጋዜጣው የገጽ ውሱንነት ገድቦን እንጂ በተወራሪ ታሪኮቻችን፣ አገር አሳሾች ነን ብለው አፈራችንን በረገጡ ባዕዳንና በሃይማኖት ሰባኪነት ሽፋን የተመዘበሩብንን አገራዊ ቅርሶችና ሀብቶች እንዘርዝር ብንል ብዛታቸው የትዬለሌ እንደሚሆን መገመት አይከብድም። በሕይወት በሚገኙ የአንድ አዛውንት ዕድሜ የሚቆጠረውን የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ታሪኮች መለስ ብለን ብናስታውስ እንኳን አገሪቱ የተራቆተችባቸውን ዘርፈ ብዙ የጥፋት ዓይነቶች ለመራር አስከፊ የኤሎሄ መቃተት እንደዳረጉን ማስታወስ ይቻላል።
የፋሽስት ወራሪ ጦር አገሪቱን በዝብዞ ያራቆተው ታሪካዊ ሰነዶችንና ቅርሶችን በመዝረፍ ብቻ ሳይሆን ከጥቃቅን የቤት ቁሳቁስ አደባባይ ላይ እስከ ቆሙ ታላላቅ ሐውልቶች ድረስ መሆኑ ለብዙዎቻችን ታሪኩ እንግዳ አይደለም።
ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት – 1980 ዓ.ም” በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ ታሪክ ጸሐፊውን ጣሊያናዊ ቶማሴሊን በመጥቀስ በሚከተሉት ውሱን ዐረፍተ ነገሮች ያሰፈረው ሃሳብ እንዲህ ይነበባል። “ጣሊያኖች በሚያዝያ ወር 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገቡ…በሚመለከቱት ነገር ሁሉ ተመሰጡ።…በዚያም ሆነ በዚህ የሚታየው ሁሉ ሀብት ስለሆነ ወታደሮቻችን ዐይናቸውን አፍጥጠው የእኛ ነው የእኛ ነው ይባባሉ ነበር። እህሉ [ሳይቀር] ተዘርቶ ሰብል ገብቶና ተሸጦ ገንዘብ አሁኑኑ ያገኙ ይመስል ሁሉም ሚሊዮኔር እንደሆኑ አድርገው ይጨዋወቱ ነበር።
ለፍተን ለፍተን በመጨረሻው እውነተኛ ቅኝ ግዛት አገኘን እያሉ እርስ በእርስ ያወሩም ነበር።” በዚህ ገለጻ ውስጥ ብዙ የሚተነተኑ ጠቋሚ ሃሳቦች ስላሉ ወራሪው ሠራዊት በአምስት ዓመታት ቆይታው ውስጥ ምን ምን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጭካኔዎችንና ዝርፊያዎችን እንደፈጸመ በህሊናችን ውስጥ ለመሣል አያዳግተንም። “ከተምች የቀረውን አንበጣ በላው፣ ከአንበጣ የተረፈውን ደጎብያ በላው፣ ከደጎብያ የተረፈውን ኩብኩባ ፈጀው” (ትንቢተ ኢዮኤል ምዕ. 1፡4) እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ በቃል ኪዳን አጋርነት ስም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የገባው የእንግሊዝ ጦር ከኢጣሊያ ወረራ የተረፈው የአገሪቱ ሀብትና ቅርስ አልበቃ ብሎት በኢጣሊያኖቹ የተቋቋሙትን ድርጅቶች ሳይቀር ሙሉ ለሙሉ በመነቃቀል በቅኝ ግዛት የአፍሪካ አገራት በኩል ጠራርጎ በመዝረፍ ማጓጓዙ በሚገባ ተመዝግቧል።
ለአብነት ያህልም የተወሰኑትን እናስታውስ። ሲቲ ጋራዥ (C.I.T.I workshop) በዓመት ውስጥ 600 ተሽከርካሪዎችን ለመጠገን አቅም የነበረውን ድርጅትና ፔሬሊ በመባል ይታወቅ የነበረውን የጎማ ፋብሪካ ከባለሙያዎቹ ጋር በኬንያ በኩል አጓጉዞ ዘርፏል። 700 ኪዩቢክ ሜትር ኦክስጂን የማምረት አቅም የነበረውን ፋብሪካ ከእነ ሙሉ ድርጅቱ በኤርትራ በኩል፣ ሐረር የሚገኝ አንድ ማተሚያ ቤት፣ የወለል ንጣፍ ማምረቻ ድርጅት በታንዛኒያ በኩል፣ የእንጨት መሰንጠቂያ ግዙፍ ፋብሪካ፣ ላንቻ ይባል የነበረውን ጋራዥ፣ ዘመናዊ የመድኃኒት ማምረቻ ድርጅት፣ የብረታ ብረት ማቅለጫ ፋብሪካ፣ መጠኑ በውል የማይታወቅ ገንዘብ፣ ወርቅና የማይተኩ ቅርሶችን ያለ ከልካይ ሙጥጥ አድርገው በመዝረፍ ከአገር አስወጥተዋል።
(ኢትዮጵያና ታላቋ ብሪታኒያ የዲፕሎማሲ ታሪክ…ከ1798 -1966 ዓ.ም።) “ኤሎሄ! አሌሄ! ላማ ሰበቅታኒ!” እያለች ኢትዮጵያ የቃተተችበት ሌላው ታሪካችን ይህንን ይመስላል።
በጻእረ ሞት የሚንፈራገጠው የሕወሓት መሰል ዝርፊያ፤
ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ መርገምትና የኤሎሄ ምክንያት ስለሆነው ወራሪው ሕወሓት ብዙ እየተጻፈና ብዙም እየተነገረ እንዳለ ይገባኛል። ተገቢ የታሪክ ምዕራፍ ተሰድሮለት ዝርዝሩ በአግባቡ ሲሰነድ ያኔ የዘረፋውና የጭካኔው ጥግ ፍንትው ብሎ ይገለጣል። ከእኛም አልፎ ለመላው የዓለም ሕዝቦች ማስተማሪያም ይሆናል።
ይህ ቡድን ከባዕዳን ወራሪዎች በከፋ ደረጃ የፈጸማቸውና ያስፈጸማቸው ሰብዓዊና ቁሳዊ ክፋቶችና ግፎች በቃላት ለማስረዳት እንደሚያዳግት በካሁን ቀደምት ጽሑፎቼ ደጋግሜ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ። በአጭሩ እንድገመው ከተባለ የጎረቤትና የአውሮፓ ወራሪዎች በየዘመናቱ ከፈጸሙብን የግፍ ድርጊቶች የሕወሓቱ ቢበልጥ እንጂ የሚተናነስ አይሆንም።
ከማዕድ ቤት ቁሳቁሶች እስከ የአደባባይ ቅርሶች፣ ከኪዮስክ እስከ ባንኮች፣ ከጤና ተቋማት እስከ የትምህርት ማዕከላት፣ ከግለሰቦች የንግድ ድርጅቶች እስከ ፋብሪካና ኢንዱስትሪዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማት እስከ የቅርስና የባህል መዘክሮች ያልበዘበዙት፣ ያልዘረፉትና ያላወደሙት የለም።
ለዚህ ጭካኔው መገለጫ የሆኑ በእምባ የታጀቡ የኤሎሄ መቃተቶችን በየሚዲያው እየተከታተልን ስለሆነ መቅሰፍትነታቸውንና የብልግና ድርጊቶቻቸውን በቋንቋ ብርታት ለመግለጽ ይፈታተናል። በእርግጠኝነት ለመመስከር የሚቻለው ግን እነዚህ የወራሪ ጀሌዎች ሰብዓዊያን ብቻ ሳይሆኑ የአውሬነት ባህርያቸው የጎላ መሆኑን ነው።
ደፍረን እንጠይቅ!?
ለመሆኑ ሕወሓት የዘረፈው “ምርኮ” ተጓጉዞ ከደጃፉ የደረሰለት የትግራይ ሕዝብ እንዳሻህ ተጠቀምበት ተብሎ በየጎጡና በገበያ መካከል ሲዘረገፍለት ምን እያወራ ተገበያየ? ከድሃው የአማራና የአፋር ሕዝብ ተዘርፈው በተወሰዱት የሕክምና መገልገያዎችና መድኃኒቶች “ታክማችሁ ዳኑ?” ሲባሉስ ምን መልስ ይሰጡ ይሆን? ልጆቻቸውን በተዘረፉ የትምህርት መሣሪያዎች “አስተምሩ ሲባሉ” ከየት አመጣችሁ ብለው ጠይቀው ይሆን? በተዘረፉ የትምህርት ቤቶች፣ የኮሌጆችና የዩኒቨርሲቲ ንብረቶች እንዲማሩ የሚጋበዙ ወጣቶችስ ምን ዓይነት እውቅት እንዲገበዬ ይጠበቃሉ? ኑሯቸውን በአግባቡ ማሸነፍ ከተሳናቸው ዜጎች ጉሮሮ፣ ማዕድ ቤቶችና ማሳ ላይ የተዘረፉት እህሎች፣ ከመስክና ከበረት የተነዱት እንስሳት በግዳይነት ሲጣሉለት የትግራይ ሕዝብ አመስግኖ የሚቀበላቸው በምን ቋንቋ እየመረቃቸው ይሆን? ብዙ ጥያቄዎችን መደርደር ቢቻልም ለጊዜው ታሪክ ኃላፊነቱን ሙሉ ለሙሉ ተረክቦ እውነታውን በፀሐይና በአደባባይ ፊት እስኪያሳጣው ድረስ “በሆድ ይፍጀው” ትዕግሥት ፍትሕን ተስፋ አድርገን እንጠብቃለን።
በኤሎሄ መካከል የሚደመጥ አገራዊ ሃሌ ሉያ!
ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ይፋ ጦርነት ከፍቶ የከፋ ግፍ መፈጸሙ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ይህ አሸባሪ ቡድን መላዋን ኢትዮጵያ አጥንቷን ግጦ፣ መቅኒዋን መጦ እርቃኗን እንዳስቀራትም ይታወቃል። ሰብዓዊና ቁሳዊ አውዳሚነቱ በቅርቡ ተሟልቶ እንደሚገለጽ ተስፋ ማድረጋችን እንደተጠበቀ ሆኖ ሌላውን የሃሌ ሉያ ገጽታ ማየቱ የተሻለ ይሆናል። በኤሎሄ በሚወከለው በዚህ ሁሉ ግፍ መካከል የመከፋፈል አደጋ ላይ ወድቃ የነበረችው ኢትዮጵያ ተበረታታ ቆማለች። ልጆቿ በአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ልዩነታቸውን አቻችለው ተቃቅፈው ዝማሬያቸው ሃሌ ሉያ ሆኗል። ለሃያ ሰባት ዓመታት የተዘራው የከፋፋይነት ሴራ ከሽፏል።
ኢትዮጵያ ከተኮረኮደችበት የእግር ብረት እየተላቀቀች ነው። አገሪቱ እንድትበታተን የተሴረበት “የሕገ መንግሥት” ገመናም እየተራቆተ እውነታው ወደ ብርሃን እየተገለጠ ነው። የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ኤሎሄ ለአፍሪካ አገራት ዘላቂ የሆነ የሃሌ ሉያ መነቃቃት እየፈጠረ መሆኑንም እያስተዋልን ነው። ራሳቸውን ኮፍሰው የኖሩ ምዕራባውያን አገራትም በኤሎሄያችን ማግሥት የሃሌ ሉያ ዝማሬያችንን ከፍ አድርገን ልንዘምር ዳር ዳር እያልን መሆኑ በግድም ቢሆን እየተዋጠላቸው ነው። ኢትዮጵያ አሸብርቃ ለዓለም የምትገለጥበት ጊዜው ሩቅ አይደለም። ፈጣሪ ሆይ ተመስገን! ለካስ በኤሎሄ ማግሥት የሚዘመረው የሃሌ ሉያ ዝማሬ ከአጥናፍ አጥናፍ የመሰማትና የመናኘት አቅሙ ከፍ ያለ ነው!? ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2014