ኢትዮጵያዊነት የጋራ ማንነት ያለው ተባብሮና ተከባብሮ የሚኖር እንዲሁም የጋራ ታሪክ ያለው ሕዝብን የሚወክል ነው። ኢትዮጵያ ሲባል ቀደምት ሥልጣኔዎችን የጀመረችና ያስፋፋች፣ በውስጧ ዘመን ተሻጋሪ ቅርሶችን የያዘችና ደማቅ አሻራዎችን ያሳረፈች አገር ነች።
ከዚህም ባለፈ ለሌሎች አገራት የነፃነት ተምሳሌት ሆና የአፍሪካ አገራት ባንዲራዋን በተለያየ መንገድ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
ስለ ኢትዮጵያ ብዙ መናገር ይቻላል። የቅርብ ዘመን ታሪካችንን ብንቃኝ አገሪቱን ከንጉሣዊ አስተዳደር ጀምሮ ደርግም ኢህአዴግም በፈለጉበት ሁኔታ ሲያስተዳድሯት ቆይተዋል። እዚህ ጋር መረሳት የሌለበት ጉዳይ ግን ሁሉም መንግሥታት በጉልበት ሥልጣን መያዛቸውን ነው። ቀረብ ካለው ብንጀምር የደርግ አስተዳደር የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት በጉልበት ከነጠቀ በኋላ አገሪቱን በመራበት አስራ ሰባት ዓመታት ጦርነት ውስጥ ነበር።
የኤርትራና የትግራይ ነፃ አውጪ ቡድኖች ዓላማቸውን ለማሳካት ከደርግ መንግሥት ጋር ሲዋጉ ቆይተው በማሸነፋቸው ወደ ሥልጣን ሊመጡ ችለዋል።
የትግራይ ክልልን ነፃ ለማውጣት ሕወሓት ሰፊ ትግል አድርጎ ዓላማውን ከሚደግፉለት ቡድኖች ጋር በመቀናጀት ኢህአዴግን መሰረተ። በኢህአዴግ ስምም ሕወሓት የበላይነቱን በመያዝ ሃያ ሰባት ዓመታትን በሥልጣን ላይ ቆየ። የሕወሓት/ኢህአዴግ ቡድን በሥልጣን በነበረበት ወቅት የትምህርት ፖሊሲውን የአገር አንድነትን በሚያዛባ መልኩ በመቅረፅ ትውልዱ እንዲማር በማድረጉ ዘረኝነትና አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል።
በጤናው ዘርፍ ደግሞ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶች ወደአገር እንዲገቡ በማድረግ፣ አቅም የሌላቸው ሐኪሞችን በመመደብና በፖለቲካ አመለካከት ብቻ የሕክምና እውቀት የሌላቸውን ሰዎች በመሰብሰብ ሆስፒታሎች እንዲመሩ በማድረጉ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የጤና ኪሳራ ሲያደርስ ቆይቷል።
በመንገድና በመሠረተ ልማት ዘርፍ ደግሞ በሙስናና በብልሹ አሠራር የተተበተበ ሥርዓት በመዘርጋት የአገሪቱ መንገዶች ገና አገልግሎት ሳይሰጡ እንዲፈርሱ አድርጓል። አቅም የሌላቸውን የመንገድ ኮንትራክተሮች ጨረታ እንዲያሸንፉ በማድረግ አገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ውድመት እንዲመጣ አድርጓል። ሕወሓት/ኢህአዴግ ይቃወሙኛል ብሎ የሚያስባቸውን ግለሰቦች አስከፊ በሆነ እስር ቤት ከማሰቃየት ባለፈ ደብዛቸው እንዲጠፋ ማድረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ስለ ሕወሓት ከዚህም በላይ
በሥልጣን በነበረበት ወቅት የሠራቸውን ብዙ ግፎች ማንሳት ይቻላል። ከዚህ ሁሉ በኋላ ነበር የኢህአዴግ አሠራርና አመራር ወደ ብልሹነት በመቀየሩ ከውስጥ ያሉት አመራሮች ለውጥ መምጣት አለበት ብለው ያመኑት። እናም 2010 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ሕወሓትን ከማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን በማባረር የለውጥ ኃይሉ ሥልጣኑን ለመቆጣጠር በቃ። ካለፉት ሦስት ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ የግጭትና የሞት ዜና መስማት የየለት ተግባር ሆኗል። ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት ተስኗቸው በተለያዩ ጊዜያት የድረሱልን ጥሪ ሲያሰሙም ቆይተዋል።
ይህን ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል ተብሎ በመንግሥት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን ሲሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በሽብርተኛነት እንዲጠራ ተወስኖበታል። ወደኋላ ስንመለስ ከለውጡ በኋላ በውጪ የሚገኙ ተቃዋሚ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በይቅርታ ወደ አገራቸው እንዲገቡ ተደረገ። የተወሰኑ ተቃዋሚ የነበሩ ቡድኖች ከነትጥቃቸው በትግራይ ክልል በኩል ከኤርትራ ገቡ። እነዚህ ቡድኖች በሕወሓት ደማቅ አቀባል የተደረገላቸው ሲሆን ምን ተመካክረው እንደተለያዩ ፈጣሪ ይወቀው። ነገር ግን የዚህ ቡድን ከነትጥቁ መግባት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ተደጋጋሚ የሰው መፈናቀልና ሞት ዜና እንዲሰማ ምክንያት መሆን ጀመረ።
የሕወሓት ቡድንም ባሰማራቸው ጀሌዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የዜጎች ሕይወት እንዲጠፋ የማድረጉን ሥራ አቀላጥፎ ቀጠለ። እዚህ ጋር መረዳት ያለብን ጉዳይ ግን ሕወሓት በሥልጣን በነበረበት ወቅት በቀረፀው የትምህርት ፖሊሲ የተማሩ ወጣቶች በገንዘብ ተገዝተው የሚኖሩበትን ከተማ ሲያወድሙ መመልከት የተለመደ ተግባር መሆኑን ነው።
ሽብርተኛው ሕወሓት እነዚህ ሁሉ ግፎች አልበቃ ብለውት በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመፈፀም በግልፅ አገር የማፍረስ ሥራውን ጀመረ። የፌደራል መንግሥት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ የአገር መከላከያ ኃይሉ እንዲወጣ አድርጓል። ይህን ተከትሎ ታድያ የሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ከተደበቀበት ዋሻ በመውጣት በአሸናፊነት መንፈስ ለድጋሚ ጦርነት እየሸለለ ብዙ የአማራና የአፋር ክልል ቦታዎችን ለመውረር በቃ።
በአማራ ክልል ላይ የሽብርተኛ ቡድኑ ጥቃት በመሰንዘሩና ለቀጣይ ጦርነት ነጋሪት በመጎሰሙ የአማራ ክልል ነዋሪ በክተት አዋጅ ተሰባስቦ ለመዋጋት ወደ ግንባር እየዘመተ ይገኛል። በዚህ ክተት አዋጅ አዛውንቶች ሳይቀሩ ወደ ግንባር ሄደው ሕወሓትን ለመፋለም ታጥቀው ዘምተዋል። በተጨማሪም ሌሎች በአገሪቱ የሚገኙ ክልሎች ለዘመቻው ልዩ ኃይላቸውን ከመላክ ጀምሮ ወጣቶች መከላከያን እየተቀላቀሉና እየደገፉ አብሮነታቸውን አበሰሩ። በዚህም የኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ለመቆም ቋምጦ የመጣው አሸባሪ ቡድን በመከላከያ ሠራዊት፤ በፋኖና በየክልል ልዩ ኃይሎች ጥሩ ቅጣት ቀምሶ በእብሪት ከያዛቸውና ንጹሃንን በግፍ ከጨፈጨፈባቸው ንብረት ካወደመባቸው አካባቢዎች ከገባበት ፍጥነት በላቀ እየፈረጠጠ ለመውጣት በቃ።
ይህ አንጸባራቂ ድል እንደተጠበቀ ሆኖ በአማራም ሆነ በአፋር ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ቀደምት የሽብርተኛው ሕወሓት አባላትና ተላላኪዎች ከያሉበት እየታደኑ ካልተወገዱ ድሉ ዘላቂ አይሆንም። በተለይ አማራ ክልል የሽብርተኛ ቡድኑን እየመሩ ሲያዘርፉና ሲያስገድሉ የነበሩ ባንዳዎች እንዳሉ ይታወቃል።
ስለዚህ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ የሽብርተኛ ቡድኑ ደጋፊዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተገቢው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። ሌላው በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ ተከፋይ ካድሬዎች ሥራ በፍጥነት እልባት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆን አለበት። ምክንያቱም ሕዝቡን እያሸበሩና ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲሄድ በማድረግ ለሽብርተኛ ቡድኑ ሽፋን በመስጠታቸው ከፍተኛ ጥፋት እንዲደርስ ምክንያት ነበሩ።
የሽብርተኛ ቡድኑን ሽለላ እየተቀባበሉ የሚዘግቡት የውጭ መገናኛ ብዙኃንን ወደ ጎን ትተን በዚሁ አገራችን ሽብርተኛ ቡድኑን የሚደግፉ የማኅበራዊ ሚድያ አንቀሳቃሾችም ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል።
እነዚህ አካላት ሕወሓት በጀመረው ጦርነት ረሀብ፣ መደፈር፣ ሞት እንዲሁም ሰብዓዊ ቀውስ መፈጠሩን በመዘንጋት አሁንም ጦርነት እንዲባባስ ፀሎት በማድረግ ላይ ናቸው። የሚገርመው እነዚህ አካላት ይህን የሚያደርጉት አዲስ አበባ በየጭፈራ ቤቱ ዳንኪራ እየደለቁ መሆኑ ነው።
ባጠቃላይም ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የሕዝቦችን መብት በማስከበር ለማስተዳደር የሽብርተኛው ሕወሓት ቡድን አባላትና ደጋፊዎች ተጠራርገው መወገድ አለባቸው። ይህ መሆን ካልቻለ ግን ሁሌም ሞትና መፈናቀል እየሰሙና እየተመለከቱ መኖር ዕጣ ፋንታችን ይሆናል ማለት ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ አንድነት የሚረጋገጠው በሕወሓት መውደም ላይ መሆኑን ሁሉም ሕዝብ ተረድቶ ሽብርተኛ ቡድኑን ለማጥፋት በአንድነት ሊነሳ ይገባል። የመንግሥት አመራርም በውስጡ ያሉትን አፍቃሪ ሕወሓቶችን ነጥሎ ለማውጣት እራሱን መፈተሽ አለበት።
የመንግሥት ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የሽብርተኛው ሕወሓት ቡድን እንዲጠፋ የማድረጉ ሥራ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኅብረተሰብ ጥረት መሆን አለበት። ለዚህም የየክልሉ መንግሥታትና ኅብረተሰቡ ሽብርኛው የሕወሓት ቡድን ዛሬም ነገም የኢትዮጵያ አንድነት ጠር መሆኑን በመገንዘብ ሊሠሩ ይገባል የዕለቱ መልእክቴ ነው።
በግሪም አዝማች
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2014